Thursday, June 13, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

​​​​​​​ፈጣንና የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ልማት መዋዕለ ንዋይ ፍሰትና የመዋቅራዊ ሽግግር አስፈላጊነት በኢትዮጵያ

በፕላንና ልማት ኮሚሽን

በግልጽ እንደሚታወቀው በምጣኔ ሀብት ዘርፉ ውስጥ ከሚከናወኑ ፈርጀ ብዙ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች መካከል በተለይም የኢንዱስትሪ ልማት፣ ዓይነተኛ የልህቀትና የብልፅግና፣ የሥልጣኔም እንዲሁም የተደማሪያዊ ዕድገት መለያ ማጠንጠኛ ማዕከል ነው። ይህ በኢንዱስትሪ ዘርፉ ማዕቀፍ ሥር የሚፈጠረው ዓይነታዊ ዕድገትና ሽግግር የተለያዩ የዓለም አገሮች እንደየደረሱበት ደረጃ ያደጉ፣ በማደግ ላይ ያሉ፣ ታዳጊና የደሃ ደሃ አገሮች በሚል ደረጃዊ ክፍፍል ለመመደብ መገለጫ በመሆን ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንፃር ሲዳሰስ በ 18ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ገደማ በብሪታኒያ ጀምሮ በተከታዩ ምዕት ዓመት አብዛኛውን ምዕራብ አውሮፓንና አሜሪካን ያዳረሰው የኢንዱስትሪ አብዮት በኅብረተሰብ ባህል፣ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገትና የአስተሳሰብ ሽግግር በማምጣት ረገድ ከየትኛውም የሰው ልጅ ዕርምጃ ይልቅ ወሳኝነት ነበረው። ይኸው አብዮት በሰው ልጆች ሥልተ ምርታዊ ሽግግር ታሪክ ውስጥ በቴክኖሎጂ፣ በምጣኔ ሀብት፣ በማኅበራዊ ኑሮና በባህል ትሩፋት ረገድ ሥር ነቀል ለውጥን ያስከተለ ዓብይ እመርታ ስለመሆኑ ሌላ ማስረጃ የለውም። በጊዜው በተፈለሰሙ የተለያዩ ግኝቶች የእጅ ሥራ ተግባር በኢንዱስትሪ አመራረት ሥልቶች እንዲተካ፣ የብረታ ብረትና የጨርቃ ጨርቅ አመራረት ቴክኒክ እንዲረቅ ጥርጊያ ከፍተዋል። እንዲሁም የመንገዶች፣ የባቡር ሐዲዶችና የባሕር መተላለፊያ መስመሮች መስፋፋታቸው ለንግድ መጠናከር መበጀቱም የዚያኑ ያህል ነባራዊ ሀቅ ነው። የኢንዱስትሪ ዕድገት ለነፃ ገበያ የኢኮኖሚ ሥርዓት መስፋፋት የመጥቀሙን ያህል የበለጸገ እያልን ለምንጠራው የዓለም ክፍልም የተሻለ የኑሮ ሁኔታ ምንጭ ሊሆን መብቃቱ አልቀረም፡፡

 በሌላ በኩል በዚህ የኢንዱስትሪ ልማት ፀጋ የታደለው አንዱ የዓለም ክፍል ዛሬ በ 21ኛው ክፍለ ዘመን በዘመናዊ የሥልጣኔ ደረጃ ገስግሶ በሚገኝበት ጊዜ ባንፃሩ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች ታዳጊ እየተባለ የሚጠራው ወገን በመሆን የዜጎች የኑሮ ሁኔታ በሒደት መሻሻል ቀርቶ አገሮቹ የዜጎችን መሠረታዊ ዕለታዊ ፍላጎቶች እንኳ ማሟላት ተስኗቸው መቀጠሉ ነው። በአንዱ የዓለም ክፍል የሰው ልጅ በቅንጦት በሚኖርበት ሌላው ደግሞ የአገራችን ዜጋ የዕለት ጉርስ አጥቶ፣ የዕድገት ተስፋው መንምኖና ሰብዓዊ ክብሩ ተዋርዶ ነው የሚታየው። እንደ አንድ የታዳጊ ዓለም አገር ከዚህ የድህነት አረንቋ መውጫ መንገድ አለን ወይ? ብለን ብንጠይቅ የሕዝቡ የዕድገት ዕጣ በመጀመርያ ደረጃ በራሱ በኅብረተሰቡ የአስተሳሰብ፣ የሥራና አሠራር ለውጥ ዕርምጃ የሚወሰን ቢሆንም በምጣኔ ሀብታዊ ዘርፎች ውስጥ አሁን ካለንበት ተፈጥሮ ከተጫነው ኋላቀር የግብርና ዘርፍ ተላቀን ወደ ኢንዱስትሪያዊ ልማት መዋቅራዊ ሽግግር ማድረግ አንዱና ዋነኛው መሆኑ አሌ የማይባል ሀቅ ነው፡፡

