Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉየኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት በግማሽ መቀነስ አለበት

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት በግማሽ መቀነስ አለበት

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

ይህንን ጽሑፍ ‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከየት ወዴት›› በሚል ርዕስ በግንቦት 2010 ዓ.ም. ባሳተምኩት መጽሐፍ ከገጽ 392 እስከ 397 ያሠፈርኩት ነው፡፡ ዛሬ በድጋሚ አሻሽዬ ላቀርበው የወደድኩት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አሁን ካለበት ሁኔታና ሰሞኑን ካነበብኩት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ገዳ በ2012 ዓ.ም. በተረጎሙት ታዋቂው ፖላንዳዊ ኢኮኖሚስት ሚካኤል ካልስኪ መጽሐፍ ውስጥ በምዕራፍ ሰባት፣ ‹‹በህንድ የሦስተኛው አምስት ዓመት ዕቅድ የልማት ወጪዎች አሸፋፈንና ችግሮቹ ላይ አንዳንድ ትዝብቶች›› በሚል ርዕስ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ሳምንታዊ ዘገባ በሚባለው ታዋቂ የህንድ የምርምር መጽሔት ላይ በ1960 ዓ.ም. ከወጣው ጽሑፍና ከእኛ ያለፉት ሦስት ዓመታት የዋጋ ንረት ጋር አንባቢያን እንዲያመሳክሩ ነው፡፡

የካልስኪ መጽሐፍ ከአቅርቦት ጎን የሴክተርና የፕሮጀክት የልማት ኢኮኖሚክስ አንፃር ተመልክቶ፣ የአገሪቱ ዕድገት ምንም ዓይነት የዋጋ ንረት በመሠረታዊ ዕቃዎች ላይ ማምጣት የለበትም ይላል፡፡ እኔም በቅርቡ የለውጥ ኃይሉ መታወቂያ በሆኑት የዋጋ ንረትና የብር ተመን መውደቅ በሚል ርዕስ በሪፖርተር ጋዜጣ ባወጣሁት ጽሑፍ፣ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦት (Money Supply) የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲና የልማት ወጪ አሸፋፈን የገንዘብ አስተዳደር ልቅነት (Financial Liberalization) የልማት ኢኮኖሚ እየተጋጩ ለዋጋ ንረትና ለብር ምንዛሪ ውድቀት እየዳረጉን እንደሆነ፣ ማክሮ ኢኮኖሚውንና የልማት ኢኮኖሚውን ጎን ለጎን በመዳሰስ ለማሳየት ሞክሬያለሁ፡፡ ይህ ምክር ደግሞ አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት የዋጋ ንረት ጋር ተነፃፅሮ መመርመር ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

ፕሮፌሰር ዓለማየሁን ለዚህ ታላቅ ወገናዊ ሥራቸው እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ላመሠግናቸው እወዳለሁ፡፡ ኢኮኖሚስት ነኝ ያለ ብቻ ሳይሆን ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚጨነቅ ሁሉ እንዲያነበው እመክራለሁ፡፡ የካልስኪ መጽሐፍ እኔ እንደተረዳሁት የሚያዘነብለው ወደ የክፍለ ኢኮኖሚና የፕሮጀክቶች አስተዳደራዊ የአቅርቦት ጎን ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ ሲሆን፣ ሊተረጉሙልን ቃል በገቡት የኬንስ መጽሐፍም ስለገቢና የኢኮኖሚ ዕድገት የፍላጎት ጎን ኢኮኖሚያዊ ትንታኔ ብዙ ነገር እንደምናይ ተስፋዬ እጅግ ትልቅ ነው፡፡

