Tuesday, February 27, 2024

አወዛጋቢዋ ሰማንታ ፓወር በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በ2011 ዓ.ም. ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ፌሽታን፣ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ደግሞ በተለይም በምዕራባውያኑ ዘንድ ከፍተኛ ዝና በማትረፍ የዓለማችን ትልቁን የሰላም ኖቤል ሽልማት አግኝተዋል፡፡

እያደር እየዋለ በተለይም ጥቅምት 24  ቀን 2013 ዓ.ም. ሕወሓት ከ20 ዓመታት በላይ በትግራይ ክልል የቆየው የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸሙ፣ የፌደራል መንግሥት የሕግ ማስከበር ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ ከጀመረ በኋላ ከምዕራባውያን በተለይም ከአሜሪካ ጋር ያለው ግንኙነት መሻከር ጀመረ፡፡ ከተለያዩ አገሮች መንግሥታትም ሆነ ተቋማት በጉዳዩ ላይ ለመምከርና ሁኔታውን ለማየት ወደ አገር ቤት እየመጡ ከኢትዮጵያ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረው ከተመለሱ በኋላ፣ ለወከሏቸው አገሮችና ተቋማት ስለኢትዮጵያ የሚያቀርቧቸው ሪፖርቶች በተቃራኒው እየሆኑ የበለጠ ቅራኔ እንጂ የተሻለ የዲፕሎማሲ ትርፍ ማግኘት እንዳልተቻለ፣ በተለያዩ ጊዜያት የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ለአብነትም አዲስ የተሾሙት የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ አምባሳደር ጄፍሪ ፊልትማን በግንቦት ወር መጀመርያ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ውይይት ካደረጉ በኋላ፣ ከአሜሪካ መንግሥት በኩል እየመጣ ያለው ጫናና ግፊት በርትቷል፡፡

ወደ አፍሪካ ቀንድ ጉዟቸውን ከማድረጋቸው አስቀድሞ ከፎረን ፖሊሲ መጽሔት ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረጉት ፊልትማን፣ ‹‹የኢትዮጵያ ቀውስ ከተባባሰ የሶሪያን ቀውስ የልጅ ጨዋታ ያስመስለዋል፤›› በማለት ተናግረው የነበረ ሲሆን፣ ከጉብኝታቸው በኋላ ደግሞ በአገሪቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ላይ አገራዊ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ በማስመር፣ የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ክልል መቆየቱ ግን ለዚህ እንቅፋት ይሆናል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ግንቦት 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ በትግራይ ክልል ያለው የንፁኃን ሞትና ከ5.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት ውስንነት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያሳስበው ገልጸው ነበር፡፡

በተጨማሪም የፈደራል መንግሥት የኤርትራና የአማራ ክልል ወታደሮችን ከትግራይ ክልል እንዲያስወጣ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናት በትግራይ ክልል ተፈጽሟል የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲያጣሩ ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ቀውስ እንዲፈጠርም ሆነ እንዲወሳሰብ በማድረግ ተጠያቂ ናቸው ባላቸው ግለሰቦች በሥራ ላይ ባሉና በቀድሞዎቹ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታት ባለሥልጣናት፣ የወታደራዊና የደኅንነት አባላት፣ እንዲሁም የአማራ ክልል አመራሮችና መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ የሕወሓት አባላት ላይ የቪዛ ዕቀባ እንዲደረግ ያሳወቀው ግንቦት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር፡፡

ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው የመልስ መግለጫ የቪዛ ዕቀባውና ተያያዥ ውሳኔ የሁለቱን አገሮች የቆየ ወዳጅነት የሚሸረሽር መሆኑን ገልጾ፣ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት መልሳ እንድትፈትሽ የምትገደድ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ግንቦት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣው የብሔር ክፍፍል በእጅጉ ያሳስበኛል በማለት፣ በትግራይ ክልል የሚታየው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ፆታዊ ጥቃት ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ሊቆም እንደሚገባ የኢትዮጵያን መንግሥት አሳስበዋል፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሊንዳ ግሪንፊልድ ሰኔ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በፀጥታው ምክር ቤት በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ ቀርበው በተናገሩበት ወቅት መንገዶች እንዲከፈቱ፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ እንዲቀርብ፣ እንዲሁም ግጭት ውስጥ የገቡ አካለት እንዲነጋገሩና ጦርነቱ እንዲቆም እንፈልጋለን ማለታቸው ይታወሳል፡፡

እነዚህንና መሰል ጫናዎች በበረቱበት በዚህ ጊዜ የፌደራል መንግሥት ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ ክልል ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ወዳጆች ሲቀርቡ የነበሩ የመፍትሔ ሐሳቦችን የፌደራል መንግሥት ሲያጤናቸው መቆየቱን በመግለጽ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በተከታታይ ያቀረበውን ጥያቄ መንግሥት ከተለያዩ አቅጣጫዎች በመመልከት የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉን ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡

ይሁን እንጂ የተናጠል ተኩስ አቁሙን ያልተቀበለው በአሸባሪነት የተፈረጀው ሕወሓት በአማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎችን አልፎ በበርካታ አካባቢዎች ትንኮሳዎችን እንደሚያደርግ በተለያዩ ጊዜያት እየተናገረ የሚገኝ ሲሆን፣ በተመሳሳይም የአማራ ክልል መንግሥት ራስን በማዳን የህልውና ዘመቻ የሚለውን የአፀፋ ውጊያ በሁለቱ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች የተለያዩ ክልሎች ልዩ ኃይል አባላትን በማሠለፍና የክልሉን ሕዝብ የክተት ዘመቻ በመጥራት ዘመቻ ላይ ይገኛል፡፡

በዚህ የጦር ቀጣና ውስጥ ከለጋሽ ድርጅቶችና ከኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ ክልል ሕዝብ መድረስ የነበረበት የዕለት ደራሽ ምግብ አቅርቦት በአግባቡ እንዳይደርስ፣ በአፋር ክልል በኩል የሕወሓት ታጣቂዎች ተሽከርካሪዎች እንዳይተላለፉ እያደረጉ መሆኑን ከሰሞኑ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡

በዚህ ሁሉ ወጀብ ውስጥ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (usaid) ኃላፊ አወዛጋቢዋ  ሰማንታ ፓወር  የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናትን በማነጋገር በትግራይ ክልል ረሃብን ለመከላከል ያልተገደበ የሰብዓዊ ረድኤት ተደራሽነት እንዲፈቀድ ጫና ለመፍጠር፣ እንዲሁም በሌሎች በግጭት በተጎዱ የኢትዮጵያ አካባቢዎች አጣዳፊ ችግር ላይ ላሉ ሰዎች መድረስ የሚቻልበት መንገድ እንዲመቻች ለመነጋገር በሚል ምክንያት አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡

በ44ኛው የአሜሪካ  ፕሬዚዳንት  ባራክ  ኦባማ  የሥልጣን  ዘመን  የመንግሥታቱ ድርጅት  28ኛዋ  የአሜሪካ  ቋሚ  አምባሳደር  የነበሩት  50 ዓመቷ ጋዜጠኛ፣ የውጭ ፖሊሲ አማካሪና  የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ በመባል የሚታወቁት ሰማንታ ፓወር በሱዳንናኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የአምስት ቀናት ጉበኝት ቅዳሜ ሐምሌ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. በሱዳን ነበር የጀመሩት፡፡

በፕሬዚዳንት ኦባማ ዘመን ለስምንት ዓመታት ባገለገሉበት ጊዜያት የአሜሪካ መንግሥት በተለያዩ አገሮች ውስጥ በሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት ስም ጣልቃ እንዲገባ፣ ተከራካሪና ወትዋች እንደነበሩ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

በፕሬዚዳንት አባማ ዘመን በነጩ ቤተ መንግሥት በነበራቸው ቆይታአሜሪካ መንግሥት ለሰብዓዊነት ሲባል በተለያዩ አገሮች ውስጥ ግጭት ሲከሰት የመግባት ግዴታ እንዳለባት፣ እንዲሁም የወታደራዊ የኃይል ዕርምጃን በከፍተኛ ሁኔታ ከሚደግፉ አማካሪዎች ውስጥ ጎልቶ ስማቸው ይነሳል፡፡ ለአብነትም በሊቢያና በሶሪያ የተደረገውን የአሜሪካን መንግሥት ጣልቃ ገብነት በመደገፍ ይታወቃሉ፡፡

ይሁን እንጂ  በፕሬዚዳት ጆ ባይደን የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ሆነው የተሾሙት  ሰማንታ ፓወር በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝት ከተሰማ በኋላ፣ ጉብኝቱ ምን ዓይነት አንድምታ አለው በሚል ኢትዮጵያውያን በሁለት ጎራ የተከፈሉ ሐሰቦች ሲያንፀባርቁ ተስተውለዋል፡፡