 በመሆኑም አገራችንን ከዚህ መሰሉ የድህነት አዙሪት ለማውጣት በሚያስችል መልኩ ኢኮኖሚያችንን በዘላቂነት ለማሳደግ፣ መዋቅራዊ ሽግግርን ዕውን ለማድረግ፣ አስተማማኝ የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የማይዋዥቅ የውጭ ምንዛሪ ግኝት ምንጭ ለመፍጠር፣ ብሎም የገቢ ሸቀጦችን ለመተካት ጠንካራ የኢንዱስትሪ ልማት ወሳኝ ነው። ይሁን እንጂ የምንመኘውን ዓይነት መዋቅራዊ ሽግግርና ዙሪያ መለስ ትስስር ለመፍጠርና ዘርፉን ለማስፈንጠር እንዳይቻል አግቶ የሚይዘው ቁልፉ ማነቆ የኢንዱስትሪ ዘርፉ በተለይም የአምራች ኢንዱስትሪው ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ ከሰባት በመቶ በታች መሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም ዘርፉን ጠለቅ ብለን ስንቃኘው ሳንወድ በግድ የምንጋፈጠው እውነታ ቢኖር በጎጆ ኢንዱስትሪ መሰል ቀላል ማኑፋክቸሪንግ ንዑስ ዘርፎች የተዋጠ ብሎም ከውጭ በሚመጡ የማምረቻ ግብዓቶች ላይ በከፍተኛ ደረጃ ጥገኛ መሆኑ ሲሆን፣ ይህም በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ያለው ፋይዳ እዚህ ግባ የማይባል እንዲሆን አድርጎታል። ይህ ለዘመናት የባጀ ማነቆ የአገሪቱን የልማት አጀንዳ በአንፃሩ በድህነት ቅነሳ፣ በመልካም አስተዳደር ለውጥና በፀረ ሙስና ትግል ደረጃ የተወሰነ አድርጎታል። በእርግጥ የዘርፉን ዕድገትን አንቀው የያዙት ውጫዊ ተፅዕኖ ብቻ ሳይሆኑ የውስጣዊ የአመለካከትና የስትራቴጂ ልጓሞች በመሆናቸው እነዚህ ቤት ሠራሽ እክሎች ሁሉን አቀፍ መፍትሔን ይጠይቃሉ። ከሁሉም በላይ የአገራችን መለያ ገጽታ ረሃብና ድህነት ሆኖ ሊቀጥል አይገባውም፣ ብለን በቁርጠኝነት ከተነሳን ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ልማት ተገቢው ሁኔታ መመቻቸት ይኖርበታል።

 በጥቅሉ ስናየው መንግሥት በለውጡ ማግሥት በዘርፈ ብዙ ስብራቶች የተሽመደመደውን ኢኮኖሚ መረከቡ ጆሮ ላይ የተቀመጠ ቅርታ ድምፅ ሲሆን፣ ለዚህ ስብራት ሁነኛ መፍትሔ እንዲሆን አገራችንን በዝቅተኛ የኢንዱስትሪያላይዜሽን ደረጃ ላይ ብሎም ደካማ የምርትና ምርታማነት ዕርከን ላይ እንድትገኝ ያደረጉ ተግዳሮቶችን በአግባቡ ለይቶ የአገራችንን ኢኮኖሚ ከውድቀት የታደገውን የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮገራም ቀርጾ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

ይህ የኢኮኖሚ ማሻሻያ የኢንዱስትሪ ዘርፉን በተለይም የአምራች ኢንዱስትሪና የማዕድን ልማትን እንደ ቁልፍ የትኩረት መስክ ለይቷል፡፡ በመሆኑም በሚገባ ተምረው ሥራ ያልተፈጠረላቸው ወጣቶች፣ ትርፍ አምርተው የኢንዱስትሪ ግብዓት ትስስር ያልተፈጠረላቸው አርሶና አርብቶ አደሮች፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በፈጠረው የግብዓት ውስንነት ፋብሪካዎቻቸው በሙሉ አቅማቸው ማምረት ያልቻሉ ባለሀብቶች ጉዳይን መንግሥት በወጉ ተረድቶ በየዘርፉ የተለያዩ የመልሶ ማበጀት ሥራዎችን ደረጃ በደረጃ እያከናወነ ይገኛል፣ በዚህም ተስፋ ሰጪ ውጤቶችንም አስመዝግቧል።

 ለእነዚህ የመልሶ ማበጀት ሥራዎች ስኬታማነት ዓይነት መገለጫ ከሚሆኑት መካከል የተቀናጀ የኃይል ልማትና የመንገድ መሠረተ ልማቶች ዝርጋታ ቀዳሚው ነው፡፡ በፋይናንስ አቅርቦት በኩል ደግሞ ከሁለት ሦስት ዓመታት በፊት አብዛኛው ብድር በዋናነት ለመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይውል የነበረ ሲሆን፣ አሁን ይህንን በመቀየር ሦስት አራተኛ የብድር አቅርቦት ለግሉ ዘርፍ በተለይም ለአምራች የግሉ ዘርፍ እንዲውል መደረጉ የሥራ ማስኬጃ እጥረትን በማቃለል የዘርፉን ምርት ከማሳደጉም በተጓዳኝ ለሥራ ዕድል መፈጠር ቀዳሚ በር ከፍቷል፡፡

ሌላው በአገራችን የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለይም በውጭ የቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት አልሚዎች ዘንድ እንደማነቆ ሆኖ ከፍተኛ የሥጋት ምንጭ ሆኖ በአገራችን ንግድ መሥራትን ከባድ አድርጎ የቆየውን የደደረ ቢሮክራሲ በመቀየር ዘርፉን ከማደናቀፍ ይልቅ ማሳለጥ ላይ ለማድረግ ከሕግ ማዕቀፍ ቀረጻ ጀምሮ እስከ ተቋማዊ አደረጃጀት ያሉ ሰፋፊ ሥራዎች ተጀምረዋል፣ አንዳንዶቹም ወደ ትግበራ ገብተው ተገልጋዮች ከማለዳው ፍሬያቸውን መቋደስ ጀምረዋል፡፡ በዚህ ረገድ ካሉ ጅምሮች መካከል የአንድ መስኮት አገልግሎት፣ የኦንላይን የጉምሩክ አገልግሎት፣ ኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ የመሳሰሉት ከብዙ በጥቂቱ ማሳያዎች ናቸው።

