Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገር​​​​​​​የምዕራባውያንን ጫና ለመከላከል በኅብረት እንነሳ!

​​​​​​​የምዕራባውያንን ጫና ለመከላከል በኅብረት እንነሳ!

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ                               

‹‹ሰው በአገሩ ሰው በወንዙ ማንነቱ ታውቆ እንኳን እህል ውኃ ቢበላስ መቅመቆ›› ይሉ ነበር አባቶቻችን፡፡ ዘርቶ ማብቀል አቅቶን ይሆን? ወይስ መሬት፣ ውኃና የሚሠራ የሰው ኃይል ጠፍቶብን ይሆን? በስንዴ ዕርዳታ ኮሮጆዎቻችንን በድርበብ ሠፍረው እየሰጡን ይህንን አድርጉ፣ ይህንን ካላደረጋችሁ ወየውላችሁ እያሉ የሚያሸብሩን ለምን ይሆን? ወገኖቼ ይብቃን እንጂ፣ የማንም ኩታራ የዕርዳታ ሊቅ እያለን ማላገጫው ሆነን ለብዙ ዘመናት ታግሰናል። ዛሬ ግን በቃን የሚል ወጣት መሪ ደፍሮና ቆርጦ እንደ አያት አባቶቹ ከተነሳ እንርዳው፡፡ የፖለቲካ ሽኩቻውን ለአለሁ አለሁ ባይነት ለጊዜው እናቆየውና አሁን የተጋረጠብንን የጋራ ችግራችንን በኅብረት ልክ እንደ ዓድዋው፣ እንደ 1924 ዓ.ም. የኦጋዴንና የመሳሰሉት እነ ዓለማየሁ ጎሹ በተሰውበት ዓይነት ለአገር አንድነት ለኢትዮጵያ ክብርና ኩራት አብረን ተዋድቀን ነባሩን ክብርና ኩራታችንን ለአንዴና ለመጨረሻ እናሳያቸው። ይህ ነው ኢትዮጵያዊነት፡፡

መልከኝነት፣ ባላባትነት፣ ምስለሌነት፣ ጭቃ ሹምነት ወይም ገራድነት የሚያጓጓው አገርና ክብር ሲኖር ብቻ ነው። አገሩን ለሸጠውማ ጣሊያን የደጃዝማችነት ማዕረግ ሰጥቶ አልነበረምን? ለምሳሌ ኃይለ ሥላሴ ጉግሣ አገሩን ለቢሊዮን ሊሬ ሸጦ ጀግኖች የአገራቸውን ነፃነት ካስመለሱ በኋላ፣ ያ ደጃዝማችነትና የራስነት ማዕረግ እስከ መጨረሻው የውርደት ማቅ አልብሶት፣ እኛም ዛሬ ስሙን በምሳሌነት እየጠቀስን ነው። ወገኖቼ የፖለቲካ ሊቀ ሊቃውንት ለሚያልፍ የጠላት ውዥንብር መጠቀሚያ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ። ያለንን መሪ ደግፎና ደጋግፎ የአገርን ክብር ማስጠበቅ እንጂ፣ የጊዜን ሁኔታ በማየት አገራችንን ከውርደት እንዴት እንደምንታደጋት ተገንዝባችሁ ለአንድነት ተነሱ። ኢትዮጵያ የሦስት ሺሕ ወይም ከአምስት ሺሕ ዓመታት በላይ ታሪክ አላት ሲባል የሚቆርጣቸውና የሚቆፈንናቸው እንዳሉ ባውቅም እውነቱን መናገር አያሳፍርምና ተናገርኩት።

- Advertisement -

ታዲያ የትናንቷ እንግሊዝ የቀደሟትን ሁሉ ከታሪክ ገጽ አጥፍታ ያልቻለቻት ኢትዮጵያን ብቻ ስለሆነ፣ ልክ ከዛሬ 154 ዓመታት በፊት (May 13,1867) የቀራትን የታሪክ ቀደምቷን ኢትዮጵያ ለማጥፋት ወስና እንደ ዛሬዎቹ ሹመት ፈላጊዎች ተመርቶ በገባ ጄኔራል ናፒር የግልበጣው ዝግጅት በሚገባ ቢከናወንም፣ ምንም ቢሆን አገሬን አሳልፌ አልሰጥም ባይ ኢትዮጵያዊያን አብረውና ተባብረው የመጣውን ጠላት በግንባር ለመግጠም ተነሱ፡፡ የመጣው ጠላት ጦርነት ሳይገጥም አዝማሚያውን እንዲገነዘብ አድርገው ሸኙት፡፡ ኢትዮጵያም በነፃነቷ ኖረች፡፡ ዓድዋም መጣና ለጥቁር ሕዝብ ሁሉ ተምሳሌት ሆኖ አለፈ። ከዚያም ደግሞ የማይጨው ጦርነት ተጀመረ፡፡ ከሃዲዋ እንግሊዝ አሁንም ኢትዮጵያን ለሽያጭ በማቅረብ የራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ ስትል ከጣሊያንና ጀርመን ጋር ተወዳጀች፡፡ የራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲያመቻት ግፈኛውን ጣሊያን የኢትዮጵያ ገዥ እንዲሆን በዓለም ፊት አፀደቀች።

