የፋይናንስ ደኅንነት ማዕከልና ፌዴራል ፖሊስ በጋራ ባደረጉት ምርመራ፣ በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር የተጠረጠሩ ባለሀብቶች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተሰማ፡፡ ምርመራው በስፋት መቀጠሉም ታውቋል፡፡
የፋይናንስ መረጃና ደኅንነት ማዕከል ጤናማ ባልሆኑ የንግድና የባንክ ሒሳብ እንቅስቃሴ ላይ ተመሥርቶ ባደረገው ምርመራ በንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ነጋዴዎች የሚሳተፉበት ሰፋ ያለ ሕገወጥ የብርና የውጭ ምንዛሪ ዝውውር ቡድንን መለየቱን፣ ያሰባሰበውንም መረጃ መሠረት በማድረግ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመር ለፌዴራል ፖሊስ ማስተላለፉን የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በፋይናንስ ደኅንነት ማዕከል በተደረገው ምርመራ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ተሳትፎ አድርገዋል ተብለው የተጠረጠሩት አብዛኞቹ ግለሰቦች በአስመጪና ላኪ የንግድ ዘርፍ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች መሆናቸውን፣ የተወሰኑትም በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚሳተፉ እንደሆኑ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ማክሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. አመሻሽ ላይ የፌዴራል ፖሊስ ባወጣው መግለጫ ከአዲስ አበባ እስከ ቶጎ ጫሌ በተዘረጋ ሕገወጥ የውጭ ምንዛሪና የገንዘብ ዝውውር ኔትወርክ ውስጥ ተሳትፎ ሲያደርጉ ነበር ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ሲጠቀሙባቸው ከነበሩ ሰነዶችና በርካታ ገንዘብ ጋር በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አስታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹ ከሕወሓት ቡድን ጋር ሥውር ግንኙነት እንደነበራቸው፣ የተፈጠረው ኔትወርክም የሚንቀሳቀሰው ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር ለሕወሓት ቡድን ሲደርስና ሲደግፍ እንደነበረ መግለጫው አመልክቷል፡፡
‹‹የሕወሓት ቡድን ቀድሞ በሠራው ኔትወርክ በንግድ ተቋማት የሚሰበሰበውን የውጭ ምንዛሪ በሕገወጥ መንገድ ከአገር እንዲወጣ በማድረግ፣ ለሽብር ቡድኑ ዋነኛ የፋይናንስ ምንጭነት ሲያገለግልና ከአዲስ አበባ ዶላር ከጥቁር ገበያ እየሰበሰበ መንግሥት እንዲዳከምም ሲሠራ ነበር›› ብሏል፡፡
ፖሊስ ከወንጀል ድርጊቱ ጋር ቀጥተኛ ተሳትፎ አድርገዋል ያላቸውን ስድስት ዓለም አቀፍ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች፣ 11 ግለሰቦች፣ በ15 የባንኮ ሒሳቦች አሥር ሚሊዮን 276 ሺሕ ብር ከ100 በላይ የባንክ ደብተሮች ጋር በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ መጀመሩን አስታውቋል።
በቁጥጥር ሥር የዋለው ቡድን በአዲስ አበባ ሕጋዊ አሠራርን ሽፋን በማድረግ መንግሥት እንዲዳከምና ከውጭ ወደ አገር ውስጥ ለሚያስገባቸው ጥሬ ዕቃዎች የውጭ ምንዛሪ እጥረት እንዲያጋጥመው፣ እንዲሁም የኑሮ ውድነትን አባብሶ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲነሳ ለማድረግ እየሞከረ እንደነበር የፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