ሌላው የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ እንዲጫወት የሚጠበቅበት ቁልፍ ሚና አገራችን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታስገባቸውን ሸቀጦች አቅም በፈቀደ በውስጥ አቅም ለማሟላት መሞከር ነው፡፡ በዚህ ረገድ መሠረታዊ የሚባሉት እንደ ዘይት፣ ስኳርና ስንዴ ያሉት በዚህ ምድብ ተካተቱ ሲሆን ከፍተኛ የማምረት አቅም ያላቸው የዘይት ፋብሪካዎች በግል ባለሀብቶች ተገንብተው ሥራ የተጀመረ ሲሆን፣ የስኳር ዘርፍ መዋቅራዊ ማሻሻያና ወደ ግል አልሚዎች የማሸጋገር ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ለመዋቅራዊ ሽግግርና የኢኮኖሚ ቅርፀ ልውጠት ዓይነተኛ የፖሊሲ ማስፈጸሚያ የሆነውን የጉምሩክ ታሪፍ ትመናና አሠራር ስርዓት በአግባቡ ጥቅም ላይ የማዋል ሥራ በተጓዳኝ ተሠርቷል፡፡ ባለፉት ጥቂት የለውጥ ማግሥት ወቅቶች መንግሥት በዚህ ብቻ ሳይገደብ በእጁ የሚገኙ የፊስካል ፖሊሲ መሣሪያዎችን በመጠቀም የአገር ውስጥ አምራቾችን ለማበረታታት በሚያስችል መልኩ በአገር ውስጥ በቂ አቅም በፈጠርንባቸውና መፍጠር ለምንችልባቸው ምርቶች የታሪፍ ከለላ ለመስጠት ከውጭ በሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ የመጣልና አስፈላጊና በአገር ውስጥ የማይገኙ ግብዓቶችን ታሪፍ በመቀነስ የአገር ውስጥ አምራቾችና ምርቶችን የማበረታታት ሥራ ተሠርቷል።

 ይህ የታሪፍ ከለላ ከውጭ መከላከልን ብቻ ትኩረት ያደረገ አሁን ባለው የሉላዊነት ዘመን መንግሥት በር ዘግቶ የበረኝነት ሚና መጫወቱ የማያዋጣና ዘላቂነትም የሌለው በመሆኑ አምራቾችን ወደ ማትጋት ለማሳደግ በየዘርፎች ውስጥ ያለውን የእሴት ሰንሰለት በዝርዝር በማጥናት አምራቾች በሚጨምሩት እሴት መጠን ማበረታቻ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ ተሸከርካሪና ሌሎች የሚገጣጠሙ ምርቶች የሚያመርቱ አምራቾች እንደሚጨምሩት የእሴት መጠን የተለያየ ማበረታቻ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ከላይ በአልፍ ገደም ለማመላከት እንደተሞከረው መንግሥት በእጁ ያሉትን የገንዘብ፣ የሕግና የፖሊሲ አቅሞች በመጠቀም የወሰዳቸው ከላይ የተጠቀሱት ዕርምጃዎችና የተገኙ ውጤቶችና የሌሎች አገሮች ተሞክሮን በመውሰድ በቀጣይ አሥር ዓመታት በተሻለ መልኩ የአገሪቷን የኢኮኖሚ ችግሮች ለመፍታትና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለማምጣት ጠንክሮ እንደሚሠራ ማሳያ ነው።

 የኢንዱስትሪ አብዮት በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከፍተኛ ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ (ወይም ለአገሮች ዕድገት ማርሽ ቀያሪ እንደሆነው ሁሉ) እንዳመጣ በቅርብ ዓመታት ደግሞ የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት በማስመዝገብና መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት በተምሳሌትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ለዚህ ተጠቃሽ ስኬታቸው ማጠንጠኛ ነጥብ ከሆኑት ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ እርስ በርሱ የተሰናሰለና የተቀናጀ የልማት ዕቅድ መጠቀምና የዕቅዱን ገቢራዊነት ለማስረገጥ ደግሞ በተመረጡ ንዑስ ዘርፎች የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ማጎልበት ናቸው፡፡

በተጨማሪም ይህን መሠል የልማት ዕቅድ ማዘጋጀትም ሆነ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን ማበረታታት ብቻውን ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጣ እንደማይችል አስቀድመው በመገንዘብ ሊጎለብቱ በተፈለጉ ስትራቴጂክ ዘርፎች መካከል ያለው የኋልዮሽና የፊትዮሽ ትስስር መፍጠርና እነዚህ ትስስሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከሩ እንዲሄዱ በመደረጉ ከተወሰኑ አሥርት ዓመታ በኋላ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፅዕኖ ፈጣሪ ኢኮኖሚ ለመገባት ችለዋል፡፡ እነዚህ አገሮች ይህን መሰል የተናበበ ተቋማዊ፣ መዋቅራዊ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ሥርዓት በመዘርጋታቸው በአሁኑ ሰዓት የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ከዓለም አጠቃላይ ኢኮኖሚ ከ28 በመቶ በላይ ድርሻን መቆጣጠር ችለዋል፡፡

 እንደ ኮሪያና መሰል ሩቅ ምሥራቅ አገሮች ይህ ቅንጅታዊ ድርጊት በአንድ ዘርፍና ወጥ የዕቅድ ማዕቀፍ ሥር ብቻ የሚከናወን ሳይሆን በየአምስት ዓመቱ በዕቅድ ሒደቱና ልዩ ትኩረት በሚሰጣቸው ዘርፎች (Priority Activities) ላይ ተገቢ ክለሳ በማድረግና የአገሮቹን ብልጫ ተወዳዳሪነት የሚያጎለብቱ ንዑስ ዘርፎች እያፈራረቁ በመምረጥ ትኩረት በመስጠት ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ ይህም የተንሰራፋ አገራዊ የጥሪት ብክነትንና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን በመቀነስ የግሉን ዘርፍ የኢንቨስትመንት ትኩረት አቅጣጫ በማስቀመጥና የተሰባጠረና ዘላቂ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር በማድረግ ረገድ የተቀናጀ የዕቅድ ማዕቀፍ መኖሩ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡

በአንፃሩም እነዚህ አገሮች በቂ የፋይናንስ ግኝትን ከሠለጠነ የሰው ኃይል አቅርቦት ጋር በማስተባበር ለትኩረት ዘርፎች አስፈላጊውን ቴክኖሎጂ በማቅረብ አመርቂ ዕድገት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ለዚህም የኢንዱስትሪያዊ ሽግግር በቂ ዕውቀትና ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ለማፍራት የልህቀት ማዕከል እንዲሆኗቸው በቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ላይ ትኩረት በማድረግ በብዛት የሰው ጉልበት ለሚጠቀሙ ዘርፎች የሚፈለገው ክህሎት ያለው የሰው ኃይል ማቅረብ ችለዋል፡፡

ለአብነት እንዲሆነን የኮሪያን ተሞክሮ ብንጠቅስ በመጀመርያው የዕድገት ዘመን በጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ በግብርና ማቀነባበር፣ በእንጨት ሥራና በኅትመት ላይ ትኩረት ተሰጦ ሲሠራ የነበረ ሲሆን ለነዚህ ዘርፎች የምርት ሒደት የሚያስፈልግ የሰው ኃይል በዘርፎቹ የተወሰነ ክህሎት ያለው በመሆኑ ለቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ተቋማት ልዩ ትኩረት ተስዕጦ የሚፈለገው የሰው ኃይል ማቅረብ ችለዋል፡፡ በቀጣዩ የዕድገት ዕቅድ ዘመን በኬሚካል፣ በብረታ ብረትና በማሽነሪ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ በመጀመርያው የዕድገት ዘመን ለቀላል ኢንዱስትሪዎች በግብዓትነት ይውሉ የነበሩና ከውጭ አገር ይገቡ የነበሩትን የማምረቻ ማሽኖች በአገር ውስጥ በማምረት ከጊዜው ጋር የዘርፎችን የላዕላይ ትስስር (Vertical Integration) ከማቀናጀት ባለፈ አገሪቱ ጠንካራ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እንድትገነባ አስችሏታል፡፡ ጠቅለል አድርገን ስናየው ከላይ የተዘረዘሩት ፖሊሲዎች ፈጣን ዕድገት ማምጣት ብቻ ሳይሆን አገሮቹ ተጨባጭ መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጡ አስችሏል፡፡

የቀጣዮቹ አሥር ዓመታት የኢንዱስትሪ ቅኝት በኢትዮጵያ

 

በአገራችን በተለይም ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት የአምራች ኢንዱስትሪውን ንዑስ ዘርፍ ለማሳደግ ሰፊ ጥረት እያደረገ ቢሆንም፣ የአገር ውስጥ የግል ባለሀብቱን በአምራች

ኢንዱስትሪው ልማት የዋና ተዋናይነት ድርሻውን እንዲወጣ ከማድረግ አኳያ የተሠራው ሥራ እምብዛም አጥጋቢ አይደለም፡፡ በአገር ውስጥ የግሉ ሴክተር በኢንዱስትሪው ዕድገት ላይ በሚፈለገው ደረጃ የሚገባውን ሚና ተጫውቷል ለማለትም አያስደፍርም፡፡ እንዲሁም ቀደም ሲል በተቀረፀው የአገራችን የኢንዱስትሪ ፖሊሲ ሰነድ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የግል ባለሀብት ለኢንዱስትሪው ልማትና ዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር ወይም ዋና ተዋናይ ነው፡፡

የግሉ ባለሀብት የኢንዱስትሪ ልማት ሞተር ይሁን ሲባል የአገር ውስጥ ባለሀብት ዋነኛው ኃይል የሚሆንበት፣ የውጭው ባለሀብት በአገር ውስጥ ባለሀብቱ ላይ በተደራቢነት በሰፊው ተሳታፊ የሚሆንበት፣ በሁለቱም ድምር አቅም የአገራችን የኢንዱስትሪ ልማት የሚፋጠንበት ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ሰነዱ ያስረዳል፡፡ ምክንያቱም ከሁለቱ አንዱ ብቻውን የምንፈልገውን ፈጣን ዕድገት ሊያረጋግጥ ስለማይችል አጣምረን መጠቀም እንዳለብን ይገልጻል፡፡