ለአብነትም ከሚንፀባረቁ ሐሳቦችም መካካል የኃላፊዋ ጉዞ የኢትዮጵያ መንግሥትን በሱዳን በኩል የሰብዓዊ ድጋፍ መተላለፊያ መስመር እንዲከፈት ጫና ለማሳደር መሆኑን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ቅደመ ሁኔታዎችን እንዲቀበል ለማግባባትና በሰብዓዊ ዕርዳታ ሰበብ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት ፍላጎት መኖሩን ሐሳቦች ሲሰነዘሩ ተስተውሏል፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊት የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በትዊተር ገጻቸው በአሁኑ ወቅት ቀውስ ውስጥ ያሉ እንደ ኢራቅ፣ የመን፣ ሊቢያና ሶማሊያ ባልጠበቋቸው ምክንያቶች እዚህ ቀውስ ውስጥ እንደገቡ በመጥቀስ በአሁኑ ወቅት በትግራይ ረሃብ ተከሰተ በሚል አዲስ ትርክት በመፍጠር፣ ኢትዮጵያንና የአፍሪካ ቀንድን ለመበታተን የተጀመረ ሴራ መሆኑን በመጠቆም የዚህ ዓይነቱ መንገድ ሊቆም እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በተመሳሳይ ከሦስት ቀናት በፊት የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በትዊተር ገጻቸው፣ ኢትዮጵያውያን በድምፃቸው መምረጣቸውን፣ ከጀርባ ሆኖ የመንግሥት ሥርዓት ለመቀየር መጎንጎን ለኢትዮጵያውያን ንቀት ነው በማለት የሚዲያ ተቋማት እውነታውን ሊዘግቡ ይገባል ሲሉ አጠር ያለ ጹሑፍ አሥፍረዋል፡፡

የአሜሪካ መንግሥት መልዕክተኛዋ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣታቸው እየተሰሙ ያሉ የተደበላለቁ ስሜቶች ምን አንድምታ ይኖራቸዋል ሲል ሪፖርተር የተለያዩ ምሁራንን አነጋግሯል፡፡

በስትራቴጂክ ጉዳዮች ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ዳርእስከዳር ታዬ (ዶ/ር)፣ ሰማንታ ፓወር ምንም ዓይነት ተፅዕኖ ፈጣሪ ቢሆኑም፣ የአሜሪካን መንግሥት ውሳኔዎች በአንድ ሰው ብቻ የሚወሰኑ ባለመሆናቸው የሚሰማው ሁካታ ለአሜሪካ ኤምባሲ የሕዝብ አስተያየቶችን ለመዳሰስና ኢትዮጵያውያን ለአሜሪካ ያላቸውን አመለካካት ለመገምገም ከመጥቀም ባለፈ ፋይዳው ብዙም እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡

 ነገር ግን የመልዕክተኛዋ ጉዳዩ የከፋ ሊሆን የሚችለው ከዚህ በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፊሪ ፊልትማን ያደረጉት ጥረት ሲታይ ከዚያ አንፃር ምንም መሻሻል እንደሌለ ዓይተው ሪፖርት የሚያደርጉ ከሆነ፣ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገው ጫና ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በዚህም የተነሳ መሬት ላይ መሆን ያለበት ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እንደሚስተጋባው መተረማመስ ሳይሆን፣ መንግሥት የራሱን የሆነ እውነታ ይዞ ማስረዳትና መግለጽ የበለጠ አትራፊ ያደርጋዋል ብለዋል፡፡

ሰማንታ ፓወር ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ከበርካታ የመረጃ ምንጮች ስለጉዳዩ ተረድተው ስለሚመጡ፣ እንደ አገር የራሳቸው የሆነ ሥጋትና ፍላጎትም ስለሚኖራቸው በኢትዮጵያ በኩል ትክክለኛውን ነገር መግለጽ ከተቻለ መግባባት ላይ እንደሚደረስ ጠቁመዋል፡፡

የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት መንግሥትን ከሕወሓት ጋር ተደራደር የሚል  ሐሳብ በቀጥታ ሊያቀርቡ ባይችሉም እንኳን፣ መንግሥት ችግሩን በአጭር ጊዜ የማይፈታ ከሆነ ተገዶም ቢሆን ወደ ድርድር መግባቱ አይቀርም ብለዋል፡፡

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ እንዳለ ንጉሤ (ዶ/ር)፣ ከአሜሪካ ተልከው የመጡት ሰማንታ ፓወር እንደ ማንኛውም ጊዜ ወደ የትኛውም አገር ሲሄዱ የሚጠበቀው ዋነኛ ነገር፣ የአሜሪካን ፍላጎትና ጥቅም እንደሚያስጠብቁ ታስቦ መሆኑን መረዳት ይገባል ይላሉ፡፡

ነገር ግን በአፍሪካ ቀንድ ቀይ ባህር አካባቢ የአሜሪካን ጥቅምም ሆነ የአካባቢውን ሰላም ከማስጠበቅ አንፃር፣ በታሪክም ሆነ በታላቅነቷ የኢትዮጵያን ያህል ሚና ሊወጣ የሚችል አገር እንደሌለ እነሱም ያውቁታል ብለዋል፡፡

በአሜሪካ የዲፕሎማሲ ታሪክ ዴሞክራቶች በውጭ ጉዳያቸው ላይ የሚያሳልፏቸው ውሳኔዎችና የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ብዙ ጊዜ በማተራመስ ላይ ያተኮሩ እንደሆኑ በመጥቀስ፣ ብዙውን ጊዜ ዴሞክራቶች የፖለቲካ ግላዊነት የሚታይባቸውና በደላላ የተሞላ አልፎ አልፎም ከአሜሪካ ጥቅም ጋር የሚጋጭ ተግባር ውስጥ ገብተው እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

‹‹ለአብነትም በቅኝ ግዛት አስተሳሰብ ሠርተው ያመጡት የሕወሓት ቡድን ኢትዮጵያውያን በአንድ ላይ ሲቆሙበት ሲያዩ፣ አሜሪካንና የተቀሩት ምዕራባውያን አይዋጥላቸውም፡፡ ስለዚህም የተከፋፈለች አገር ለማየት ይህን በአሸባሪነት የተሰየመ ድርጅት ለመደገፍ ይንቀሳቀሳሉ፤›› ብለዋል፡፡

መጀመርያ ላይ ምርጫ አታካሂዱ ብለው መናገራቸውን የገለጹት እንዳለ (ዶ/ር)፣ አንድ የዴሞክራሲ አቀንቃኝ ነኝ ከምትል አገር ይህ መሰማቱ የዲፕሎማሲ ቀውስ ነው በማለት ይገልጹታል፡፡ ‹‹በመሆኑም አሜሪካኖች ከቢላደን ጋር እንዳልተደራደሩ ሁሉ፣ ከሕወሓት ጋር ተደራደሩ ይላሉ የሚል እምነት የለኝም፤›› ብለዋል፡፡

ሰማንታ ፓወር ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ዋነኛ ኃላፊነታቸው የወከላቸውን አገር ወይም መንግሥት በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ በበኩሏ ባላት የውጭ ጉዳይ መርህና ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመሥርታ መነጋገር አለባት ያሉት ደግሞ በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መመህሩ አቶ ዓለሙ አራጌ ናቸው፡፡

በመሆኑም የአሜሪካ ልዑኳ በቀደመ ታሪካቸው ምንም ዓይነት ስምና ዝና ቢኖራቸውም፣ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለማየት ስትመጣ በእርግማን ወይም በምርቃት ሳይሆን በመርህ ደረጃ ቁጭ ብሎ በመነጋገር እንደሆነ አቶ ዓለሙ አስረድተዋል፡፡

በሰማንታ ፓወር መምጣት መልካም አጋጣሚምና መሰናክሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ በመግለጽ፣ ‹‹ለዚህ ሁሉ ችግር መንስዔዎቹ ግን የውስጥ ጉዳዮቻችን በመሆናቸው አሁንም በውስጥ ጉዳይ ከመከፋፈል ጠንካራ የሆነ ማንነት መገንባቱ አሸናፊ ያደርጋል፤›› ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከአሜሪካ ተወካይ ሲመጣ የግድ እኔን ውደዱ ሳይሆን ያለውን የመረጃ ክፍተት በመሙላት፣ እንደ መንግሥት ሊኖሩ የሚችሉ ዕድሎችን መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ አሳስበዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር በመሆኗ ገና አዲስ ሰው ሲመጣ በመደነጋገርና በዘመቻ ሐሳብን ማስቀየር እንደማይቻል የገለጹት አቶ ዓለሙ፣ ከዚህ በተሻለ ኢትዮጵያ የትኛውንም አገራዊ ጉዳይ ልታከናውን የሚገባው ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን ለአገራዊ ጥቅም አስፈላጊ ናቸው ተብለው የሚታመንባቸው ጉዳዮች ድርድርንም ጨምሮ፣ መንግሥት በራሱ ያለ ሦስተኛ ወገን ሊያደርግ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡

የአሜሪካ ዴሞክራቶች ከውስጥ ጉዳያቸው በበለጠ ዓለም አቀፍ ጉዳያቸው የጎላ በመሆኑ የተለያዩ ተቋማትን በመጠቀም በአገሮች ላይ ጉዳያቸውን የማስፈጸም ጫና እንደሚያሳድሩ የገለጹት አቶ ዓለሙ፣ አሜሪካ ምንም ዓይነት ነገር ልታመጣ ብትችል እንኳ ነገሩ ሊመዘን የሚችለው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና የአገረ መንግሥቱ ህልውና ላይ ተመሥርቶ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -