ወላጆች በዶላር የዕለት ምንዛሪ ተመን ክፈሉ ተብለዋል
ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚሠሩ 26 የማኅበረሰብና ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ውስጥ፣ በስድስቱ ላይ ወላጆች ቅሬታ እንደቀረበባቸው ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ላይ ቅሬታ የቀረበባቸው በወርኃዊ ክፍያ ጭማሪ መጋነን ምክንያት መሆኑን፣ በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ጥራት ማረጋገጥ ዘርፍ ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን ንጋቱ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ በአሥር ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ላይ ቅሬታ የቀረበባቸው ቢሆንም አራቱ ከወላጆች፣ ከተማሪዎችና ከመምህራን ማኅበር ጋር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን፣ የስድስቱ ትምህርት ቤቶች ግን እስካሁን ችግራቸው እንዳልተፈታ ሙሉቀን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ወርኃዊ ክፍያቸው በዶላር የዕለት ምንዛሪ ተመን አድርገዋል ተብለው ቅሬታ የቀረበባቸው፣ ዋን ፕላኔትና ኢንተሌክቹዋል ትምህርት ቤቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡ በዋን ፕላኔት ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የክፍያ ጭማሪ ሲያደርጉ ከሦስት ወራት በፊት ማሳወቅ እንዳለባቸው ትምህርት ሚኒስቴር መመርያ ያዛል፡፡
ይሁንና የዋጋ ጭማሪ ሊደረግ መሆኑን የተነገራቸው ሁለት ሳምንት ሲቀረው እንደነበር ያስረዱት ወላጆች፣ ትምህርት ቤቱ መመርያ የጣሰ አሠራር ተከትሏል ብለዋል፡፡ የዋን ፕላኔት ትምህርት ቤት ወርኃዊ የክፍያ ጭማሪ ከ42 በመቶ ወደ 35 በመቶ የወረደ ቢሆንም፣ የተቀረውን ለተለያዩ የትምህርት ግብዓቶች ተብሎ ለአንድ ተማሪ እስከ 10,000 ብር እንደሚከፍሉ ገልጸዋል፡፡
አዲስ ተማሪ የሚያስመዘግቡ ወላጆች በዶላር የዕለት ምንዛሪ ተመን ታሳቢ ያደረገ የአከፋፈል ሥርዓት በመደረጉ ቅሬታ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ በኢንተሌክቹዋል ትምህርት ቤት ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ አምና ለአንድ ተማሪ በዓመት 120,000 ብቻ ይከፍሉ እንደነበርና አሁን ግን 100,000 ብር ጭማሪ ተደርጓል፡፡
ይህ ክፍያ የሚፈጸመው በዶላር (በዕለት የውጭ ምንዛሪ ተመን ነው) ቢባልም፣ ትምህርት ሚኒስቴር ግን በዶላር መጠየቅ እንደማይችሉና ነገር ግን በዕለቱ የውጭ ምንዛሪ ተመን መሠረት ማስከፈል ይችላሉ መባላቸውን ወላጆች ተናግረዋል፡፡ የወላጆች፣ የተማሪዎችና የመምህራን ኅብረት (ወተመ) አመራረጥና አመሠራረት፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች በሚያሟሉት መሥፈርት መሠረት ራሳቸውን እንዲያበቁ መጋቢት 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ለ26 ትምህርት ቤቶች መመርያው እንዲደርቸው ትምህርት ሚኒስቴርን አስታውቋል፡፡
የሥርዓተ ትምህርትና የተማሪዎች ቅበላ፣ የአደረጃጀትና የሰው ኃይል፣ የትምህርት ቤት መሠረተ ልማት፣ የፈቃድ አሰጣጥ፣ ዕድሳትና ክፍያን በተመለከተ በዝርዝር መመርያው ላይ መሥፈራቸው ተገልጿል፡፡ የምዝገባ ክፍያን በተመለከተ ከወርኃዊ ክፍያ 25 በመቶ መብለጥ እንደሌለበትና ትምህርት ከተጀመረ በኋላ ዋጋ ጭማሪ ማድረግ እንደማይቻል መመርያው ቢገልጽም፣ በዶላር (የቀን ዋጋ ምንዛሪ ተመን) ማስከፈል እንደሚችሉ ግን የተባለ ነገር የለም፡፡
የዋን ፕላኔት ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ጀማል ኢብራሂም እንደሚሉት፣ የውጭ ኢንቨስትመንት ፈቃድ ያላቸው በሙሉ ከትምህርት ሚኒስቴር ፈቃድ ያገኙ ናቸው፡፡ ዋን ፕላኔት ትምህርት ቤት ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት መሆኑን፣ ከትምህርት ሚኒስቴርም ፈቃድ እንዳላቸውና በዶላር ማስከፈልም ከሌሎች ትምህርት ቤቶች የተለየ እንዳልሆነም አስረድተዋል፡፡
በመጋቢት 2013 ዓ.ም. ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መመርያ መሠረት የወላጆች፣ የተማሪዎችና የመምህራን ኅብረት መመሥረታቸውንና ከአስተዳደሩ ጋር በመሆን ሦስት ስብሰባዎች የተጠራ ቢሆንም፣ መመርያ በሚያዘው መሠረት 51 በመቶ ወላጆች አልተገኙም ብለዋል፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር መመርያ መሠረት በተደጋጋሚ ስብሰባ ተጠርተው ወላጆች ባለመምጣታቸው መጨረሻ ስብሰባ ላይ በተገኙ ወላጆች 42 በመቶ ጭማሪ፣ በ2013 ዓ.ም. ለገቡ ተማሪዎች 27 በመቶ ጭማሪ፣ ለ2014 ዓ.ም. ለሚመዘገቡ አዲስ ተማሪዎችም አምስት በመቶ ቅናሽ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡
በወተመ አማካይነት በተሰጠው አስተያየት መሠረት ከ42 በመቶ ወደ 34 በመቶ ጭማሪውን በመቀነስ ለ2013 ዓ.ም. ለገቡ ተማሪዎች 23 በመቶ የነበረው 18 በመቶ መቀነሱን፣ ለአዲስ ተመዝጋቢዎች ከአምስት በመቶ ወደ 17 በመቶ ቅናሽ መደረጉን አቶ ጀማል ገልጸዋል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር ዓለም አቀፍና የማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች ለማስተዳደር ወጥ የሆነ ሕግ ሳይኖረው መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡ የትምህርት ጥራት፣ የሥርዓተ ትምህርትና የክፍያ ሥርዓትን በተመለከተ የአሠራር ክፍተቶች እንዳሉበት አስረድተው፣ በሚያዝያ ወር ችግሩን ለመፍታት መመርያ መውጣቱን ገልጸዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት መሥፈርት መሠረት እንሠራለን እያሉ የሚያስተምሩ፣ በዚህ ደረጃ መሠረት የሚያስከፍሉ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን የትምህርት ሥርዓት እየተገበሩ ዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ነን የሚሉ፣ ክፍያቸውም በዓለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች መሠረት ያደረጉ መኖራቸውን ሙሉቀን (ዶ/ር) አረጋግጠዋል፡፡
የክፍያ ጭማሪን በተመለከተ በወተመ አማካይነት በስምምነት እንዲሆን መመርያው እንደሚያዝ ዋና ዳይሬክተሩ ቢናገሩም፣ በስድስት ትምህርት ቤቶች ላይ ቅሬታ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡ እስካሁን በዶላር የዕለት ምንዛሪ ተመን ያደረጉ ትምህርት ቤቶች ሁለት መሆናቸውን ገልጸው፣ እንዲያስተካክሉ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