ሆኖም በተጨባጭ ዘርፉ ሲታይ እዚህም እዚያም የተበታተነ፣ በግብዓት ምርት ውጤት ትስስር ያልተናበበና በሚገባ ያልተቀናጀ እንዲሁም ለአመለካከት መንሸዋረር የተጋለጠ ሲሆን፣ ይህን መሰሉ የምርትና አመራረት ሥርዓት ቀጣይነት ላለው የተራዘመ ቀውስና መዋዥቅ ክፉኛ ተጋላጭ ሊሆን እንደሚችል ለመረዳት ከምጣኔ ሀብት ሀሁ አንዱን መገንዘብ ብቻ በቂ ነው፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተለየ ማበረታቻና ድጋፍ ፓኬጆች አዘጋጅቶ ከጥቂት ዓመታት በፊት ወደ ሥራ የገባ ቢሆንም፣ ነገር ግን አሁን በተግባር እየታየ ያለው አብዛኛው የአገር ውስጥ የግል ባለሀብት የመጀመርያ ምርጫው አምራች ኢንዱስትሪው ሳይሆን የንግድ፣ ሪል እስቴትና የአገልግሎት ዘርፎች ናቸው፡፡ ይህ የሚያመለክተው የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ሲነፃፀር የግል ባለሀብቶችን ትኩረት የማይስብና ተመራጭ ያልሆነ መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር ተያይዞ ሁለት አሰናካይ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ አንደኛው ቀድመው በአምራች ኢንዱስትሪ የተሰማሩ አብዛኛዎቹ ባለሀብቶች በብዙ ችግሮችና ማነቆዎች ምክንያት ውጤታማ ባለመሆናቸው ወደ ዘርፉ መግባት ለሚፈልግ ባለሀብት ጥሩ አርዓያ ስላልሆኑት ሁለተኛው በንግድና አገልግሎት ዘርፎች የሚገኘው ትርፍ በጣም የተጋነነና ሳቢ በመሆኑ ነው፡፡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ለዘርፉ መቀንጨር ሌላው ከልካይ ጉዳይ በአምራች ኢንዱስትሪ የተሰማራው ባለሀብት ለዘርፉ ዕድገት የሞተርነት ሚናውን እንዲጫወት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖ ያላቸው ባለድርሻ አካላት ዘርፉን በተፈለገው ደረጃ ለማሳደግ ሁሉም የየራሳቸው ድርሻ ቢኖራቸውም ድርሻቸውን በመወጣት በኩል በቂ ትኩረትና የተግባር እንቅስቃሴ እንዳላደረጉ ነው፡፡

በተጨባጭ እንደምናየው የኢትዮጵያን የረዥምና አጭር ጊዜ የኢኮኖሚ ዕድገት ዘላቂ ለማድረግ፣ ራዕይ ለማሳካት ጠንካራና ተወዳዳሪ የሆነ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መገንባት ወሳኝና አስፈላጊ ነው፡፡ መንግሥት የአገራችንን የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ተሞክሮና የግል ባለሀብቱን አጠቃላይ አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት ለዘርፉ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ማዕቀፎችን በማዘጋጀት የተሻለ አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጠር ጥረት አድርጓል፡፡ ነገር ግን ባለፉት አሥር ዓመታት በተለይ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የተፈለገውን ያህል የዕድገት ውጤት አላስመዘገበም፡፡ ለዚህም በአምራች ኢንዱስትሪው ውስጥ የተስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮችና ማነቆዎች የኢንዱስትሪ ዘርፉ አመራርና አደረጃጀት ችግር፣ የማበረታቻና ድጋፍ አቅርቦት ችግር፣ የፋይናንስና ብድር አቅርቦት ችግር፣ የኢንዱስትሪ ግብዓት አቅርቦት ችግር፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ምርቶች ገበያና የተሳለጠ የንግድ ሥርዓት አለመኖር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ልማት አለመፋጠን፣ በአምራች ኢንዱስትሪ ባለሀብቱ በራሱ የተስተዋሉ ችግሮችና ውስንነቶችና ለአምራች ኢንዱስትሪ የመሬትና መሠረተ ልማት በበቂ ሁኔታ አለማቅረብ በመሠረታዊነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡

በመሆኑም በመንግሥት በኩል ይህንን ዘርፍ ከመሠረቱ ለመቀየርና ወደ መዋቅራዊ ሽግግር ሥልጠት ለማምጣት የወደፊት የምርት ሒደት ትስስርን ታሳቢ በማድረግ፣ የምርትና ምርታማነት ማጎልበትን፣ የጥራት ቁጥጥርን፣ የአገሪቱን አጠቃላይ የሀብት ሒደትና የውስጥ አቅምን ባገናዘበ መልኩ ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የኢንዱስትሪ ዘርፎችን ደረጃ በደረጃ መለየት ያስፈልጋል። ለዚህም አገሪቱ ያላትን ዕምቅ የሰው ኃይልና የግብርና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ግምት ውስጥ በማስገባት የመጀመርያውን አምስት ዓመት የግብርና ምርቶችን በጥሬ ዕቃነት የሚጠቅሙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ላይ በማተኮር አስተማማኝ የኢንዱስትሪ መሠረት መገንባት ይገባል።

ይህ የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ (Agro-Processing Industry) በተለይ በግብርና ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ያላቸውን እንደ እኛ ያሉ አገሮች ወደ ኢንዱስትሪ ለማሸጋገር በእጅ ያለ ተጨባጭ አቅም ነው። የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የአርሶ አደሩን ምርቶች በግብዓትነት ስለሚጠቀሙ አርሶ አደሩ ለማምረቻ ኢንዱስትሪ ግብአት ሊሆን የሚችሉ የገበያ ምርቶችን እንዲያመርት ይበረታታል። ከዚህ በተጨማሪ አግሮ ኢንዱስትሪ በበቂ ሁኔታ ሲስፋፋ አርሶ አደሩ በቂ ገበያ ስለሚያገኝ ምርታማነቱን ለማሳደግ ይበረታታል። የምርት ጥራቱንም ያሻሽላል። የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የግብርና ምርቶችን የፋብሪካ ግብዓት ሊሆኑ በሚችሉበት የጥራት ደረጃ ለማቅረብ የማጠብ፣ የማድረቅና የማጥራት ወዘተ… ከፍተኛ የሰው ኃይል የሚጠይቅ የቅድመ ምርት ሥራዎችን ስለሚሻ ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል። በጥሬው ወደ ውጭ ሲላኩ በነበሩ ምርቶች ላይ በተለያየ ደረጃ እሴት መጨመር ስለሚያስችል ለሠለጠነ የሰው ኃይል የሥራ ዕድል ይፈጥራል። እሴት በመጨመር ወደ ውጭ ከሚላክ ምርት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ያስችላል። ሆኖም ግብርናን መሠረት ያደረጉ ኢንዱስትሪዎች በዓይነትና በመጠን ሊስፋፉ የሚችሉት የግብርናው ዘርፍ ከወቅቱ ሲዘምንና ሲዳብር ነው። ለዚህም ለግብርናው ዘርፍ አስፈላጊ የሆኑ የምርትና ምርታማነት ማሻሻያ ግብዓቶችን ማለትም ማዳበሪያና ሌሎች ግብዓቶችን እንዲሁም ቴክኖሎጂዎች በአገር ውስጥ ለማምረት ትኩረት የሚሰጥባቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ እያደገ የመጣውን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ለማገዝ በጥሬ ዕቃነት የሚያገለግሉና እንደ ብረትና ሲሚንቶ የመሳሰሉ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በአገር ውስጥ ማምረት ያስፈልጋል። እነዚህ ኢንዱስትሪዎች የምርት ሒደታቸውን በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎች እንዲጠቀሙ በማድረግ የእሴት ሰንሰለቱን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ዘርፍ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተስፋ ያሳየ ዘርፍ ቢሆንም ለምርት ግብዓትነት የሚጠቀምባቸው በአብዛኛው ከውጭ በሚመጡ ጥሬ ዕቃዎች ነው፡፡

