ዘመን ባንክ የቦርድ ሰብሳቢ መረጠ
አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክን በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ በቆዩት አቶ ጌታቸው ሰለሞን ምትክ አዲስ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት መሰየሙ ሲገለጽ፣ ዘመን ባንክ የቀድሞን የባንኩን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሚያስ እሸቱን የቦርድ ሰብሳቢ ሆነው እንዲያገለግሉ መርጧል፡፡
የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አድርጎ በአቶ ጌታቸው ምትክ የሰየማቸው አቶ ዳንኤል ተከስተን ሲሆን፣ አቶ ዳንኤል የባንኩ ፕሬዚዳንት ሆነው እስከተሰየሙበት ድረስ የባንኩ የቢዝነስ ስትራቴጂ ሞደርናይዜሽን ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው፡፡
እንደ ምንጮች ገለጻ፣ አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በፕሬዚዳንትነት ሲያገለግሉ በቆዩት አቶ ጌታቸው ከኃላፊነታቸው የለቀቁት በገዛ ፈቃዳቸው ነው፡፡ ሆኖም ከባንኩ አካባቢ የተገኘው መረጃ ደግሞ አቶ ጌታቸው ምትክ አዲስ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት የተሰየመው አቶ ጌታቸው ረዥም ዕረፍት ከመውጣታቸው ጋር የተያያዘ መሆኑን የሚጠቁም ነው፡፡ ምንጮቻችን ግን አቶ ጌታቸው ኃላፊነታቸውን የለቀቁት በተደጋጋሚ ባቀረቡት የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ መሠረት የባንኩ ቦርድ ጥያቄያቸውን ተቀብሎ ያሰናበታቸው መሆኑን ነው፡፡
አቶ ጌታቸው ከአንድ ዓመት በፊት ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው ቦርዱ የተወሰነ ጊዜ እንዲሠሩ ስላግባባቸው ኃላፊነቱን ይዘው ቆይተው ነበር፡፡ ሆኖም በድጋሚ ይህንኑ የሥራ የመልቀቂያ ጥያቄ በማቅረባቸው ቦርዱ ጥያቄያቸውን ሊቀበል በመቻሉ ነው፡፡
ዘመን ባንክም አዲስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ሰይሟል፡፡ አዲስ የተመረጠው የዘመን ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ የመረጣቸው የቀድሞውን የባንኩን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ኤርሚያስ እሸቱን ነው፡፡ አቶ ኤርሚያስ የዘመን ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተሰየሙት እስካሁን ባንኩን በቦርድ ሰብሳቢነት ሲያገለግሉ የቆዩትን ፕሮፌሰር አበበ ድንቁ (ዶ/ር/ኢንጂነር) ተክተው እንዲያገለግሉ ነው፡፡
ዘመን ባንክ በታኅሳስ 2013 ዓ.ም. ባደረገው የዳይሬክተሮች ቦርድ ምርጫ አዲስ የተመረጡት የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት አቶ ኤርሚያስን የቦርድ ሰብሳቢ አድርገው ከመሰየማቸው ባሻገር ምክትል ቦርድ ሰብሳቢም እንደመረጠ ታውቋል፡፡ የባንኩ አዲሷ ምክትል ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡት ወ/ሮ እንዬ ይመር ናቸው፡፡
አቶ ኤርሚያስ ከዘመን ባንክ መሥራች አባላት መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ ባንኩን በምክትል ፕሬዚዳንትነት አገልግለው እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከዘመን ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ከለቀቁ በኋላም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ማገልገላቸውም ይታወሳል፡፡ በአቶ ኤርሚያስ የቦርድ ሰብሳቢነት የሚመራው አዲሱ ቦርድም ከቀድሞው ቦርድ ኃላፊነቱን ተቀብሎ ሥራ መጀመሩም ታውቋል፡፡
ዘመን ባንክ በኢንዱስትሪው ውስጥ አሥር ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በ2013 የሒሳብ ዓመት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት 1.45 ቢሊዮን ብር አትርፏል፡፡
ባንኩ በ2013 መጨረሻ ላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ወደ 19 ቢሊዮን ብር የብድር ክምችቱ ደግሞ 14.3 ቢሊዮን ብር መድረሱን መግለጹ አይዘነጋም፡፡