Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት​​​​​​​በቶኪዮ ኦሊምፒክ ሴቶች 800 ሜትር እንዳትካፈል የተደረገችው አትሌት ጉዳይ ጥያቄን አስነሳ

​​​​​​​በቶኪዮ ኦሊምፒክ ሴቶች 800 ሜትር እንዳትካፈል የተደረገችው አትሌት ጉዳይ ጥያቄን አስነሳ

ቀን:

በቶኪዮ ኦሊምፒክ በመካከለኛ ርቀት በ800 ሜትር ማጣሪያ ለመወዳደር ተዘጋጅታ የነበረችው ኢትዮጵያዊቷ ወርቅውኃ ጌታቸው ድንገት መታገዷ ጥያቄ አስነስቷል፡፡

 ውድድሩን ሐምሌ 22 ቀን 2013 ዓ.ም. ለማከናወን ከስፍራው የተገኘችው ወርቅውኃ እንደማትወዳደር ሲገለጽላት በተፈጠረው ድንገተኛ ነገር ስሜቷ መነካቱ ተገልጿል፡፡

በተለይ በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን በኩል መረጃ የማድረስ ክፍተቶች መኖራቸው የችግሩ መንስዔ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

የመከላከያ ስፖርት ክለብ አትሌት የሆነችው ወርቅውኃ፣ በአዲስ አበባ በተከናወነው የኢትዮጵያ ሻምፒዮን ላይ ተሳትፋ በበላይነት ማጠናቀቋን ተከትሎ፣ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ መመረጧ ይታወሳል፡፡

ሆኖም ቶኪዮ ከደረሰች በኋላ የቴስቶስትሮን መጠኗ ከሚፈቀደው በላይ በመሆኑ፣ መወዳደር እንደማትችል የዓለም አትሌቲክስ መወሰኑ ተገልጿል፡፡

ከስምንት ወራት በላይ በቆየው የኦሊምፒክ ዝግጅት ከስድስት ጊዜ በላይ የተለያዩ ምርመራዎችና ክትትል የተደረገላቸው አትሌቶቹ፣ ውጤታቸው ለዓለም አትሌቲክስ ሪፖርት ሲደረግ እንደቆየ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሕክምና ባለሙያ አያሌው ጥላሁን (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡

እንደ ሕክምና ባለሙያው አስተያየት ከሆነ፣ አትሌቷ ወደ ቶኪዮ ከማምራቷ ቀደም ብሎ ስለ ጉዳዩ ለማማከር ሲሞከር አትሌቷን ማግኘት አልተቻለም፡፡ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና በኦሊምፒክ ኮሚቴ መካከል በነበረው እሰጣ ገባ ምክንያት አለመግባባት መፈጠሩን ተከትሎ ወደ ስፍራው ማቅናቷን ገልጸዋል፡፡

ሆኖም በአትሌቷ ተፈጠረ በተባለው እክል ምክንያት ከውድድር ወጪ ብትሆንም በቶኪዮ ያለው የልዑካን ቡድን ጉዳዩ በአግባቡና የሥነ ልቦና ጉዳት በማያደርስ መልኩ ለአትሌቷ አለማሳወቁ አግባብ እንዳልሆነ አያሌው (ዶ/ር) አክለዋል፡፡ 

የዓለም አትሌቲክስ እ... 2018 400 እና 800 ሜትር ርቀት የሚሮጡ ሴቶች የሆርሞን መጠኛቸውን የሚደነግግ ደንብ ያወጣ ሲሆን፣ የአትሌቶች ቴስቶስትሮን ከተወሰነ ገደብ በታች መውረድ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

በተጨማሪም እንደዚህ ዓይነት ችግር የሚገጥማቸው አትሌቶች የተለያዩ መድኃኒቶችን ወስደው የሆርሞናቸውን መጠን መቀነስ፣ እንዲሁም ከ800 ሜትር በላይ ባሉ ርቀቶች ላይ መሳተፍ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያዊቷ ወርቅውኃ ከ3000 ሜትር በላይ ባሉ ርቀቶች ላይ መሳተፍ እንደምትችል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሕክምና ባለሙያው አያሌው (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

የሦስት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮና እና የኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳልያ አሸናፊዋ ደቡብ አፍሪካዊቷ ካስተር ሴሜንያ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ አልተሳተፈችም፡፡ አትሌቷ በቀድሞ የዓለም አትሌቲክስ ማኅበር (አይኤኤኤፍ) ከመጠን በላይ ቴስቶስቶሮን አለብሽ ተብላ ክስ ከቀረበባት በኋላ ሆርሞኑን የሚቀንስ መድኃኒት መውሰድ እንዳለባት ቢነገራትም የጎንዮሽ ጉዳት አለው በሚል ሳትወስድ ቀርታለች፡፡ አትሌቷ እ.ኤ.እ በ2009 እና 2015 ላይ ፈቃደኛ ሆና መድኃኒቱን ብትወስድም የጎንዮሽ ጉዳት እንዳጋጠማት ተገልጿል፡፡

በዚህም ምክንያት ለሦስት ዓመታት ያህል በፊርማ ውድድር ለመወዳደር አልቻለችም፡፡ ደቡብ አፍሪካዊቷ አትሌት ወደ ቶኪዮ በ5000 ሜትር ለመሮጥ ብትሞክርም በወቅታዊው የአየር ንብረት ምክንያት መካፈል አለመቻሏ ተጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...