Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትለአራት ኦሊምፒያድ ከወርቅ ሜዳሊያ የራቀው የኢትዮጵያ ወንዶች 5000ሜ ሩጫ

ለአራት ኦሊምፒያድ ከወርቅ ሜዳሊያ የራቀው የኢትዮጵያ ወንዶች 5000ሜ ሩጫ

ቀን:

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መድረክ መሳተፍ ከጀመረችበት እ.አ.አ. 1956 ሜልቦርን ኦሊምፒክ ጀምሮ በረዥም ርቀቱ ከሮም ኦሊምፒክ ወዲህ በርካታ ሜዳሊያዎችን ሰብስባለች፡፡ ከኦሊምፒክ ተሳትፎ ባሻገር፣ በዓለም ሻምፒዮናና በተለያዩ መድረኮች ላይ ኢትዮጵያን ወክለው መሳተፍ የቻሉ አትሌቶች፣ በረዥም ርቀቱ ውድድራቸውን በበላይነት  ሲጨርሱ ታይተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን የተሠለፉበት የ5000ሜ እና 10,000ሜ ውድድሮች ወርቁን ማን ያስገኛል የሚለው ጉዳይ እንጂ በነርሱ የበላይነት በአብዛኛው እንደሚጠናቀቅ አይጠረጠርም፡፡

እ.ኤ.አ. 2008 በቤጂንግ ኦሊምፒክ በቀነኒሳ በቀለ በ5000ሜ ካመጣችው የወርቅ ሜዳሊያ በኋላ፣ ወርቅ ማምጣት አልተቻለም፡፡ ኢትዮጵያ በሞስኮ ኦሊምፒክ በ‹‹ማርሽ ቀያሪው›› ምሩፅ ይፍጠር ፈር ቀዳጅነት ነበር ወርቅ ማምጣት የቻለችው፡፡

- Advertisement -

ከዚያ ጊዜ በኋላ በኦሊምፒክም ሆነ በዓለም ሻምፒዮና ላይ በርቀቱ ሜዳሊያ ማምጣት የተለመደ ነበር፡፡ በ2012 ለንደን ኦሊምፒክ ደጀን ገብረመስቀል አማካይነት የብር ሜዳሊያን ማግኘት የቻለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን፣ በ2016 ሪዮ ኦሊምፒክ ደግሞ በነሐስ ሜዳሊያ መመለስ ችሏል፡፡

በዘንድሮ ቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክለው የተጓዙት ጌትነት ዋለ፣ ንብረት መላክና ሚልኬሳ መንገሻ ነበሩ፡፡ ገና ከምርጫው ጀምሮ ክርክር ያልተለየው ይኸው ርቀት በእንጥልጥል አልፎ፣ ለፍጻሜ መድረስ የቻለው ሚልኬሳ ነበር፡፡ ሚልኬሳ በማጣሪያው 13፡31.13 በማጠናቀቅ ነበር ስድስተኛ ደረጃን ይዞ በነበረው ጥሩ ሰዓት ወደ ፍጻሜ ማለፍ የቻለው፡፡

ከወቅቱ የዓለም 10ሺ እና 5ሺ ሜትር ክብረ ወሰን ባለቤት የሆነው ዑጋንዳዊ ጆሾዋ ቺፕቴጌ 12፡58.15 በሆነ ሰዓት የወርቅ ሜዳሊያ በራሱ እጅ ማስገባት ችሏል፡፡ ቺፕቴጌ በ10ሺ ሜትር ፍጻሜ በሰሎሞን ባረጋ የተነጠቀውን ወርቅ በ5ሺ ሜትር ማካካስ ችሏል፡፡ በቀነኒሳ በቀለ በቤጂንግ ኦሊምፒክ ተይዞ የነበረውን 12፡57.82 ሰዓት ርቀቱን በግማሽ ሰከንድ በማሻሻል ጭምር ዑጋንዳዊው ማሸነፍ ችሏል፡፡

እሱን ተከትሎ ካናዳዊው መሐመድ አህመድ 12፡58.61 በሆነ ጊዜ ሁለተኛ ደረጃ ሲወጣ፣ አሜሪካዊው ፓውል ቺሊሞ 12፡59.05 ጊዜ ሦስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡

የመጨረሻዎቹ ዙሮች በጥሩ አያያዝ ሲጓዝ የነበረው ሚልኬሳ 13፡08.50 በሆነ ጊዜ አሥረኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡

ቀድሞ በኢትዮጵያና በኬንያ አትሌቶች የበላይነት ይያዝ የነበረው ርቀቱ፣ ዘንድሮ በካናዳና አሜሪካ አትሌቶች መያዝ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ከስምንት ወራት በላይ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በርቀቱ ብቃት ያላቸውን ልጆች ይዞ መዘጋጀት አለመቻሉ በርካቶችን አስቆጭቷል፡፡

ከዚህም ባሻገር በኢትዮጵያ አትሌቲክስና ኦሊምፒክ ኮሚቴ መካከል አለመግባባት መፍጠሩ በአትሌቶቹ ላይ የሥነልቦና ጫና ሳያሳድር እንዳልቀረ እየተነገረ ይገኛል፡፡ አትሌቶች ከሚፈልጉት ርቀቶች ወጪ እንዲሮጡ ማድረግና ጥሩ ብቃት ያሳዩበትን ርቀት እንዲሮጡ ያለመፍቀድ ችግር እንደ ነበር ተገልጿል፡፡

በተለይ በ10ሺ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘት የቻለው ሰሎሞን ባረጋ በ5ሺ ሜትርም መሮጥ የሚችልበት አቅም እያለው፣ መጠቀም አለመቻሉና በ3ሺ ሜትር መሰናክል ድንቅ ብቃት ላይ የነበረውን ጌትነት ዋለን እንዲሠለፍ መደረጉ ተገቢ አይደለም ሲሉ አስታየታቸውን የሰጡ በርካቶች ናቸው፡፡

ይሄም ትችት ሊነሳ የቻለው ለዑጋንዳ የወርቅ ሜዳሊያ ማስገኘት የቻለው ቺፕቴጌና እሱን ተከትሎ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቀው ካናዳዊው መሐመድ አህመድ በሁለቱም ርቀቶች ላይ መካፈላቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ከውድድሩ ፍጻሜ በኋላ አሸናፊው ዑጋንዳዊ ለጋዜጠኞች በሰጠው አስተያየት የ10,000 ሜትር አሸናፊው ሰሎሞን ባረጋ በውድድሩ ቢኖር በጣም ከባድ ይሆንብኝ ነበር ማለቱን የሪፖርተር ዘጋቢ ገልጿል፡፡ 

በሌላ በኩል በርቀቱ ልምድ ያለውና ዶሃ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ሞ ፋራን ረቶ የወርቅ ሜዳሊያ ማምጣት የቻለውን ሙክታር ኢድሪስ በማጣሪያው አምስተኛ ደረጃን መያዙን ተከትሎ፣ በቡድን ወስጥ አለመካተቱ ክርክር ያስነሳ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ ሆኖም አትሌቱ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መሠረት ወደ ቶኪዮ ቢያመራም፣ መዘግየቱን ተከትሎ መካፈል አልቻልም ነበር፡፡

በዚህ ውዝግብ ወስጥ ታጅቦ በርቀቱ የተካፈለው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በርቀቱ ያለምንም ሜዳሊያ አጠናቋል፡፡ ይኼም ውጤት ብሔራዊ ፌዴሬሽንና ኦሊምፒክ ኮሚቴ ችግሮቻቸውን እንዲፈቱ በር ይከፍታል የሚለው የበርካቶች አስተያየት ነው፡፡

ሴቶች 3,000 ሜትር መሰናከል

ኢትዮጵያ በመካክለኛ ርቀት ላይ ያላት ውጤት እምብዛም የሚጠቀስ ባይሆንም፣ መሳተፍ ከጀመረች ግን ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህም እሸቱ ቱራ እ.ኤ.አ. 1980 በሞስኮ ነሐስ፣ ሶፊያ አሰፋ 2012 በለንደን ብር ሜዳሊያ እንዲሁም ከ41 ዓመት በኋላ በለሜቻ ግርማ ቶኪዮ 2021 የብር ሜዳሊያ ማግኘት ተችሏል፡፡

