ኮቪድ-19 በኢኮኖሚውና በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች ላይ ተፅዕኖ አሳድሮ ቆይቷል፡፡ አሁንም ይህ ተፅዕኖ አልተቀረፈም፡፡ ወረርሽኙ ተፅዕኖ ካሳረፈባቸው ቢዝነሶች ውስጥ የንግድ ትርዒትና ባዛሮች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
በየዓመቱ በቋሚነት ሲካሄዱ የነበሩ የንግድ ትርዒትና ባዛሮች በዚሁ ወረርሽኝ ምክንያት እንዲሰረዙ ተደርገዋል፡፡ በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ጎብኚዎችና ሸማቾች ይስተናገዱባቸው የነበሩ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች ከአንድ ዓመት በላይ እንደቀደመው ያለመካሄዳቸው አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ትልልቅ የሚባሉ የንግድ ትርዒቶች ይስተናገዱባቸው የነበሩ እንደ አዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልና ሚሊኒየም አዳራሾች እንደ ቀደመው ጊዜ ማንኛውንም ዓይነት የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮችን ያለማስተናገዳቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ እንዲያጡም ምክንያት ሆኗል፡፡
በኢትዮጵያ በተሻለና በቋሚነት በየዓመቱ የንግድ ትርዒቶችን በማዘጋጀት የሚታወቀው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ እነዚህን ቋሚ የንግድ ትርዒቶች ባለማድረጉ ከዝግጅቶች ያገኝ የነበረውን ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዳሳጣው ንግድ ምክር ቤቱ ገልጿል፡፡
ይህ ብቻ ሳይሆን ንግድ ምክር ቤቱ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት የሚያስተዳድር በመሆኑ እርሱ ከሚያሰናዳቸው የንግድ ትርዒቶች ሌላ ለሌሎች የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች ዝግጅት በማከራየት የሚያገኘውም ገቢ እንዲቋረጥ አድርጓል፡፡ ይህም የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የከተማ አስተዳደሩ ሊያገኝ ይገባ የነበረውን ገቢ እንዳሳጣው ያመላክታል፡፡
በተለይ በዓላትን አስታከው የሚሰናዱ የንግድ ትርዒቶች በጨረታ የሚሰጡና ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኙ ከመሆናቸው አንፃር፣ በአንድ የበዓል የንግድ ትርዒት በአነስተኛ ግምት ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ ይገኝባቸው የነበሩ ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው በኮቪድ-19 ምክንያት የንግድ ትርዒቶቹ ባለመደረጋቸው ነው፡፡
በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በንግድ ምክር ቤቱ በቋሚነት በዓመት ውስጥ ይካሄዱ ከነበሩ አራት የንግድ ትርዒቶች ሌላ በዓመት በተለያዩ ዘርፎች ከ40 በላይ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች ይካሄዱ እንደነበርም ይታወሳል፡፡
አሁን ግን ይህ ከፍተኛ ገንዘብ ሲንቀሳቀስበት የነበረው የቢዝነስ ዘርፍ በኮቪድ-19 ውስጥም ቢሆን መልሶ ለማስጀመር የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በመወሰኑ የ2014 ዓ.ም. አዲስ ዓመት የንግድ ኤግዚቢሽንና ባዛር ይጀመራል፡፡
ከዚህም ቀደም እንደሚያደርገው ሁሉ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የአዲሱን 2014 ዓ.ም. የንግድ ትርዒትና ባዛር ለማዘጋጀት ባወጣው ጨረታ መሠረት እዮሃ የተባለው ድርጅት ጨረታውን በማሸነፉ ከዓመት በኋላ ማዕከሉ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡
ከአንድ ዓመት በላይ ተቋርጦ የነበረው የንግድ ትርዒትና ባዛር ተፅዕኖው በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም፡፡ ከንግድ ትርዒቶቹና ባዛሮች ጋር ተያይዞ በየትርዒቱ ይቀርቡ የነበሩ የመዝናኛ ፕሮራሞችን የሚያካሄዱ ድርጀቶችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ያገኙት የነበረውን ተጨማሪ ገቢ አ ሳጥቷል፡፡፡
በንግድ ትርዒቶቹ በጊዜያዊነት ተቀጥረው ይሠሩ የነበሩ ሠራተኞችን ሥራ አስተጓጉሏል፡፡ ከሸማቾችም አንፃር ሲታይ አንዳንድ ምርቶች ላይ በቅናሽ ሊገኙ የሚችሉ ምርቶችን እንዳያገኙ በማድረግም ረገድ የእነዚህ የንግድ ትርዒቶች መቋረጥ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የንግድ ትርዒት በማዘጋጀት ፋና ወጊ በመሆን የሚጠቀስ ነው፡፡ የንግድ ትርዒት ማዘጋጀት የጀመረውም ከ25 ዓመታት በፊት እንደሆነ ይታወቃል፡፡
አዲስ ዓመት፣ ገና እና የትንሳዔ በዓላት ሰሞን ማዕከሉ ከሌሎች ጊዜያት በተለየ ሰፊ ግብይት የሚካሄድበት ነው፡፡ አልባሳት፣ የቤትና የቢሮ ዕቃዎች፣ የታሸጉ ምግቦችና መጠጦች፣ ዘመን አፈራሽ ኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች፣ መኪናዎች፣ ማሽነሪዎች፣ የሴቶች መዋቢያዎችና የመሳሰሉ ዕቃዎች በሰፊው ለሸማቹ የሚቀርቡባቸው ናቸው፡፡ የንግድ ትርዒቶቹ በቀን ከ40 ሺሕ እስከ 50 ሺሕ ጎብኚዎች የሚስተናገዱባቸው ናቸው፡፡
ከንግድ ምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ የሚያመለክተውም፣ ዓለም አቀፍ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል ሲባል በኤግዚቢሽን ሥራ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት ኮሮና ካሳደረው የንግድ ድባቴ በመውጣት በአዲስ መንፈስ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ እየሠራ መሆኑን ነው፡፡
በንግድ ምክር ቤቱ አዘጋጅነት በ2014 ዓ.ም. አራት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒቶችንና ባዛሮች ይዘጋጃሉ፡፡ በምክር ቤቱ የሚዘጋጁት አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት፣ ግብርና፣ የምግብ ኤግዚቢሽንና የማኑፋክቸሪንግ ኤግዚቢሽኖች ናቸው፡፡
የሜዲካል ንግድ ትርዒትና የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት የሚረዳ የግብርና ውጤቶች ባዛሮች በዕቅድ መያዛቸውንም የንግድ ምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከ20 በላይ ቢዝነስ ለቢዝነስ ውይይቶችና የተለያዩ ቢዝነስ ፎረሞች እንደሚካሄዱ በዝግጅቶቹም የኮቪድ-19 የጥንቃቄ መመርያዎች ተግባራዊ ይደረጋሉ፡፡