Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊፓስፖርትን ከጉዞ ሰነድነት ባለፈ ለሌሎች አገልግሎቶች መጠቀም ተገቢ አለመሆኑ ተገለጸ

  ፓስፖርትን ከጉዞ ሰነድነት ባለፈ ለሌሎች አገልግሎቶች መጠቀም ተገቢ አለመሆኑ ተገለጸ

  ቀን:

  ፓስፖርትን ከጉዞ ሰነድነት ባለፈ በተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኘት መጠቀም ተገቢ አለመሆኑ ተገለጸ፡፡

  ይህ የተገለጸው የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ የወሳኝ ኩነት ምዝገባን ለማሻሻል ያስጠናውን የተቀናጀ ሁለንተናዊ ጥናት የማስተግበሪያ ስትራቴጂዎችን የተመለከተ ሥልጠና፣ ለተለያዩ የሚዲያ ባለሙያዎች ቅዳሜ ነሐሴ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. በአዳማ ድሬ ኢንተርናሽናል ሆቴል በሰጠበት ወቅት ነው፡፡

  የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክትር አቶ ሙጂብ ጀማል እንዳስታወቁት፣ ከዓለም አቀፋዊ የጉዞ አገልግሎት ውጪ በሆኑ የተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ቦታዎች ላይ ፓስፖርትን እንደ አንድ ማስረጃ የመጠቀም እንቅስቃሴ ይስተዋላል፡፡ ከዚያ ውጪ በተለያዩ በመገናኛ ብዙኃን በሚተላለፉ ማስታወቂያዎች፣ ፓስፖርትን እንደ መታወቂያ ማቅረብ ትችላላችሁ በሚል የሚተላለፈው መልዕክት የተሳሳተ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

  ፓስፖርት ሰዎች ከአንድ አገር ወጥተው ወደ ሌላ አገር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ውስጥ በሌላ አገር ላይ ማንነታቸውን እንዲታወቅና ለመዘዋወር እንዲችሉ ተብሎ የተዘጋጀ ሰነድ እንደሆነ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህንን የጉዞ ሰነድ ለሌላ አገልግሎቶች ማዋል ትክክል እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡

  የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍራኦል ጣፋ፣ አንዳንድ ሰዎች ተቋማት  ፓስፖርትን እንደ መታወቂያ አይቀበሉንም የሚል ወቀሳ እንደሚያቀርቡ ጠቁመው፣ ሆኖም ወቀሳው ትክክለኛ እንዳልሆነና በተቋማቱ ተቀባይነት በማለት የተገለጸው ጉዳይ ትክክል እንደሆነ ገልጸዋል።

  ፖስፖርት ለአንድ አገልግሎት የተዘጋጀ ሰነድ እንደሆነ የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ይህም ለጉዞ ሰነድነት ብቻ አንደሆነ አስታውቀዋል። በተለይ በዚህ ወቅት ሰዎች ፓስፖርትን እንደ ነዋሪነት መታወቂያ ካርድ የመጠቀም ዝንባሌያቸው እየጨመረ መጥቷል የተባለ ሲሆን፣ ለጉዞ ሰነድነት ከመጠቀም ውጪ አገልግሎት ላይ መዋሉ ተገቢ አለመሆኑ ተሰምሮበታል።

  ፓስፖርት እንደ ተራ ነገር ተሰጥቶ ለአገልግሎት የሚውል ነገር አይደለም ያሉት አቶ ፍራኦል፣ የኢትዮጵያ ፓስፖርት የራሱ የሆነ የደረጃ ኢንዴክስና ይህም የፓስፖርቱን ፕሮቶኮል የአሰጣጥ ሒደት እንዳለው አስታውቀው፣ በመሆኑም ይህንን ሰነድ ከጉዞ አግባብ ውጭ ለሆነ ጉዳይ መጠቀም ትክክለኛ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

  ኤጀንሲው በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የዜጎች እንቅስቃሴ የመቆጣጠር ተልዕኮ እንደተሰጠው፣ ይህም በኤርፖርት ምን ያህል ሰው ከአገር እንደወጣ መቆጣጠር፣ እንዲሁም ድንበር ላይ ያለውን ኬላ የመቆጣጠር ኃላፊነት ስላለበት በዚህ ሁሉ የቁጥጥር ሒደት ውስጥ የተለያዩ ሰዎች ፓስፖርትን ለሌላ ዓላማ ሲጠቀሙበት እንደሚስተዋልም ገልጸዋል፡፡

  ከዚህ ጎን ለጎን ለኤጀንሲው ፈተና ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የሌሎች ጎረቤት አገር ዜጎች፣ በተለያየ መንገድ የኢትዮጵያን ፖስፖርት የሚያገኙበት ሁኔታ እንደሆነ የገለጹት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ በተለይ እነዚህ የአገሮቻቸውን ፓስፖርት የማግኘት ዕድል ያጡ ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩባቸው የተለያዩ አካባቢዎች የነዋሪነት መታወቂያን በተለያየ ዘዴ ፓስፖርት ለማግኘት የሚቀርቡበት ሁኔታ እንደሚያጋጥም አስታውቀዋል፡፡

  የፓስፖርት መረጃ ከሚወሰድባቸው ጉዳዮች አንዱ የነዋሪነት መታወቂያ እንደሆነ የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ ሌላም የልደት ሰርተፊኬት እንደሚጠየቅና እነዚህ ሁሉ ነገሮች ከተሟሉ በኋላ በትክክል የአገሪቱ ዜጋ መሆኑን ለማረጋገጥ ቃለ መጠይቅ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡ ሆኖም ዜጎች እነዚህን ጥያቄዎች ብዙ ጊዜ በአዎንታ እንደማይቀበሉ ገልጸው፣ ኤጀንሲው ግን በትግራይ ተወላጆችና በኤርትራውያን መሀል ያለውን  ልዩነት ለማወቅ፣ የሶማሌ ክልል ተወላጆችንና የጎረቤት አገር ሶማሊያ ዜጎችን ለመለየት፣ በጋምቤላና በደቡብ ሱዳን ዜጎች መካካል ያለውን ልዩነት በመረዳት ፓስፖርት ለመስጠት ይህንን ዓይነት አሠራር መተግበር የግድ እንደሚል አስታውቀው፣ ዜጎችም ይህንን መረዳት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

  ከላይ የተቀሰውን ችግር ለመቅረፍ ኤጀንሲው የብሔራዊ መታወቂያ ሥራን ተግባራዊ የማድረግ እንቅስቃሴ ተግባራዊ እንደሚያደርግ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህ ዓይነቱ መታወቂያ በአሻራ ስለሚሰጥና የፓስፖርቱም እንደዚህ ስለሚከናወን ችግር እንደማይፈጠር ተጠቁሟል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...