በአገሪቱ ባንኮች ከፍተኛ ባለአክሲዮኖችንና ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ለመቆጣጠር የሕግ ማሻሻያ አደርጓል
የባንክ ዕዳና ግብር ባለመክፈል ውሳኔ የተሰጠባቸውና በፍርድ ቤት ኪሳራ የታወጀባቸው ከፍተኛ ድርሻ መያዝ አይችሉም
ብሔራዊ ባንክ የባንኮችን ተቀማጭ ገንዘብና ገንዘብ ነክ ሰነዶች የሚገዛበትና መልሶ የሚሸጥበት ገበያ የሚያቋቁም መመርያ አውጥቶ ወደ ሥራ መግባቱን አስታወቀ፡፡
በብሔራዊ ባንክ ዋና ገዥ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ተፈርሞ ይፋ የሆነው አዲስ መመርያ “Open Market Operations and Standing Facilities Directive” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፣ የባንኮችን ተቀማጭ ገንዘብና ገንዘብ ነክ ሰነዶች የሚገዛበትና መልሶ የሚሸጥበት፣ እንዲሁም የገንዘብ እጥረት ለገጠማቸው ባንኮች የሚያበድርበት ግልጽ ገበያ ነው።
የገበያ ሥርዓቱ የባንኮችን የገንዘብ እጥረት ችግር ለመፍታትና የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ያለመ ሲሆን፣ የገበያ ሥርዓቱን ለማቋቋም የወጣው መመርያም ከሐምሌ 26 ቀን 2013 ዓ.ም. አንስቶ ወደ ሥራ መግባቱ ታውቋል።
ሁሉም የአገሪቱ ንግድ ባንኮች በፈቃደኝነትና ከብሔራዊ ባንክ ጋር ስምምነት በመፈራረም፣ በገበያ ሥርዓቱ መሳተፍ እንደሚችሉ መመርያው ያመለክታል።
በብሔራዊ ባንክ መሪነት በሚከናወነው በዚህ ግልጽ የገንዘብና ገንዘብ አከል ሰነዶች ገበያ ላይ ባንኮች ተቀማጭ ገንዘባቸውንም ሆነ ሌሎች ገንዘብ አከል የክፍያ ሰነዶችን ለብሔራዊ ባንክ መሸጥ፣ መልሶ መግዛትና ገንዘብ አከል ሰነዶችንና ንብረቶችን በዋስትና በማስያዝ መበደር እንደሚችሉ መመርያው ያስረዳል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በዚህ ገበያ ለመሳተፍ ከተስማሙ ባንኮች ተቀማጭ ገንዘብ መሰብሰብ የሚያስችለው ሲሆን፣ የሚሰበስበው ተቀማጭ ገንዘብ ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ በብሔራዊ ባንክ ይዞታ ሥር የሚቆይና ቋሚ የወለድ ምጣኔ የሚከፈልበት እንደሆነም መመርያው ያመለክታል።
ይህንን ገበያ በመጠቀም ተቀማጭ ገንዘብን የመሰብሰብ ተግባር በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋዘር የገንዘብ መጠንን በመቀነስ፣ የዋጋ ግሽበትን ለማረጋጋት ተብሎ የተቀመጠ ነው።
የገንዘብ ፍሰት እጥረት የገጠማቸው ባንኮች ይህንኑ ገበያ በመጠቀም ገንዘብ አከል ሰነዶችንና ንብረቶችን በዋስትና በማስያዝ፣ መበደር የሚችሉ እንደሆነም መመርያው ይገልጻል።
ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ ገበያ ውስጥ ብሔራዊ ባንክ ራሱ የሚያወጣውን የዕዳ መክፈያ ሰነድ፣ መንግሥት የሚያወጣውን ተመሳሳይ የዕዳ መክፈያ ሰነድ (ቦንድ) በመሸጥ፣ በባንኮች የሚገኝ የተከማቸን ገንዘብ ከኢኮኖሚው ውስጥ መሰብሰብ የሚያስችል እንደሆነ መመርያው ያስረዳል።
እንደ ነገሩ ሁኔታ በአግባቡ የተፈረሙና በባለቤቱ በጀርባ በመፈረም የተረጋገጡ የሐዋላ ሰነዶች፣ የተስፋ ሰነዶች (ፕሮሚሰሪ ኖት)፣ ተካፋዮችና ሌሎች የገንዘብ መክፈያ ሰነዶች በቅናሽ ወይም በድጋሚ ቅናሽ በማድረግ የሚገዛበት ወይም የሚሸጥበት እንደሚሆንም መመርያው ያመለክታል።
ብሔራዊ ባንክ ይህንን መመርያ ያወጣው በማቋቋሚያ አዋጁ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ብሔራዊ የገንዘብና ብድር አቅርቦት በተፈለገው መጠን መገኘትን፣ የወለድ ተመንና ሌሎች ክፍያዎችን የመወሰንና የመቆጣጠር፣ እንዲሁም ባንኮችና ሌሎች ገንዘብ ተቋማት የአጭርና የረዥም ጊዜ የብድር አገልግሎት እንዳስፈላጊነቱ እንዲያገኙ የማድረግ ሥልጣን በማቋቋሚያ አዋጁ ተሰጥቶታል።
በተጨማሪም ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሚዛናዊ ዕድገት ተስማሚ የሆነ የተረጋጋ የዋጋና የምንዛሪ ምጣኔ ማስፈን፣ ከባንኮች ጋር ስላለው የብድር ግንኙነትና በባንኮችና በሌሎች የገንዘብ ድርጅቶች ስለሚሰጡ የብድር አገልግሎቶች መመርያ የማውጣት ሥልጣን ይሰጠዋል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸው ባለሙያዎች እንደሚሉት ብሔራዊ ባንክ ኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወረውን ገንዘብ ለመሰብሰብ ይረዳው የነበረው አስገዳጅ የ27 በመቶ ቦንድ ሽያጭ ቀሪ በመሆኑና ሌላኛው የፖሊሲ መሣሪያ የሆነው የግምጃ ቤት ሰነድ ጨረታ ላይ የሚሳተፉ የባንኮች ፍላጎት በመቀነሱ አዲስ ባወጣው መመርያ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚዘዋወር ገንዘብን ለመሰብሰብ መሣሪያ አድርጎ እንዲጠቀም ያስችለዋል፡፡
በሌላ በኩል በአገሪቱ ባንኮች ውስጥ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ የሚይዙና የባንክ ሥራን የሚመሩ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ለመቆጣጠር፣ የሕግ ማሻሻያ አደርጎ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።
ይህ መመርያ በአገሪቱ ባንኮች ውስጥ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ የያዙ ግለሰቦችና በባንክ አስተዳደር ሥራ የሚሰማሩ መካከለኛና ከፍተኛ አመራሮች፣ ወይም በመመርያው ስያሜ መሠረት ተፅዕኖ ፈጣሪ ሰዎችን ለመቆጣጠር ያለመ ነው።
በመሆኑም ሁሉም ባንኮች ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ እንዲያዝ ከመፍቀዳቸው አስቀድሞ፣ ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ የሚይዘውን ሰው ወይም ሕጋዊ ሰውነት ያለው አካል ለብሔራዊ ባንክ ማፀደቅ ይጠበቅባቸዋል።
ለመንግሥት መከፈል የነበረበትን ግብር ያልከፈሉ፣ የባንክ ዕዳቸውን በመክፈል ረገድ ችግር ያለባቸው ወይም ያቋረጡ፣ እንዲሁም በባንክ ሐራጅ ንብረታቸው የተሸጠባቸው ሰዎች በየትኛውም ባንክ ውስጥ ከፍተኛ ባለድርሻ መሆን እንደማይችሉ የተሻሻለው መመርያ ይደነግጋል።
በወንጀል ክስ የተፈረደበት፣ በፍርድ ቤት ኪሳራ የታወጀበትና እንዲሁም መልካም ሥነ ምግባር የሌለው መሆኑ የተረጋጠጠ ሰው በባንኮች ውስጥ በአመራርነት ማገልገል፣ እንዲሁም ከፍተኛ ድርሻ መያዝ እንደማይችል መመርያው ያስረዳል፡፡