የፌዴራል መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ማውጣቱን ተከትሎ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የፈረጀው የሕወሓት ኃይል በስምምነት ላይ የተመሠረተ የተኩስ አቁም ለማድረግ የሚችልባቸውን ባለ ሰባት ነጥብ ቅድመ ሁኔታ ማቅረቡ አይዘነጋም።
የፌዴሬል መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት በማወጅ ሠራዊቱን ከትግራይ ክልል ለማስወጣት የወሰነው የተለያዩ ምክንያቶችን መሠረት በማድረግ መሆኑን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ከእነዚህ ምክንያቶች አንዱ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ ቀውስ ምላሽ ለመስጠትና የክልሉ አርሶ አደሮችም የክረምቱን የእርሻ ወቅት ተረጋግተው መጠቀም ይገባቸዋል በሚል ምክንያት እንደሆነ አስረድተው ነበር።
ከሁሉም በላይ ግን ከትግራይ ክልል ጋር ተያይዞ በአገሪቱ ላይ እያንጃበበ ያለው የውጭ መንግሥታት ተፅዕኖና ጂኦፖለቲካዊ ጫናዎች በመሠረታዊነት ተጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ እንዳስረዱት የትግራይ ክልል ቀውስና ውጊያ እንዲያበቃ የሚፈልግ ብዙ ኃይል እንደሌለ፣ ከዚያ ይልቅ ውጊያው እንዲቀጥል ታቅዶ የተሸረበ ሴራ መኖሩን አስረድተዋል።
ይህ ሴራ እስከ የፌዴሬል መንግሥቱን እስከማስወገድ የደረሰ ዕቅድ የተጠነሰሰበት ስለመሆኑም ጠቁመዋል። ‹‹ለዶሮ በሽታ በሬውን የማረድ ሁኔታ አግጦ መምጣቱን ተመልክተናል›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህም ምክንያት መንግሥታቸው በትግራይ ጉዳይ ላይ የስትራቴጂ ለውጥ ማድረጉን ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግሥት ሌላው የተናጠል የተኩስ አቁም ለማወጅ ምክንያት ያደረገው፣ ለትግራይ ሕዝብም ሆነ ለሕወሓት ኃይል የጥሞና ጊዜ የሚሰጥ እንደሆነም ተናግረዋል።
በዚህ የጥሞና ጊዜም በግጭቱ እየተሳተፉ ያሉ ኃይሎች የፌዴራል መንግሥትን ጨምሮ የማሰላሰያ ጊዜ ያገኛሉ ብለዋል። በዚህም ለትግራይ ክልል ቀውስ ከጦርነት የተሻለ የመፍትሔ አማራጭ ሊገኝ እንደሚችል፣ የጥሞና ጊዜውም ለዚህ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ሊኖረው እንደሚችል ታሳቢ ተደርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን በዝርዝር ባያስረዱም የተናጠል የተኩስ አቁም መታወጁን የሚገልጸው የፌዴራል መንግሥት መግለጫ ግን፣ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔው ከሕወሓት ኃይሎች መካከል ለቀውሱ ፖለቲካዊ መፍትሔ የሚሹ በመኖራቸው ለእነሱ ዕድል ለመስጠት የሚያግዝ ስለመሆኑ ገልጿል።
ከላይ የተገለጹትን የፌዴራል መንግሥት አመክንዮች ተከትሎ ሕወሓት ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ፣ በቅድሚያ ሊሟሉ ይገባሉ ያላቸውን ባለ ሰባት ነጥብ ቅድመ ሁኔታዎች ይፋ አድርጓል።
ሕወሓት ሰኔ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ካስቀመጣቸው ቅድመ ሁኔታዎች መካከልም የጎረቤት አገር የኤርትራ ወታደሮች፣ እንዲሁም የአማራ ክልል ኃይሎች ከትግራይ ክልል እንዲወጡና ከጦርነቱ በፊት ወደነበሩበት እንዲመለሱ የሚጠይቀው ይገኝበታል።
ጦርነቱን ተከትሎ በትግራይ ክልል ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግባቸው፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ የሚለው ደግሞ ሌላኛው ቅድመ ሁኔታ ነው።