ይህ ደግሞ የዘርፉን ኢኮኖሚዊ ፋይዳ ውስን እንዲሆን ከማድረግ በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሪ ከአገር እንዲወጣ፣ ከሌሎች ዘርፎች ጋር ልል ትስስር እንዲኖረውና በቂ የሥራ ዕድል እንዳይፈጥር አድርጎት ቆይቷል፡፡ ለጥሬ ዕቃነት የሚያስፈልጉት ግብዓቶች ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቁ በመሆኑ መንግሥት ለዘርፍ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ፣ የተማረ የሰው ኃይል ማቅረብና በቂ ካፒታል የሚቀርበበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

የሁለተኛ ደረጃ ኢንዱስትሪ ልማት (ማለትም ሁለተኛው አምስት ዓመት)

በቀጣዩ የዕቅድ ዘመን ደግሞ አጠቃላይ ኢኮኖሚውና የኢኮኖሚው መሠረት ልማት ላይ በቂ ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ወደ ከፍተኛ ካፒታልና የሠለጠነ የሰው ኃይልና ከፍተኛ ዕውቀት ወደ ሚጠይቁ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ የኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚን መገንባት ያስችላል፡፡ ከዚህ አንፃር ሁለተኛው የኢንዱስትሪ ልማት ዕቅድ ሁለት መልክ እንዲኖረው ተደርጎ ይቀረፃል፣ ይኽውም አንደኛው በመጀመርያው የኢንዱስትሪ ልማት ዕቅድ ዘመን የተሠሩትን ኢንዱስትሪዎች በማሻሻል (Industrial Upgrading) ምርትና ምርታማነትንና ጥራትን ማረጋገጥ ሲሆን፣ ሁለተኛው ከፍተኛ ዕውቀትና ካፒታል ላይ የተመሠረቱ ብሎም የመፈብረኪያ መሣሪያዎች ማምረቻ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት ነው።

በመሆኑም በመንግሥት በኩል ኢኮኖሚው የሚፈልገውን የሰው ኃይል በማዘጋጀትና የፖሊሲ ማዕቀፎችን በማዘጋጀት የተሻለ የኢንዱስትሪ መሠረት መጣልና ለኢንዱስትሪውም ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡

ከዚህም ባለፈ አገሪቱ የምታስገባቸውን የካፒታል ምርቶች በአገር ውስጥ ምርቶች በመተካት ዘርፉን ማበረታታትና ማዘመን ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ በሁለተኛው አምስት ዓመታት የትራንስፖርት ዕቃዎችን ብረታ ብረቶችንና ሌሎች ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችን በአገር ውስጥ በመተካት አገሪቱን በኢንዱስትሪ የበለፀገች እንድትሆን ያግዛል።

እነዚህ እርስ በርሳቸው የተመጋገቡና አዳጊያዊ ለውጥ የሚያስመዘግቡ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፎች በራሳቸው በጥብቅ መሠረት ላይ የተዋቀረ ሰንሰለታዊ ተመጋጋቢነት በመፍጠር የማይነቀነቅ የልማት ምንጭ ከመሆናቸውም በላይ ለሌሎች ኢንዱስትሪዎች የሠርቶ ማሳያና የግብዓት ማዕከል በመሆን አገሪቱ ልትደርስበት ካለመችው የበለፀገና የተረጋጋ ምጣኔ ሀብታዊ ሥርዓት መዳረሻ መንገድና ለአገራዊ ብልፅግና አንዱ መገለጫ ለሆነው የዜጎች የኑሮ ጥራት ፅኑ መደላድል ይሆናሉ፡፡

