Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተሠራጨው የአፈር ማዳበሪያ ከቀደሙት አራት ዓመታት የ39 በመቶ ብልጫ...

  በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የተሠራጨው የአፈር ማዳበሪያ ከቀደሙት አራት ዓመታት የ39 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተጠቆመ

  ቀን:

  የአፈር ማዳበሪያን በብቸኝነት እያስመጣ የሚያሠራጨው የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በመላው አገሪቱ ያሠራጨው የአፈር ማዳበሪያ ከቀዳሚዎቹ አራት ዓመታት የ39 በመቶ ብልጫ እንዳለው አስታወቀ፡፡

  ኮርፖሬሽኑ ይህን ያስታወቀው የ2013 ዓ.ም. የበጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸሙን አስመልክቶ፣ ማክስኞ ነሐሴ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. በዋና መሥሪያ ቤቱ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው፡፡

  የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደ ማርያም እንዳስታወቁት፣ የግብርና ሚኒስቴር በሚያቀርበው የሥራ ዝርዝርና ፍላጎት መሠረት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ600 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ የአፈር ማዳበሪያ፣ ፀረ አረምና ፀረ ተባይ ኬሚካሎች ተገዝተው በመላው አገሪቱ ተሠራጭተዋል፡፡

  ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ 18.1 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ አገር ለመግዛት አቅዶ እንደነበር የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ከዚህ ውስጥ የ16.3 ሚሊዮን ኩንታል ግዥ ተፈጽሞ እስከ ተጠናቀቀው የበጀት ዓመት መጨረሻ ወደብ መድረሱን፣ ከዚህ ውስጥ 16.2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ደግሞ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ ዩኒየኖች እንደተሠራጨ አስረድተዋል፡፡

  በ2012 ዓ.ም. አጠቃላይ በአገሪቱ ተሠራጭቶ የነበረው የአፈር ማዳበሪያ 14.5 ሚሊዮን ኩንታል እንደነበረ የተገለጸ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የማዳበሪያ ዋጋ ንረትና የኮቪድ ወረርሽኝ ተፅዕኖዎች እንደተጠበቀ ሆኖ ከ16 ሚለዮን ኩንታል በላይ ለማሠራጨት እንደተቻለና ይህም ሥርጭት በ2012 ዓ.ም. ከነበረው የ27.8 በመቶ፣ እንዲሁም ከቀዳሚዎቹ አራት ዓመታት ጋር ሲነፃፀር የ39.7 በመቶ ዕድገት አለው ተብሏል፡፡

  አዳዲስ የግብርና ግብዓቶችን ከማስተዋወቅ አኳያ 52,444 ሊትር ፈሳሽ ማዳበሪያ በተጠናቀቀው የበጀት እንደተሠራጨ፣ ይህም በዋናነት በመስኖ አትክልትና ፍራፍሬ የሚያለሙ አርሶ አደሮችና ባለሀብቶች እንደሆኑ ተጠቁሟል፡፡

  አቶ ክፍሌ እንዳስታወቁት፣ የዓለም ገበያ የማዳበሪያ ዋጋ በከፍተኛ ጨምሯል፡፡ ሆኖም ኮርፖሬሽኑ በራሱ ገቢ የሚተዳደር የንግድ ተቋም እንደመሆኑ መጠን፣ የተደረገውን ከፍተኛ ጭማሪ በአርሶ አደሩ ላይ ከማስተላለፍ ይልቅ ሊደርስ የሚችለውን ኪሳራ በኩንታል 3.25 ብር በጠቅላላው 60 ሚሊዮን ብር ኮርፖሬሽኑ በመውሰድ፣ እንዲሁም መንግሥት ማዳበሪያው ከወደብ ወደ ዩኒየኖች የሚጓጓዝበትን 4.5 ቢሊዮን ብር የአገር ውስጥ ትራንስፖርት ወጪ በመሸፈን ሥርጭቱ እንደተከናወነ አስታውቀዋል፡፡

  በተጠናቀቀው የምርት ዘመን በ13,742 ሔክታር መሬት በዘር በመሸፈን 310,892 ኩንታል ምርት ለማምረት ኮርፖሬሽኑ ዕቅድ እንደነበረው የተጠቆመ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 13,239 ሔክታር መሬት ላይ 284,432 ኩንታል ምርት እንደተገኘ ተገልጿል፡፡

  የዘር ማምረት አፈጻጸሙ ከቀደሙት አራት ዓመታት የተሻሻለ ቢሆንም በታቀደው መጠን እንዳይሆን ካደረጉት ነገሮች መካከል በትግራይ ክልል በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት፣ በትግራይ ክልል ባሉ ወረዳዎች የተባዙ ዘሮችን ማሰባሰብ ባለመቻሉ ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

  በአገር ውስጥ የማዳበሪያ ሥርጭቱ ሒደት በጥሩ ሁኔታ ሲሠራጭ እንደቆየ የተገለጸ ሲሆን፣  በትግራይ ክልል ላይ የተናጠል የተኩስ ማቆም ዕወጃ እስኪደረግ ድረስ የማዳበሪያና ምርጥ ዘር ሥርጭት ሲከናወን እንደቆየ፣ በዚህም 350 ሺሕ ኩንታል ማዳበሪያና ከ40 ሺሕ በላይ ምርጥ ዘር እንደቀረበ፣ ይህም ከመስኖ የተረፈውን ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያላካተተ እንደነበረ፣ ሆኖም ከተናጠል የተኩስ ዕወጃ በኋላ ለማሠራጨት እንዳልተቻለ ተገልጿል፡፡

  በአገሪቱ ያለው የዘር አቅርቦት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ እየጨመረ እንደሚገኝ ያስታወቁት አቶ ክፍሌ፣ ይህንን ፍላጎት ለመመለስ የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ እንደሚገኙና በከልል ደረጃ የሚገኙ የምርጥ ዘር ድርጅቶች ተጨማሪ መሬቶችን እየወሰዱ ዘርን በዓይነትም በመጠንም እየጨመሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

  የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የልማት ድርጅት እንደመሆኑ መጠን ከውጭ አምጥቶ የሚያቀርባቸው የማዳበሪያ ምርቶችን ያለ ምንም ትርፍ ለገበሬው እንደሚያከፍፍል የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህ የሆነው አንድም የአርሶ አደሩን የመግዛት አቅም ለማሳደግ በሌላ በኩል ደግሞ የግብርና ምጣኔ ሀብቱን ለማሳደግ በሚል ነው ብለዋል፡፡ ከሌሎች ሥራዎችም ኮርፖሬሽኑ የሚያገኘው ትርፍ ከ22 በመቶ እንደማይበልጥ፣ ያም ሆኖ ግን ኮርፖሬሽኑ ከጠቅላላው አገልግሎቱ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 159 ሚሊዮን ብር ለማግኘት አቅዶ 174 ሚሊዮን ብር የሚሆን ገቢ እንዳገኘ ተገልጿል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...