Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለም​​​​​​​ክፍፍልን የፈጠረው የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ከፓርቲያቸው ኃላፊነት መነሳት

​​​​​​​ክፍፍልን የፈጠረው የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ከፓርቲያቸው ኃላፊነት መነሳት

ቀን:

ከዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ ተነፃፃሪ ሰላም ባገኘችው ደቡብ ሱዳን ዳግም ብጥብጥ ያስነሳል የተባለው ክስተት ያጋጠመው ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ነው፡፡

ከደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር በነበራቸው አለመግባባት ከምክትል ፕሬዚዳንትነት ሥልጣናቸው ተሰናብተው የነበሩትና በደቡብ ሱዳን ለአሥር ዓመታት ያህል በዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት ዋነኛ ተዋናዩ ሪክ ማቻር፣ ዛሬ ላይ ደግሞ ከራሳቸው ንቅናቄ በገጠማቸው ተቃውሞ ከሥልጣን ተነስተዋል ተብሏል፡፡

የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር የሚመሩት የሱዳን ፒፕል ሊብሬሽን አርሚ ኢን ኦፖዚሽን (ኤስፒኤልኤ አይኦ)፣ ባለፈው ሳምንት እሳቸውን ከንቅናቄው መሪነት ያነሳ መሆኑን የዘገበው አልጀዚራ፣ ንቅናቄው መከፋፈሉንም አመልክቷል፡፡

ሪክ ማቻር መነሳት አለባቸው ብሎ ውሳኔ ባሳለፉና በተቃወሙ አባላት መካከልም የተኩስ ልውውጥ መደረጉና ሰዎች መሞታቸውም ተነግሯል፡፡

ከዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ በተደረሰው ሥልጣን የመጋራት ስምምነት ወደ ቀደመ ሥልጣናቸው ምክትል ፕሬዚዳንትነት የተመለሱት ማቻር፣ ከንቅናቄያቸው መሪነት መነሳታቸውን አልተቀበሉትም፡፡

የኤስፒኤልኤ አይኦ መከላከያ ቃል አቀባይ በማቻር ደጋፊዎችና ተቀናቃኞች በኩል ሞት ያስከተለ ግጭት መፈጠሩን አስታውቀዋል፡፡

ማቻር አያስፈልጉንም ያሉ አባላት እሳቸውን ከኃላፊነት ብቻ ሳይሆን ከመከላከያ ሠራዊቱ መሪነትም ነው ያነሷቸው፡፡

አልጀዚራ ማቻርን ጠቅሶ እንዳሰፈረው፣ እሳቸውን ከሥልጣን አንስተናል ያሉት አባላት ‹‹ሰላም አደፍራሾች›› ናቸው፡፡ ማቻር ‹‹ሰላም አደፍራሾች›› ይበሉ እንጂ የእሳቸው ወታደራዊ ክንፍ መሪዎች ማቻርን ከመሪነት ያወረዱት የእነሱን ፍላጎት ማስጠበቅ ባለመቻላቸው ነው፡፡

በማቻር ንቅናቄ አባላትና ወታደር ውስጥ ክፍፍል መፈጠሩ፣ በማቻርና በሳልቫ ኪር መካከል በ2018 የተደረሰውን የሥልጣን ክፍፍል ስምምነትም ሊቀለብሰው ይችላል ተብሏል፡፡

ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ካርቱም ነፃነቷን ስታውጅ የተመሠረተው የመጀመርያው መንግሥት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ያገለገሉትና በኋላም በተፈጠረ አለመግባባት ከሥልጣን ተወግደው በስደትና በጦርነት የቆዩት ማቻር በመጀመርያው የሥልጣን ዘመናቸው ሁለት ዓመት አገልግለው ነው በፕሬዚዳንቱ ሳልቫ ኪር ከሥልጣን የተባረሩት፡፡

ይህም ለማቻርና ለኪር ታማኝ የሆኑ የደቡብ ሱዳን ወታደሮች ተከፋፍለው የእርስ በርስ ጦርነት እንዲጀምሩ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ እንዲፈናቀሉ፣ እንዲራቡ ብሎም እንዲሞቱ አድርጓል፡፡

ሁለቱን ተቀናቃኞች ወደ ሰላም ለማምጣት ተደጋጋሚ ድርድር ተደርጎ የተሳካውና ደቡብ ሱዳን የተሻለ ሰላም ያገኘችው በቅርቡ ቢሆንም፣ ዛሬ ላይ ደግሞ ሪክ ማቻር  ፍላጎታችንን አላስጠበቁም ያሉ የቀድሞ ደጋፊዎቻቸው ፊት አዙረውባቸዋል፡፡

እሳቸው ደግሞ ይህንን ውሳኔ ያሳለፉትን የቀድሞ አባላታቸውን የወታደራዊ ንቅናቄው ዕዝ ካውንስል አባላት አይደሉም ሲሉ ከካውንስሉ ፍቀዋቸዋል፡፡

ከማቻር ወታደሮች የሰላም ስምምነት ከተደረሰም በኋላ ስምምነቱን አንፈርምም ያሉ መኖራቸውና አሁን ላይ የተፈጠረው መሰነጣጠቅ የደቡብ ሱዳንን መረጋጋት ዳግም ያናጋዋል ሲል ሮይተርስ አስፍሯል፡፡

ነፃነቷን ከተቀዳጀት ብዙም ሳትቆይ ለእርስ በርስ ግጭት የተጋለጠችው ደቡብ ሱዳን የኢኮኖሚ ውድቀትና አስከፊ የተባለ ረሃብ ገጥሟታል፡፡ ይህንን ይለውጣል የተባለ የሰላም ስምምነት ቢደረግም፣ ከተደራዳሪው አንዱ የሆነው የምክትል ፕሬዚዳንቱ ሪክ ማቻር ንቅናቄ ተከፋፍሏል፡፡ ይህ ደግሞ ሥጋት ደግኗል፡፡

 በመሆኑም ችግሮች ሳይባባሱ በውይይት መፈታት አለባቸው ሲል ቀጣናዊው የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ድርጅት ኢጋድ አስታውቋል፡፡

pdf

ኢጋድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹን አስቸኳይ ስብሰባ ከመጥራት ባለፈም፣ የደቡብ ሱዳን ጉዳይ አፋጣኝ ምላሽ ይፈልጋል ብሏል፡፡

የተከፋፈለው ኤስፒኤልኤ ለውይይት በር እንዲከፍትም ጠይቋል፡፡ በሪክ ማቻር በሚመራው ኤስፒኤልኤ መካከል በተፈጠረ ግጭት ቢያንስ 30 ያህል መገደላቸውን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ ተቀናቃኞች ማቻርን ከንቅናቄው ሥልጣን አውርደናል ባሉ ማግስት ነው፡፡

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ኤስፒኤልኤ በመካከሉ የተፈጠረውን ልዩነት ሰላማዊ በሆነ ውይይት እንዲፈታ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢጋድ ለዓመታት የዘለቀው የደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በሰላማዊ ውይይት እንዲፈታ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ 400 ሺሕ ያህል ዜጎች ያለቁበትን ጦርነት ለማስቆምም ጉልህ ሚና ነበረው፡፡

  • ጥንቅር በምሕረት ሞገስ
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...