ከሬሚታንስ ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል
ሬሚታንስ (ከውጭ የሚላክ የውጭ ምንዛሪ ገቢ) እና ወጪ ንግድ በ2013 በጀት ዓመት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እንዳስገኙ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የተገኘው መረጃ አመለከተ፡፡ በአሁኑ ወቅት በጥቁር ገበያ የአንድ ዶላር ዋጋ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ የጨመረ ቢሆንም፣ በ2013 በጀት ዓመት ከሬሚታንስ የተገኘው ገቢ በአንድ ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ከወጪ ንግድ ደግሞ ከስድስት መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ብልጫ ያለው መሆኑ ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ በ2013 የሒሳብ ዓመት በሬሚታንስ ወደ አገር ቤት የገባው የገንዘብ መጠን ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ተጠግቷል፡፡ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከሬሚታንስ የተገኘው ገቢ አምስት ቢሊዮን ዶላር ነበር፡፡
በ2013 የሒሳብ ዓመት በዘጠኝ ወራት 4.4 ቢሊዮን ዶላር ከሬሚታንስ የተገኘ ሲሆን፣ በቀጣዮቹ ወራት ከ1.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ጭማሪ በማሳየቱ ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የሬሚታንስ ገቢ ሊገኝ ችሏል፡፡
ከወጪ ንግድና ከሬሚታንስ የተገኘው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ከ9.6 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን መረጃው ያመላክታል፡፡
ከሌሎች ዓመታት በተሻለ ዘንድሮ ከሬሚታንስ የተገኘው ገቢ መጨመር እንደ አንድ ምክንያት ከሚጠቀሱት ውስጥ በኮቪድ-19 ምክንያት ተዳክሞ የነበረው የዓለም ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት መልሶ ማንሠራራቱ ይጠቀሳል፡፡
በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አንድ የኢኮኖሚ ባለሙያ፣ በተለይ በአሜሪካና በአውሮፓ ያለው ኢኮኖሚ እያንሰራራ መምጣት ወደ አገር ቤት የሚላከውን ገንዘብ ሊያሳድገው እንደቻለ ጠቁመዋል፡፡
ሥራ አቋርጠውና ሠራተኛ ቀንሰው የነበሩ ኩባንያዎች መልሰው ሠራተኞች በመቅጠር ወደ ሥራ እየተመለሱ መሆኑ ለሬሚታንሱ መጨመር ምክንያት ይሆናልም ብለዋል፡፡
ለኢኮኖሚው ማንሰራራት በአሜሪካ በኮቪድ-19 ምክንያት ሥራቸው ተስተጓጉሎ የነበሩ አየር መንገዶች በአሁኑ ወቅት የባለሙያ እጥረት እያጋጠማቸው ነው መባሉ አንድ ማሳያ ሊሆን እንደሚችል፣ ይህ ደግሞ ሬሚታንሱ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው እኚሁ ባለሙያ ጠቁመዋል፡፡
አሁን ወደ ኢትዮጵያ በሬሚታንስ መልክ እየገባ ያለው የውጭ ምንዛሪ ሊገባ ከሚችለው አንፃር አሁንም ዝቅተኛ የሚባል መሆኑን ያስታወሱት ባለሙያው፣ ዜጎች ከውጭ የሚልኩትን ገንዘብ በሕጋዊ ቻናል የመላክ ልምዳቸውን ማዳበር እንደሚኖባቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
እንደ ሬሚታንስ ገቢው ሁሉ ዘንድሮ በአገሪቱ የወጪ ንግድ ታሪክ ከፍተኛ የተባለው የውጭ ምንዛሪ የተገኘበት ሆኗል፡፡ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር መረጃም ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ ከወጪ ንግድ ገቢ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ያገኘበት ዓመት እንደሆነ አመልክቶ፣ የዘንድሮ የ3.6 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከቀዳሚው የ2012 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀርም ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አለው ብሏል፡፡
ከሁለቱ የውጭ ምንዛሪ ምንጮች የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ከፍተኛ የሚባል ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ከውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ጋር በተያያዘ በተለይ በጥቁር ገበያ ከፍተኛ የሆነ ጭማሪ የታየበት ሆኗል፡፡ አንድ ዶላር በጥቁር ገበያ እስከ 70 ብር እየተመነዘረ ነው፡፡ ይህም ምንዛሪ ዋጋ እስካሁን ያልታየ ከፍተኛ የሚባል ሲሆን፣ ከሰሞኑ በጥቁር ገበያ የታየው ጭማሪ ከተለያዩ ወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ ስለመሆም እየተነገረ ነው፡፡
የኢኮኖሚው ባለሙያው ግን አሁን ላይ የጥቁር ገበያው የምንዛሪ ዋጋ ለማሻቀቡ ምክንያት ራሱን የቻለ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም፣ ቀድመው የነበሩት የፍላጎትና የአቅርቦት ችግር ለችግሩ መባባስ ምክንያት ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