በመጪው ጥቅምት 2014 ዓ.ም. በእንግሊዝ ግላስኮው ከተማ በሚካሄደው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ የኢትዮጵያን ድምፅ ያንፀባርቃሉ የተባሉ ስምንት ኢትዮጵያውያን መመረጣቸውን ብሪቲሽ ካውንስል አስታወቀ፡፡
የተመረጡት ወጣቶች ኮፕ26 በሚባል የሚጠራው 26ኛው በአየር ንብረት ላይ በሚያተኩረው ስብሰባ የመሪዎችና የዘርፉ ተዋናዮች የሚሳተፉበት ሲሆን ከ 30,000 በላይ ታዳሚዎች እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
የብሪቲሽ ካውንስል በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የተለያዩ የፈጠራ ሥራዎችን ያከናወኑና የተሸለሙ፣ እንዲሁም ለፈጠራ ሥራቸው በቀጣይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ወጣት ፈጣሪዎችን፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ከፍተኛ ሻምፒዮንስ ተወካዮች ጋር ሐምሌ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. አስተዋውቋል፡፡
ወጣቶቹ የበርካታ የሥራ ፈጠራና ሽልማት ባለቤት ሲሆኑ፣ ብሪቲሽ ካውንስል በተለያዩ የማወዳደሪያ መሥፈርት እንደመረጣቸው ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2020 በእንግሊዝ ሊካሄድ ታስቦ የነበረው የአየር ንብረት ለውጥ ስብሰባ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት መራዘሙ ይታወሳል፡፡
በመጭው ጥቅምት ወር በሚካሄደው ስብሰባ ተሳታፊዎች መካከል ዩዝ ፕሪንት የተባለ የወጣቶች ተቆርቋሪ ድርጅት መሥራች እንዲሁም የወጣቶች ስምምነት ለአየር ንብረት ለውጥ ተባባሪ መሥራች ያሬድ አበራ ይገኝበታል፡፡
በተመሳሳይ የተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጥምረት ዳይሬክተር ጆዳሂ በዛብህ፣ ከቬድካ ስኮላርሺፕ ፕሮግራም ከ100 ዓለም አቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ውስጥ የመደባትና ሪዚሊያንት 40 የተባለ ድርጅት መሥራች ቤተልሔም ደጀኔ ይገኙበታል፡፡
እንዲሁም ሌሎቹ ተሳታፊዎች፣ ህሊና ተክሉ ከሲድ ቦንብ ተብሎ የሚጠራ የፈጠራ ሥራ ባለቤትና የአየር ንብረት ለውጥ በአፍሪካ የተባለ ድርጅት መሥራች፣ አቤል ኃይለጊዮርጊስ በቀርከሃ ዛፍ የሚሠራ ሳይክልና የተለያዩ መሣሪያዎች ለማምረት ሐሳቦችን ያመነጨ፣ ዓምደሥላሴ አማረ ዩቶፓና ፕላኔት ፈርም የተባሉ ሁለት ድርጅቶች መሥራች ናቸው፡፡
በሌላ በኩል የትራሽ ፎር ካሽ የተባለ ኢኒሼቲቭ መሥራች ናንሲ ቹቤት እና ኢዘዲን ከማል የተባለ ወጣት የ37 ፈጠራዎች ባለቤትና አይከን አፍሪካ የተባለ ድርጅት መሥራች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ ኢዘዲን በተጨማሪም በብሪቲሽ ካውንስል ዴሲቲኔሽን ዜሮ የተባለ የአየር ንብረት ፈጠራ ውድድር ላይ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበና በፈጠራ ሥራዎቹ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሽልማት ያገኘ ወጣት ነው፡፡