በተጨማሪም ያለ ቅድመ ሁኔታ ዓለም አቀፍ በረራዎች በትግራይ ከሚገኙ አየር ማረፊያዎች በቀጥታ ጉዞ በማድረግ ሰብዓዊ ዕርዳታ ማቅረብ እንዲችሉ እንዲፈቀድ፣ እንዲሁም ያለ ምንም ገደብ የሰብዓዊ ዕርዳታ ወደ ትግራይ ክልል የሚቀርብበት መንገድ እንዲመቻች፣ ብሎም ከቤት ንበረታቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ እንዲደረግ በመጀመርያው ቅድመ ሁኔታዎች ውስጥ ተካቷል።
በማከልም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት እንዲከበርና ይህም ወደፊት ለሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት ድርድሮች ዋነኛ መሠረት እንዲሆን በማለትም፣ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ ይፋ ባደረገው ቅድመ ሁኔታ ውስጥ ተቀምጧል።
በተጨማሪም የፌዴራል መንግሥት በ2013 ዓ.ም. ለትግራይ ክልል የመደበው ዓመታዊ የድጎማ በጀት እንዲለቀቅና የትኛውም የፌደራሉ መንግሥት ወታደራዊና የፀጥታ ኃይል ወደ ትግራይ መግባትም ሆነ መንቀሳቀስ የማይችሉ መሆኑን፣ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ያስቀመጠው መሟላት የሚገባው ቅድመ ሁኔታ እንደሆነ የሕወሓት ኃይል በመግለጫው አስታውቋል።
ከላይ በተዘረዘሩት የሕወሓት ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የፌዴሬል መንግሥት እስካሁን ያለው ነገር ባይኖርም፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ወደ ትግራይ ክልል በየብስም ሆነ በአየር ትራንስፖርት እንዲገባ ፈቃድ መስጠቱና በተወሰነ ደረጃም ዕርዳታ ወደ ትግራይ ክልል በአየርና በየብስ ትራንስፖርት መድረሱ ይታወቃል።
ይሁን እንጂ የሕወሓት ኃይል የትግራይ ክልል አካባቢዎችን በስፋት ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ አፋር ክልል በመዝለቅ በወሰደው የማጥቃት እንቅስቃሴ፣ የየብስ የዕርዳታ አቅርቦት እንቅስቃሴ እክል ገጥሞታል።
የፌዴራል መንግሥት በአየር ትራንስፖርት የሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲቀርብ በወሰነው መሠረት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች መነሻቸውንና መድረሻቸውን አዲስ አበባ አድርገው ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ በረራ እንዲያካሂዱ በሰጠው ፈቃድ የተጠቀሙት ድርጅቶች ውስን ናቸው። ነገር ግን የፌዴራል መንግሥት አዲስ አበባ ሳያርፉ በቀጥታ ከውጭ ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ በረራ እንዲደረግ እንደማይፈቅድ በማሳወቁ ይህንን መሰል በረራ አልተደረገም።
ሕወሓት በአፋር ክልል ከሚያካሂደው የማጥቃት እንቅስቃሴ በተጨማሪ፣ በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል ያላቸውን የትግራይ ክልል የአስተዳደር ወሰን አካባቢዎች ለማስለቀቅ የጀመረውን ውጊያ ቀጥሎበታል።
ሁኔታዎች በዚህ መንገድ በቀጠሉበት ባለፈው ሳምንት ሕወሓት ቀደም ሲል የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ መሟላት አለባቸው ሲል ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ላይ ክለሳ በማድረግ ቅድመ ሁኔታዎቹን ይፋ አድርጓል።
በአዲሱ ቅድም ሁኔታ ሕወሓት ምን አለ?
ሐምሌ 20 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ የተደረገው የተሻሻለ ቅድመ ሁኔታ፣ ‹‹በፍጥነት እየተቀያየረ ያለው ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ በአገሪቱ ሰላምና ደኅንነት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ ከግምት በማስገባት፣ የትግራይ መንግሥት ከዚህ ቀደም የተኩስ አቁም ለማድረግ ያቀረባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ማሻሻል አስፈልጎታል ብሏል።
ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ፍላጎቱ አለኝ ያለው ሕወሓት፣ ዳግም ባወጣው የተኩስ አቁም ቅድመ ሁኔታዎች ላይ የተከሰተውን ችግር ለመፍታት ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ውይይትና የሽግግር ሒደት እንዲካሄድ በማለት አዲስ ነጥብ በቅድመ ሁኔታነት አስቀምጧል።
‹‹አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አገሪቱን መምራት የሚያስችለው ሕገ መንግሥታዊ መብት የለውም›› የሚለው ይኸው የአዲሱ ቅድመ ሁኔታ ቀዳሚና ልዩ ነጥብ፣ ‹‹በአገሪቱ የተከሰቱት ፖለቲካዊና ሕገ መንግሥታዊ ችግሮችን ለመፍታት ዋና የፖለቲካ ተዋናዮችን ያቀፈ አካታች ፖለቲካዊ ሒደትና የሽግግር ሥርዓት እንዲካሄድ›› በማለት በቅድመ ሁኔታነት በማቅረብ ይኸው እንዲተገበር ብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የትግራይ ክልል መንግሥት በድርድር የሚደረስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ቅድመ ሁኔታዎች መሟላት አለባቸው ሲል፣ ከዚህ ቀደም ካወጣው የአቋም መግለጫ ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው ስድስት ነጥቦችን ዘርዝሯል።
ከእነዚህ ነጥቦች የመጀመርያው በትግራይ ተቋርጠው የቆዩ እንደ ኤሌክትሪክ፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ የባንክ፣ የትራንስፖርት፣ የጤናና የንግድ እንቅስቃሴዎች በፍጥነት መጀመር አለባቸው የሚለው ነው።
የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት የሆኑትን ጨምሮ ማንነታቸውን መሠረት ተደርጎ የታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፣ እንዲሁም በመላው አገሪቱ የትግራይ ተወላጆች የጅምላ እስር ይቁም ይላል።
የ2013 ዓ.ም. እና የ2014 ዓ.ም. በጀት በፍጥነት መለቀቅ እንዳለበት፣ የኤርትራ ጦርና የአማራ ኃይሎች ከትግራይ ይውጡ (ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ መረጋገጥ አለበት) ብሏል።
ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ ለሁሉም ዓይነት የትራንስፖርት አማራጮች በርካታ መተላለፊያ ኮሪደሮች ክፍት መደረግ አለባቸው የሚሉት ቅድመ ሁኔታዎች በአቋም መገለጫው ላይ ሠፍሯል።
የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ከላይ የተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎች ተፈጻሚ ሆነው፣ ይህም በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ለሕዝብ ይፋ መደረግ አለበት ይላል መግለጫው።
ቅድመ ሁኔታውን ማሻሻል ለምን አስፈለገ ?
ሕወሓት የቀደመውን ባለሰባት ነጥብ ቅድመ ሁኔታ ለማሻሻል ግልጽና ዝርዝር ያሉ ምክንያቶችን አልገለጸም። ይሁን እንጂ ጥቅል ምክንያቱን አስፍሯል። ይኸውም፣ ‹‹በፍጥነት እየተቀያየረ ያለው ወታደራዊና ፖሊቲካዊ ሁኔታ በአገሪቱ ሰላምና ደኅንነት ላይ ሊኖረው የሚችለውን ተፅዕኖ ከግምት በማስገባት፣ ከዚህ ቀደም የተኩስ አቁም ለማድረግ ያቀረባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ማሻሻል አስፈልጓል፤›› ብሏል።
ሕወሓት ከገለጸው አመክንዮ በተለየ ሊጠቀስ የሚችል ምክንያት ይኖር እንደሆነ በሚል ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በዓለም አቀፍ ተቋም ውስጥ በአማካሪነት የሚሠሩ የግጭት ጉዳዮች ተንታኝ፣ ሕወሓት ይፋ ባደረገው የተሻሻለ ወይም የተከለሰ ቅድመ ሁኔታ ውስጥ በመሠረታዊነት ሊጠቀስ የሚችለው እንድ ነጥብ እንደሆነ ይገልጻሉ።
ሕወሓት ባስቀመጠው የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታም ሆነ በተሻሻለው ውስጥ ከሰብዓዊ ዕርዳታና ከበጀት ጋር ተያይዘው የተነሱት ቅድመ ሁኔታዎች ውኃ የማይቋጥሩ መሆናቸውን የሚያስረዱት ባለሙያው፣ ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት የተጠቀሱት ነጥቦች የፌዴራል መንግሥት ኃላፊነቶች መሆናቸውን ነው።
ከላይ የተጠቀሱትን ጨምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶች ማለትም የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎቶች በትግራይ ክልል ሊጀመሩ ይገባል የተባሉት ነጥቦች፣ በቅድመ ሁኔታነት ባይቀርቡም የመንግሥት ኃላፊነቶች እንደሆኑ ያስረዳሉ።
በቀደመው ቅድመ ሁኔታም ሆነ በተሻሻለው ቅድመ ሁኔታ የተጠቀሰውና ድርድርን መሠረት ያደረገ መፍትሔ የሚፈልገው በአማራ ክልል ቁጥጥር ሥር የገቡት፣ ቀደም ሲል የትግራይ ክልል የአስተዳደር ወሰን ውስጥ የተካለሉት አካባቢዎች ጉዳይና በኤርትራ ጦር ቁጥጥር ሥር የሚገኙት አካባቢዎች ጉዳይ እንደሆኑ ይገልጻሉ።
በተሻሻለው ቅድመ ሁኔታ ውስጥ እነዚሁ አስቸጋሪ ነጥቦች ከመካተታቸው በተጨማሪ፣ ‹‹ሁሉን አቀፍ ፖለቲካዊ ድርድር›› በማለት የቀረበው አዲስ ቅደመ ሁኔታ መኖሩን የሚያስረዱት ተንታኙ፣ ይህ ቅድመ ሁኔታ ሲቀመጥ መነሻ የሆነው ‹‹አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አገሪቱን መምራት የሚያስችለው ሕገ መንግሥታዊ መብት የለውም›› የሚለው ምክንያት፣ የፖለቲካ ድርድር ለማድረግ አስቸጋሪ ሁኔታ ሊፈጥር እንደሚችል አስረድተዋል።
ከላይ በተገለጸው አዲስ የቅድመ ሁኔታ ነጥብ ሕወሓት የአገሪቱን አጠቃላይ የፖለቲካ ጉዳይ ለትግራይ ክልል መፍትሔ እንደ ቅድመ ሁኔታ እንዳስቀመጠ ገልጸዋል።
የፌዴራል መንግሥት በሕወሓት አመራሮች ላይ ሰሞኑን ክስ መመሥረቱ ሕወሓት ይህንን ቅድመ ሁኔታ እንዲያስቀምጥ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የሚገልጹት ባለሙያው፣ የፌዴራል መንግሥት በከፍተኛ ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ከሚገኙት የፖለቲካ አካላት ጋር ድርድር እንደማያደርግ አቋም ቢይዝ ተብሎና ይህንን አቋም ለመቃረን የገባ አዲስ ቅድመ ሁኔታ እንደሆነ ያስረዳሉ።
የፌዴራል መንግሥት አሁን ያለውን የትግራይ ክልል ቀውስም ሆነ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ፖለቲካዊ መንገራገጭ ለመፍታት ሁሉን አሳታፊ የሆነ ብሔራዊ ውይይት እንዲያደርግ በአሜሪካ መንግሥትና በአውሮፓ ኃያላን ግፊት እየተደረገበት መሆኑ፣ የፌዴራል መንግሥትም በመጪው መስከረም 2014 ዓ.ም. አዲስ መንግሥት ከመሠረተ በኋላ ብሔራዊ ውይይት ለማድረግ ለምዕራባዊያኑ ፍንጭ በመስጠቱ፣ ሕወሓትም ይህንኑ መነሻ አድርጎ አመራሮቹን ከተመሠረተባቸው ክስ ነፃ በማውጣት የውይይቱ አካል እንዲሆኑ ማድረግ ያሰበ እንደሚመስል አስረድተዋል።