Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር​​​​​​​አገር በጭንቅ ወቅት የሚያሻግራት አርበኛ ትፈልጋለች

​​​​​​​አገር በጭንቅ ወቅት የሚያሻግራት አርበኛ ትፈልጋለች

ቀን:

በሙሉቀን ካሳ

አርበኝነት ጦረኝነት ብቻ አይደለም፡፡ ፈርጀ ብዙ ተጋድሎም ነው፡፡ አርበኝነት አልሸነፍ ባይነት መገለጫ ነው፡፡ መብትን ሊገፍ ለመጣ ነፍጥ አንስተህ የምትዋደቅበት ነው፡፡ አርበኝነት አንዳች የተጫነህን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ገፍተህ ለመጣል የምትታገልበት ነው፡፡ ‹‹ተገዛ!›› ለሚልህ ‹‹አልገዛም!››፣ ‹‹እኔ ምልህን ብቻ አድርግ! ለሚልህ፣ ‹‹አላደርግም!›› ብለህ ትግል የምታደረግበት ወኔ፣ እልህ፣ ቁጭት፣ መነሳት፣ መበርታትና መዋደቅ ነው፡፡

አገራችን ዛሬ በዋናነት በሁለት ጦርነት ውስጥ ነች፡፡ በአንድ በኩል የሕወሓት የሥልጣን ጥመኛ ቡድንና መሰሎቹ የከፈተበትን ጦርነት፣ በሌላ በኩል ተጣብቷት ካለው ድህነት ለመላቀቅ የምታደርገው ግብግብ፡፡

ኢትዮጵያ እንዳለመታደል እንበለው አጋጣሚ ባሳለፍናቸው 100 እና 150 ዓመታት ውስጥ እንኳን ብናይ ከሁለትና ከሦስት አሥር ዓመታት በላይ ያለ ግጭትና ጦርነት አሳልፋ አታውቅም፡፡ አንድም ለሥልጣን፣ ሁለትም ለለውጥና ለአንድነት፣ አለበለዚያም ተንኳሽ ጎረቤት አገሮች መዳከሟን እያዩ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ  ሊያጠቋት ሲሞክሩ ህልውናዋን ለማስጠበቅ ጦርነት ውስጥ ገብታ ተዋግታለች፡፡ ይኼም ለረዥም ጊዜ ከድህነት ለመውጣት የምታደርገውን ጥረት አዳጋች አድርጎባት ቆይቷል፡፡

ኢትዮጵያ አሁናዊ ያለችበት የታሪክ እውነት ከ1969 ዓ.ም. ታሪክ ጋር የሚመሳሰል ነው፡፡ ለረዥም ዓመት በንጉሣዊ ሥርዓት አስተዳደር የነበረው በወታደራዊ ደርግ በመፈንቅለ መንግሥት ከተቀየረ ሁለት ዓመት አካባቢ ነበር፡፡ አገሪቱ ልክ እንደ አሁኑ ያልተረጋጋ ሁነት ውስጥ ያለች ትመስል ነበር፡፡ ደርግ ንጉሣዊ ሥርዓትን አስወገዶ ደሃ ተኮር ሶሻሊስት አገር ለመመሥረት ደፋ ቀና የሚልበት ነበር፡፡

 ‹‹ያለ ምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም›› ብሎ ለማስተዳደር የሞከረው ደርግ  ከውስጥም ከውጭም ጠላት ልክ እንደ አሁኑ ከዚህም ከዚያም ጉንተላ በዝቶበት ነበር፡፡ በውቅቱ ከውጭ ጠላት ታላቋን ሶማሊያን እመሠርታለሁ ያለው የሶማሊያው መሪ ጄኔራል ዚያድ ባሬ የኢትዮጵያን መዳከምና አቅሟን ዓይቶ ጦር አዘመተብን፡፡ እስከ ኦጋዴን ድረስ ግዛቴ ነው ብሎ በወረራ ለመያዝ ጦሩን አስገባ፡፡ በአገር ውስጥ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የሽምቅ ተዋጊዎች እንደ ፍልፈል በዝተው ኢትየጵያን መውጋት ጀምረው ነበር፡፡ በዚያም በዚህ እያሉ አገርን የማዳከም ሥራ ላይ አውቀውትም ይሁን ሳያውቁት ከጠላት ጋር ጭምር ተሠልፈው በባንዳነት የሠሩበት ጊዜ ነበር፡፡

በኋላም ደርግ የእናት አገር ጥሪ አድርጎ በርካታ ሚሊሻና መደበኛ ሠራዊት በማሠልጠን ዕብሪተኛውን ዚያድ ባሬ የላከውን ሠራዊት ጠራርገው ለማስወጣት ቻሉ፡፡ ከስምንት ወራት በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የቆየውን የሶማሊያን ጦር በ1970 ዓ.ም. ድባቅ ተመትቶ ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡

ሶማሊያ ብቻዋን መጥታ አልወጋችንም ነበር፡፡ እንደ አሜሪካ፣ ግብፅ፣ ሊቢያና የመሳሰሉት አገሮች በእጅ አዙርም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሠልፈው አብረው አጥቅተውናል፡፡ ይህንን ግፍ ያዩ የነበሩ የኢትዮጵያን ወዳጅ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በመደገፍ  ኩባ፣ የመን፣ ሩሲያና የመሳሰሉት በመደገፍ ከጎኗ ሆነውላት ነበር፡፡ ቆራጡ የኢትዮጵያ ልጅ ሶማሊያን ማንም ይርዳት ማንም የጦር መሣሪያ ሆነ ሥልት አልበገረውም ነበር፡፡ በተለይ የአየር ኃይሉ ብቃት የሶማሊያ አየር ኃይል ሠፈር ድረስ ሄዶ የፈጸመው ጀግንነትና አየር በአየር ውጊያ የሶማሊያን ጄቶች አመድ ያደረገበት ጀብዱ ዛሬም ድረስ በታሪክ ሲደነቅ ይኖራል፡፡

በሌላ በኩል ሶማሊያን በመደገፍ ባንዳ የሆኑት ጀብሃ፣ ሻዕቢያና ትሕነግ (ሕወሓት) የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ሶማሊያን በመደገፍ የባንዳነት ሥራ ሲሠሩ የነበሩበት የውስጥ ጠላቶች ነበሩ፡፡ አሁን የሚታየው ገጽታ ይኼ ነው፡፡ የአገራችን ታሪክም ይኼንን እውነታ የደገመ ይመስላል፡፡ በአንድ በኩል ሶማሊያን በሱዳን ተተክታ መሬታችንን ወራለች፡፡ ከጀርባዋ ግብፅን፣ አሜሪካና አንዳንድ አገሮችን አሠልፋ ልቀቂ ብትባል አለቅም ብላለች፡፡ በሌላ በኩል የያኔው የጫካ ባንዳ ሕወሓት አሁንም ልክ እንደ ያኔው ኢትዮጵያን እየወጋት ነው፡፡ የበላበትን ወጪት ሰባሪና ባንዳ ሆኖ በመጣበት ሁኔታ ታሪክ ራሱን ይደግማል የሚያስብል ነው፡፡ አየር ኃይላችን ታዲያ ከሃዲውን ጁንታ ድባቅ የመታበትና አገርን የታደገበት የሶማሊያውን ጊዜ ጀብደኝነት ያስታወሰ ነበር፡፡ በሌላ በኩል እንደያኔው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ ወዳጅ አለማጣቷና ዛሬም የሚሟገቱልን እንደ ሩሲያና ቻይና ያሉ አገሮች ሲታዩ ይበልጥ ይገርማል፡፡

ሕወሓት እንደ ዕድል ገጥሞት እንበለው ወይም የደርግን ድክመት ተጠቅሞ አገር የማስተዳደር ዕድሉን አገኝቶ መንግሥት መሆን የቻለ ነበር፡፡ ለ27 ዓመታት በጨረባ ምርጫ የኢሕአዴግ ግንባርና እህት ድርጅቶች አስተዳደር ሥርዓት ሥልጣኑን ለመጨቆኛና ለጥቅሙ ሲጠቀምበት ቆይቷል፡፡ በኋላም በሕዝብ ተቃውሞና በኢሕአዴግ የውስጥ በተፈጠረው እህትማማቾች ፓርቲ ትግል የተፈነቀለ፡፡ በዚህም ሁለት ዓመት ሙሉ በለውጥና በነውጥ አገራችን ስትናጥ ከጀርባ ዋና አስተባባሪ ሆኖ የቆየበት ጊዜ ነበር፡፡ በኋላም የሕወሓት ጁንታ ስብስብ ቡድን በሠራዊቱ ላይ በፈጸመው የክህደት ጥቃት ኢትዮጵያን ሳትወድ በግድ ወደ ጦርነት ውስጥ ከቷታል፡፡

እንደ ሕወሓት ዓይነት የእናት ጡት ነካሽ በሥልጣን ዘመኑ አገር ላይ እንዳሻው ፎልሏል፡፡ ዴሞክራሲን ጢባጥቤ ተጫውቶበታል፡፡ አገሪቱን የንግድና የፖለቲካ ሥርዓት በኔትወርክ ተቆጣጥሮ ነግዶበታል፡፡ ጋዜጠኛና ተቃዋሚን ሁሉ ሲሻው እያሰረ ወይም እየገደለና አፋልጉኝ እያለ ሲተውን ኖሯል፡፡ በቲቪ ፕሮፓጋንዳ የአገሪቱን ዕድገት ከአደጉት አገሮች ከአውሮፓና ከቻይና እኩል ጣራ አስነክቶት በማሳየት የዋሁ ወገኔን ከበሮ አስደልቆ ተጠቅሞበታል፡፡ ያደገው ግን የእነሱ ኪስና አካውንት ነበር፡፡

ከዚያ ሁሉ ድራማ በኋላም የበላይነት ሥልጣኔን ተቀማሁ በሚል መቀሌ ውስጥ ከሁለት ዓመት በላይ እየተሰበሰበ ሲዶልትና ሲያሴር ቆይቶ፣ ለዘመናት የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቀው የነበረው ሠራዊት ላይ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጦርነት ከፈተበት፡፡ ግን በለኮሰው እሳት ተለብልቦ ተመልሶ የፌዴራል ሥልጣን ለመቆጣጠር ቋምጦለት የነበረው መከነበት፡፡

በአሁኑ ጊዜ የተረፈው ጁንታ በየበረሃው ሲሽሎኮሎክ ቆይቶ ባለፈው ወር መንግሥት ያደረገውን የተናጠል ተኩስ አቁም ተከትሎ ወደ መቀሌና ሌሎች ትግራይ ከተሞች በመመለስ፣ ጨቋኝነቱንና ክፋቱን በትግራይ ሕዝብ ላይ እያዘነበ ይገኛል፡፡

ከሰላም ይልቅ ጦርነትን የመረጠ አረመኔያዊ ስብስብ እስካሁን የፈጸመው በደል አልበቃ ብሎት በትግራይና በትግራይ አጎራባች በሆኑ በአማራ፣ በአፋርና በኤርትራ ሕዝቦች ላይም ጦርነት አውጇል፡፡ ምንም የማያውቁ ዕድሜቸው ለጦርነት ያልደረሱ  ሕፃናትን እየወሰደ እየማገደና እያስፈጃቸው ይገኛል፡፡ ይህንን ዓለም አቀፍ ወንጀል እንኳን እየፈጸመ ዓለም ዝም ማለቱ ሲታይ፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሴራው ማጠንጠኛ ክር ሕወሓት መሆኑ ግልጽ ይሆናል፡፡

የሕወሓት የሽብር ቡድን በሰው ደምና ሥቃይ ካልኖርኩ የሚል የክፋት ጥግ ማሳያ የአውሬ ስብስብ ነው፡፡ በትግራይና በአጎራባች በሚኖረው ማኅበረሰብ ላይ ያደረሰው ሥቃይ እንዲህ በቀላሉ የሚነገር አይደለም፡፡ በዘር እየለየ በአሰቃቂ ሁኔታ ረሽኗል፡፡ በርካቶችን የጦርነት ሰለባ አድርጓቸዋል፡፡ ረሃቡና ሰብዓዊ ቀውሱም በተለይ በትግራይ  ተባብሶ አሁንም እንዲቀጥል እያደረገ ይገኛል፡፡

በዚህ ሰሞን አንኳን ወደ ክልሉ ዕርዳታ ጭነው በሚገቡት መኪኖች ላይ ጥቃት በመፈጸም ዕርዳታውን ሳያደርሱ እንዲቆሙ አድርጓቸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት የሽብር ቡድን ከቶም ሰላም ተሰምቶት ለሌላው ሰላም ይሰጣል ተብሎ ማሰብ፣ እስካሁን ካሉት የአሸባሪ ቡድን ባህሪ አለመማር ነው፡፡

ታዲያ አገር እንዲህ በጭንቅ ወቅት ህልውናዋን ለመፈታተንና ለመከፋፈል ከውስጥም ከውጭም ተደራጅቶ እኩይ ኃይል ሲነሳባት፣ የሚያሻግራት ጥበበኛም አርበኛም ትፈልጋለች፡፡ አባቶቻችን ለዘመናት ከውስጥም ከውጭም ጠላት ሲነሳባቸው አንድ ሆነው በመመከት፣ ይህችን የመሰለች ታላቅ አገር አስረክበውናል፡፡ አገርን ለማስጠበቅ በከፈሉትም መስዋዕትነት ከርስታቸው ተፈናቅለዋል፣ ቤተሰባቸውን አጥተዋል፣ ተርበዋል፣ ተጠምተዋል፣ ከምንም በላይ ትልቁን ውድ ሕይወታቸውን ገብረዋል፡፡ ዛሬም ይህ ትውልድ የአባቱም የእናቱም ደም አደራ አለበት፡፡ የአገርን አንድነት ጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ የማሻገር የህሊና ቃል ኪዳን ተረክቧል፡፡

አሁን እንደ ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ የመሳሰሉት ለአገር ህልውና አደጋ ጋርጠው፣ ከጠላት ጋር ኢትዮጵያን ለማፍረስ ተሠልፈዋል፡፡ ይህንን ለመመከት እንዲያስችል የእናት አገር ጥሪ በተለያየ መስኩ እየተስተጋባ ይገኛል፡፡ የመከላከያ ኃይሉን ለማጠናከር በርካታ ወታደር ይፈልጋል፡፡ ክልሎች በተናጠል የመጣባቸውን የህልውና አደጋ ለመመከት እንደ አማራና አፋር ክልሎች ለሕዝብ ጥሪ አድርገው በርካታ ሕዝብ እየተቀላቀላቸው ነው፡፡ በሌሎችም ክልሎች በአንድነት በመነሳት በርካታ ወጣቶች፣ የጦርና የሕክምና ባለሙያዎች ቡድን ወደ ማሠልጠኛ ተቋም እየተንቀሳቀሱና እየተቀላቀሉ መሆናቸው ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በሌላ በኩል ለሠራዊቱ ከማኅበረሰቡ የሚደረገው የጀርባ ደጀንነት ነውና ሁሉም አለሁ ለአገሬ በማለት ደጀንነቱን የሚያሳይበት ነው፡፡

ይኼ የሚያሳየው እኛ ከተባበርን ማንም አይበግረንም፡፡ ጣሊያን በዓድዋ ድል የተመታው በተባበረ ኅብረ ብሔራዊ ክንድ ነው፡፡ ዳግመኛም ለበቀል ወረራ መጥቶ የሽንፈት ፅዋውን ተከናንቦ የሄደው በአርበኛ እናቶቻችንና አባቶቻችን ተጋድሎ ነው፡፡ ሶማሊያን በካራማራ፣ ግብፅን በጉንደትና በጉራዕ ዳግመኛ እንዳያስቡት ተደርገው የተመቱት በአገር ፍቅር ስሜት ነው፡፡

እኛ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከተባበርን ኃያል አንበሳ እንደሆንን አሁን ለዓለም ማሳየት ያለብን ወቅት ነው፡፡ ለመከላከያ ሠራዊታችንን በማጠናከርና ድጋፍ በማድረግ፣ የአገርን ሉዓላዊነት የሚፈታተነውን ሁሉ አፍ ማስያዝ ይገባል፡፡

አለበለዚያ ግን ስንደክም ማንም ያጠቃናል፡፡ ስንበተን ማንም ይገባብናል፡፡ ‹‹የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል›› ነውና ነገሩ፡፡ ይህንን ንቀትም ድፍረትም ደግሞ እንደ ሱዳን ያሳየን የለም፡፡ ለራሷ እንኳን መቆም ያቃታት በሽግግር መንግሥት እየተመራች፣ ለሕግ የማስከበር ዘመቻን ወታደሮቻችን ከድንበር ወደ ግዳጅ ቀጣና መሄዳቸውን ዓይታ ድንበራችን አልፋ መሬታችንን ለመውረርና ለመያዝ ለጊዜው የቻለው በዚህ ሁኔታ ነው፡፡ የሚገርመው ደግሞ ማንም የውጭ ኃይል ሱዳንን እረፊ አለማለቱ ከጀርባ ያለውን ደባ ቁልጭ አድርጎ የሚነግረን አለ፡፡

በሌላ በኩል ከጦርነቱ ባልተናነሰ የተከፈተብንን የውጭ ዲፕሎማሲያዊ ጫና  ለመከላከል ሁላችንም አምባሳደር መሆን ይጠበቅብናል፡፡ በተለይ ዳያስፖራው፣ ምሁራንና ነዋሪዎች ዕለት ከዕለት ትኩረት በመስጠት በምዕራባውያን አገራችን ላይ እየተፈጠረ ያለውን የውሸት ፕሮፓጋዳና ሴራ ማክሸፍ ይገባል፡፡ የሕወሓት የጥፋት ተሠላፊዎች አገራችንን በውሸት ፕሮፓጋንዳ አጠልሽተዋታል፡፡ አንድነታችንን ከዓለም እስከ ዓለም ጫፍ በሁሉም መስክ በማጠናከርና በምንችለው ሁሉ በማድረግ፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ሚናችንን ከፍ እንድናደርግ አገር ትጠይቃለች፡፡

በሱዳን በኩል ሞክራ አልሆን ያለት ግብፅ የህዳሴውን ግድብ አሁንም ለማስቆም ዕድል ካገኘሁ በሚል በማወናበድ ላይ ነች፡፡ በአገር ውስጥ የሽብር ሥራዋን የሚሠሩላትንና የውስጥ ችግራችንን የሚያፋፍሙላት ከመደገፍ ቦዝና አታውቅም፡፡ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና መንግሥታት ላይ የሐሰት ፕሮፓጋንዳዋን በመንዛት የማሳሳት ሥራዋን ባልተቋረጠ ሁኔታ እየሄደችበት ትገኛለች፡፡ በዚህም ምን ያህል የዲፕሎማሲ  ጫና ውስጥ ከጁንታው አሻጥር ጋር በመሆን እንደከተተችን የሚዘነጋ ጉዳይ አይደለም፡፡

አንደኛው አሁን አገራችን ሁለትና ሦስት አስቸጋሪ ጉዳዮችን እያለፈች ትመስላለች፡፡ የህዳሴውን ከአንደኛው ዙር ሙሌት አትሞይም የሚል የግብፅ፣ የሱዳንና የአሜሪካ ድንፋታ አልፋ ሁለተኛውን ዙርና ከፍተኛ መጠን የሚይዘውን የውኃ ሙሌት ለማካሄድ በቅታለች፡፡ የግብፅና ሱዳን እዚህም እዚያም የመርገጥ ዲፕሎማሲ ፋይዳ ቢስ አድርጎባቸዋል፡፡ ሆኖም ግን ለወራት የመሠረቱት ጋብቻ አሁንም ትንኮሳቸውንና ጫናቸውን እንደማያቆሙ ያሳያል፡፡ በተለይ ግብፅ አርፋ የማትተኛ ቀንደኛ የኢትዮጵያን ዕድገት ጠላት ሆና የቆየች ናት፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁን ዋነኛ መጠቀሚያዋ የትሮን ፈረሱ የሕወሓት ጁንታ ቡድን መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

አገራችን ከእስካሁኑ የተሻለ ምርጫ በሰላም ማድረግ መቻሏ ተጠቃሽ ነው፡፡ ተቃዋሚዎች ብዙ ቅሬታ ቢኖራቸውም የምርጫ ቦርድ ገለልተኛነቱን መመስከር ችለዋል፡፡ ጠላቶቻችን ከምርጫ በኋላ ትበትናላችሁ ቢሉንም፣ እኛ ግን ከመቼውም ጊዜ የተሻለ ምርጫ በማድረግ አፋቸውን ማስያዝ ችለናል፡፡

ሦስተኛው የጁንታው የሽብር ቡድን ምክንያት የነበረው የዓለም አቀፍ ጫና መከላከያ ከትግራይ ክልል መውጣት ተከትሎ ጋብ ያለ ይመስላል፡፡ ያም ሆኖ ግን ሴራቸው ቆሟል ማለት አይቻልም፡፡ በክፍያና በጥቅም ትስስር ከሕወሓት ሴል ጋር ተጋምደው ያሉት ሁሉ ውስጥ ለውስጥ ሴራቸውን እየጎነጎኑ እንደሆነ በግልጽ እየታየ ያለ ጉዳይ ነው፡፡

አሜሪካ ሳትቀር ‹‹ሠራዊት በትግራይ እንዲገባ ዳያስፖራው ጠይቆኛል፤›› ብላ የአንዳንድ ጽንፈኛ ዳያስፖራ ጥያቄ የሁሉም ዳያስፖራ ፍላጎት አድርጋ ማሰማቷ፣ ከጀርባ የሚሸረብ ድብቅ ሴራ በአገር ሉዓላዊነት ላይ መኖሩን ማሳየት ጀምራለች፡፡

እንዲህ የአገሩን ህልውና ከውጭም ከውስጥም ሊፈታተን ለመጣ ጠላት በአንድነት በመቆም ‹‹እጅ አንሰጥም›› ማለትና መተባበራችንን ማሳየት ይገባል፡፡ ጀብደኝነት የምናሳይበት ወቅት ማለት አሁን ነው፡፡ አገር ከሌለ ሁሉም የለም ማለት ይቻላል፡፡ ከሶሪያ ጦርነትና ከሊቢያ ውድቀት ብዙ ብዙ ዓይተናል፡፡ አሁን ሁሉም ህልውናውንና ሰላሙን ማስጠበቅ የተጠየቀበት በመሆኑ፣ በምንችለው ሁሉ ቁርጠኛ አቋም ይዘን ልናበረክት ይገባል፡፡

የማንንም ጣልቃ ገብነት ሳንፈቅድ በጥበብና በአንድነት ባካበትነው አርበኝነት መመከት የሁሉም ግዴታ ነው፡፡ ኅብረትና አንደነት ያለው ሕዝብ ማንም ደፍሮ እንደማይነካው ከእኛ ታሪክ በላይ መመርያ የለም፡፡ የአገር አንድነትና ሰላም አስጠብቀን ስናበቃ ከዚያ ዘመቻው ወደ ድህነት ላይ ብቻ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...