ከድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉበት ሰኔ ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በጊዜ ቀጠሮ ችሎትና ክስም ከተመሠረተባቸው በኋላም በመደበኛ ፍርድ ቤት በመቅረብ ጉዳያቸውን እየተከታተሉ የነበሩት እነ አቶ ጃዋር መሐመድ ‹‹የፍርድ ቤቶች ውሳኔ በአስፈጻሚው አካል እየተከበረ አይደለም›› በማለት ለፍርድ ቤቱ ደብዳቤ በመጻፍ በተደጋጋሚ ከችሎት በመቅረታቸው ጉዳያቸው በሌሉበት ሊታይ ነው፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሽብርና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አንደኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሾቹ ተገደው እንዲቀርቡ ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም፣ ‹‹ተከሳሾች በራሳቸው ፍላጎት ፍርድ ቤት አንቀርብም ስላሉ ተከሳሾችን ፍርድ ቤት ማቅረብ አልቻልኩም›› በማለት ሐምሌ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ለፍርድ ቤቱ ምላሽ በመስጠቱ፣ ፍርድ ቤቱ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሃምዛ አዳነና አቶ ደጀኔ ጣፋ ጉዳይ በሌሉበት እንዲታይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በውሳኔው እንዳስረዳው፣ ተከሳሾቹ በሕግ የተሰጣቸውን መብት መጠቀም ፍላጎት ስለሌላቸው በሌሉበት ጉዳያቸው ይታያል፡፡
ሌሎቹ በእነ አቶ ጃዋር የክስ መዝገብ የተካተቱት ተከሳሾች በዕለቱ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ተከሳሾቹ በራሳቸውና በጠበቆቻቸው አማካይነት ለፍርድ ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ፣ በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ይዘውት የነበረውን የሞባይል ስልክ ሌሎች ሰዎች እየተጠቀሙበት መሆኑን አመልክተዋል። በቁጥጥር ሥር ሲውሉ ስልኮቻቸው በፌደራል ፖሊስ መወሰዳቸውን ጠቁመው፣ አሁን ግን ሌሎች ሰዎች ፌስቡክ እየተጠቀሙበት መሆኑን ተናግረዋል። ይህንን ተግባር የፈጸሙ ግለሰቦች በሕግ እንዲጠየቁና ከተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ጋር ግንኙነት የሌላቸው ቁሳቁሶች ተመላሽ እንዲሆኑላቸውም ጠይቀዋል።
ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ ያቀረቡትን አቤቱታ ሰምቶ ጠበቆቻቸው መመለስ አለባቸው የሚሏቸውን ዕቃዎችና ባለቤትነታቸው የየትኛው ተከሳሽ እንደሆነ በመለየት በቀጣይ ቀጠሮ ይዘው እንዲቀርቡና ትዕዛዝ እንደሚሰጥበት አስታውቋል። የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃላቸውን ስለሚሰጡበት ሁኔታ በዓቃቤ ሕግና በተከሳሾች ጠበቆች መካከል የሚደረገው ክርክር ከቆመበት እንዲቀጥል ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ፣ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹ ቃላቸውን ስለሚሰጡበት ሁኔታ አሻሽሎ ባቀረበው ሐሳብ ላይ የተከሳሾች ጠበቆች ሐምሌ 30 ቀን 2013 ዓ.ም. መልስ እንዲሰጡ ቀጠሮ ሰጥቷል።