Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የተጀመረው አፈሳ እንዲቆም መንግሥት ጠየቀ

በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የተጀመረው አፈሳ እንዲቆም መንግሥት ጠየቀ

ቀን:

በሳዑዲ ዓረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ የተጀመረው አፈሳ እንዲቆም የኢትዮጵያ መንግሥት የአገሪቱን መንግሥት ጠየቀ።

በሳዑዲ ዓረቢያ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሌንጮ ባቲ ከሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ደኤታ አህመድ ቀጣን ጋር ተገናኝተው፣ በኢትዮጵያ ስደተኞች ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መምከራቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

በውይይታቸው ወቅትም በሳዑዲ ዓረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ላይ የአገሪቱ መንግሥት ሕግ አስከባሪ አካላት የጀመሩት አፈሳ እንዲቆም፣ አምባሳደር ሌንጮ መጠየቃቸው ታውቋል።

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት የኢትዮጵያ ስደተኞችን የተመለከተ የምሕረት አዋጅ እንዲያወጣና ተግባራዊ እንዲያደርግ በመጠየቅ፣ በዚሁ ጉዳይ ላይ ውይይት ማድረጋቸውም ታውቋል።

የሳዑዲ ዓረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ አህመድ ቀጣን የቀረበላቸውን ጥያቄ በአዎንታ ተቀብለውበጉዳዩ ላይ ከሚመለከተው የአገር ግዛት ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረው የተጀመረው አፈሳና እስራት መቆም በሚችልበት ሁኔታ ላይ ተነጋግረው ምላሽ እንደሚሰጡ ቃል መግባታቸውን፣ ሪፖርተር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

የሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት በአገሪቱ የሚገኙ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ሥራ ፈላጊ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን፣ በአስገዳጅ ሁኔታ ከአገር ማስወጣት ተግባሩን ካለፈው ሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. መጀመሩ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በድንገት የተወሰነውን ይህንን ዕርምጃ በአሉታዊ መንገድ የተገነዘበው ሲሆንጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (/) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድርጊቱን በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸመ ነው ካሉት የውጭ መንግሥታት ደባ ጋር ማገናኘታቸው ይታወሳል።

በሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. በተጀመረው ኢትዮጵያውያንን ከሳዑዲ በአስገዳጅ የማስወጣት ተግባር፣ ኢትዮጵያ በሁለት ሳምንታት ውስጥ ከ40 ሺሕ በላይ በሳዑዲ የሚገኙ ዜጎቿን ወደ አገር ለማጓጓዝ ተገዳለች።

ከሳዑዲ ዓረቢያ እንዲወጡ የተደረጉት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው 40 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ውስጥ 13,781 የሚሆኑት ከትግራይ ክልል በሥራ ፍለጋ ምክንያት የተሰደዱ ሲሆኑከአማራ ክልል 13,690 ከኦሮሚያ ክልል 11,311 ከደቡብ ክልል የተሰደዱት 1,117 መሆናቸውንና የተቀሩት 1,281 ስደተኞች ከሌሎች ክልሎች እንደሆኑ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት መረጃ ያመለክታል።

ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ከተደረጉት ከ40 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች በተጨማሪ፣ በቀጣዮቹ ሳምንታትም ከሳዑዲ ዓረቢያ የሚመለሱ ስደተኞች መኖራቸውን ያመለከተው መረጃውበአሁኑ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱትን ስደተኞች ወደ ቀዬአቸው በመመለስ ለማቋቋም ታሳቢ ቢደረግም በተለያዩ አካባቢዎች ያለው የፀጥታ ችግር ይህንን እንዳላስቻለ ገልጿል።

በመሆኑም በፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ ቀዬአቸው መመለስ ያልቻሉትን ስደተኞች በአዲስ አበባና በሌሎች የተረጋጉ ከተሞች ለማቆየት፣ የኢትዮጵያ መንግሥትና ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር የሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ ጫና እንደገጠመው መረጃው ያመለክታል።

ይህ አስቸጋሪ ሁኔታም የኢትዮጵያ መንግሥትን ከሳዑዲ ዓረቢያ መንግሥት ጋር ንግግር እንዲያደርግ እንዳስገደደው ለማወቅ ተችሏል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...