በወረርሽኝ ምክንያት ለአንድ ዓመት ተላልፎ የነበረው የቶኪዮ 2020 በጋ ኦሊምፒክ፣ ከሁለት ሳምንታት በላይ ከተካሄዱት ውድድሮች በኋላ ባለፈው እሑድ ተጠናቋል፡፡
የቶኪዮ ኦሊምፒክ 2020ን ጨምሮ በ13 ኦሊምፒያዶች የተካፈለችው ኢትዮጵያ፣ በአራት አትሌቶች (ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶች) ከተገኙት 1 የወርቅ፣ 1 የብር እና 2 የነሐስ ሜዳሊያዎች ውጪ የኦሊምፒክ ቡድኗ ዝቅተኛ ውጤት በመያዝ ፈጽማለች፡፡
ከምንጊዜው በበለጠ ለስምንት ወራት ዝግጅት ያደረገው የኦሊምፒክ ቡድኑ የአትሌቶች አመራረጥን ጨምሮ በተለያዩ ችግሮችና ሳንካዎች ተተብትቦ መቆየቱ የሰላም መድረክ ለሆነው ኦሊምፒክ የሚደረገው ዝግጅት ሰላማዊ እንዳይሆን ካደረጉት ነጥቦች አንዱ ከአዲስ አበባ እስከ ቶኪዮ የዘለቀው የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች እሰጣ ገባና ውዝግብ ነው፡፡
የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቶማስ ባህ፣ የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ባለፈው እሑድ ሲጠናቀቅ ባሰሙት ዲስኩር፣ ኦሊምፒያኖቹን አትሌቶቹን ከኦሊምፒክ መሪ ቃል በመነሳት ‹‹ፈጣኖች ነበራችሁ፣ ከፍ ከፍ አላችሁ፣ ጠንክራችሁም ነበር፣ ምክንያቱም ሁላችንም በአንድነት አብረን ቆመናልና፤›› ሲሉ አስተጋብተዋል፡፡
ይህ ታላቅ ቃል ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ልዑካን ጋር ምን ያህል ተዘምዶ አለው ቢባል እውነቱ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ሁለቱም አገራዊ አካላት ባለመናበባቸው፣ በኦሊምፒክ መርሕ መሠረትም ባለመጓዛቸው ከኦሊምፒኩ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ጀምሮ በርካታ ችግሮች ተከስተዋል፡፡
ከእነዚህም አንዱና ግንባር ቀደሙ አገሮች ባህላቸውንና ትውፊታቸውን ከስፖርቱ ጋር አያይዘው በሚያንፀባርቁበት የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ ኢትዮጵያ በአንድ አትሌት ብቻ (ከአንድ ባለሙያ ጋር) ተወክላ ወደ ስታዲየሙ መግባቷ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ ተፈጽሞም የማያውቅ ክስተት ሆኖ ያለፈበት ነው፡፡
ከሰሐራ በታች ለሚገኙ የአፍሪካ አገሮች በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ዘገባ የሠራው አንገስ ቶሮውድ የተባለ የኦሊምፒክ ተንታኝ፣ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በኦሊምፒክ የሜዳሊያ ፉክክር ጎልተው አለመታየታቸው አሳዛኝ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
ሰሎሞን ባረጋ የ10,000 ሜትር ሩጫን በወርቃፀዊ ድል ማጠናቀቁ የኢትዮጵያ ቡድን አጀማመሩን ድንቅ በማድረጉ ብዙ እንድንጠብቅ አድርጎን ነበር ሲልም አንገስ መናገሩን ዲደብሊው ዘግቧል፡፡
እንደ አጀማመሯ ያልዘለቀችው ኢትዮጵያ ለሜቻ ግርማ በ3000 ሜትር መሠናክል ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ፣ ጉዳፍ ፀጋይ እና ለተሰንበት ግደይ በ5000 ሜትር እና 10,000 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያዎችን ማግኘታቸው በደረጃው ሠንጠረዥ 56ኛ ሆና እንድታጠናቅቅ አድርጓል፡፡
ይህም ውጤት ከአፍሪካ በኬንያ፣ በዑጋንዳ፣ በደቡብ አፍሪካ፣ በግብፅ ተበልጣ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
እነ ዑጋንዳ፣ ኔዘርላንድ፣ ኬንያ ታዋቂና በዓለም ገናና የሆኑ አትሌቶቻቸውን በሁለትና በሦስት ውድድሮች አሳትፈው ባለድል ከመሆናቸው አንፃር ኢትዮጵያ ከዚህ ትሩፋት ተቋዳሽ አለመሆኗን የሚያነሱ አሉ፡፡
የ10,000 ሜትር ባለወርቅ ሰሎሞን ባረጋ፣ የ5,000 ሜትር እና የ10,000 ሜትር የዓለም ክብረወሰን በእጇ ያለው ለተሰንበት ግደይ፣ የመወዳደር ዕድል ያልተሰጣቸው ለምን ነው ብለው ጥያቄም ያነሱ አሉ፡፡
ከቀደምቱ የምሩፅ ይፍጠር፣ የቀነኒሳ በቀለና የጥሩነሽ ዲባባ ድርብ ድሎችን ያስታወሱም አልታጡም፡፡
ዶቼቬሌ የኦሊምፒክ ተንታኙን አንገስን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ኢትዮጵያ ተጨማሪ ታዋቂ አትሌቶችን በቡድኑ አለመታቀፋቸው ግራ አጋብቶታል፡፡
በ5000 ሜትር በተደጋጋሚ የዓለም ባለድል የሆነው ሙክታር እድሪስ በማጣሪያው ወቅት መስፈርቱን ማሟላት ስላልቻለ አለመሳተፉን የሚገልጸው አንገስ፣ የማጣሪያ ውድድሩ የተካሄደበት ወቅት ግን ተገቢ አለመሆኑ ያመለክታል፡፡ ‹‹ማጣሪያው ለምን በበጋ ወቅት [የአውሮፓ] እጅግ በጊዜ መደረጉ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ሌሎች አገሮች እንዳደረጉት ማጣሪያው የተደረገው ዘግየት ብሎ ቢሆን ኖሮ በርካታ አትሌቶች ብቃትና ዝግጁነት ሊኖራቸው ይችል ነበር፤›› ሲል መናገሩን ዲደብሊው ጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ የኦሊምፒክ ማራቶን ታሪክ ተደርጎ በማይታወቅ ሁኔታ በወንዶች ሦስቱም ተወዳዳሪዎች፣ በሴቶች ሁለት ሯጮች ውድድሩን አቋርጠው ወጥተዋል፡፡ ለምን ይህ ሆነ ብለው የሚጠይቁ ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ሯጮች ለውድድሩ የተጓዙት ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው መሆኑ ከክረምቷ አዲስ አበባ ወደ ጠንካራው የሳፖራ በጋ ሲዘልቁ ከአየሩ ጋር ያለመለማመዳቸው በምክንያትነት ይጠቀሳል፡፡
የኦሊምፒክ ተንታኙ አንገስ እንደሚለው በሁለቱም ፆታ የማራቶን ሯጮቹ አቋርጠው መውጣት በአትሌቶቹ ዝግጅት ላይ ተገቢ ያልሆነ ነገር እንዳለ አለ፡፡
ንፅፅር ከኢትዮጵያ ቀዳሚ የኦሊምፒክ ድሎች
ኢትዮጵያ በአንድ የኦሊምፒክ መድረክ ከፍተኛ የወርቅ ቁጥር ለመጀመርያ ጊዜ ያስመዘገበችው በ2000 የሲዲኒ ኦሊምፒክ አራት ወርቅ ነው፡፡ ይኸው ታሪክ በ2008 በቤጂንግ በተመሳሳይ ወርቅ ተደግሟል፡፡ በ2012 በለንደን ሦስት ወርቅ ሲመዘገብ፣ በ2004 አቴንስ የተገኘው ሁለት ነበር፡፡ በ2016 ሪዮ እና በ2020 ቶኪዮ ግን ወደ አንድ ወርቅ ወርዷል፡፡ የሪዮ ኦሊምፒክ ከዘንድሮው ከፍ የሚለው በ1 ብርና በ3 ነሐስ ልዩነት ነው፡፡
በ32ኛው ኦሊምፒያድ ሲጠናቀቅ አሜሪካ በ39 ወርቅ፣ 41 ብር፣ 33 ነሐስ በድምሩ 113 ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ቀዳሚ ስትሆን፣ ቻይና በአንድ ወርቅ አንሳ በ38 ወርቅ፣ 32 ብር፣ 18 ነሐስ በድምር በ88 ሜዳሊያዎች ተከትላለች፡፡ አዘጋጇ ጃፓን በ27 ወርቅ፣ 14 ብር፣ 17 ነሐስ ባጠቃላይ በ58 ሜዳሊያዎች በሦስተኛነት አጠናቃለች፡፡
የአፍሪካ ደረጃ በቶኪዮ ኦሊምፒክ
የአፍሪካ ደረጃ (አጠቃላይ ደረጃ) |
አገር |
ወርቅ |
ብር |
ነሐስ |
ድምር |
1 (19) |
ኬንያ |
4 |
4 |
2 |
10 |
2 (36) |
ዑጋንዳ |
2 |
1 |
1 |
4 |
3 (52) |
ደቡብ አፍሪካ |
1 |
2 |
0 |
3 |
4 (54) |
ግብፅ |
1 |
1 |
4 |
6 |
5 (56) |
ኢትዮጵያ |
1 |
1 |
2 |
4 |
ቀጣዩን 33ኛው ኦሊምፒያድ ከሦስት ዓመት በኋላ ፓሪስ ታዘጋጃለች፡፡