የቀጣይ አሥር ዓመታት የኢንቨስትመንት ፖሊሲ አቅጣጫ

እንደሚታወቀው አገራችን የቀየሰችውን የገበያ መር ምጣኔ ሀብት ሥርዓትን ተከትሎ የኢንቨስትመንት ፖሊሲ ተነድፎ በሥራ ላይ ውሏል፡፡ በዚህም በኢኮኖሚው ውስጥ የመንግሥት ሚና የተለያዩ የልማት ኃይሎችን በማቀናጀት መምራት፣ መሠረተ ልማት በማቅረብና የሰው ሀብት ልማትን በማካሄድ እንዲሁም ፈጣንና ውጤታማ የመንግሥት አገልግሎት በመስጠት ለግሉ ዘርፍ ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የመደገፍ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሙስናና ብልሹ አሠራር ምንጮችን መዝጋትና በግሉ ሴክተር የማይሠሩ የልማት ሥራዎችን መንግሥት ገቢራዊ እንዲያደርጋቸው የሚያስችሉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡ የለውጡ መንግሥት ባለፈው ሥርዓቶች የወጡና የግሉን ዘርፍ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚገቱ ሕጎችና ደንቦች እንዲወገዱ አድርጓል፡፡ በዚህም ለውስጥም ሆነ ለውጭ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ የንግድና ኢንቨስትመንት ፖሊሲን ሥር ነቀል በሆነ መልኩ በመለወጥ መንግሥት በየጊዜው የተለያዩ ዕርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡ በየጊዜው ከታዩ ልምዶች ትምህርት በመውሰድ ጥንካሬዎቹን የማጎልበት ድክመቶቹን የማረም ምቹ ሁኔታዎች እየተፈጠሩም መምጣታቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። በሕገ መንግሥቱ የሚፈለገው ዓይነት ፈጣን ዕድገት ደግሞ ልቅ በሆነ የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ብቻ ሊረጋገጥ የማይችል በመሆኑ ካለፈው ትምህርት መውሰዱ ተገቢ ይሆናል። ልቅ የሆነ የገበያ ሥርዓት ዘላቂና ሰፊ መሠረት ያለው ዕድገት የማምጣት አቅም የለውም፡፡ ይልቁንም የሕዝብንና የመንግሥትን አቅሞች ወደ ብልሹ አሠራር እንዲሰማሩ የማድረግ አቅሙ የሰፋ ነው።

የበርካታ አገሮች ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ውጤታማ፣ ጥራት ያለውና ዘላቂ ኢንቨስትመንት የአንድ አገር የዘላቂ ልማትና የዜጎች ብልፅግና መሠረት ናቸው። በአገር ልማት ውስጥ በቂ የመዋዕለ ነዋይ ፍሰት ከሌለ ብቻ ሳይሆን በትክክልም ካልተመራ ዘርፉ ውጤታማ ካለመሆኑም በላይ የአገር ሀብት ብክነትን ያስከትላል። በመሆኑም ኢንቨስትመንት ውጤታማ፣ ጥራት ያለውና ዘላቂነት እንዲኖረው በትክክለኛው ፖሊሲ መመራት ይኖረበታል። ከኢንቨስትመንት ውጤታማነትና ጥራት ጋር ተያይዘው ከሚነሱት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ኢንቨስትመንቱ ለሥራ ፈጠራና ለምርታማነት በዘላቂነት ማደግ በሚያበረክተው ሚና የሚለካ ነው። ለዚህም የግል ባለሀብቱ ሚና አይተኬ ሚና አለው። ስለዚህም በሚቀጥሉት ዓመታት ጥራት ያለው የሥራ ዕድል በመፍጠርና ምርታማነትን በማሳደግ ላይ ባተኮረ፣ እንዲሁም የግል ባለሀብቱን (በተለይም የአገር ውስጥ ባለሀብቶችን) በአግባቡ ባሳተፈ መልኩ ሰፊ የኢንቨስትመንት ሥራዎች እንዲከናወኑ አስቻይ ሁኔታቸውን በመፍጠር እንዲሁም አስፈላጊ በሆነባቸው ዘርፎችም ከግል ዘርፉ ጋር በመጣመር በጋራ በመሥራት የዜጎችን የኑሮና የእርካታ ደረጃ ለማሳደግ አበክሮ የሚሠራ ይሆናል።

ኢንዱስትሪያላይዜሽንና ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ሚና

በአጠቃላይ በአገራችን የኢንዱስትሪው ልማትና ዕድገት ዋና ተዋናይ እንዲሆን የታሰበው የግል ባለሀብቱ በተለይም የአገር ውስጥ ባለሀብቱ በአምራች ኢንዱስትሪው

ልማት ላይ ሚናውን በታቀደው ልክ እየተጫወተ አለመሆኑና የኢንቨስትመንት ተሳትፎውም ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ሆኗል፡፡ ስለሆነም በአንድ በኩል ቀድመው በአምራች ኢንዱስትሪው የተሰማሩ የአገር ውስጥ የግል ባለሀብቶች ያሉባቸውን ማነቆዎች መፈተሽ፣ አፈጻጸማቸውን ለመገምገምና የሞተርነት ሚናቸውን ከመጫወት አኳያ ያለውን ክፍተት በመለየት የመፍትሔ ምክረ ሐሳቦች ማቅረብ፣ በሌላ በኩል ደግሞ አቅም ያላቸውና በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ የአገር ውስጥ የግል ባለሀብቶች በአምራች ኢንዱስትሪ በስፋት እንዲሰማሩ የሚያስችል አቅጣጫ የሚያሳዩ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦችና መፍትሔዎች መጠቆም ይኖርባቸዋል፡፡