መቼም ኃፍረት የሌላት ስለሆነች ጣሊያን በፈለገችው መንገድ ሳይሄድላት ሲቀር ፊቷን ወደ ኢትዮጵያ መልሳ አብረን እንሁን አለች፡፡ የቸገረው ከመሞከር ወደ ኋላ አይልምና ንጉሥ ነገሥቱ ሐሳቡን በቅንነት ተቀብለው በተሰጣቸው ዕድልና መመርያ መሠረት ተነስተው ሱዳን ከገቡ በኋላ፣ የሱዳኑ ገዥ የነበረው ፍፁም የማላውቀው ጉዳይ ነው እስካጣራ ድረስ በተወሰነ ሥፍራ ይቀመጡ ብሎ ነገራቸው፡፡ የማይጋፉት ባላጋራ ነውና በብስጭት ለተወሰነ ጊዜ እንደተቀመጡ በታኅሳስ ወር 1933 ዓ.ም. ኢትዮጵያዊያንን ከኢትዮጵያዊያን ጋር ለማለያየት መርዝ ነስናሽ የሆነ ኮሎኔል ብሮክለኽርስት በሚባል መርዘኛ የተመራ ቡድን፣ በካይሮ አድርጎ ኬንያን አካሎ ኢትዮጵያዊያንን በጎሳና በሃይማኖት እንዴት እንደሚያለያይ ዝግጅት አድርጎ መጣ፡፡ ይህንን ተንኮል የሰሙት ንጉሠ ነገሥቱ ጊዜ ሳያባክኑ በጊዜው ደጋፊያቸው ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል ቴሌግራም አድርገው በማስታወቃቸው፣ በጉዳዩ ላይ እነ ጄኔራል ዊንጌትና ሳንፎርድ ገብተውበት ይህ ተንኮለኛ ከቅሌት ጋር ከሱዳን ከእነ ተከታዮቹ ተባረረ።

እኛ ሞኞቹ የዛሬዎቹ የተጠነሰሰልንን የምንገነዘብ አይመስለኝም። ነጭ ጥቁርን ለማጥፋት ሲጥር አሁን የመጀመርያው አይደለም። ኢትዮጵያ ለጥቁሮች ነፃነት የዓለምን ማኅበር ያስጨነቀች ናት፡፡ በሌላት አቅም ለኑኩሩማ፣ ለኬንያታ፣ ለኔሬሬና ለማንዴላ፣ ወዘተ በየዓመቱ ሦስት መቶ ሺሕ ዶላር በማዋጣት ለነፃነት ትግላቸው አጋር በመሆን ከነጭ ዓይን ውስጥ ገባች፡፡ ይህም ይዋል ይደር እንጂ የኢትዮጵያን ወጣት አገርህ ወደኋላ ቀርታ ምነው በዝምታ ታልፋለህ በሚል የተንኮል ዘይቤያቸው ማታለል ጀመሩ፡፡ እንደ እነ ገርማሜ ነዋይን የመሳሰሉ ኢትዮጵያዊያንን አገራቸውን በቀላሉ የሚያለሙ፣ ፈረንሣይንና ተንኮለኛዋን እንግሊዝ በአንድ ጊዜ የሚያስመስሏት አድርገው ልባቸውን በተንኮል ስለለወጡ ለ1953 ዓ.ም. ንቅናቄ አበቋቸው። ይህም በትክክል እንዲታይ የሚረዳን ለአገራቸው ታላላቅ ሥራዎች የሠሩትን እንደ እነ ራስ አበበ አረጋይን፣ ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊን፣ አቶ መኮንን ሀብተ ወልድንና የመሳሰሉትን ሰብስበው እንዲፈጇቸው ሲያዘጋጁ፣ በዝግጅቱ አዳራሽ ውስጥ የአሜሪካ አምባሳደር እንደነበረና ግድያው ሲከናወንም በአጥር ዘሎ እንደ ጠፋ የትናትና ታሪክ ነው።

ዛሬስ ምን እየተሠራ ነው? ኢትዮጵያን ለኢትዮጵያዊያን አስበው ገነት ሊያደርጓት ይሆን? ወይስ ይህንን የዋህ ትውልድ እርስ በርሱ ካባላን በኋላ እንደ ተለመደው ጓዛችንን ጠቅልለን ገብተን እንዳሻን እንግዛቸው እያሉ ይሆን? ይህንን ጉዳይ በጥሞና እንመልከት። የእርስ በርስ መገዳደሉም የሚቆምበት መንገድ ይፈለግ፡፡ የጋራ ጥቅምን የሚያስከብር መንግሥት እየተባለ የሚጎሰመው ነጋሪት ጋብ ይበልና ወደ ልቦናችን ተመልሰን፣ ያለውን ደጋግፈን የጋራ አገራችንን ከመከራና የባዕዳንን ቀንበር ከማሸከም ካዳንን በኋላ ሁሉንም አብረን ለመሥራት እንዘጋጅ። ዛሬ ጊዜ ሰጠን ብለው አገር ለመሸጥ የሚሯሯጡትን በቁጥጥር ሥር ማዋልና አደብ እንዲገዙ ማድረግ የመንግሥት ኃላፊነት መሆኑ ታውቆ፣ ቆራጥና የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ አለበት። ተንኮል ወደ የሚሸረብበት ካምፓቸው ለመመላለስ ፈቃድ መስጠት ጨርሶ መቆም ያለበት ጉዳይ ነው። 

ኢትዮጵያዊያን በሺዎች ተሰባስበን በአንድነት ከአገራችን ላይ እጃችሁን አንሱ በማለት መልዕክት ለምዕራባዊያን ማስተላለፍ ያለብን ጊዜ አሁን ነው። መሪያችንን ለማዳከም የሚያደርጉት ሩጫ በቀላሉ መቀጨት አለበት። እንደተለመደው አንድን መሪ በሕዝቡ እንዲጠላ አድርገው ሕዝቡ ያወረደው ለማስመሰል የሚያደርጉት ሴራ ዛሬ እስከዚህ ሰዓት ድረስ አልሠራላቸውም፡፡ ነገር ግን የገንዘብ ኃይል የማይሠራው የለምና ውሎ ሲያድር የሚያመጣው ስለማይታወቅ፣ አገራችን በተንኮለኞች እጅ ከመውደቋ በፊት አስቸኳይ ዕርምጃ ይወሰድ፡፡ እንዲህ ስል መሪውን አንጠይቅ፣ አንቆጣጠር ማለቴ ሳይሆን የራሳችንን በራሳችን ለማለት ነው።  

አንድ ኃያል አገር በሌላው አገር የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ሊያተራምስ የሚችለው በአፍሪካ ብቻ ነው። ከአልማዝና ከወርቅ በተጨማሪ የማዕድናትና የበርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ባለቤት የሆነች አገር፣ ሁሌም ዕርዳታ ለማኝና ተመፅዋች ሆና ከትዕዛዛቸው እንዳትወጣ የሴራ ሰለባ ተደርጋለች፡፡ ሥልጣኔ የተባለውን ጉድ ከተጎናፀፉ ጊዜያት አንስቶ ጥቁርን የበይ ተመልካች ሲያደርጉ፣ በጣት ለሚቆጠሩ አገር ሻጮች የፈለጉትን እያደረጉ የኖሩት እስከ ዛሬ ድረስ በአፍሪካ ነው፡፡ ከሞላ ጎደል በነበረው ችግርና ድንበሯን በመጠበቅ ከዓለም ርቃ የኖረችው ኢትዮጵያ ግን ክብሯን ሳታስነካ በመቆየቷ፣ በ1967 ዓ.ም. ያመጡብን መከራ ሌላ መከራ እየወለደ መጥቶ እነሆ ዛሬ በገዛ ግዛታችን የውስጥ ጉዳይ ገብተው ሲያተራምሱን እያየን ነው። በሉ ወገኖቼ አሁንም ጨርሶ አልመሸምና ለአንድነታችንና ለነፃነታችን በማያወላውል መንፈስ አንድ ላይ እንቁም።

ዓብይን ለማጥፋት የሚደረገው ሩጫ በእውነት ለዓብይ ነው ወይስ ነባሯን ኢትዮጵያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመበታተን? ይህንን በትክክል እናጢን፡፡ ወገኖቼ ፓትሪስ ሉሙምባ ተገድሎ ማነው የተተካው? የኮንጎ ሕዝብ የሚበላው ሳይኖረው ፓትሪስን የተካው ሰው በፈረንሣይ ደሴቶች ታላላቅ ማረፊያዎችና መኖሪያ ቤቶች አልተቸረውምን? ይህ ሰው ሻርል ደጎል ከዚህ ዓለም በሞት በተለየበት ዘመን፣ ‹‹እኔ መልኬ ጠቁሮ እንጂ የደጎል የቤተሰብ ልጅ ነኝ›› ብሎ ሐዘን መቀመጡን ስንታችን ነን የምናስታውሰው? ይህንን ያህል ነው የሚያታልሉትና የሚያቀራርቡት፣ አንዱን በማስጠጋት ባለጊዜ ካደረጉት በኋላ ያ ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ዓለም ዘጠኝ ሲል ይኖራል፡፡ ነገር ግን አገሩን ለአንዴና ለመጨረሻ የሸጠ ከሃዲ ማለት ነው። እኛስ ዘንድ ይህ አዝማሚያ እየመጣ ከራስ በላይ ንፋስ ባዮች ተፈጥረው ይሆን የሚል ጥያቄ ሳያጭርብን አይቀርምና እጅግ ይታሰብበት።

ጂቡቲ ወደ እናት አገሯ እንድትመለስ ከተወሰነና ካለቀለት በኋላ ትንሽ የአስተዳደር ሁኔታዎች እስኪስተካከሉ ድረስ ጊዜ ሲወስድ፣ በጊዜ ጉዳዩን በውክልና የሚፈጽሙት አቶ አሰፋ ገብረ ማርያም ረዴ ከጎናቸው ሆነው ይረዷቸው የነበሩት ደጃዝማች ኡጋዝ ዓሊና ፊታውራሪ ሐሰን ባዕዶ ጉዳዩን በመከታተልና የርክክብ ቀኑን በሚያዘጋጁበት ጊዜ ነው ደርግ ወደ ሥልጣን የመጣውና ምንም ሐሳብ ውስጥ ያልነበረንና ያልተጠየቀን የጂቡቲ ነፃ መንግሥት እንዲቋቋም ያደረገው። ይህም የሆነበት ምክንያት ጂቡቲን ነፃ በማውጣት የራሱ የሆነ ደጋፊና የሚሰደደውን ኢትዮጵያዊ ለማጥመድ እንዲያመች ባሰበውና በቀየሰው የግል ጥቅም መሠረት፣ ምንም ጊዜ ሳይወስድበት በ1969 ዓ.ም. አጥናፉ አባተ የበዓሉ ታዳሚ በመሆን ነፃነቷ ሊከበር ቻለ። አገሪቱን ለማሳነስ ለሚደረገው ሩጫ የምዕራባዊያን ድርሻ በቀላሉ እንዳይታይ መገንዘብ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያን የባህር በር አልባ ማድረግ የተለመደ በመሆኑ የተጣወረን ይመስላል። አሁን የቀረችዋን ኢትዮጵያ ከመበታተን ማዳን ኢትዮጵያዊያን ነን ከሚሉ የሚጠበቅ ነውና በኅብረት እንነሳ።

ቢቻል በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አዲስ አበባ ሰላማዊ ሠልፍ ወጥቶ አገራችንን ልቀቁልንና በውስጥ ጉዳያችን አትግቡ የሚል መፈክር በመያዝ፣ በምዕራባዊያን ላይ ጥላቻን የሚያንፀባርቅ መልዕክት ቢተላለፍ መልካም ይሆናልና እንዘጋጅበት። ምዕራባዊያን ከሚጠሉት አንዱ መጠላትን ነው። ምናቸው ሞኝ ነው? ወዳጅ መስሎ ጠላትነትን ያውቁበታልና ነው። ሞኝ ብቻ ነው ጠብን በጠብ ለማሸነፍ የሚኳትን፡፡ ብልጦቹ ግን ወዳጅ መስለው ነው የሚያፋጁት።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ግለ ሕይወታቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን የከተቡበት ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ ለአንባቢያን ያቀረቡት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...