እኔ ጽሑፌን ስጽፍ የካልስኪን መጽሐፍ ከዚህ ቀደም አላየሁም፡፡ የምርት ዕድገት ይቀንስ የሚል የኢኮኖሚ ንድፈ ሐሳብም አጋጥሞኝ ስለማያውቅ ጽሑፉን የጻፍኩት ፈራ ተባ እያልኩ ነበር፡፡ አንድ አገር ወዳድ አንባቢም ጽሑፉ በወጣ በአሥራ አምስተኛው ቀን በሐሳቤ ባለመስማማት ሒስ አቅርቧል፡፡ ጽሑፉን በድፍረት እንድጽፍ ያስገደደኝ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ ስለሆንኩኝ ዕቅድ ምኞት ሳይሆን፣ ሊሠራ  ከሚገባ የሚቻለውንና የማይቻለውን መምረጥ እንደሆነ ስለምገነዘብ ነው፡፡ ጽሑፌ የሚከተለው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት ለቀጣይነት፣ ለሰላምና ለማኅበራዊ መረጋጋት፣ እንዲሁም ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ሲባል እስካሁን ከሚያስመዘግባቸው የአሥርና የአሥራ አንድ በመቶ ዕድገት መጣኞች በግማሽ ቀን ስለተወሰኑ ዓመታት ወደ አምስትና ስድስት በመቶ የዕድገት መጣኞች ዝቅ ማለት አለበት፡፡ የአገር ኢኮኖሚ ዕድገት ይቀንስ ሲባል ያማል፡፡ ነገር ግን ታሞ ከሥቃይ መዳን የሚቻል ከሆነ፣ እየተሰቃዩ ለረዥም ጊዜ ከመኖር ለጥቂት ጊዜ ታሞ መዳን ይሻላል፡፡ እየተራብን፣ እየታረዝን፣ መጠለያ አጥተን የፍጆታችን መጠን ከዓለም የመጨረሻውን ደረጃ ይዞ፣ በዕድገት ከዓለም አንደኛ ነን ብለን መፎከር፣ ሥቃያችንን አምቀን ይዘን በዕድገታችን ከእኛ የሚስተካከል አገር የለም ማለት አላዋጣንም፡፡ በሁለት አኃዝ ማደጋችንን ለዓለም ሕዝብ ለማውራት ፈልገን፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ለአንድ ቀን በጎበኘን ፈረንጅ የምናስመሰክረው የጉራ ወሬ ማኅበራዊ መሠረታችንን አናጋው፣ ሰላማችንን አደፈረሰው፡፡

ማንኛውም ነገር የዕጦት ወጪ (Opportunity Cost) አለው፡፡ ለመዋዕለ ንዋይ በወጣ ወጪ ብዙዎች ፍጆታ ቀርቶብናል፡፡ በተሠሩት ሕንፃዎች ልክ፣ በተዘረጉት መንገዶች ልክ፣ በተከፈቱት ዩኒቨርሲቲዎች ልክ ዜጎቻችን ተርበዋል፣ ታርዘዋል፣ መጠለያ አልባ ሆነዋል፣ ተሰደዋል፣ በበረሃ በባህርና በወንበዴዎች እጅ ሞተዋልም፡፡ የሚታዩትን ሕንፃዎች፣ መንገዶችና ዩኒቨርሲቲዎች  እየቆጠርን የማይታዩትን የተራቡ አንጀቶች፣ የታረዙ ገላዎች፣ መጠለያ ያጡ ነፍሶች፣ በኑሮ ሁኔታ የተሰደዱና እስከ ዘለዓለሙ ያሸለቡ ወጣቶቻችንን ሕይወት ሳንቆጥር በዕድገታችን እንኩራራለን፡፡

የብራችን ሸቀጣ ሸቀጥን የመግዛት አቅሙና ከውጭ አገሮች ምንዛሪዎች ጋር የመመነዛዘሪያ አቅሙ ቁልቁል ወርዶ፣ ወጣቶች በአገር ውስጥ ሠርቶ ከመኖር በውጭ አገር ሠርቶ መኖር በብር ተመንዝሮ የሚገኘው ገቢ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው አሥልተው፣ በበረሃና በባህር እየሞቱም ወደ ውጭ ለመኮብለል ልባቸው እስከሚሸፍት ድረስ የአገር ውስጥ ግብይታችን ዝቅተኛ ሆኖ ተመሰቃቅሏል፡፡ የዩኒቨርሲቲዎችን ብዛት እየቆጠርን የምናስተምራቸው ወጣቶች ተመራምረው አገር የሚያሳድጉ ሳይሆኑ፣ ለባዕዳን ሎሌ ሆነው የሚያገለግሉ መሆናቸውን እንዳናይ ዓይናችን ተጋርዷል፣ ልባችን ደንድኗል፡፡ አንዱ የሚበላው አጥቶ ፆሙን ያድራል፣ ሌላው አጠገቡ በሊሞዚን ጋብቻ ይፈጽማል፡፡ ይህ ሁሉ የአሥርና የአሥራ አንድ በመቶ ዕድገቶች ያመጡት ጣጣ ነው፡፡

 

በእርግጥ የአንድ አገር ኢኮኖሚ ዕድገት ይቀንስ ማለት ዝም ብሎ በስሜት የሚናገሩት ነገር አይደለም፣ በቂ ትንታኔና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በምን ያህል ይቀንስ የሚለውም የብሔራዊ ኢኮኖሚ ተንታኞችን፣ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንታኞችን፣ የዕድገት ሞዴሎች ባለሙያዎችንና የሌሎችንም ብርቱ ጥናት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ በባለሙያዎች ተጠንቶ ዕድገቱ ከግማሽ በታች ሊሆንም ይችላል፡፡ ጥናቱን የማጥናቱንና የማስጠናቱን ጉዳይ ምሁራንንና ባለሙያዎችን የሚሰማ መንግሥት ከተገኘ ለመንግሥት ትቼ፣ እኔ በበኩሌ ዕድገቱ መቀነስ አለበት የምልበትን አንዳንድ አሳማኝ ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡

አንደኛ የሁለት ቢሊዮን ዶላር የኤክስፖርት ሸቀጣ ሸቀጥ ሸጠን የ16 ቢሊዮን ዶላር የኢምፖርት ሸቀጥ በመግዛት፣ በየዓመቱ አሥራ አራት ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የኤክስፖርትና የኢምፖርት ጉድለት ፈጥረናል፡፡ ጉድለቱን ለመሙላት ከተሰደዱ ልጆቻችንና ከውጭ መንግሥታት የሚላክልን የዕርዳታ ዶላርም ተጨምሮ፣ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሒሳባችን የሰባትና የስምንት ቢሊዮን ዶላር ጉድለት ያሳያል፡፡ ይህን ጉድለት የምንሸፍነው ከውጭ በመበደር፣ የውጭ ኢንቨስተሮች እንዲመጡ በመለመን፣ ከካፒታል ሒሳብና ካለችው የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ተቀማጭ ላይ በመቀነስ ነው፡፡ ኤክስፖርትን በማበረታታት ጉድለቱን ለማስወገድ የተደረጉት ሙከራዎች ስኬታማ አልሆኑም፡፡ የውጭ ዕርዳታውም ቀንሷል፡፡ በተበደርነው ልክ ክፍያ ስላልፈጸምንም አዲስ ብድር ማግኘት ተስኖናል፡፡ የውጭ ኢንቨስተሮች መምጣትም እየተንገዳገደ ነው፡፡ ስለዚህም ኢኮኖሚያችንን የምናስተካክልበት ሌላ ዘዴ መፈለግ ያስፈልጋል፡፡

በብሔራዊ ኢኮኖሚ ሥሌት መሠረት በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለትና በአገር ውስጥ ኢኮኖሚ የቁጠባና መዋዕለ ንዋይ ጉድለት (The Two Gaps Model) እኩል ስለሆኑ፣ የአንዱን ጉድለት በሌላው በማጣፋት ማስተካከል ይቻላል፡፡ በአገር ውስጥ ቁጠባና መዋዕለ ንዋይ ሲመጣጠኑ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለት ይወገዳል፡፡ ለኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ የሆነው መዋዕለ ንዋይ በቁጠባ ልክ እንዲሆን መቀነስ ካለበት ለውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ሲባል፣ የኢኮኖሚው ዕድገት ቀንሶ የውስጡና የውጭ ኢኮኖሚ መስተካከል አለባቸው፡፡ በአገራዊ የፍጆታና የመዋዕለ ንዋይ ድምር የሸመታ ወጪ ጥቅል የአገር ውስጥ ምርት መጠን መካከል ባለው ልዩነት ልክ በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት የተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለትም ስለሚኖር፣ አገራዊ የሸመታ ወጪውን በጥቅል የአገር ውስጥ ምርት ልክ በማድረግ በውስጥ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለቱን ማረምም ይቻላል፡፡

