Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ቅዳሜ ሐምሌ 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ከስታዲየም ራይድ ይዤ ወደ ቃሊቲ በሚወስደው መንገድ ላይ እየተጓዝኩ ነው፡፡ ያሳፈረኝ ጎልማሳ የራይድ ሾፌር  በተሽከርካሪዎች በተጨናነቀው መንገድ ላይ እንደ ልብ ማሽከርከር ባለመቻሉ ቢቸገርም፣ እኔ ግን በዝግታ እየተጓዝን አካባቢውን በደንብ መቃኘት በመቻሌ ተደስቻለሁ፡፡ በዚህ መሀል ነበር ለገጠመኜ መነሻ የሆነውን ጉዳይ ያገኘሁት፡፡ በዚህ መንገድ ላይ ከተጓዝኩ ብዙ ዓመታት ስለተቆጠሩ አካባቢው በጣም ተለውጦብኛል፡፡ በተለይ በመንገዱ አካፋይ ላይ የባቡር መስመሩ ተዘርግቶ ሌላ አገር መስሏል፡፡ ልክ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ሲሆን ጠመንጃ ያዥ የሚባለው ሥፍራ ስንደርስ፣ መንገዱ ከተሽከርካሪዎች በተጨማሪ በሰዎች ተሞልቷል፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ስንጠይቅ የባቡር ማቋረጫው ላይ አንድ ግለሰብ በመገጨቱ ምክንያት መሆኑን ሰማን፡፡ የራይድ ሾፌሩ ከበው የሚያዩትን  እያሳየኝ፣ ‹‹ወይ የእኛ ሰው ለራሱ አይሠራ ሌላውን አያሠራ…›› እያለ በንዴት መሪውን በቡጢ ይጠልዛል፡፡

ሾፌሩ ሰው የተሰበሰበበትን ቦታ ባየ ቁጥር ይህንኑ ንዴቱን መሪውን በቡጢ በመጠለዝ እየገለጸ፣ ‹‹ይገርምሃል በየሄድኩበት ሥፍራ ሁሉ አንድ ችግር ወይም ሥራ ካለ የእኛ ሰው ከቦ መመልከት ይወዳል፡፡ ሌላው ቀርቶ ሰዎች ሲደባደቡ ከመገላገል ይልቅ ፊልም የሚያዩ ይመስል ብዙ ሰዎች ከበው ማየት ይቀናቸዋል…›› እያለ ተብሰለሰለ፡፡ ‹‹እንግዲህ ምን ይደረግ? ድህነት በገነነበት አገር ውስጥ እኮ የሥራ ዕድል በስፋት ስለሌለ ሰው ምን ያድርግ?›› በማለት ለማስተዛዘን ስሞክር፣ ‹‹ተው! ተው! ወንድሜ! ምን ነካህ? ሥራን ካልናቅን በስተቀር በጣም ብዙ የሚሠሩ ነገሮች አሉ፡፡ በሱስና በወሬ ካልተጠመድን በስተቀር ብዙ ጥቅም የሚገኝባቸው ሥራዎች አሉ፡፡ እኛን የሚያደኸየን ለወሬ የሚገብር ስንፍና ብቻ ነው…›› አለኝ፡፡

ይኼ የራይድ ሾፌር እንደነገረኝ የዛሬ አሥር ዓመት ገደማ ከደብረ ብርሃን ወጣ ብሎ ከሚገኝ ገጠራማ አካባቢ ነው ወደ አዲስ አበባ የመጣው፡፡ አዲስ አበባ ደርሶ ዘመድ ወይም ድጋፍ የሚያደርግለት ሰው ሳይኖረው፣ ራሱን ለማኖር ሥራ የጀመረው ሾላ ገበያ አካባቢ ዕቃ በመሸከም ነበር፡፡ እሱን ከሚመስሉ ሰዎች ጋር በጋራ ቤት ተከራይቶ የሚያገኘውን ከቆጠበ በኋላ ሎተሪ ማዞር ጀመረ፡፡ ከዚያም አትክልት ተራ አካባቢ እየተሸከመም እየደለለም ገንዘቡን ጠርቀም ካደረገ በኋላ መኪና ማሽከርከር መለማመድ ጀመረ፡፡ ጥርሱን ነክሶ ልምምዱን ከጨረሰ በኋላ ሦስተኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ ማውጣቱን አስረዳኝ፡፡ ለተወሰኑ ወራት ሚኒ ባስ ካሽከረከረ በኋላ ላዳ ታክሲ ተቀጥሮ መሥራት መጀመሩን ነገረኝ፡፡

‹‹እኔ በተፈጥሮዬ ያሰብኩትን ዓላማ ለማሳካት እንቅልፍ አጥቼ የማድር ሰው በመሆኔ ቀንና ሌሊት ያለማቋረጥ መሥራት ጀመርኩ፡፡ ሆስፒታል ለአስቸኳይ ሕክምና ከሚሄዱ ሕሙማን ጀምሮ በመጠጥ ጥምቢራቸው የዞረባቸውን ጨምሮ ቀንና ሌሊት እያገለገልኩ ዕቁብ መጣል ጀመርኩ፡፡ በፀባዬ ምክንያት ከቀረቡኝ ሰዎች ሳይቀር ድጋፍ ተደርጎልኝ ላዳ ታክሲዋን ከባለቤቷ ገዝቼ የራሴ አደርግኳት፡፡ አትክልት ተራ እያለሁ በቀን እስከ 200 ብር አገኝ ነበር፡፡ ያኔ ጓደኞቼ በጫትና በመጠጥ ሱስ ሲናውዙ ዓላማ ነበረኝና እኔ የላዳ ታክሲ ባለቤት ሆንኩ፡፡ ከዚያ ደግሞ ይህችን ያሪስ ገዝቼ ራይድ እሠራለሁ፡፡ አሁን ደግሞ የራሴን ቤት ለመሥራት ደፋ ቀና እያልኩ ነው…›› እያለ ሲነግረኝ በጣም አስገረመኝ፡፡

የራይድ ሾፌሩ እንደሚለው በአገራችን ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ስንፍና አለ፡፡ ብዙ ሰዎች በመንግሥት ካልተቀጠሩ በቀር ምንም ዋስትና የሌላቸው ይመስል ይጨናነቃሉ አለኝ፡፡ ‹‹በግል ድርጅት ተቀጥረው የሚሠሩ ብዙ ሰዎች ደስተኞች አይመስሉም፡፡ የራሳቸውን ሥራ ለመጀመር ደግሞ ፍላጎት የሌላቸው ብዙ ናቸው፡፡ ይኼ ዓይነቱ የጥገኝነት አስተሳሰብ ደግሞ ሰዎች ተስፋ እንዲቆርጡ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ ሠፈሬ ውስጥ የማውቃቸውን ወጣቶች ሥራ ስለሌላቸው ለምን ያገኙትን እንደማይሠሩ ስጠይቃቸው ይስቁብኛል፡፡ አንዱ በተለይ ‹ጎዳና ላይ ከመሥራት በረሃብ መሞት ይሻለኛል› ሲለኝ ገረመኝ፡፡ ለሲጋራና ለጫት ሲሆን ግን ልመናቸው አይጣል ነው፡፡ ይኼንን የጤንነት ነው ትለዋለህ?›› ሲለኝ ምንም ምላሽ አልነበረኝም፡፡

‹‹በቅርቡ የማገባት ዕጮኛዬ ወንድሞች በቤተሰብ ትከሻ ላይ ነው የሚኖሩት፡፡ የራሴን እውነተኛ ታሪክ ነግሬያቸው እንዴት ከጥገኝነት መላቀቅ እንዳለባቸው ስመክራቸው የማወራቸው ሁሉ ተረት መሰላቸው፡፡ እነሱ ከተንቀሳቀሱ ድጋፍ እንደማደርግላቸው ስነግራቸው ‹ይልቅስ እሱን ተወውና መጨበሺያውን አምጣው› ሲሉኝ ተስፋ ቆረጥኩ፡፡ ይኼ አያናድድም?›› ሲለኝ አንገቴን በመስማማት ነቀነቅኩኝ፡፡ ቃሊቲ ደርሰን ከመሰነባበታችን በፊት የራይድ ሾፌሩ እንዲህ አለኝ፡፡ ‹‹ሰው ሥራ ፈቶ የሚሠራን ከቦ ሲያይ ብቻ አይደለም የምናደደው፡፡ ከሁሉ በላይ የሚያበሳጨኝ አንተ ደም ተፍተህ ያገኘኸውን ገንዘብ በነፃ ካልሰጠህ የሚወጣልህ አጓጉል ስያሜ ነው፡፡ ስስታም፣ ቀብቃባ፣ ቋጣሪ፣ ወዘተ ትባላለህ፡፡ የሥራ ፈጣሪነትህና ታታሪነትህ ሳይሆን በሥራ ፈቶች  የወጣልህ ስም በየሄድክበት ይከተልሃል፡፡ ወይ አይሠሩ ወይ አያሠሩ… ሌሎች አሉልህ ደግሞ ወጣቱን ለሥራ ከማንቀሳቀስ ይልቅ ለማይረባ የፖለቲካ ዓላማቸው አሽከር ለማድረግ ጦርነት ውስጥ የሚማግዱት፡፡ እነዚህ ደም የጠማቸው አረመኔዎች የስንቱን ወጣት ራዕይ አጨናግፈው፣ ደሙን ደመ ከልብ እያደረጉት ደረታቸውን ነፍተው በፌስቡክና በዩቲዩብ ሲመፃደቁ ደሜን ያፈሉታል፡፡ ለማንኛውም ከድህነትም ሆነ ከጦርነት ውስጥ ለመውጣት ጭንቅላትን ማሠራት የሚጠቅም ይመስለኛል፡፡ ካልሆነ ግን አገራችን ደም የጠማቸው አውሬዎች መፈንጫ መሆኗ አይቀሬ ነው…›› እያለ ውስጡ እየተንገበገበ ብዙ ነገሮች ከነገረኝ በኋላ ተለያየን፡፡ ስንቶች ይሆኑ ውስጣቸው የሚጨሰው?

(ሰለሞን ዘውዱ፣ ከጃክሮስ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...