Saturday, May 25, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያላቸው የአረም ኬሚካሎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው...

ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ያላቸው የአረም ኬሚካሎች ወደ አገር ውስጥ ገብተው እየተሠራጩ እንደሆነ ተገለጸ

ቀን:

የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በተያዘው የምርት ዘመን የሚደርሱ ሰብሎችን ከአረም ለመከላከል የሚያስችለውን ኬሚካል፣ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ወደ አገር ውስጥ በማስገባት እያሠራጨ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡

ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደ ማርያም ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የሰብልን ምርታማነት ውጤታማ ከሚያደርጉ ጉዳዮች አንዱ የአረም ኬሚካል በመሆኑ ኮርፖሬሽኑ በተያዘው የበጀት ዓመት ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ኬሚካልን በአየርና በመርከብ ወደ አገር ውስጥ እያስገባ ነው፡፡

በተያዘው የክረምት ወቅት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሰብል ዝርያዎች  እየበቀሉ ስለሆነ ትልቁ ጉዳይ አረምን መከላከል እንደሆነ ያስታወቁት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህንን ሥራ ለማገዝ ለአገልግሎት የሚውሉ የአረም መከላከያ ኬሚካሎች በበቂ መጠን እየገቡና በክልሎች አማካይነት ወደ የተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች  እየተሠራጩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በአገሪቱ በተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ እዚህ ግባ የማይባሉ ትራክተሮችን ኮርፖሬሽኑ አምጥቶ እንዳከፋፈለ ያስታወቁት አቶ ክፍሌ፣ ከዚያ ይልቅ የመለዋወጫ ዕቃዎችን የማከፋፈል ሥራ በስፋት እንደተከናወነና በተያዘው የበጀት ዓመት ግን 58 ትራክተሮች ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተገዝተው እየገቡ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከአጭር ጊዜ አንፃር የተጠናቀቀውን የበጀት ዓመት የተመለከተ ግምገማ አድርጎ  በዓመቱ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ያመላከተ ውጤት እንደተገኘ ያስታወሱት አቶ ክፍሌ፣ ይህም ኮርፖሬሽኑ የልማት ድርጅት በመሆኑ የልማት ወጪውን ሸፍኖ ከፋይናነስ ስኬታማነት አንፃር ከዕቅዱ በላይ መፈጸሙን አስታውቀዋል፡፡

የልማት ክፍተቶችን እየሞሉ ከማስቀጠል አንፃር መሠረታዊ መደላድል ሊፈጥሩ የሚችሉ ሥራዎች መከናወናቸው ተገልጿል፡፡ ይህም የሰው ኃይል፣ የማሽን፣ የመሬት ምርታማነትን ከማሻሻልና ከማሳደግ ጋር ተያይዞ ቁልፍ ችግሮች በጥናት መለየት እንደተቻለ ተገልጿል፡፡ በተለይም በኮርፖሬሽኑ እጅ ያሉ መሬቶች ችግራቸው ምንድነው? የሚለው ላይ ጥናት ተደርጎ በቀጣይ የመሬት ለምነት እያነሰ የሚሄድባቸው ቦታዎች ላይ ተገቢውን የግብርና ቴክኖሎጂ በመጠቀም፣ መሬት እንዳይታጠብ የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንደሚገባ በዝርዝር እንደተመከረበት አስታውሰዋል፡፡

አቶ ከፍሌ እንዳስታወቁት አብዛኛው በኮርፖሬሽኑ እጅ የሚገኙ መሬቶች አሲዳማነት የሚስተዋልባቸው ስለሆኑ፣ ይህንን በላይም ስቶን አክሞ ለማስወገድ የተወሰኑ ሔክታሮች ላይ የሙከራ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ከግብርና ማሽን ጋር በተገናኘም ማሽኖች ተጠግነው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆን ስላላባቸው ባለሙያዎችን ከማሠልጠን ባለፈ ከትራክተር አንስቶ እስከ ኮንባይነሮችና የምርት ግብዓት ማጓጓዣ መኪኖች ዝግጁ እንዲሆኑ፣ የጥገና ሥራዎች በ2014 ዓ.ም. የዝግጅት ምዕራፍ እየተሠሩ እንደሆነ አቶ ክፍሌ ተናግረዋል፡፡

የዘር ብዜት በሚከናወንባቸው አካባቢዎች በተለይም በአንዳንዶቹ የዝናብ እጥረት አጋጥሞ እንደነበር ያስታወሱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ሆኖም አብዛኞቹ ቦታዎች ላይ ብቅለታቸው መልካም እንደሆነና ኮርፖሬሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ቦንጋ አዲስ ባገኘው 1,070 ሔክታር መሬት ላይ ወደ 273 ሔክታር እየተዘራ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በአካባቢው ያልተሞከሩ ሰብሎችን ጭምር እየተሞከሩ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡

ከግብርና ግብዓት አቅርቦት ሥርጭት አንፃር ከትግራይ ክልል ውጪ በሌሎች አከባቢዎች ግብዓቶችን የማሠራጨት ችግር እንደሌለ ያስረዱት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ቀደም ሲል ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመሆን የተወሰኑ ግብዓቶች ቢገቡም በዚህ ወቅት ባለው ሁኔታ ግን ወደዚያ አካባቢ መግባት አስቸጋሪ እንደሆነና በተቀሩት ክልሎች ግን ቀድሞ ሥራዎች እንደተጠናቀቁ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...