ሁለተኛ ምርታማነት ሳያድግ የአንዳንድ ሰዎች ደመወዝ በአሥር ዓመት ውስጥ ከ5,000 ብር ተነስቶ ሰላሳ እጥፍ በማደግ 150,000 ብር ደረሰ፡፡ ከዚህ በታች የሚያገኙትም ቢሆኑ ከምርታማነታቸው ጋር የሚመጣጠን አይደለም፡፡ እያንዳንዳችን ምን ሠርተን ምን አገኘን ብለን ብንጠይቅ፣ ራሳችንን በራሳችን ሳንታዘብ አንቀርም፡፡ ሕንፃ ላይ የፈሰሰ ካፒታል ለባለቤቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር የወር ገቢ ቢያስገባም፣ ለአገር ግን ምርታማነቱ ዝቅተኛ ነው፡፡ የንግድ ትርፍ ለነጋዴው ከመቶ በመቶ በላይ ገቢ ቢያስገኝም፣ በምርታማነት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ የብዙዎቻችን ምርታማነት ከሸሚዛችን በላይ ያጠለቅነው ከራቫታችንን እንኳ አያክልም፡፡ ገቢያችን ግን በወርቅ አምባርና ሐብል አጥለቅልቆናል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት ‹‹ግላዊና ብሔራዊ ኢኮኖሚያችን›› በሚል ርዕስ ባሳተምኩት መጽሐፍ ውስጥ እንደ መፈክር የደጋገምኩት፣ ‹‹ከምርታማነታችን በላይ በምናገኘው የግለሰብ ገቢ ልክ አገሪቱን እያከሰርን፣ የመጪውን ትውልድ ተስፋም እያጨለምን ነው›› የሚለው ስንኝ ዛሬም ድረስ ትክክል ሆኖ፣ ነገም ለከርሞም ትክክል ሆኖ ይቀጥላል፡፡ የግለሰብ ገቢ ከምርታማነት በላይ መሆን በሸቀጦች ዋጋ ማሻቀብም እየታየ ስለሆነ፣ በዋጋ አወሳሰን ሥርዓት አምራቹ ብቻ ሳይሆን ሸማቹም ዋጋ የመወሰን አቅም እንዲኖረው፣ በዋጋ አወሳሰን አቅርቦትና ፍላጎት እኩል ሚና እንዲኖራቸው፣ ከምርታማነት በላይ ያደገው የግለሰብ ገቢ መቀነስ ስላለበት ለዚህ ሲባል የኢኮኖሚው ዕድገት መገታት አለበት፡፡

ሦስተኛ ኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ለመቀነስ ያለ ልፋትና ለሌሎች የሚጠቅም አገልግሎት ሳይሰጡ በሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ኪራይ (Economic Rent) ጥቂቶች ከበሩ፣ ብዙዎች ደኸዩ፡፡ ኢኮኖሚያዊ ኪራይ ማለት ለሌላው የሚጠቅም ሥራ ሳይሠሩ ሳይለፉ የሚያገኙት ገቢ ማለት ነው፡፡ ኢኮኖሚያዊ ኪራይ የሚፈጠረው ሰዎች የአገሪቱን ሀብት አተልቀው ከትልቁ ለየአንዳንዱ የሚገኘውን ጥቅም አብዝቶ መከፋፈል ይልቅ፣ ካለው የአገሪቱ ሀብት ውስጥ የራሳቸውን ድርሻ ለማተለቅ ሲጥሩ ነው፡፡ የአሥርና የአሥራ አንድ በመቶው ዕድገት በሰፊው ሕዝብ ጥረት፣ ድካምና ላብ የተፈጠረ ተጨማሪ እሴት ቢሆንም፣ በኢኮኖሚያዊ ኪራይ መልክ ጥቂቶች የሚሰበስቡት ስለሆነ፣ ዕድገቱ ቢቀንስ ሰፊው ሕዝብ አይጎዳም፣ የጥቂቶቹ ኢኮኖሚያዊ ኪራይ ገቢ ነው የሚቀንሰው፡፡

አራተኛ  የካፒታል ክምችት መዛባትን ለመቀነስ፣ በመሠረቱ በኢኮኖሚ ጥናት የተረጋገጠው ሀቅ ደሃ ገቢውን ለፍጆታ ያውላል፣ ሀብታም ግን ቆጥቦ መዋዕለ ንዋይ ያፈሳል የሚል ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ግን ደሃው በ‹‹ባጃጅ ትሸለማለህ›› እየተማለለም እንዲቆጥብ ይደረጋል እንጂ፣ ሀብታም አይቆጥብም፡፡ ሀብታም የደሃውን ቁጠባ ወስዶ ሕንፃ ይሠራበታል፡፡ በአዲስ አበባ የተገነቡት ሕንፃዎች በሙሉ የተሠሩት ደሃው አንጀቱን አስሮ ባስቀመጠው ቁጠባ ነው፡፡ ለገጠሩ ቆጣቢዎች በሚከፈለው ከዋጋ ንረት ያነሰ የቁጠባ ወለድ መጣኝ ምክንያት ንብረቱ በየጊዜው ስለሚቀንስ፣ የገጠሩ ሀብት ተሟጦ ወደ ከተማ ሸሽቶ በሕንፃ ግንባታ ላይ ስለፈሰሰ፣ ለገጠሪቱ ኢትዮጵያ ድገት መሠረት የሚሆን የካፒታል ክምችትም በገጠር አልተፈጠረም፡፡ ግብርናው ሳያድግ ኢንዱስትሪው ስለማያድግ፣ ገበሬው በቁጠባው እንዳይከስርና የገበሬው ገቢ እንዲጨምር የቁጠባ ወለድ መጣኝ ቢያንስ ከዋጋ ንረት በላይ መሆን አለበት፡፡ የቁጠባ ወለድ መጣኙ መስተካከል መዋዕለ ንዋይን ስለሚገታ፣ የከተማው ሕንፃ ግንባታ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መቀነሱ አይቀርም፡፡

አምስተኛ የዋጋ ንረትን ለመግታት፣ የዋጋ ንረት ማለት መንግሥት በየእያንዳንዳችን ኪስ ውስጥ ብዙ ጥሬ ገንዘብ አስቀምጧል ማለት ነው፡፡ ብዙ ብሮች ጥቂት ሸቀጦችን ያሳድዳሉ ማለት ነው፡፡ በደርግ መውደቂያ ዓመታት ነጠላ አኃዝ ቢሊዮን ቁጥር የነበረው የጥሬ ገንዘብ መጠን ዛሬ አምስት መቶ ቢሊዮን ደርሷል፡፡ ጥሬ ገንዘቡ እንዲበዛ የሚያደርጉት ብሔራዊ ባንክ በሚያሠራጨው ምንዛሪዎች (ብርና ሳንቲሞች) እና ንግድ ባንኮች ብሮቹን አርብተው ስለሚያበድሩ ነው፡፡ ለኢኮኖሚው የሁለት አኃዝ ዕድገት ሲባል፣ መንግሥት የበጀት ጉድለት ውስጥ መግባቱ፣ የፊስካል ፖሊሲና ኢኮኖሚውን ለማስፋፋት በገበያው ውስጥ የተሠራጨው የጥሬ ገንዘብ ብዛት አስፋፊ ሞኒተሪ ፖሊሲ፣ የሥራ አጥነትን ችግር ሳያስወግዱ በዋጋ ንረት ላይ ብቻ ተፅዕኖ የፈጠሩና በመፍጠር ላይ ያሉም በመሆናቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ቀውስ አስከትለዋል፡፡

2011 በጀት ዓመት የቀረበው 50 ቢሊዮን ብር የበጀት ጉድለት ያለበት 346 ቢሊዮን ብር የመንግሥት በጀት የቁጠባና የመዋዕለ ንዋይ ክፍተትን፣ ብሎም የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ተንቀሳቃሽ ሒሳብ ጉድለትን ከማስፋት፣ ምርታማ ባልሆነ ሥራ የግለሰቦችን ገቢ ከማሳደግ፣ ኢኮኖሚያዊ ኪራይን ከመፍጠር፣ አልፎ ተርፎ በእርግጣዊ ኢኮኖሚው (Real Economy) ላይ የሚፈጥረው ዕድገት አይኖርም፡፡ ለሁለት አኃዝ የኢኮኖሚ ዕድገት ሲባል፣ በዓመት በአማካይ በሃያ ስምንት በመቶ የሚያድገው የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትም የዋጋ ንረት ፈጥሮ የሀብት ክፍፍሉን ከደሃው ወደ ሀብታሙ አሸጋገረ እንጂ፣ ለሕዝብ የሚጠቅም የኢኮኖሚ ዕድገት አላመጣም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ከሁለቱ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት ስም ሕዝብን የሚጎዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚመስሉ፣ ግን ካልሆኑ ድርጊቶች እንዲቆጠብ የኢኮኖሚ ምሁራን ምክራቸውን ሊለግሱት ይገባል፡፡

ስድስተኛ መንግሥት መር ልማታዊ ኢኮኖሚ ማለት የግድ ድርጅቶች የመንግሥት ይዞታ ይሆናሉ ማለት ሳይሆን፣ የማምረቻ ሀብት በግል ይዞታም ይሁን በመንግሥት የኢንዱስትሪ ዕድገቱን፣ የዋጋ አወሳሰን ሥርዓቱንና የሀብት ድልድሉን ለገበያው ከመተው፣ በዕቅድ ጣልቃ በመግባት በቅድሚያ ሊያድግ የሚገባውን ኢንዱስትሪ መርጦ ፖሊሲውን፣ ስትራቴጂውንና ዕቅዱን ለዚያ ተግባር ያውላል ማለት ነው፡፡ ይህን የልማታዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ከሀብት ይዞታ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር የለም፡፡ ከሀብት ይዞታ ጋር የሚገናኝ ቢሆን ኖሮ ሶሻሊስታዊ ወይም ካፒታሊስታዊ፣ ወይም ከፊል ካፒታሊስታዊና ከፊል ሶሻሊስታዊ የኢኮኖሚ አስተዳደር ይባል ነበር፡፡ በመንግሥት ይዞታ ሥር መሆን የሚገባቸው ድርጅቶች ከልማታዊ መንግሥትነት ውጪ የሆነ ታሪካዊ አመጣጥ አላቸው፡፡ ከዚህም ውስጥ አንዱ ገበያው ለኅብረተሰቡ ሊያቀርባቸው የማይችላቸው ወይም ቢችልም ኅብረተሰቡን በዋጋ አወሳሰን ሊበዘብዝባቸው የሚችሉ ድርጅቶች ይገኙበታል፡፡

በቅርቡ በመንግሥት ለግል ባለሀብቶች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ እንዲሸጡ ከተወሰኑት ድርጅቶችም፣ ከፊሎቹ በገበያ መር ኢኮኖሚ ቢተዳደሩ የሚመረጥና ከፊሎቹ መንግሥት መር ሆነው በዕቅድ ቢተዳደሩ የሚመረጡ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የቱ በየትኛው የሚለው በእያንዳንዱ ላይ ጥልቅ ጥናት ተደርጎ የሚወሰን ነው፡፡ ከዚህ አለፍ ሲልም፣ ኢኮኖሚያዊ አስተዳደርም ከጊዜው ጋር ስለሚለዋወጥ በዚህ ዘመን በብዙ ልማታዊና ገበያ መር አገሮች የሚታመንበት የኢኮኖሚ አስተዳደር መንግሥትም ሆነ የግል ባለሀብት በተናጠል በግላቸው የኅብረተሰብን ፍላጎት ማርካት ስለማይችሉ፣ በሽርክና ሊሠሩባቸው የሚችሉ በርካታ መሠረተ ልማቶች እንዳሉ የታመነበት ጊዜ ነው፡፡ በአየር መንገዱ የሚጓጓዘው ሀብታሙ የኅብረተሰብ ክፍል ነው፡፡ መብራት በዝቅተኛ ዋጋ ሊቀርብ የሚገባው ግን ለደሃው ኅብረተሰብ ነው፡፡ በይዞታ አስተዳደር ወግ ሳይሆን፣ በልማታዊ መንግሥት የኢንዱስትሪ ‹‹ዕድገት ዕቅድ ተኮር ወይስ ገበያ ተኮር?›› ምርጫ ከአምራቹ አንፃር ብቻ ሳይሆን፣ የዋጋ አወሳሰን ሥርዓትንና ተደራሽነትን ማዕከል አድርገው ከሸማቹ አንፃር ሊታይም ይገባል፡፡ ሆኖም መንግሥት ጥልቅ ጥናት ሳይደረግ፣ የውጭ ምንዛሪ ስለቸገረው ብቻ ይህንን ርምጃ ወስዶ ከሆነና ዋናው ምክንያትም የኢኮኖሚውን የሁለት አኃዝ ዕድገት ለማስቀጠል የተደረገ መንገታገት ከሆነ፣ በዚህ ጊዜያዊ ዕርምጃ ብቻ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱን በዘላቂነት መፍታት ስለማይቻል ስህተት ነው፡፡ የውጭ ኢኮኖሚ ጉድለትን በውስጥ ኢኮኖሚ ማስተካከያ ማረም ብቻ ነው ዘላቂ መፍትሔ፡፡

ሰባተኛ ከኢኮኖሚው የሁለት አኃዝ ዕድገት በላይ ሊያስጨንቁን የሚችሉ በርካታ ፈተናዎች ተጋርጠውብናል፡፡ ኢኮኖሚያችን የሚፈጥረው ማኅበራዊ ቀውስ አድጎ ሳይበታትነን በፊት ጊዜ መሻማት አለብን፡፡ ኢኮኖሚውን ለማስተካከል በኢኮኖሚስቶች ተጠንተው የገበያ ኢኮኖሚ ሥርዓት ሊያስተካክላቸው ይችላል የሚባሉት የገበያ ኢኮኖሚው እንዲሠራ ነፃ በማድረግ፣ የገበያ ኢኮኖሚ ጉድለት አለበት በተባለበት ቦታም የሸማቹን አቅም በሚገነቡ የብሔራዊ ኢኮኖሚ ፖሊሲና የአምራቹን አቅም በሚገነቡ የግል አምራች ድርጅቶች ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ለአገር ዕድገት ይጠቅማሉ የሚባሉ፣ በሌሎች አገሮች ተግባራዊ የተደረጉ ሥር ነቀል ርምጃዎች ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተገናዝበው መወሰድ አለባቸው፡፡ ለምሳሌም ዝቅተኛውን የሠራተኛ ክፍያ ደመወዝ ወለል በሕግ መወሰን፣ የትርፍ ህዳግን በሕግ መወሰን፣ ቁሳዊ ሀብት በማያፈራና ለባለቤቱ ብቻ የትርፍ ገቢ በሚያመጣ እንደ ሕንፃ በመሳሰለ ሀብት ላይ አዳጊ የሀብት ግብር (Progressive Property Taxation) እና አዳጊ የአከራይ ተከራይ ግብር መጣል የመሳሰሉት ዕርምጃዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ የሀብት ሥርጭት ፍትሐዊነትን የሚያሰፍኑ ፖሊሲዎች ሲቀረፁ የኢኮኖሚውን ዕድገት እንደሚቀንሱት ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...