ተጨማሪ የዕርዳታ ማቅረቢያ መንገድ እፈልጋለሁ ብሏል
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የሰብዓዊ ጉዳዮችና የአስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ማስተባበሪያ ሥር የሰብዓዊ ዕርዳታ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ማርቲን ግሪፊትዝ፣ በትግራይ በየቀኑ ከ100 በላይ የጭነት ተሸከርካሪዎች የሚያጓጉዙት ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ አስታወቁ፡፡ ይኼንንም ለማድረስ አንድ መንገድ ብቻ ሳይሆን ተጨማሪና አስተማማኝ መንገድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በቅርቡ ይኼንን ኃላፊነት የለቀቁትን ማርክ ኮውኮክን ተክተው በተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የተሾሙት ግሪፊትዝ የሹመታቸውን የመጀመሪያ ጉዞ በኢትዮጵያ ለስድስት ቀናት ያደረጉ ሲሆን፣ ከዚህ መካከል ሁለት ቀናት በትግራይ ቆይታ አድርገዋል፡፡ የመጀመሪያ ጉዟቸውን በኢትዮጵያ ለማድረግ የወሰኑትም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥልቅ የሆነ አጋርነትን ለማሳየትና ተመድ ለኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛነቱን ለመግለጽ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቆይታቸውን ማጠናቀቂያ በማስመልከት ማክሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በትግራይ ክልል አሁንም ድረስ የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ ችግር አለ ብለዋል፡፡ የክልሉ የዕርዳታ ፍላጎት ከፍተኛ ቢሆንም፣ የተፈጠረው ችግር ዕርዳታ ማድረስን አዳጋች አድርጎታል ብለዋል፡፡
በትግራይ ክልል እንዳለ የሚነገረው ሰብዓዊ ቀውስ የተጋነነ ሳይሆን እውነተኛና የተረጋገጠ እንደሆነና ሪፖርት የሚደረገው ያንኑ ምሥል በሚያሳይ ሁኔታ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ለዚህም ከመንግሥት ጋር በቅርበት በመሥራት የዕርዳታ አቅርቦቱን ብቁ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የትግራይ የሰብዓዊ ቀውስ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች እየተዛመተ እንደሚገኝና ከአፋር ክልል 54 ሺሕ ሰዎች፣ ከአማራ ክልል ደግሞ 200 ሺሕ ሰዎች በግጭቶች ሳቢያ መፈናቀላቸውን፣ በእነዚህ አካባቢዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ እንዲቻል ከአማራ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አገኘሁ ተሻገር ጋር ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡
ሆኖም ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ የሚያገለግለው አንድ መንገድ ብቻ መሆኑ፣ እንዲሁም ግጭቱ አሁንም ባለመርገቡ ድጋፉን ለማድረስ አዳጋች እንዳደረገው ያስታወቁት ግሪፊትዝ፣ ወደ ትግራይ ክልል ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ ተጨማሪ መንገድ ማግኘት ያስፈልጋ፤ ብለዋል፡፡ ይሁንና ይኼ መንገድ ከሱዳን ጋር ያለውን ድንበር ለማለት እንደሆነ የተጠየቁት ኃላፊው፣ እንዲህ ያለው መንገድ ዓለም አቀፍ ድንበርን የሚያቋርጥ በመሆኑና ውስብስብ አሠራሮች ስለሚኖሩት የሚያዋጣ እንዳልሆነ በመጠቆም፣ በአገር ውስጥ እንዲህ ያለውን አማራጭ መንገድ ማመቻቸት የግድ ይላል ብለዋል፡፡
ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አውሮፕላኖች የአየር ጉዞ ማድረጊያ ፈቃድ በኢትዮጵያ መንግሥት እንደተሰጠና ረቡዕ ሐምሌ 28 ቀን 2013 ዓ.ም. አንድ አውሮፕላን ተጨማሪ ዕርዳታ ይዞ ወደ ትግራይ እንደሚበር አስረድተው፣ የአየር ትራንስፖርት ውድ ስለሚሆን አስተማማኝ የመሬት ትራንስፖርት ማቅረብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጋቸውንም ተናግረው፣ “ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ ተጨማሪ መንገድ የሚያስፈልግ መሆኑን እንደሚያምኑ ነግረውኛል፤” ብለዋል፡፡
የሚፈለገውን ያህል የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ ባለመቻላቸው የዕርዳታ አቅራቢዎች ጭንቀት ገብቷቸዋል ያሉት ኃላፊው፣ አሁን በትግራይ ክልል ውስጥ ለመንቀሳቀስ አንፃራዊ ነፃነት ቢኖርም አቅርቦት ግን የለም ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ክልል በሚደረገው የሰብዓዊ ዕርዳታ እንቅስቃሴ በግጭት የሚሳተፉ አካላት መካከል መንቀሳቀስ ስለሚጠይቅ ከትግራይ ክልል አስተዳደር ኃላፊዎች ጋር በቅርበት መሥራት ይጠይቃል በማለት፣ “ይኼ ማለት ግን ገለልተኛ ሳንሆን እንቀራለን ማለት አይደለም፣ የትኛውንም ወገን አንደግፍም፤” ሲሉ በቅርቡ በኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበባቸውን ትችት አጣጥለዋል፡፡ ይሁንና የተወሰኑ የድርጅቱ ሠራተኞች ይኼንን የገለልተኝነት ሕግ ጥሰው ከተገኙ፣ ሪፖርት ሊደረግላቸው እንደሚገባና አጣርተው ዕርምጃ እንደሚወስዱ አስታውቀዋል፡፡
ኢትዮጵያ መንግሥት በቅርቡ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮችና የአስቸኳይ ረድኤት አቅርቦት ማስተባበሪያ ሥር፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ትክክለኛ ያልሆኑ መረጃዎችን በማሠራጨትና የሕወሓትን ኃይል የትግራይ መከላከያ ሠራዊት ብሎ በመጥራት ጥፋት እየፈጸመ ነው ሲል መክሰሱ ይታወሳል፡፡
ነገር ግን ጥፋተኞችን ለይቶ ማቅረብ ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊው፣ አጠቃላይ ውንጀላ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሠራተኞች አደጋ ላይ እንዲወድቁ ያደርጋል ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡ እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት መሥራት እንደሚፈልጉ፣ ለዚህም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሁሉም ሚኒስትሮች መልካም ምላሽ እንደሰጧቸው ተናግረዋል፡፡