መንግሥት በአሁኑ ወቅት እንደ ግብ ያስቀመጠው በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት አጠቃላይ የኢኮኖሚ ፖሊሲ አቅጣጫ ጥራት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገትና የጋራ ብልፅግና የሚያረጋግጥ ጠንካራና አካታች የገበያ መር ሥርዓት መገንባት ላይ የተመሠረተ ነው። ይህም የግል ዘርፉን በማብቃትና በማጎልበት፣ የመንግሥትን ሚና ከግሉ ዘርፍ ጋር በማስተሳሰር የኢትዮጵያውያንን የመበልፀግ ፍላጎት በተጨባጭ በማሟላት ተግባራዊ እንዲሆን ይደረጋል። ይሁን እንጂ እስካሁን በተለያዩ ጊዜያት በተከተልናቸው የኢኮኖሚ ፖሊሲና ኢንቨስትመንት ፖሊሲ አቅጣጫዎችና ሌሎች ምክንያቶች የግሉ ዘርፍ ተሳትፎና የዕድገት ደረጃ ዝቅተኛ ሆኖ ቆይቷል። ይህም ሁኔታ የግሉ ዘርፍ በኢንቨስትመንት፣ በዘላቂ ሥራ ፈጠራ፣ በምርታማነት ዕድገት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በምርት ጥራትና ተወዳዳሪነት፣ በጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ድርሻ፣ በወጪ ምርት ተሳትፎና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ማበርከት የሚገባውን አስተዋጽኦ በተገቢው ሁኔታ እንዳያበረክት አድርጓል። የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ውስጥ በተለይም በኢንዱስትሪያላይዜሽን ሒደቱ ላይ ያለውን ሚና ለማሳደግና የተሻለ የውድድር ሜዳ ለመፍጠር ባለፉት ሦስት ዓመታት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። ከዚህም ውስጥ የቴሌኮም ዘርፍን ነፃና ገለልተኛ በሆነ አግባብ ማስተዳደር የሚያስችል የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ተቋቁሟል። በዚህም የቴሌኮም ዘርፉን የገበያ መዋቅር የበለጠ የሚያሻሻልና በዘርፉ ውድድርን የበለጠ እንዲጎለብት የሚያደርጉ ከዘጠኝ በላይ መመርያዎች በባለሥልጣኑ ለባለድርሻ አካላት ውይይት እንዲቀርብ ማድረግ የተቻለ ሲሆን የቴሌኮም ዘርፉን በከፊል ወደ ግል የማዘዋወር አብዛኛው ሒደትን ማከናወን ተችሏል።

በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ በባቡርና ኢነርጂ ዘርፎች እንዲሁም በኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን ያሉትን ሁኔታዎች ወደ ተሻለ ውድድርና ቅልጥፍና ለማድረስ የተለያዩ የሪፎርም ሥራዎች ማከናወን ተችሏል። በተጨማሪም በሎጂስቲክስ ዘርፍ ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ፖሊሲ ፀድቆና ብሔራዊ የሎጂስቲክስ ካውንስል ተቋቁሞ ወደ ተግባር ማስገባት የተቻለ ሲሆን ደረቅ ወደብን የማልማትና የማስተዳደር ሥራ ለግሉ ዘርፍ ክፍት እንዲሆን ተደርጓል። ከዚህም በተጨማሪ ከ62 ዓመት በኋላ ተሻሽሎ በቅርቡ የፀደቀው የንግድ ሕግ ለኢንዱስትሪ ልማትና ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ ሚና ይኖረዋል። ለኢንዱስትሪ ልማት የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ባለሀብት ከፍተና ሚና መጫወት እንደሚኖረባቸው እናምናለን። በተለይም የአገር ውስጥ ባለሀብቱ በተለያዩ ምክንያቶች ቅድሚያ የሚሰጠው ሲሆን፣ ድርሻውም በሒደት እየተሻሻለ የሚሄድ ይሆናል። ለምሳሌ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የተወሰኑ ሼዶች በተለየ መልኩ ለአገር ውስጥ አምራቾች እንዲቀርቡ የተደረገው ጅማሮ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ ፓርቲያችን ብልፅግና የአገራችን የግል ዘርፍ የማኑፋክቸሪንግ የተሳትፎ ባህሉና አቅሙም በተለያዩ ምክንያቶች ዝቅተኛ በመሆኑ የተነሳ የአገር ውስጥ የግል ዘርፍ ለማበረታታት በግሉ ዘርፍ የማይደፈሩ አንዳንድ ዘርፎች በግል መንግሥት ትብብር ሊገነባና በሒደት ለግሉ ዘርፍ የማስተላለፍ ሥራ ሊሠራ ይችላል ብሎ ያምናል። በተጨማሪም ውጤት ተኮርና ፍትሐዊ ማበረታቻዎችን በመቅረፅ ጥራት ያለው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ የዕውቀት፣ የፋይናንስ፣ የውጪ ምንዛሪና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር ከአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ጋር የማስተሳሰር ሥራ በትኩረት ይሠራል። በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ለኢንዱስትሪ ልማት አስቻይ የኢንቨስትመንት ምኅዳርን፣ የኃይልና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን፣ የሠለጠነና በክህሎት የዳበረ የሰው ኃይልን፣ የፋይናንስና የውጭ ምንዛሪን፣ የሎጂስቲክስ፣ ከዘመኑ ጋር መራመድ የሚችል የኢንዱስትሪ ፖሊሲን፣ ሌሎች የማስፈጽሚያ ሥልቶችን፣ እንዲሁም አስፈላጊ የሕግ ማዕቀፎችና አሠራሮችን መዘርጋት የመንግሥት ሚና ሲሆኑ የኢንዱስትሪ ልማቱ በዋናነት በግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት መምጣት እንዳለበት ብልፅግና ያምናል። ለዚህም አበክሮ ይሠራል። በአጠቃላይ ፓርቲያችን አገራችን ኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት እንዲቻል በተለይም የኢንዱስትሪያላይዜሽን ሒደቱ እንዲፋጠን፣ የግሉ ዘርፍ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ እንድያድግ በዚህም ሳቢያ ምቹ የሥራ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ዜጎች መብት ደኅንነትና ክብር ተጠብቆላቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሠሪዎችና ሠራተኞች በነፃ የመደራጀትና የመደራደር መብትን ጨምሮ በሕግ የተደነገጉ መብቶች ተከብሮላቸው፣ የጋራ ራዕይ በመሰነቅ ለአገሪቱ ልማት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ፣ መሠረታዊ የሥራ ላይ መብቶች እንዲከበሩ፣ ምርትና ምርታማነት እንዲያድግና ተወዳዳሪነት እንዲጨምር፣ የኢንዱስትሪ ሰላም በዘላቂነት እንዲሰፍን በአጽንኦት የሚሠራ ይሆናል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles