ድምፃዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ምሽት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ገላን ኮንዶሚኒየም አካባቢ በተኮሰው ሽጉጥ ግድያ እንደፈጸመበት ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በሰውና ሰነድ ማስረጃዎች አረጋግጦበታል የተባለው ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ፣ ተባባሪ መሆናቸው የተረጋገጠባቸው ተከሳሾች ከበደ ገመቹ በ18 ፅኑ ዓመታትና አብዲ ዓለማየሁ በስድስት ወራት እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤት ማክሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. ውሳኔ ሰጠ፡፡
የቅጣት ውሳኔውን የሰጠው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ የፀረ ሽብርና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ሲሆን፣ ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ በእያንዳንዳቸው ላይ ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ በመውሰድና ከአገሪቱ ሕግ ጋር በማገናዘብና በመመርመር ነው፡፡
ዓቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ በቀረበው የቅጣት ማክበጃ፣ ተከሳሾቹ ጨለማን ተገን አድርገው ወንጀሉን መፈጸማቸውን፣ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ የባቡር ሐዲድ ብረት በመስረቅ ወንጀል ተከሶ በዋስ እንደወጣ፣ የባጃጅ ሾፌር አስገድዶ አቅጣጫ በማስቀየር አስፈራርቶ በመቀማትና ጭድ ውስጥ ደብቆ ተይዞና ተከሶ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ክሱ መቋረጡን ጠቁሞ፣ የቀደሙ ሁለት የወንጀል ሪከርዶችን እንዳሉበት አስመዝግቦ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በተጨማሪም በመኖርያው አካባቢው ማኅበረሰቡን በማወክ በመጥፎ ባህሪ እንደሚታወቅ አስታውቆ በቅጣት ማክበጃ እንዲያዝለት፣ ተከሳሹ ተልዕኮ ተቀብሎና አስቦበት ድምፃዊ ሃጫሉን የገደለ መሆኑን በማስረዳት በሞት እንዲቀጣም ጠይቆ ነበር፡፡
ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ያቀረበውን የቅጣት ማክበጃ በመቀበል ተከሳሽ ጥላሁን በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ የወሰነ ሲሆን፣ ከቅጣት አወሳሰን መመርያ ቁጥር ሁለት ውጪ በሞት ይቀጣልኝ ሲል ያቀረበውን ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡
ተከሳሽ ከበደ ገመቹ ለቤት መሥሪያ እናቱ በሰጡት ገንዘብ ፈቃድ ሳይኖረው ሕግ ተላልፎ ፈቃድ የሌለው ሕገወጥ ሽጉጥ ገዝቶ ለአንደኛ ተከሳሽ ጥላሁን ያሚ መስጠቱን፣ በዕለቱ መጠጥ ቤት አምሽተው ሃጫሉን ከገደሉ በኋላ ከሕግ ሸሽቶ አዳአ ድሬ ላይ የተያዘ መሆኑን በመጠቆም፣ በቅጣት ማክበጃነት እንዲያዝለትና በቅጣት አወሳሰን መመርያው መሠረት እንዲቀጣ ዓቃቤ ሕግ የቅጣት ማክበጃ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ፍርድ ቤቱም የቅጣት ማክበጃውን በመቀበል ተከሳሹ በ18 ዓመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በአሥር ሺሕ ብር ዋስ በውጭ ሆኖ ሲከራከር የከረመውና በብይን ጥፋተኛ የተባለው ሦስተኛ ተከሳሽ አብዲ ዓለማየሁን ፍርድ ቤቱ ያመበትን ቅጣት እንዲጥልበት በጠየቀው መሠረት፣ ፍርድ ቤቱ በስድስት ወራት እስራት እንዲቀጣ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን የሰጠው ተከሳሾቹ ያቀረቡን ማቅለያ በመያዝ ሲሆን፣ እስራቱም ተፈጻሚ የሚሆነው እጃቸው ከተያዘበት ሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