Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገር​​​​​​​ባርነት ያረከሰውን ነፃነት አይቀድሰውም!

​​​​​​​ባርነት ያረከሰውን ነፃነት አይቀድሰውም!

ቀን:

በመርሐ ፅድቅ መኮንን ዓባይነህ

አብዝቶ ለጀሮ የሚሻክረው ሰሞነኛው የታምራት ላይኔ የነተበ ንግግር ራሱ ‹ተዓምር› የሚያሰኝ ሆኗል፡፡ እ.ኤ.አ. ጁላይ 28 ቀን 2021 ለዓባይ ሚዲያ ጋዜጠኛ መዓዛ መሐመድ ትመስለኛለች፣ በሁለት ተከታታይ ክፍሎች ሰጥቷል ተብሎ ዩቲዩብ ላይ የተለቀቀውን አስደማሚ ቃለ ምልልስ በአንክሮ ተከታተልኩት፡፡

አረጋዊው ጠቅላይ ሚኒስትር በዚያ ቃለ ምልልሱ፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ ነፃነት ግንባር (ትህነግ) ቀድሞውንም ቢሆን በአሸባሪነት መፈረጅ አልነበረበትም›› ሲል አስደምጦን አረፈው አይደል? ‹‹እናያፍሬ መጡ፣ ማኅበሩን ሊጠጡ››፣ አለች አያቴ፡፡ አንድ ጊዜ ለባርነት ካደርክ እኮ መዳኛ የለህም ጎበዝ!

በጠንካራ ፕሬዚዳንት ሥር ድኩም ጠቅላይ ሚኒስትር

እኔ በበኩሌ እንደ ብዙዎች ሁሉ ታምራት ላይኔን ለወጉ ያህል እንኳ ‹ጠቅላይ ሚኒስትር› ብሎ ለማስታወስና በተከበረ ማዕረጉ ለመጥራት በጣም ይቸግረኛል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ የመለስ ዜናዊ ታማኝ ባለሟል እንጂ፣ እውነተኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር ለማለት አያስደፍርም፡፡ ለአምባገነኑ የሽግግር ወቅት ፕሬዚዳንት ከመላላክና ረቂቅ የውሳኔ ሐሳቦችን አዘጋጅቶ ለፊርማ ከማቅረብ የዘለለ ሥልጣን ያለው ሰው አልነበረም፡፡ ይህንን ሀቅ ካላበደ በስተቀር ራሱም ቢሆን ፈጽሞ አይክደውም፡፡

እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ከእሱ ይልቅ በፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ሥር ያገለግል የነበረው ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስ የተሻለ መብት ነበረው ብዬ አምናለሁ፡፡

ለነገሩ ሕዝብ በቀጥታ የመረጠው ወይም በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የተሰየመ ካልሆነ በስተቀር፣ አንድ ርዕሰ መንግሥት ለራሱ ዓላማ የሾመው የትኛውም ጠቅላይ ሚኒስትር ተብዬ ግለሰብ ቢበዛ የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆኖ ከማገልገል የበለጠና ትርጉም ያለው ሥልጣን እንደምን ሊኖረው ይችላል?

ለዚህ እኮ ነው ብልጣ ብልጡ መለስ ዜናዊ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት ባወጣ ማግሥት፣ ከብዙዎቹ የአፍሪካ አምባገነኖች በተለየ ሁኔታ የፕሬዚዳንትነቱን የሥራ ድርሻ ሲበዛ አኮስምኖ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን በእጁ ያደረገው፡፡

ያም ሆኖ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንበረ ሥልጣኑን በጨበጡ ማግሥት ‹ቀደምት የኢትዮጵያ መሪዎች› ነበሩ ያሏቸውን ጡረተኞች በታላቅ ክብር ጠርተው በቤተ መንግሥት ባስተናገዱበት ወቅት፣ ውለታ ቢሱን ታምራት ላይኔን ጭምር አልዘነጉትም ነበር፡፡

‹‹ታሞ የተነሳ እግዜርን ረሳ›› እንዲሉ ይህ ተጋባዥ እንግዳቸው ነው እንግዲህ ዛሬ ላይ በቴሌቪዥን ብቅ ብሎና ዓይኑን በጨው አጥቦ በለውጡ ጉሮሮ ላይ አጥንት ሊሰኩ፣ በህዕቡም ሆነ በአደባባይ ከሚውተረተሩት ግንባር ቀደም አሸባሪዎች ጋር ለማሴር አብሮ ሲንከላወስ በትዝብት የምናስተውለው፡፡ ‹‹ያዲያቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይለቅም›› አሉ እማ ፈንታ፡፡

ስንት ማንኪያ ‹ታምራት› ላድርግልህ? የዛሬውን አያድርገውና ታምራት ላይኔ በትግል ጓዶቹ የከረረ ግምገማ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ዙፋኑ ወርዶ የተንኮታኮተ ሰሞን፣ በሥልጣን ብልግና ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ይመላለስ በነበረበት ወቅት ‹ስኳር› የሚል ተለዋጭ የተጸውኦ ስም ወጥቶለት ነበር፡፡ እንዲያውም ከዚሁ ስያሜ ጋር በተያያዘ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሚገኘው ኢትዮጵያ ሆቴል በረንዳ ላይ ተሰባስበን ቡና ስንጠጣ ሾካካነት አብዝቶ የሚያጠቃው አንድ መናጢ ጓደኛችን፣ በተሟሟቀው ጨዋታ መሀል ገብቶ የተቀዳልኝን ቡና ስኒ ወደፊቴ እያስጠጋ ‹‹ጋሽ መርሐ ስንት ማንኪያ ታምራት ላድርግልህ?›› እንዳለኝ አስታውሳለሁ፡፡

ሹፈቱ በቶሎ ያልገባኝና ከወደ ገጠሪቱ ኢትዮጵያ የመጣሁት እርጥብ ባላገር ታዲያ በሁኔታው ግራ እንደተጋባሁ የተመለከቱት ሌሎች ሳቢሳ ጓደኞቻችን ወዲያውኑ ቀበል አድርገው፣ ‹‹ስንት ማንኪያ ስኳር ያስፈልግሃል? ማለቱ እኮ ነው አልገባህም እንዴ?›› ባሉኝ ጊዜ፣ አካባቢውን በማያቋርጥ ሳቅና ሁካታ እንደ ቀወጥነው ብዙዎቻችን ዛሬም ድረስ አንዘነጋውም፡፡

ለካስ በያኔው የመዲናችን የአነጋገር ዘዬ ‹ታምራት› ማለት ‹ስኳር› ማለት ኖሯል፡፡ ይታወስ እንደሆን ነውር የማያውቀው የወያኔ ቁንጮ መለስ ዜናዊ ነበር የታምራትን መጠሪያ ስም ሳይቀር ወደ ስኳርነት የቀየረው፡፡

ታምራት ላይኔ ለአስከፊው የወያኔ አገዛዝ አድሮ ለሥርዓቱ ቀጣይነት የግል ሰብዕናውን ሳይቀር በመስዋዕትነት ከማቅረብ ያልተመለሰ መሸ በከንቱ ፍጡር ይመስለኛል፡፡

ያኔ ገና በወጣትነቱ እንኳ በቀልኩበት ለሚለው ገናና ማኅበረሰብ ይቅርና ለራሱና ለቤተሰቡ ቅንጣት ታህል ክብር መስጠት የተሳነው ይህ የድሮ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ እነ አቶ መለስ ከብላቴናነቱ አንስቶ ከጫኑበት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተምህሮ አፈንግጧል በማለት ወንጅለውት ሳለ፣ እርሱ እንደሚለው የቆመለትን ሕዝባዊ ዓላማ ዘንግቶ በከፋ ንቅዘት መበላሸቱንና የኪራይ ሰብሳቢነት ሰለባ መሆኑን በይፋ አምኖ በአደባባይ ሲናዘዝና ለተመለከተው ሁሉ የመጨረሻ መሳለቂያ ሲሆን በጊዜው ሁላችንም አዝነንለት፣ አንዳንዶቻችን ደግሞ አፍረንበት ነበር፡፡

ታዲያ ጨዋታን ጨዋታ ያመጣዋል እንዲሉ ያችን የታምራትን የ‹ተበላሽቼ ነበር› አዋራጅ ኑዛዜ፣ በወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) በአንድ ቀዝቃዛ ምሽት ከመኖሪያ ቤታቸው ሆነው በቀጥታ ቴሌቪዥን የመከታተል አጋጣሚ ነበራቸው፡፡ ዶ/ር ነጋሶ በዓይናቸው በብረቱ የሚያዩትን ለማመን እስኪቸግራቸው ድረስ ራሳቸውን እየነቀነቁ፣ ‹‹ወቸው ጉድ፣ ምን ዓይነት ዘመን ላይ ደረስን እናንተዬ?››… እያሉ አብዝተው ሲደነቁና ሲደመሙ በድንገት ከወደ ጓዳ ብቅ ብለው የተመለከቷቸው የውጭ ዜጋ ባለቤታቸው፣ ‹‹አወይ አለመታደልህ፣ ይህንንም አልነገሩህ እንዴ?›› ሲሉ እንደ ተዘባበቱባቸው በጊዜው ስለመቀለዱ አንድ ሌላ ከይሲ ወዳጄ የሰማውን አጫውቶኛል፡፡

ለመሆኑ  የትሕነግ  በሽብርተኝነት  መፈረጅ  ታምራት  ላይኔን  ለምን  ያን  ያህል አበሳጨው?

ሰውየው በእርግጥ ለዚህ ቁጭቱ መንታ ምክንያቶችን ሲሰጥ አድምጠነው ይሆናል፡፡ እንደ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አስተያየት ከሆነ ትሕነግ በአሸባሪነት ለመፈረጅ የበቃበት አንደኛው ምክንያት አስቀድሞ ለ27 ዓመታት ያህል የመንግሥቱን ሥልጣን ጨብጦ የቆየበትን ዕድልና አጋጣሚ እየተጠቀመ በዜጎች ላይ ሲፈጽመው ከኖረው አረመኔያዊ ግፍና ሰቆቃ የተነሳ፣ በብዙኃኑ ዘንድ አስቀድሞ የተጠላ በመሆኑ ያንኑ ለማጠናከርና እዚያው ላይ ‹‹ሚስማር ለመምታት›› በማሰብ ነው፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በሕግ ማስከበር ስም የሚካሄደው ደም አፋሳሽ ግጭት በሰላማዊ ውይይትና ድርድር ዕልባት ሊያገኝ ይገባዋል ሲል ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት ላይ በጊዜው ሲያሰማ የነበረውን ጩኸትና ይኸው እያሳደረ የመጣውን ጫና ለመቋቋም ያመች ዘንድ፣ ከሽብርተኛ ድርጅት ጋር አልደራደርም የማለት ሰበብ ለማግኘት ነው ሲል የውክልና መላምቱን አስተጋብቶልናል፡፡

መዓዛ ከዚህ አልፋ ጥያቄዎቿን ትንሽ ዘለግ በማድረግ፣ ‹‹ለመሆኑ መጀመርያ በትግራይ ክልል ለተፈጠረውና አሁን አሁን ወደ ሌሎች አጎራባች ክልሎች እየተዛመተ ለመጣው አደገኛ ቀውስ መነሻ ተደርጎ የሚወሰደውንና ከስምንት ወራት በፊት በሰሜን ዕዝ ላይ የሰነዘረውን ወታደራዊ ጥቃት እንዴት ይመለከቱታል?›› ስትል ታምራት ላይኔን ጠይቃው ነበር፡፡

ጉደኛው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ግን በተለመደው ተንበርካኪነቱ ይበልጥ ሲገፋበት ተደምጧል፡፡ ታምራት፣ ‹‹ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰሜን ዕዝ ላይ ተሰንዝሯል የተባለው ጥቃት በእርግጥ ወንጀል አይደለም ብዬ አልከራከርም፤›› ሲል ቀስ በቀስ እየተንኳተተም ቢሆን ወደ እውነታው ለመጠጋት ይሞክር እንጂ፣ ‹‹ዝርዝር ሁኔታው ወደፊት የበለጠ መጣራት ይኖርበታል፤›› ሲል አንዳች ኃፍረት ሳይሰማው በአደባባይ ለማላገጥ ፈጽሞ አልከበደውም፡፡

ይኸው አነጋገሩ አግራሞት የጫረባት በሚመስል ድምፀት ትንታጓ ጋዜጠኛም ቀጠል አድርጋ፣ ‹‹ቡድኑ ጥቃቱን በቀጥታ ራሱ እንደፈጸመው በአደባባይ እያመነ ምኑ ነው የሚጣራው? ማንስ ነው የሚያጣራው?›› በማለት ኮስተር ብላ ባፋጠጠችው ጊዜ መፈናፈኛ ስላጣና ጭራሹን ስለተምታታበት፣ ‹‹ለፍትሕ ሲባል ጉዳዩ በገለልተኛ አካል ሊታይ ይገባዋል ማለቴ ነው እኮ፤›› ሲል በወገናዊነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ ማሰሪያ ውሉ በጠፋበት አነጋገር ሲንተባተብ አድምጠነዋል፡፡ ብራቮ መዓዛ፣ በሙያሽ እደጊ፣ ተመንደጊ ብያለሁ፡፡

እንደ መውጫ

የሽብርተኝነት ወንጀል በፀባዩ ዓለም አቀፍ ወንጀል ከመሆኑም በላይ ዘርፈ ብዙ ደረጃዎች እንዳሉት መታወቅ ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ የሽብርና ተዛማጅ ወንጀሎችን በቀጥታ መፈጸም ብቻ ሳይሆን፣ ይህንኑ ወንጀል በሚፈጽሙ ግለሰቦች ወይም ቡድኖችም ሆነ ሥልጣን ባለው የመንግሥት አካል አማካይነት በሽብርተኝነት ከተሰየሙት ድርጅቶች ጋር በማናቸውም ዓይነት መንገድ መተባበር፣ ወይም እነዚያኑ ወገኖች በአደባባይ መደገፍ፣ ማሞገስም ሆነ ማሞካሸት በራሱ የሚያስጠረጥርና ምናልባትም የሚያስቀጣ ወንጀል ነው፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በአገሪቱ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ተሻሽሎ የወጣውን የሽብርና ተዛማጅ ወንጀሎች መከላከያና መቆጣጠሪያ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 ዓ.ም. አንቀጽ 3 እና አንቀጽ 9 ድንጋጌዎች በዋቢነት ይመለከታል፡፡

ማንም ሰው ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ ወይም ርዕዮተ ዓለማዊ ግቦችን ለማራመድ አስቦ አንድን ሕዝብ ወይም የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ለማስፈራራት ወይም መንግሥት፣ የውጭ አገር መንግሥትም ሆነ ዓለም አቀፍ ድርጅት አንድን የሆነ ተግባር እንዲፈጽም ወይም እንዳይፈጽም ለማስገደድ ወይም በዚሁ አካል ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማሳደር በተወጠነ ዕቅድ በማንኛውም ሰው ላይ ከባድ የአካል ጉዳት ያደረሰ ወይም እንዲደርስ ያደረገ፣ የሰውን ሕይወት አደጋ ላይ የጣለ፣ የጠለፋ ወይም የአፈና ድርጊት የፈጸመ፣ በንብረት፣ በተፈጥሮ ሀብትም ሆነ በአካባቢ ላይ ጉዳት ያደረሰ ወይም ሕዝባዊና ማኅበራዊ አገልግሎትን ከክፉኛ ያስተጓጎለ እንደሆነ የሽብር ወንጀል እንደፈጸመ ተቆጥሮ ከአሥር ዓመት በማያንስና ከ18 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል የአዋጁ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ (1) በማያሻማ ቋንቋ ይደነግጋል፡፡

የተፈጸመው የሽብር ወንጀል በሰው ላይ የሞት አደጋን ያስከተለ፣ ወይም ታሪካዊ ወይም ባህላዊ ቅርሶችን ያበላሸ፣ በንብረት፣ በተፈጥሮ ሀብት፣ ወይም በሕዝባዊ ወይም ማኅበራዊ አገልግሎት አውታሮች ላይ ከፍ ያለ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጉ የተረጋገጠ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ቅጣቱ ከ15 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ በሚዘልቅ ፅኑ እስራት፣ ወይም በሞት እንደሚያስቀጣ የአዋጁ አንቀጽ 3 ንዑስ አንቀጽ (2) በአጽንኦት ያስጠነቅቃል፡፡

ለመሆኑ በተጠቀሰው አዋጅ አንቀጽ 18 ንዑስ አንቀጽ (1) ድንጋጌ ሥር የተመለከቱትን መሥፈርቶች ስለማሟላቱ በሚገባ ተጣርቶ በሽብርተኝነት የተሰየመው የትሕነግ ቡድን፣ የመንግሥቱን ሥልጣን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ በቆየባቸው ድፍን 27 ዓመታት ቀደም ሲል ከተዘረዘሩት አስከፊ ወንጀሎች ውስጥ በአጋጣሚም ቢሆን ያልፈጸመው የትኛውን የወንጀል ድርጊት ይሆን?

ሕጋዊ ሰውነት ያለው ማናቸውም ድርጅት በሽብርተኝነት ሊሰየም የሚችለው ቀድሞ ነገር፣ ‹‹የሽብር ወንጀልን ዓላማው አድርጎ የሚንቀሳቀስ ወይም የዚሁ ድርጅት ሥራ አመራር ወይም ውሳኔ ሰጪ አካል ወንጀሉን በአሠራርም ሆነ በግልጽ የተቀበለው ወይም አፈጻጸሙን የመራ ወይም ተፈጽሟል ተብሎ በሚታመነው ወንጀል ውስጥ፣ በየትኛውም ደረጃ እጁ ያለበት ወይም የተሳተፈ መሆኑ ሲረጋገጥ ወይም በአሠራር ወይም በአፈጻጸም ወንጀሉ የድርጅቱ መገለጫ ሆኖ ሲታይ፣ ወይም አብዛኛው የድርጅቱ ሠራተኞች ወንጀሉን አስቀድመው በሚያውቁበት አኳኋን የሚንቀሳቀሱ እንደሆነ ነው፡፡

በሌላ አነጋገር የድርጅቱ ሥራ አመራር አባላት ወይም ሠራተኞች ወንጀሉን መተዳደሪያ ሙያቸው አድርገው የያዙት መሆኑ ሲታወቅ፣ ወይም ድርጅቱ ወንጀሉን በአሠራርም ሆነ በውጤት ደረጃ በፀጋ የተቀበለው ወይም የራሱ አድርጎ የወሰደው ሲሆን፣ ‹‹የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ያንን ድርጅት በሁለት ሦስተኛ የአብላጫ ድምፅ በአሸባሪነት ሊሰይመው፤›› ይችላል፡፡

በመሠረቱ ሕግ አውጪው ምክር ቤት የአንድን ድርጅት በፍርድ ቤት በኩል በወንጀል መከሰስ ወይም መቀጣት የግድ መጠበቅ ሳያስፈልገው በአሸባሪነት የመሰየም፣ የማፍረስና ሀብቱን መንግሥት እንዲወርስ የመወሰን መብት እንዳለው ጭምር ከወዲሁ መታወቅ ይኖርበታል፡፡

እንግዲህ ከዓባይ ሚዲያ ጋር ያካሄደውን ዝርዝር ቃለ ምልልስ በውል ተከታትሎ የአቶ ታምራትን ትክክለኛ ሥፍራ ለጉዳዩ አግባብነት ባለው በዚሁ የልዩ ወንጀል ሕግ ማዕቀፍ ውስጥ አበክሮ መፈለጉ፣ የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት የቤት ሥራ ይሆናል፡፡ የእኔን እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በሕግ ሙያ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በ1981 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው የሕግ ፋከልቲ ያገኙ ሲሆን፣  በሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በተመድ የሰላም ዩኒቨርሲቲ ጣምራ ትብብር ይካሄድ ከነበረው የአፍሪካ ፕሮግራም በሰላምና በደኅንነት ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በቢሮ ኃላፊ ማዕረግ የርዕሰ መስተዳድሩ ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው በማገልገል ላይ ናቸው፡፡ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...