Thursday, June 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አቋርጦት የነበረውን የገቢ ንግድ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ሊጀምር ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዘገየው ሕንፃ በጥቂት ወራት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለገቢ ንግድ ሲያቀርብ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ለረዥም ጊዜ አቋርጦ የነበረ ቢሆንም፣ በቅርቡ መልሶ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ባንኩ ለገቢ ንግድ በተለይ ለግል ዘርፉ ያቀርብ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ ከአንድ ዓመት በላይ እንዲቋረጥ ያደረገው በውጭ ባንኮች የነበሩበትን ክፍያዎች ማጠናቀቅ ስለነበረበት ነው፡፡

በባንኩ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ዙሪያ ያነጋገርናቸው የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንዳመለከቱት፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ተቋርጦ የነበረው ትልቅ ችግር የነበረበት ከመሆኑም በላይ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ለገቢ ንግድ ከማዋል ይልቅ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች መስጠት በማስፈለጉ ነው፡፡ 

በቅርቡ ለገቢ ንግድ የሚቀርበውን የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ዕቃ ግዥ ለሚፈጽሙ በመጀመር ሌሎች የገቢ ንግድ የውጭ ምንዛሪ ጥያቄዎችን ማስተናገድ ይጀመራል ተብሏል፡፡

ባንኩ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦቱን ሳይሰጥ የቆየበትን ምክንያት በተመለከተም፣ ባንኩ የነበረበትን የተቀማጭ ገንዘብ ችግሩን ማኔጅ ለማድረግ የውጭ ምንዛሪ ደጋግሞ በመመደቡ ምክንያት ይህንን የተከማቸ ክፍያ ቀድሞ በመክፈል ባንኩን በቅድሚያ ነፃ ማድረግ በመፈለጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ለአገር ውስጥ በተለይ ለገቢ ዕቃዎች የሚፈቀደውን የውጭ ምንዛሪ በመግታት ለውጭ ዕዳ ክፍያ ቅድሚያ መስጠቱም ባንኩ መጀመርያ ተዓማኒነቱን ማረጋገጥ ስለነበረበት ነው ብለዋል፡፡

የፀጥታ ችግሮችም ሀብት በመሻማታቸው ባንኩ የውጭ ምንዛሪ ሳያቀርብ ለመቆየቱ እንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል ሲሉ አቶ አቤ አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ በውጭ ምንዛሪ ሲፈጸሙ የነበሩ ክፍያዎች በመቃለላቸው በቅርቡ ለገቢ ንግድ የውጭ ምንዛሪ ማቅረብ እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡ ባንኩ ቀደም ብሎ በየሦስት ወሩ ሲያቀርብ የነበረውን የውጭ ምንዛሪ አሁን መልሶ ከመጀመር ባለፈ ከፍ ያለ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ለማቅረብ ማቀዱንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

እስካሁን በጣም አስቸኳይ ናቸው ለተባሉና በተለየ ሁኔታ ለተፈቀዱ ብቻ የውጭ ምንዛሪ ሲቀርብ እንደነበር ተገልጿል፡፡ 

ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ጠይቋል የተባለው አዲሱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃም በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡ ያልቃል ተብሎ ከሚጠበቀው ጊዜ በላይ የወሰደው ይህ ባለ 48 ወለል ሕንፃ፣ የኮንትራት ውሉ በውጭ ምንዛሪ ክፍያ የሚፈጸም በመሆኑና ለሕንፃው የሚያስፈልጉ አብዛኞቹ ግብዓቶች በውጭ ምንዛሪ ተገዝተው ስለሚገቡ የሕንፃውን ወጪ ከፍ አድርጎታል፡፡ እስካሁን ወደ ሰባት ቢሊዮን ብር እንደወጣበት የሚገመት ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ የቀሩት የማጠናቀቂያ ሥራዎች አልቀው ለአገልግሎት እንዲበቃ ርብርብ እየተደረገም ነው ብለዋል፡፡

ይህ ሕንፃ እጅግ ውስብስብ ስለመሆኑ የሚገልጹት አቶ አቤ ‹‹ከሚታሰበው በላይ ውስብስብ ነው፡፡ የሚሠራበትም ቴክኖሎጂ ትንሽ ጠንከር ያለ በመሆኑ ትክክለኛነት ይፈልጋል፤›› ይላሉ፡፡

በዓይነትም በመጠንም የበዛ ዕቃ የሚፈልግ ሕንፃ ሲሆን፣ አንድ ዕቃ ጎደለ ሲባል በቅርብ የማይገኝና ለዚሁ ሕንፃ ተብሎ ተመርቶ የሚመጣ በመሆኑ ሥራውን ከበድ አድርጎት እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡

አንድ ስህተት ካለ ያንን ለማስተካከል ሲባል ሲወሰድ የነበረው ጊዜ ቀላል አልነበረምም ይላሉ፡፡ ሕንፃውን በቶሎ ለማጠናቀቅ በሳምንት ሦስት አራት ቀን በቦታው በመገኘት ክትትል የሚያደርጉ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አቤ፣ የእነርሱንም ጊዜ ሲወስድባቸው መቆየቱን ተናግረዋል፡፡  

ለሕንፃው ግንባታ መዘግየት ሌላው ምክንያት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ነው፡፡ በአንድ ወቅት የግንባታ ሥራውን የሚያከናውኑት ቻይናውያን አብዛኞቹ በኮቪድ በመጠቃታቸው ግንባታው ለሁለት ወር እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡ ወደ ትክክለኛው ሥራ ለመግባትም ጊዜ በመውሰዱ የሕንፃው ግንባታ ሊዘገይ ችሏል፡፡ በኮቪድ ምክንያት ከውጭ የተመረቱ የሕንፃው ግብዓቶችን በተገቢው ጊዜ አስጭኖ ማምጣትም አስቸጋሪ ነበር፡፡

እንዲህም ሆኖ ግን አሁን ብዙው ነገር እያለቀ በመሆኑ በመስከረምና በጥቅምት ሥራውን ለማጠናቀቅ ይቻላል የሚል እምነት እንዳለም ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ በምሥራቅ አፍሪካ ረዥሙ ሕንፃ በመሆን የሚጠቀስ ሲሆን፣ በአፍሪካ አምስተኛው ረዥሙ ሕንፃ ይሆናል ተብሏል፡፡

 በ2007 ዓ.ም. ግንባታው የተጀመረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታው በስድስት ቢሊዮን ብር ይጠናቀቃል ተብሎ የተጀመረ ሲሆን፣ አሁን አጠቃላይ የግንባታ ወጪው ወደ ሰባት ቢሊዮን ብር እየተጠጋ ነው፡፡      

አራት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የታቀደውን የሕንጻ ግንባታ የሚያከናውነው የቻይና መንግሥት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ነው፡፡ የማማከርና የመቆጣጠር ሥራ ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የቻይና መንግሥት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ የአፍሪካ ኅብረት ሕንፃን መገንባቱ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች