የፌዴራሉ መንግሥት በቅርቡ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ወታደራዊ ክንፍና የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጥምረት እንዳላስደነቀው፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና የዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩም ሐሙስ ነሐሴ 6 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፣ ጥምረቱ አዲስ ስላልሆነ ለመንግሥት አስገራሚ አልሆነም ብለዋል፡፡
የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በማለት ራሱን የሚጠራውና መንግሥት ሸኔ የሚለው ታጣቂ ቡድን አዛዥ የሆኑት ድሪባ ኩምሳ (ጃል መሮ) በቅርቡ ለአሶሼትድ ፕረስ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ከሕወሓት ጋር ጥምረት ፈጥረው እየሠሩ እንደሚገኙ የተናገሩ ሲሆን፣ ይኼም በዋናነት መረጃ መለዋወጥ ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል፡፡
የተደረገው ስምምነት ጎን ለጎን ተሠልፈው ለመዋጋት እንዳልሆነ ቢናገሩም፣ ይኼ የሚሆንበት ዕድል እንዳለና የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደርን ለመጣል የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
ቢልለኔ በመግለጫቸው የዚህ ጥምረት ይፋ መሆን አዲስና አስገራሚ ባይሆንም፣ ከወቅቱ ጋር ታይቶ ሊገመገም ይገባዋል ብለዋል፡፡ ከሁለት ዓመታት በላይ መንግሥት ሕወሓት ኦነግ-ሸኔን በተላላኪነት ሲጠቀምበት እንደቆየ በመጠቆም፣ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ግን ከእነሱ እስከሚሰሙት ድረስ ማመን አልፈቀዱም ነበር ብለዋል፡፡
መንግሥት በዚህ ዓመት መጀመርያ ላይ ኦነግ-ሸኔንና ሕወሓትን አሸባሪ በማለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መፈረጁ ይታወሳል፡፡
የኦነግ ጦር አዣዥ ድሪባ ኩምሳ ከሕወሓት ጋር የጋራ ጠላትን ከማጥፋት አንፃር ከመግባባት መድረሳቸውን በመጥቀስና ወታደራዊ ትብብርም እንደሚያደርጉ በማሳወቅ፣ ይኼም ጠየቅላይ ሚኒስትሩን አስተዳደር እስከ ማስወገድ ይኼዳል ብለዋል፡፡
እነዚህ ሁለቱ ወገኖች አሸባሪ ተብለው የተፈረጁ መሆናቸውን ያስታወሱት ቢልለኔ፣ ጥምረታቸውን ይፋ ማድረጋቸው አገሪቱ እንዳትረጋጋ በጥፋት ድርጊቶች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
ዘጠነኛ ወሩን የያዘው የትግራይ ክልል ጦርነት ወደ አማራና አፋር ክልሎች መስፋፋት የጀመረ ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ በርካታ ንፁኃን ለሞትና ለመፈናቀል ተዳርገዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው የትግራይ፣ የአማራና የአፋር ክልል ተጎጂዎች በግጭቶች መስፋፋት ሳቢያ ድጋፍ ለማድረስ አዳጋች እየሆነ እንደመጣ በዓለም አቀፍ ሰብዓዊ ድጋፍ አቅራቢዎች ሲነገር ቆይቷል፡፡