Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​​​​​​​እነ ነውር ጌጡ!

መንገዱ በጉም ተሸፍኖ ከቦሌ ወደ ፒያሳ ኪሎ ልንጓዝ ነው። ‹‹እስኪ ረጂም መብራት አብራ…›› ወያላውከፊል ከወገቡ በመስኮት ወጥቶ ዓይኑን የጨለመው ጉም ላይ ያፈጣል። ‹‹አጭር ያላበራን ሰዎች በምን አቅማችን ረዥም አብርተን እንደምንዘልቀው እንጃ…›› ትላለች ጋቢና የተሰየመች የቀይ ዳማ። ‹‹ዝም አትይውም? ነገር ሊያመጣብኝ አስቦ ካልሆነ በቀር መቆም ሲገባኝ ረዥም እያበራሁ ብሄድ ለምርመራ መፈለጌ ይቀራል?›› ይላታል ሾፌሩ። ‹‹ጉድ እኮ ነው እናንተ? ጉም በመሆኑ በማብራትህ ማን ነው አንተን ጥፋተኛ ብሎ ለምርመራ የሚፈልግህ? ኧረ እባካችሁ ዝም ብላችሁ በሕዝብ የተመረጠ ስም አታጥፉ?›› ባዩ ደግሞ ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጠ ጎልማሳ ነው። ‹‹አሁን እኔ መንግሥት የሚል ቃል ወጣኝ? ፖሊስ የሚል ቃል ወጣኝ?›› ሲል ሾፌሩ፣ ‹‹የለም! ሐኪም ማለትህ ነዋ…›› አለው ጎልማሳው በነገረኛ አንደበት። ‹‹ጉድ እኮ ነው እናንተ? ማን ነው በሕዝብ የተመረጠው?›› ሲል አንዱ ሾፌሩ ሳቅ እያለ፣ ‹‹አንተ ደግሞ የአራዳ ልጅ አይደለህ እንዴ አረጋጋው እንጂ…›› ብሎ መሀል ሲገባ ነገሩ ረገበ፡፡ በጉም ምክንያት ንትርክ!

ይኼን ጊዜ ወያላው እጁን አፉ ላይ አድርጎ፣ ‹‹ከምንጊዜው ጠብ ጀመራችሁ በፈጣሪ? በቃ እኔ ከሌለሁ ቀጣናው መረጋጋት አይችልም ማለት ነው?›› እያለ ማፌዝ ጀመረ። ‹‹ይልቅ ስላቁን ትተህ እሱን መፋቂያ ወዲያ ጣል…›› ብሎ ሾፌሩ ገላመጠው። ‹‹እንዴ! በገዛ ጥርሴ? በገዛ መፋቂያዬ? በገዛ ድዴ? እንዲህም ደግሞ ተጀመረ?›› ብሎ ጎልማሳውን ሊያግባባ ሲጠቅሰው፣ ‹‹ምን ትጠቅሰኛለህ? ይኼም ያልዳበረው ዴሞክራሲያችን፣ የብሔር ችግራችንንና የዘር ጣጣችንን ነው ብለህ ስድብ ለመጀመር ነው?›› ብሎ አፋጠጠው። ‹‹ኧረ ፍሬንድ ረጋ በል። ቢሆንስ ደግሞ ከመቼ ወዲህ ነው ትችት ስድብ የሆነው?›› ከማለቱ መሀል መቀመጫ ከጎኔ የተቀመጠች ጠይም ቆንጆ፣ ‹‹አላዋቂ ተቺና ገምጋሚ ነኝ ባይ ሁሉ እየተነሳ ፖለቲከኛ ልሁን ካለበት ዕለት አንስቶ…›› አለችው። አዳሜ ይኼን ጎራ ከፍሎ ሽምቅ መጠባጠብን ወዶት ነው ወይስ ትርፍ ይገኝበት ጀምሯል? ዘንድሮ ያለ ትርፍ ስንዝር የሚጓዝ ጠፍቷላ!

በጭጋግ ውስጥ የምታዘግመው ታክሲያችን ሞልታለች። ወያላው ቀልቡን ሰብስቦ ተቀምጧል። ከጎልማሳው ፍጥጫ በኋላ ቀልደኝነቱም ዋዘኝነቱም ርቀውት የቆጠረውን ገንዘብ ደጋግሞ ይቆጥራል። ‹‹ኧረ በቃህ! ነው ወይስ እንቁልልጭ መሆኑ ነው?›› አለው መጨረሻ ወንበር እግሩን ጎማ ላይ ዘርግቶ የተቀመጠ ወጣት።እኔን ነው?” ይላል ወያላው። ‹‹ታዲያ ካንተ ሌላ የቆጠረ አለ? ብሩም እኮ ቶሎ የሚያረጀው አንድም እንዲህ እንዳንተ ቆጥረው የማይጠግቡ ሰዎች አሥር ጊዜ ሲፈትጉት ነው፤›› አለው። ‹‹ካልክስ…›› ብላ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ወይዘሮ ጉሮሮዋን ጠራረገች። ‹‹…ካልክስ አሉልህ ባልዋሉበትና ባልሠሩበት ሥፍራ ጎታቸውን ሞልተው ጥሪታቸውን አካብተው ያልተነቃባቸው። እሱስ እያየነው የሰበሰበውን ነው የሚቆጥረው…›› ስትለው፣ ‹‹እኔ ምለው? ተቆጣጣሪ የሚባሉት የት ሄደው ነው ግን ምድረ ዘራፊ የድርሻውን ይዞ ጠያቂ የሌለው?›› አለች ከጎኗ። ተጀመረ!

 ‹‹እሱን እንኳን እዚህ ታክሲ ውስጥ አይደለም ምክር ቤቱም ግራ የተጋባበት ነገር ሆኗል አሉ። አሉ ነው እንግዲህ። የእኛ አገር ምክር ቤት መቼና እንዴት ግራ እንደሚጋባ በግልጽ መረጃ ባንሰማም…›› አለቻት ወይዘሮዋ መልሳ። ‹‹ይቅርታ አልገባኝም…›› ሲል ጎልማሳው ተጠማዞ ዞሮ፣ ‹‹ይለፈኝ! እኔም ለራሴ የተናገርኩት አልገባኝም…›› ብላ ወይዘሮዋ ሳቀች። ‹‹እሺ መተላለፉ እንዳለ ሆኖ መንግሥት ተረኛ ሌባ ሲፈለፈል ዝም ብሎ የሚያየው እስከ መቼ ነው ተባለ?›› ብላ ከጎኔ የተቀመጠችዋ ስትጠይቅ ደግሞ፣ ‹‹ቅርንጫፉን ትቶ ግንዱን የመንካት ወኔ እስኪያዳብር መሰለኝ። እንጃ ግን መሰለኝ ነው…›› ባዩዋ ጋቢና የተቀመጠችዋ ቀዘባ ናት። ውበትና ነገር ሲጣመሩ ደግሞ አንዳንዴ አላሳልፈን ያለውን መሰናክልዙምያደርጉታል መሰል? ወይስ እንደ አተያያችን ይለያይ ይሆን? ውበትና ትንተና እንደ ተመልካቹ ነው እንዳትሉ ብቻ!

‹‹እንዲያው መኖርን የመሰለ ነገር የለም። የማቱሳላ ዕድሜን ይስጣችሁ…›› ብላ ወይዘሮዋ ወራጅ አለች። በእሷ ምትክ አንድ አዛውንት ተተኩ። ‹‹እስኪ ይታያችሁ በዚህ ኑሮ ላይ የማቱሳላ ዕድሜ ተጨምሮበት…›› ትላለች አጠገቤ የተቀመጠችው። ‹‹ሌላ አንድ ሺሕ ዓመት በኑሮ ውድነት፣ በፍትሕ ዕጦት፣ በጦርነት፣ በመፈናቀልና በእሪታ ልንዘልቅ?›› ይላል መጨረሻ ላይ የተቀመጠ ወጣት። ‹‹ኧረ እባካችሁ ተው ዕድሜ ፀጋ ነው፡፡ አሁን ለምን ኖርኩ ይባላል?›› አዛውንቱ ጨዋታችንን ተቀላቀሉ። ‹‹ምን እናድርግ አባት? በአፈር ቤት የማቱሳላን ዕድሜ መመኘት እንዴት ይሆናል?›› ትላለች ከጋቢና። እንዴ ይኼ ሁሉ ሕንፃ የት ሄዶ ነው የአፈሩ ቤት ጎልቶ ያታያችሁ? የኮንዶሚኒየም ቤት ባለይዞታነታችንን ሳናመሠግን ደግሞ ባለቪላ አንሆንም…›› ብለው አዛውንቱ የልምምጥ ያህል አደብ ግዙ አሉ፡፡ ማን ሰምቶ!

‹‹የለም አባት እያወራን ያለነው መላውን አገር የተመለከተ ጨዋታ ስለመሰለን ነው። ኑሮ ለአንዳንዱ ቦሌና አካባቢውን፣ ለአብዛኛው ግን የጋርይዮሽ ዘመንን ስለሚያስታውስ ነው። አይመስልዎትም?›› አለቻቸው ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተየሰመችው። ‹‹እህ መቼስ ምን ይደረግ ታዲያ? ተማሩ ሲሉን መማር አንወድ። ተደራጁ ሲሉን አይዋጥልን። ተይውና ሌላውን ኮንዲሚኒየም ምዝገባ ስንቱ ሰው ነው በሽማግሌ ተመክሮና ተዘክሮ ሲመዘገብ የኖረው? እኔ ልጄ ኮንዶሚኒየም ቤት ዕጣ ሲወጣልህ በህልሜ ታይቶኛልና ተመዝገብ ስለው ምን እንዳለኝ ታውቂያለሽ?›› ሲሏት ከፊል ገጿን ፈገግታ እየሸበሸበው፣ ‹‹ምን አለዎት?›› አለቻቸው። ‹‹ይገርምሻል ምን እንደታየው አላውቅም፣አይ አባቴ ነገ ማንም ተነስቶ በማን መሬት ላይ እያለ ፉከራ የሚያሰማ ጀብደኛ በሚኖርበት አገር ምን አለፋኝሲለኝ ተናድጄ ነበር፡፡ ለካ እሱ ነብይ ነበር…›› ብለው ተከዙ። ቆየት ብለው፣ ‹‹እንዲህ ነው ይኼውልሽ የእኛ ነገር…›› ብለዋት ሲቆዝሙ ብዙዎች አንገታቸውን ደፍተው ነበር፡፡ ወይ ይኼ ጎዳና!

ጉዟችን ቀጥሏል። ወያላው ሒሳብ ተቀብሎ መልስ እየመለሰ፣ ‹‹መስኮትመስኮት…›› ብሎ ድንገት ጮኸ። ‹‹መስኮት ዝጉ፣ በአዲስ አበባና አካባቢው ያለው ከባድ ቅዝቃዜ አልተቻለም። ወንድም ዝጋው….›› ብሎ መጨረሻ ወንበር ወደ ተመቀጠው ወጣት ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ። ‹‹ምነው ልጄ? በስንት ውጣ ውረድ ያልተበገርን ሰዎች፣ ስንቱን የጠላት ወረራ ድባቅ መተን አሳፍረን ያስመለስን በቅዝቃዜ እናልቃለን ብለህ ፈራህ?›› አዛውንቱ በማስተዛዘን ወያላውን ያዩታል። ‹‹ወደን ሆነ እንዴ የምንሸነፈው? ተገደን እኮ ነው!›› በወዲያኛው ጥግ የተቀመጠ ባለባርኔጣ ወጣት ከመጨረሻ ረድፍ አስተጋባ። ‹‹መቼ ይሆን ድል አድራጊ የምንሆነው?›› ትጠይቃለች መሀላቸው የተየሰመች። ‹‹ምንድነው ሰው የሚያወራው? የተወራው ስለቅዝቃዜ ሆኖ ኳስና ፖለቲካ እየቀላቀሉ መናገር በቃ ፋሽን አደረገው?›› ትለኛለች ከጎኔ። ይኼን ስትል ጎልማሳው ሰማት። እንዴት አይሰማ!