በዘንድሮ ቶኪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ በ3,000 ሜትር መሰናክል በመቅደስ አበበ፣ ሎሚ ሙለታና ዘርፊ ወንድማገኘ ነበር የተወከለችው፡፡ ለፍጻሜ መድረስ የቻለችው መቅደስ አበበ ብቻ ነበረች፡፡ በኦሊምፒክ የመጀመርያ ተሳትፎዋን ያደረገችው መቅደስ፣ በፍጻሜው በ9፡06.16 አራተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡ ኢትዮጵያ ከ2012 ለንደን ኦሊምፒክ ድል በኋላ በርቀቱ ሜዳሊያ ማምጣት ተስኗታል፡፡ በሪዮ ኦሊምፒክ ሶፊያ አሰፋ፣ ሕይወት አያሌው እንዲሁም እቴኔሽ ዲሮን ብትወከልም፣ ለፍጻሜ ያለፉት ሶፊያና እህቴነሽ አምስተኛና 15ተኛ ደረጃን ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለይ በግል ውድድሮች ላይ ድንቅ ብቃት ሲያሳዩ ቢስተዋልም፣ አገራቸውን ወክለው ለዓለም ሻምፒዮናና ኦሊምፒክ ላይ ሲካፈሉ፣ በተመሳሳይ ብቃት ሲያሳዩ አይስተዋልም፡፡ በዚህም ርቀት ላይ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ አሠልጣኞች እንዲሁም አትሌቶች ችግራቸውን በጋራ መፍታት ይኖርባችዋል፡፡

ለአራት ኦሊምፒያድ

1,500 ሜትር ሴቶች

የሴቶች 1,500 ሜትር ከሞስኮ ኦሊምፒክ ጀምሮ መሳተፍ የጀመረችው ኢትዮጵያ፣ በአምሳለ ወልደገብርኤል ተወክላ ማጣሪያውን ማለፍ አልቻለችም ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በተለያዩ ኦሊምፒክ ጨዋታዎች ላይ በመካፈል በ2012 ለንደን ኦሊምፒክ በአበባ አረጋዊ የነሐስ ሜዳሊያ ስታገኘ፣ በ2016 በሪዮ ኦሊምፒክ ገንዘቤ ዲባባ የብር ሜዳሊያን ማግኘት ችላለች፡፡

በ2000 የሲድኒ ኦሊምፒክ ቁጥሬ ዱለቻ አራተኛ ደረጃን ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ፍሬወይኒ ገብረእግዚአብሔር፣ ድርቤ ወልተጂ እንዲሁም ለምለም ኃይሉ በ1,500 ሜትር ኢትዮጵያን የወከሉ አትሌቶች ናቸው፡፡

ሆኖም ወደ ፍጻሜው ማለፍ የቻለችው ፍሬወይኒ ነበረች፡፡ ፍሬወይኒ እ.እ.አ. 2019 አፍሪካ ጨዋታ ላይ 800 ሜትር መካፈሏን ተከትሎ፣ ሰኔ ወር ላይ ባደረገችው የኦሊምፒክ ቅድመ ማጣሪያ ውድድር ተከትሎ ወደ ቶኪዮ ማምራት ችላለች፡፡

በዚህም መሠረት በርቀቱ የረዥም ጊዜ ልምድ ካላቸው እንደነ ሲፋን ሐሰንና ኬንያዊቷ ቼፔንጌቲች ጋር ነበር ፍጻሜ ላይ የተገኘችው በፍጻሜው ቼፔንጌቲች 3፡35.11 በሆነ ጊዜ የኦሊምፒክ ክብረ ወሰን ጭምር በበላይነት ሲጠናቀቅ፣ ፍሬወይኒ 3፡57.60 አራተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች፡፡

ምንም እንኳን ፍሬወይኒ ሜዳሊያ ማምጣት ባትችልም፣ በመጀመርያ ኦሊምፒክ ተሳትፎ አራተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ በመልካም ጎኑ ይጠቀሳል፡፡ 

ለአራት ኦሊምፒያድ

20 ኪሎ ሜትር ዕርምጃ ፍጻሜ

ኢትዮጵያ በብቸኝነት በዕርምጃ የተወከለችው የኋላዬ በለጠ ከአምስት ኪሎ ሜትር በላይ ሳትጓዝ ለማቋረጥ ተገዳለች፡፡ ከሪዮ ኦሊምፒክ ጀምሮ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀቶች ላይ ኢትዮጵያን ወክላ የተወዳደረችው አትሌቷ፣ በ2019 በዶሃ ዓለም ሻምፒዮና 16 ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡ ኢትዮጵያን በበርካታ ውድድሮች ላይ በብቸኝነት ላይ በመወከል የምትታወቀው አትሌቷ፣ ለኅትመት እስገባንበት ጊዜ ያቋረጠችበት ምክንያት አልተገለጸም፡፡

በሁሉም ዓለም አቀፍ እንዲሁም አገር አቀፍ ውድድሮች ላይ በብቸኝነት አገሯን ወክላ ከምትካፈለው የኋላዬ ዓይነት ሌሎች ተተኪዎች ማሳደግ እንደሚገባ አስተያየት ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...