Tuesday, May 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​​​​​​​የኢትዮጵያውያንን ዕንቢተኝነት የሚጠይቀው የዶላር ጥቁር ገበያ

በኢኮኖሚው ውስጥ የሚሠሩ አሻጥሮች ለአገር አደጋ መሆናቸውን በተደጋጋሚ ስንናገር ቆይተናል፡፡ አሻጥረኞች ስለአገርና ስለሕዝብ ደንታ ቢሶች በመሆናቸው በማንኛውም ወቅት ሕገወጥ ተግባራትን ከመፈጸም አይቦዝኑም፡፡ ዛሬ አገር እንዲህ በተጨነቀችበት ሰዓት ይህንን ጊዜ እንዴት ተጋግዘንና ተባብረን እንለፈው ከሚል ይልቅ አጋጣሚዎችን እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም አገርን ያደማሉ፡፡

ሆን ብለው ኢኮኖሚያዊ ቀውስና መናጋት እንዲፈጠር በእጃቸው ያለውን ገንዘብ ችግሮቻችንን ለማወሳሰብ መጠመዳቸውም የለመደ አመላቸው መገለጫ ነው፡፡ ከሰሞኑ የዶላር የምንዛሪ ዋጋ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የማሻቀቡ አንዱ ሚስጥርም ለአገር ደንታ የሌላቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አገር ለማዳከም ከሚጥሩ ወገኖች ጋር በመሆን የሚሸርቡት ሴራ ሊሆን እንደሚችልም ይታመናል፡፡

ዛሬ የኑሮ ውድነት ጣራ በነካበት በዚህ ሰዓት እንዲህ ያለውን ደባ መፈጸም በራሱ የሚያመለክተው ሕዝቡን የበለጠ በማማረር ቀውስ እንዲፈጠር ያላቸውን ምኞት ነው፡፡ በኢኮኖሚው ውስጥ አሻጥር በመፍጠር የሚፈጸሙ በደሎች በተለያዩ መንገዶች የሚገለጹ፣ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያሻቸውና በአንድ ሰሞን ዘመቻ ብቻ የሚቆሙም አይደሉም፡፡ እግር በእግር መከታተልን ይጠይቃል፡፡

ከሰሞኑ በዶላር የምንዛሪ ዋጋ ማሻቀብ ዙሪያ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ እንደገለጹት፣ ችግሩ አሻጥር ያለበት ነው፡፡ ከወቅታዊ አገራዊ ችግርና ንብረትን ከማሸሽ ጋር የተያያዘም ሆኖ የሚታይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥሩ አማራጫቸው ባሻቸው ገንዘብ ዶላር መሸመት አንዱ ነው፡፡

ወትሮም የጥቁር ገበያ ኢኮኖሚዊ ጉዳት እየታወቀ የማያዳግም ዕርምጃ ያለመወሰዱም ችግሩ አፍጥጦ እንዲታይ ማድረጉ ግን ሊታወስ ይገባል፡፡  

በዓለም ላይ የዶላር ጥቁር ገበያ የደራባት ብቸኛዋ አገር ኢትዮጵያ ናት እስከሚባል ድረስ የጥቁር ገበያው እንዳልታየ መታለፉ ዛሬ ላይ የበለጠ ዋጋ እያስከፈለ ነው ማለት ይቻላል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አፍንጫ ሥር ጭምር ደርቶ የሚታየው የዶላር ምንዛሪ ወይም የጥቁር ገበያ የጠነከረ ዕርምጃ ባለመወሰዱ አገር ለማፈራረስ ለተሰናዱ ወገኖች ጭምር መጠቀሚያ እየሆነ ነው፡፡ የዶላር ጥቁር ገበያው የሚሠራው ደግሞ ሕጋዊ ናቸው በሚባሉ ነጋዴዎች ጭምር ነው፡፡

ይህንን ጥቁር ገበያ ለማጥፋት ወይም ተፅዕኖው ጉልቶ እንዳይወጣ ለማድረግ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች የማያዳግሙ ባለመሆናቸው ዛሬ ወደገባበት ቀውስ ቢያደርሰንም፣ ትርጉም ያለው ዕርምጃ ለመውሰድ አሁንም ጊዜው አልረፈደም፡፡

እንደዚህ ያሉ አሻጥሮች አድገው አድገው ጉዳቶቻቸው ከፍተኛ ሊሆን መቻሉን በተግባር የሚያሳዩን ከሰሞኑ ባንኮች ብድር ላልተወሰነ ጊዜ አትስጡ መባላቸው ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ዕርምጃ ሲወስድ ዕርምጃው ምን ያህል ትክክል ነው የሚለው ጥያቄ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሕገወጥ ተግባራት ቀድሞ በትክክል ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው አለመደረጉ ውሎ አድሮ አደጋቸው የከፋ ለመሆኑ አንድ ማሳያ ይሆናል፡፡

የጥቁር ገበያው ሆን ተብሎ ጣራ እንዲነካ ለምን ሆነ ብለን ውስጠ ሚስጥሩን እንፈትሽ ከተባለም ብዙ ነገሮች ሊመዘዙ ይችላሉ፡፡ ነገሩን የከፋ የሚያደርገው ግን ለተለያዩ ሥራዎች ከባንክ የሚሰጡ ብድሮች ሳይቀሩ በጥቁር ገበያው ዶላር እየተሸመተበት ነው መባሉ ነው፡፡

ነገሩ ተንኮል ያለበት ቢሆንም እነዚህ ሕገወጥ ግለሰቦች በፈጸሙት ደባ ሕጋዊ ተበዳሪዎች ብድር እንዳያገኙ፣ ባንኮችም አበድረው እንዳይጠቀሙ ማድረጉን ስንረዳ እንደ አገር እየተጎዳን መሆኑን ያሳያል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ነገሩን የበለጠ አሳዛኝ የሚያደርገው በተንኮል ከተጠመዱት ግለሰቦች ባሻገር የዶላር ምንዛሪ ከፍ ማለትን ተከትሎ በአጋጣሚው የተሻለ የምንዛሪ ዋጋ አገኘሁ ብሎ ወደ ጥቁር ገበያው የሚያማትሩ ግለሰቦች መኖራቸው ነው፡፡ መቼም እንደ አገር ካሰብን አገርን ሊጎዱ በሚችሉ ተግባራት ላይ መሰማራት፣ በተለይም በዚህ ወቅት አገርን ሊጎዳ እንደሚችል እየታወቀ የጥቁር ገበያውን ማድመቅ ከወንጀሎች ሁሉ የከፋ ወንጀል ነው፡፡

ስለዚህ የጥቁር ገበያውን በማጦዝ አገራዊ ኢኮኖሚውን በሚጎዱ ተግባራት ላይ ዜጎች እጃቸውን ባያስገቡ፣ በተለይም በዚህ ጊዜ ሊገኝ የሚችል ጥቅም ከአገር ህልውና አይበልጥምና አሻጥረኞችን ባለመተባበር ሕጋዊ መስመርን ተከትሎ መሥራት ተገቢ ይሆናል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ አገሪቱ የምትፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከፍ ለማድረግ የዳያስፖራው ድርሻ ከፍተኛ ስለመሆኑ ይታወቃልና ከውጭ ወደ አገር የሚላክ የውጭ ገንዘቦች ሕጋዊ መስመራቸውን ይዘው እንዲገቡ በማድረጉ ረገድ አደራ ማለት ያስፈልጋል፡፡

የጥቁር ገበያው ምንዛሪ ዋጋ ከፍ ብሏል በሚል ከሕጋዊ መንገዱ ውጪ ወይም በባንክ መላክ እየተቻለ ለተወሰነ ጥቅም የጥቁር ገበያው ሰለባ በመሆን የአገርን ጉዳት ከፍ ከማድረግ መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡

እንደ ዜጋ አገሬ የምትጠቀመው በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ ብልክ ነው ብሎ ማሰብ በተለይ በዚህ ወቅት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ መንግሥት ጥቁር ገበያውን ለማዳከም መውሰድ ካለበት ዕርምጃ ባሻገር ለጥቁር ገበያው መድራት አንዱ ምክንያት ያፈነገጡ ተግባራት ነውና ዳያስፖራው ይህንን ተገንዝቦ ለአገር ጥቅም ሲባል ከውጭ ወደ አገር የሚላከውን ገንዘብ ሕጋዊ ያድርግ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት