Sunday, April 2, 2023

ከሕግ ማስከበር ወደ ህልውና ዘመቻ የተቀየረው ቀውስ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በትግራይ ከልል የሚንቀሳቀሰውና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተሰየመው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ታጣቂዎች ኃይል ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ባደረሰው ጥቃት፣ የፌዴራል መንግሥት ለስምንት ወራት ያህል የሕግ ማሰከበር ዘመቻ ሲያደርግ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ በትግራይ ክልል ውስጥ የነበረው ግጭት እንዲቆም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ሰብዓዊነትን መሠረት በማድረግና ተጨማሪ ጉዳት በማያስከትል ሁኔታ የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ላቀረበው ጥያቄ፣ የፌዴራል መንግሥት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆን የተኩስ አቁም ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

የተኩስ አቁም ስምምነቱን ያልተቀበለው ሕወሓት በአማራና በአፋር ክልሎች በርካታ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎችን በተለያዩ ግንባሮች አሰማርቶ በሁለቱም ክልሎች በርካታ ቦታዎችን እየተቆጣጠረ፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን እያፈናቀለ፣ በርካቶችን እየገደለና ንብረትን እየወረሰ፣ በተቆጣጠራቸው አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የእኔ የሚለውን አስተዳደር ተወካይ እየሾመ እንደሆነ በተለያዩ መንገዶች ሲገለጽ ይሰማል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማክሰኞ ነሐሴ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በሕወሓት ታጣቂዎች በአፋር ክልል በአንድ የሕክምና ተቋም የተጠለሉ ከ200 በላይ ሰዎች እንደታረዱ፣ ከ300,000 በላይ ዜጎች ደግሞ እንደተፈናቀሉ አስታውቋል፡፡

በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የቆቦ ከተማ አስተዳደር፣ የራያ ቆቦ፣ የግዳን፣ የአንጎትና የጉባላፍቶ የገጠር ወረዳዎች ብቻ በሕወሓት ታጣቂዎች ወረራ ምክንያት የተፈናቀሉና አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ቁጥር ከ150 ሺሕ በላይ መድረሱን፣ የዞኑ አስተዳደር ሐምሌ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በማኅበራዊ ድረ ገጹ አስታውቋል፡፡

የተጠቀሰው ቁጥር በመርሳና በደሴ ከተሞች በግለሰብ ቤቶች ተጠግተው የሚኖሩትን የኅብረተሰብ ክፍል ሳይጨምር በወልድያና በመርሳ ከተሞች ብቻ፣ በጊዜያዊነት በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው አስቸኳይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የሕወሓት ታጣቂዎች የአማራና የአፋር ክልሎች አጎራባች ነዋሪዎችን በመግደልና በመዝረፍ ገበሬዎችን እንዳያርሱ እንዳስተጓጎሉ፣ ገዳማትን ሳይቀር እንደዘረፉ፣ የዕርዳታ መኪኖችን ወደ ትግራይ ከመግባት እንዳገዱና መንግሥት መቀሌ ውስጥ ያከማቸውን እህል ካልዘመታችሁ አንሰጥም ብለው እንደከለከሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል፡፡

በራያ፣ በወልቃይት ጠገዴ፣ በዳንሻ፣ በዋግ ሰቆጣ፣ በማይፀብሪና በአፋር ሚሌ አካባቢዎች ጥቃት ከመፈጸም አልፎ በሰሜን በወሎ ከተሞች ተኩለሽ፣ ኩልመስክ፣ ሙጃና ጋሸናን አልፎ ላሊበላን የተቆጣጠረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ዋና መቀመጫ የሆነችውን ወልድያ ከተማን ለመቆጣጠር በአቅራቢያ ያሉ ቦታዎች ማለትም መርሳና ጉባ ላፍቶ ከተሞች እንደገባ ይነገራል፡፡ እሑድ ለሰኞ አጥቢያ የሕወሓት ታጣቂዎች ወደ ወልድያ ከተማ አንዳንድ አካባቢዎች የከባድ መሣሪያ ተኩስ ማድረጋቸውን የወልድያ ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ሰኞ ነሐሴ 3 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የሕወሓት ታጣቂዎች በወልድያ ከተማ ሰላማዊ ሕዝብ ላይ በሰነዘሩት የመድፍ ጥቃት ለጊዜው ቁጥራቸው ባልታወቁ ንፁኃን ላይ የሕይወትና የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሕወሓት ታጣቂዎች በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎችን በኃይል ወረዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ሰርገው በገቡባቸው ቦታዎች ግድያ፣ ዘረፋና አስገድዶ መድፈር እየፈጸሙ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት በላሊበላ በኩል ሰርጎ የገባ ኃይል ብሎ የሚገልጸውና ከተማዋን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው የሕወሓት ታጣቂ ኃይል፣ ሐሙስ 29 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀኑ 8 ሰዓት አካባቢ ወደ ከተማው እንደገባ ሪፖርተር በላሊበላ አቅራቢያ አካባቢዎች ተጠልለው ከሚገኙ ነዋሪዎች ማረጋገጥ ችሏል፡፡

