በኢትዮጵያ ጡት ማጥባት ሲያያዝ የመጣ መልካም ባህልና በጎ ምግባር ነው፡፡ ለረዥም ጊዜ ጤና፣ ለተስተካከለ ሥርዓተ ምግብና የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ጠቀሜታውም የጎላ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሕፃናት ያላቸው ወላጆች በሙሉ ብቃቱ የተረጋገጠ የጡት ማጥባት የምክር አገልግሎትና ድጋፍ ከጤና ተቋማት፣ ከሥራ ቦታቸውና ከማኅበረሰቡ ሊያገኙ ይገባል፡፡ ጡት ማጥባትን በመጠበቅ፣ በማስተዋወቅና በመደገፍ ዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት የሁሉም ኃላፊነት እንደሆነ ይመከራል፡፡
የጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ሕፃናት ጤና ዋና ዳይሬክተር መሠረት ዘለዓለም (ዶ/ር) ይህንኑ ሐሳብ ይጋራሉ፡፡ እንደ ዋና ዳይሬክተሯ እምነት ጡት ማጥባት ለሰው ልጆች የተሰጠ ተፈጥሮአዊና ሰብዓዊ መብት በመሆኑ ሊከበር ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ 97 በመቶ ያህሉ የኢትዮጵያ እናቶች ለረዥምና ለአጭር ጊዜ ጡት እንደሚያጠቡ ይታወቃል፡፡
ይህም ሆኖ ግን ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ከሆኑት ሕፃናት መካከል የመጀመርያውን ስድስት ወራት ጡት በአግባቡና ሳይንሳዊ መንገድን በተከተለ አኳኋን የሚጠቡ 59 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑ፣ የቀሩት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እንደማያጠቡና በሕክምና ባለሙያዎች ያልታዘዙ ልዩ ልዩ ነገሮችን እንደሚያቀምሷቸው ነው የተናገሩት፡፡
‹‹ጡት ማጥባትን መጠበቅ የጋራ ኃላፊነት!!›› በሚል መሪ ቃል ከሐምሌ 25 ቀን እስከ ነሐሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የተካሄደውን የጡት ማጥባት ሳምንትን አስመልክቶ ሐምሌ 28 ቀን በተካሄደው ሥነ ሥርዓት ላይ ዋና ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት በወላጆች ግፊት ከሚቀምሱትም ልዩ ልዩ ነገሮች መካከል ጥሬ ቅቤ ማዋጥ፣ ሻይና በስኳር የተበጠበጠ ውኃ መጠጣት ወይም ማጋት ይገኙበታል፡፡ እነዚህም ሁኔታዎች ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ስድስት ሚሊዮን ሕፃናት መቀንጨር አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ ይህንንም የጤና ሚኒስቴር በ2011 ዓ.ም. ባካሄደው የሕዝብና የጤና ዳሰሳ ላይ መረጋገጡን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ሁኔታውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሕፃናትን ከመቀንጨር፣ ከተወሳሰበ የምግብ እጥረት ችግር ለመታደግ እንዲቻል የ1000 ቀናት ንቅናቄ እየተከናወነ መሆኑን፣ አንዱና ዋነኛው ሥራም ጡት ማጥባትን በተሻለ መንገድ እንዲሆን ማድረግ መሆነን ጠቅሰዋል፡፡ ማኅበረሰቡም የተሻለ ዕውቀትና ልምድ እንዲኖረው ለማስቻል ማስገንዘቡ ጠንከር ባለ መልኩ እንደሚከናወን አስረድተዋል፡፡
ከዚህም ሌላ መቀንጨርን ለማስቀረት የሚያስችል የቅድመ መከላከል ተግባር ማከናወንና ችግሩ ያለባቸው ሕፃናትን የከፋ ሁኔታ ውስጥ እንዳይገቡ መታደግ ከ1000 ቀናት ንቅናቄዎች መካከል የሚጠቀሱ ተግባራት መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
እንደ ዋና ዳይሬክተሯ አባባል መቀንጨር ብዙና የተወሳሰቡ ተግዳሮቶች ያሉት ሲሆን በዛው ልክም ዘርፉ ብዙ ምላሽ ይጠይቃል፡፡ ምክንያቱም ይህ የተክለ ቁመና ጉዳይ ሳይሆን ከአዕምሮ ብስለት፣ ከትምህርት አቀባበል አቅም ጋር የተሳሰረ፣ በተለይም በፈጠራ ሥራ ላይ ትኩረት ማድረግና ዓለም በሚያራምደው ሳይንሳዊ ፍጥነት ውስጥ ኢትዮጵያን በዛው ልክ የሚያሻግር ትውልዱ ማፍራትን የሚጠይቅ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጤና ተቋማትም ለጡት ማጥባት ምቹ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ገልጸው፣ እስካሁንም ድረስ 14 የመንግሥት ጤና ተቋማት ለጡት ማጥባት ምቹ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ዕውቅና እንደተቸራቸው አስረድተዋል፡፡
የምግብና መድኃኒት አስተዳደር ባለሥልጣን የምግብ ኢንስፔክሽን ባለሙያ አቶ በትረ ጌታሁን፣ ‹‹የእናት ጡት ለሕፃናት ተወዳዳሪ የማይገኝለት ምግብ ነው፡፡ ከምግብም ባለፈ በሽታን የመከላከል አቅሙንና በአመጋገብ ሒደት ላይ ሊከሰት የሚችለውን የጤና ችግር ከመከላከል አንፃር ጠቀሜታው የጎላ ነው፤›› ብለዋል፡፡
እናቶች በተለያየ ምክንያት ማጥባት በማይችሉበት ጊዜ ለሕፃናት ሰው ሠራሽ ወተት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው፣ አቅርቦቱም ተገቢውን የፅዳትና ደኅንነት መስፈርትን ያሟላ ሊሆን እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡ ባለሥልጣኑም ለሕፃናት የሚውለው ምግብ መስፈርቱን አሟልቶ እንዲመረት ወይም ወደ አገር ውስጥ እንዲገባና እንዲከፋፈል ለማድረግ የሚያስችል የቁጥጥርና ክትትል ሥራ እንደሚያካሂድ አስረድተዋል፡፡
ከዚህ አኳያ እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ከባለሥልጣኑ ዕውቅና አግኝተውና ተመዝግበው ወደ አገር ውስጥ የገቡ 5170 የምግብ ዓይነቶች ሲሆኑ ከእነዚህም ውስጥ 121 ያህሉ የሕፃናት ምግቦች መሆናቸውን ነው ያመለከቱት፡፡
የወተት አምራች ድርጅቶች በሚያወጧቸው ማስታወቂያዎች ምክንያት የእናት ጡትን ከማጥባት ይልቅ ሰው ሠራሽ ወደሆነው ወተት የማዘንበል ሁኔታ እንደሚታይ በማስታወቂያዎች ሳቢያ የሚደርሰውን ጫና ለመቆጣጠር የጡት ወተት ላይ ሊደረግ የሚገባውን ጥበቃ በተመለከተ ዓለም አቀፍ መመርያ እንደወጣ ይህንንም መመርያ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ እየተተገበረ እንደሚገኝ ነው የገለጹት፡፡
የጤና ሚኒስቴር የፕሮግራም ዘርፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ያደታ እንደገለጹት፣ ጡት ማጥባት በልጆች አስተዳደግና ትምህርት አቀባበል እንዲሁም ባጠቃላይ ጤናማና መልካም ዜጎችን ከማፍራት አኳያ መተኪያ የለውም።
ባለፉት ሦስት አሠርታት በሥርዓተ ምግብ ላይ መንግሥት ባከናወነው ተግባር በምግብ እጥረትና አለመመጣጠን ችግር የሚጠቁ ሕፃናትን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ እንደተቻለ፣ በዚህም የተነሳ የመቀንጨር ችግር ከነበረበት 58 በመቶ ወደ 37 በመቶ፣ መቀጨጭ ከ12 በመቶ ወደ ሰባት በመቶ ዝቅ እንዲል ማድረጉን ሚኒስትር ዴኤታው ሳይገልጹ አላለፉም፡፡