Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናአዲስ የሚመሠረተው መንግሥት ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ሁሉን አቀፍ ውይይት እንደሚያደርግ ተገለጸ

አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት ከተቃዋሚ ኃይሎች ጋር ሁሉን አቀፍ ውይይት እንደሚያደርግ ተገለጸ

ቀን:

በመጪው መስከረም 2014 ዓ.ም መጨረሻ የሚመሠረተው አዲሱ መንግሥት ተቃዋሚ ኃይሎችንና ሌሎች የሚመለከታቸውን አካላት ያካተተ፣ ሁሉን አቀፍ አገራዊ ውይይት እንደሚኖር መንግሥት አስታወቀ፡፡

ይህንን ያስታወቁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኰንን፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮች ምክትል ዋና ጸሐፊና የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፊትስ ጋር በአዲስ አበባ ዓርብ ሐምሌ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በተነጋገሩበት ወቅት ነው፡፡

አቶ ደመቀ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ማብራሪያ ባይሰጡም፣ ከምርጫው በኋላ የሚመሠረተው መንግሥት ለአገራዊ ውይይት መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

አቶ ደመቀ መንግሥት በትግራይ ክልል ከአንድ ወር በፊት ያካሄደውን የተናጠል ተኩስ አቁም ቀጣይነት ላይ ያለውን ቁርጠኝነት በመግለጽ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ያስረዱ ቢሆንም፣ ነገር ግን ሕወሓት እያካሄዳቸው ያሉ ጥቃቶች የመንግሥትን የተናጠል ተኩስ አቋም ሊገዳደሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም ሕወሓት ሕፃናትን ለጦርነት በመመልመልና በመጋበዝ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው የትግራይ ክልል አካባቢዎች እንዳይደርስ የሚያደርገውን ጥቃት  ተመድ ሊያወግዝና ተጠያቂ ሊያደርግ እንደሚገባ፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡

ምክትል ዋና ጸሐፊው በኢትዮጵያ እያደረጉት ያለው የመጀመርያ ጊዜ ጉብኝት በትግራይ ክልል ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦትና ጥረት ለመገምገም፣ እንዲሁም በአፋርና በአማራ ክልሎች ጉብኝት ለማድረግ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዋና ቢሮው በኩልም ሆነ በአዲስ አበባ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከጀመረ ጀምሮ ያደረገው ዕገዛ እንዳልነበረ ገልጸዋል፡፡

ከዚህም ጋር ተያይዞ በድርጅቱ በኩል የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ እውነትነታቸው ያልተረጋገጡ መረጃዎችን ሲያስተጋባ መቆየቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳዘነው አቶ ደመቀ አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት ምንም እንኳ የተናጠል ተኩስ አቁም ቢያደርግም፣ ሕወሓት ሕፃናትን በማስታጠቅ የትንኮሳና የግጭት መንገድ መምረጡን መናገራቸው ተጠቁሟል፡፡

ሕወሓት በሚያደርገው ትንኮሳ የተነሳ ወደ ትግራይ ክልል መግባት የነበረባቸው 170 ምግብና ምግብ ነክ የሆኑ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የጫኑ ተሽከርካሪዎች መንገድ ላይ የቆሙ መሆኑን በመጥቀስ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ 40 ያህሉ ወደ መቀሌ እንቅስቃሴ መጀመራቸው ተገልጿል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ እንደሚያሳየው በሕወሓት ጥቃት  ሳቢያ፣ በአፋርና በአማራ ክልሎች ብቻ ከ220 ሺሕ በላይ ዜጎች በመፈናቀላቸው መንግሥት ለእነዚህ ዜጎች ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ  ነው፡፡

ምክትል ዋና ጸሐፊው በበኩላቸው ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት እንደሚሠሩ በመግለጽ፣ በትግራይ ክልል የተመናመነው የዕርዳታ አቅርቦት በበቂ ሁኔታ መቅረብ አለበት ማለታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ያመለክታል፡፡

ሐሙስ ሐምሌ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. የስድስት ቀናት ጉብኝታቸውን የጀመሩት ምክትል ዋና ጸሐፊው፣ ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥትና ሌሎች የበላይ ኃላፊዎች ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...