አቶ ግዛቸው ምንም እንኳ የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች ሰርገው በገቡባቸው አካባቢዎች እየተደመሰሱ መሆናቸውን ቢገልጹም፣ የሰሜን ወሎ አካባቢዎች በታጣቂዎች ቁጥጥር ሥር እንደሆኑ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ከትግራይ ክልል ተነስቶ በቆቦ ከተማ በማድረግ ወደ ወልድያ የተጓዘው የሕወሓት ታጣቂ ቡድን በተቆጣጠረው የሰሜን ወሎ የሙጃ ከተማ፣ የትግራይ ክልል ባንዲራን ከመስቀል ጀምሮ የራሳቸውን የአስተዳደር መዋቅር እንዳደራጁ ከአካባቢው ነዋሪዎች ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡

ሙጃና ኩል መስክ የተባሉ ከተሞችን ከተቆጣጠሩ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከእነዚህ ከተሞች በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ የምትገኘውን ጥንታዊቷን የላሊበላ ከተማ ያለ ምንም የጥይት ተኩስ ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን ሪፖርተር ካነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች ለማጋገጥ ተችሏል፡፡

ታጣቂዎቹ የላሊበላ ከተማዋን ከመቆጣጠራቸው አንድ ቀን አስቀድሞ በከተማው ይገኙ የነበሩ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል፣ የከተማው ፖሊስና ሌሎች የፀጥታ ኃይሎች  በዋዜማው ቀድመው እንደወጡና ነዋሪዎችም የክልሉ ልዩ ኃይልም ሆነ ሌሎች የፀጥታ አካላት ከተማዋን ለቀው እንዳይወጡ ትግል ቢያደርጉም፣ እንዳልተሳካላቸው የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡

ላሊበላ ከተማ በሕወሓት ታጣቂዎች ቁጥጥር ውስጥ ከገባበት ቀን ጀምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና ተቋማት ድምፃቸውን እያሰሙ ቢሆንም፣ የኢንተርኔት አገልግሎትና የስልክ መስመሮች በመቋረጣቸው ምክንያት ከአካባቢው ነዋሪዎች ወይም ከክልሉ መንግሥትም ሆነ ከፌዴራል መንግሥት በኩል በሥፍራው ምን እየተከናወነ እንደሆነ ማወቅ አልተቻም፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማክሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የተነሳውን የክህደት ኃይል ለመደምሰስ ብርቱና የማያዳግም ክንዳቸውን እንዲያሳርፉ ሲል ጥሪ አቅርቧል፡፡

መግለጫው በተናጠል ተኩስ አቁም ላይ የሚገኘውን የአገር መከላከያ ሠራዊት ወደ ዘመቻ የሚመለስ ይሁን አይሁን በግልጽ ባያመላክትም፣ በተደረገው ጥሪ ዘመቻውን ለመሳተፍ ዕድሜያቸውና አቅማቸው የሚፈቅድላቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ የመከላከያ ሠራዊቱን፣ ልዩ ኃይሉንና ሚሊሻውን በመቀላቀል የአገር ዘብነታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ አክሎም፣ ‹‹ሕወሐት ሰላማዊ ሰዎች አስመስሎ በየአካባቢው ያሰማራቸው ሰላዮችና የጥፋት ተላላኪዎችን ለመከታተልና ለማጋለጥ እንዲቻል፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ዓይንና ጆሮ በመሆን ከፀጥታ አካላት ጋር በቅርበት ሊሠራ ይገባል። የሃይማኖት አባቶች በፀሎት፣ የአገር ሽማግሌዎች በምክር፣ ሁሉም ዜጋ በችሎታው ኢትዮጵያን ብሎ ይቁም፤›› በማለት ጥሪ አቅርቧል፡፡

የመከላከያ  ሚኒስቴር የሕዝብ  ግንኙነት ዳይሬክተር  ኮሎኔል  ጌትነት አዳነ የሕወሓት ታጣቂዎች በአማራና አፋር ክልሎች እያደረሱ ያለውን ወረራና ዝርፊያ፣ እንዲሁም ግድያ የመከላከያ ሠራዊት እንዴት እየተከታለው ነው በማለት ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ሠራዊቱ በተኩስ አቁም ላይ እንዳለና ነገር ግን በአንዳንድ አካባቢዎች ጠላትን የመከላከል ሥራ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በጋይንት ጨጨኾ አቅጣጫ በመቄት ወረዳ ደብረ ዘቢጥ አካባቢ የሕወሓትን ኃይል ለመዋጋት የተሠለፉትን የመከላከያ ሠራዊት፣ የልዩ ኃይል፣ የሚሊሻና የአማራ ወጣት (ፋኖ) አደረጃጀት በአካል በመገኘት እንቅስቃሴያቸውን መጎብኘታቸውን በማኅበራዊ ድረ ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡

በጉብኝታቸው ወቅትም በአሸባሪው ኃይል በአፋርና በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው እኩይ ወረራ፣ ጥቃት፣ ዘረፋና ግድያ በመመከትና የማያዳግም ዕርምጃ በመውሰድ ኢትዮጵያን በጋራ እንድንታደግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመሥገን ጥሩነህ ማክሰኞ ነሐሴ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ለአንድ የመንግሥት ሚዲያ በሰጡት ቃለ መጠይቅ፣   የሕወሓት ቡድንን በአጭር ጊዜ ለማጥፋት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በጋራ እየሠሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም ስትራቴጂ ተነድፎ እየተሠራ እንደሆነ፣ በአማራና በአፋር ግንባር የፌዴራል የደኅንነትና የፀጥታ መዋቅር በስፋት ሥምሪት በመውሰድ ታጣቂ ቡደኑን ከአማራና ከአፋር ክልሎች ለማስወጣት ብቻ ሳይሆን፣ ከምድረ ገጽ ለማጥፋት እንደታሰበ አመላክተዋል፡፡

ከአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የገጠርና የከተማ ወረዳዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተፈናቃይ ወደ ደቡብ ወሎ አስተዳር ዞን ዋና መቀመጫ ደሴ ከተማ በመግባቱ ሳቢያ፣ የከተማውን ነዋሪዎች ሁለንተናዊ ደኅንነት ለመጠበቅ በሚል የተሽከርካሪና የሰው የእንቅስቃሴ ለመወሰን፣ የደሴ ከተማ አስተዳደር ከነሐሴ 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የሰዓት ዕላፊ ገደብ ማስቀመጡን አስታውቋል፡፡

በዚህም የከተማው ነዋሪዎች ከምሽቱ 2:00 ጀምሮ ከተፈቀደላቸው የፀጥታ አካላት፣ የፀጥታ ተቋማትና የጤና ተቋማት ተሽከርካሪዎች ውጪ የትኛውም ዓይነት እንቅስቃሴ የተከለከለ መሆኑንና የሦስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ምሽቱ 12:00 ሰዓት ብቻ እንዲሆን መወሰኑን አስታውቋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በሱዳንና በኢትዮጵያ የነበራቸውን የአምስት ቀናት ጉብኝት አጠናቀው ወደ አሜሪካ የተመለሱት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይዲ) ዋና ኃላፊ ሰማንታ ፓወር፣ የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት ታጣቂዎች ከውይይት ይልቅ ጦርነትን መርጠዋል ሲሉ ወቀሳ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ መቀመጫውን ካደረገ ኤንፒአር ከተባለ የሬዲዮ ጣቢያ ጋር ቆይታ የነበራቸው ሰማንታ ፓወር የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግሥት ሁሉን አቀፍ የሆነ ውይይት ከማድረግ ይልቅ የጦር ኃይል እያዘመተ እንደሆነ፣ እንዲሁም የሕወሓት ታጣቂዎች የፌዴራል መንግሥቱን በማሸነፍ ድል መቀዳጀት የሚፈልጉ በመሆናቸው ለውይይት ዝግጁ አይደሉም ብለው ነበር፡፡

በአሁኑ ጊዜ የሕወሓት ታጣቂዎች በአማራና በአፋር ክልል በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ተፈናቅለው ለአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ጠባቂነት መዳረጋቸው በተለያዩ ጊዜያት ሪፖርት መደረጉ አይዘነጋም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -