የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እስከ ሐሙስ ነሐሴ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ ከአሥር ሺሕ በላይ የሚሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን፣ በትግራይ ክልል ከሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች በማስወጣት እንዳጓጓዘ አስታወቀ፡፡
ከአንድ ወር አስቀድሞ መንግሥት የአገር መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል እንዲወጣ ካደረገ በኋላ በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲዎቹ ባለመውጣታቸው ምክንያት፣ የተማሪዎቹ ወላጆች በመንግሥትና በተመድ ላይ ግፊት ሲያደርጉ እንደቆዩ ይታወሳል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር በተጠናቀቀው ሳምንት መጨረሻ ላይ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው፣ በትግራይ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች መደበኛ ትምህርት እየተከታተሉ የቆዩ ተማሪዎች ከሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው መመለስ ቢገባቸውም፣ በፀጥታ ችግር ምክንያት ጉዞአቸው እንደተስተጓጎለ አስታውቋል፡፡
በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አማካይነት ከሐምሌ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ፣ ወደ 2,000 የሚጠጉ ተማሪዎች ከክልሉ መውጣታቸው ከዚህ በፊት መዘገቡ አይዘነጋም፡፡ በተጠናቀቀው ሳምንት ሚኒስቴሩ እንዳስታወቀው፣ ከፌዴራልና ከአፋር ፖሊስ ኮሚሽኖችና ከትራንስፖርት ማኅበራት ጋር በመተባባር እስከ ነሐሴ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ 2,355 ከአዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ 2,992 ከአክሱም ዩኒቨርሲቲ፣ 3,668 ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም 1,149 ተማሪዎችን ከራያ ዩኒቨርሲቲ እንዳጓጓዘ አስታውቋል፡፡ በአጠቃላይ 10,164 ተማሪዎች በሰመራ በኩል እስከ ኮምቦልቻና አዲስ አበባ መጓጓዛቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
ተማሪዎቹ በደረሰባቸው የጉዞ መስተጓጎል ሳቢያ ከተሰጣቸው የዕረፍት ጊዜ አንድ ወር ያህል እንደባከነ ያስታወቀው ሚኒስቴሩ፣ ተማሪዎቹ ተጨማሪ የዕረፍት ጊዜያቸው ታሳቢ እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ በ2013 ዓመት የትምህርት ዘመን ከአዲግራት፣ ከአክሱምና ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲዎች ተመራቂ የነበሩ ተማሪዎች ባልተጠናቀቁ የትምህርት መርሐ ግብሮች ምክንያት ትምህርታቸውን አጠናቀው አለመመረቃቸውን አስታውሶ፣ በቀጣይ በሚያወጣው መመርያ መሠረት ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን አጠናቀው እንዲመረቁ እንደሚያመቻች ገልጿል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ክልል በሚገኙ አራት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በክረምት ፕሮግራም ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ ተማሪዎች በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ወደ ተቋማቱ መጓጓዝ እንዳልቻሉ ተገልጾ፣ እነዚህን ተማሪዎች በተመለከተ በቅርቡ እንደሚያስታውቅ ገልጿል፡፡ እስከዚያው ድረስ ተማሪዎቹን ምላሹን በትዕግሥት እንዲጠባበቁ አሳስቧል፡፡
ከሁለት ሳምንታት አስቀድሞ ልጆቻቸውን ከትግራይ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች እንዲያስመጣላቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የጠየቁ ወላጆች፣ ድርጅቱ እንዲያሟሉ የጠየቃቸው በርካታ ፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታዎች እንዳስቆጣቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