‹‹እኔ ግን ዝም ብዬ ሳስበው ከባዱ ቅዝቃዜ ያለው ፌስቡክ ውስጥ ይመስለኛል፡፡ ይኼ አሁን ያልሽውን ጨምሮ…›› ብሏት አረፈው። ‹‹የቅዝቃዜ ቫይረሱ አስተላላፊዋ ትንኝ ክሊክ ናት እያላችሁ ነው? ኧረ እባካችሁ አሁንም እንደ ዛሬ መቶ ዓመት አናስብ ፕሊስ?›› ባዩዋ ጋቢና የተሰየመችው ናት። ‹‹ኢንፍሉዌንዛ ነው የወባ ወረርሽኝ የተከሰተው?›› ይላል ግራ የገባው ደግሞ። ሲጣራለት ወዲያው መልሶ፣ ‹‹ታዲያ ቅዝቃዜን ከትንኝና ከክሊክ ጋር እዚህ ምን አመጣው?›› ብሎ ይጠይቃል። ሁሉም ዝም። ‹‹አያድርስ! ሲያመን አንስማማ፣ ሲሻለን አንስማማ፣ ደግሞ ብለን ብለን አሁን በቅዝቃዜ ስንወረር ያለ ታሪካችን ያለ ገድላችን መስማማት አቆምን?›› ብለው አዛውንቱ ቢናገሩ ደግሞ፣ ‹‹ኧረ አባባ የቅዝቃዜንና የጦርን ወሬ እየለየን እናውራ እባክዎ። እንኳን ውጊያ ጨምረንበት እንዲሁም የክተት አዋጁ ሥራ አላሠራ ብሎናል…›› ሲል ጎልማሳው፣ ‹‹ለአገር ህልውና ደንታ የሌለው ምድረ ንክኪ እኮ ነው ያስቸገረን፡፡ ሥራ የሚቀጥለው የህልውና ጦርነቱ በድል ሲጠናቀቅ ነው፣ እስከዚያ ግን በአንድ እጅ ማረሻ በሌላ እጅ ጠመንጃ የግድ ነው…›› ስትል ጎልማሳው ጭጭ አለ፡፡ ማን ቀላምድ አለው!

‹‹አሁን ከዚህ ሁሉ ምናለበት ሰላም አስፍነን አገራችንን ብናለማ? አገር ማልማት ይሻላል ወይስ ማውደም?›› ሲሉ አዛውንቱ ነገር አመጡ። ‹‹በየት በኩል ፋዘርወደፊት ሲራመድ አንዱ ወደኋላ ይጎትታል። አንዱ ሲያልም ሊላው ይቃዣል። አንዱ ሲያሟላ ሌላው ያጎድላል። ከዚህ ሁሉ ደግሞ የባሰን ባልተጨበጠ ወሬ እንጀራ ጋጋሪ መብዛቱ ነው። አቤት ስንቱ! ስንቱ!›› ስትል በንዴት የጋቢናዋ ወያላው፣ ‹‹መጨረሻ!›› ብሎ በሩን ከፈተው። ‹‹እንደ አንድ ሆነን የጋራ ራዕይ መቅረፅ ቢሳነን እንዴት እንደ ብዙ መተባበር፣ መቀራረብ፣ መደማመጥ፣ ችግርን ማጥራትና ማጣራት ያቅተናል? በጉንጭ አልፋ ወሬ ሆድ ይሞላል እንዴ? በሐሰተኛ ወሬ አገር ያድጋል እንዴ? ከገዛ ወገን ጋር እየተላተሙ ይዘለቃል እንዴ? በገዛ ወገን ላይ መደንፋትና መሸለል ሥልጣኔ ነው እንዴ? በጋራ ጥረት መገንባት ያለባትን አገር ካላፈረስን እያሉ ማቅራራት ነውር አይደለም እንዴ? በግራ በቀኝም ኧረ እየተስተዋለ? ነውር ጌጥ አይደለም…›› የሚለው የአዛውንቱ ድምፅ ነበር፡፡ መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት