በበጋ ወቅት የዝናብ ተጠቃሚ የሆኑት የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ ቆላማ አካባቢዎች፣ በመጪው በጋ የዝናብ እጥረት ሊገጥማቸው እንደሚችል ብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
በበጋ ወቅት የዝናብ እጥረት ይገጥማቸዋል የተባሉት የቦረናና የጉጂ ቆላማ ዞኖች፣ ደቡብ ኦሞ፣ ደቡብ ምሥራቅ ሶማሌ አካባቢዎች መሆናቸው የተገለጸው ዓርብ ነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. ኤጀንሲው በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው፡፡
የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ፣ የበጋ ወቅት ሁለተኛ የዝናብ ጊዜያቸው የሆኑት አካባቢዎች የዝናብ እጥረት ሊገጥም ስለሚችል ከወዲሁ ውኃ መያዝ እንደሚያስፈልጋቸው አሳስበዋል፡፡
የህንድ ውቅያኖስና የፓስፊክ ውቅያኖስ ወለሎች በመቀዝቀዛቸው ምክንያት፣ በኢትዮጵያ የበጋ ወቅት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ እጥረት ሊያስከትሉ ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የዓለም አቀፍ የትንበያ ማዕከላት የዳይናሚካልና የስታትስቲካል መረጃዎችን ዋቢ አድርገው ያስረዱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የህንድ ውቅያኖስና የፓስፊክ ውቅያኖስ ወለሎች መቀዝቀዛቸው ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በዚህም ምክንያት በበጋ ወቅት ዝናብ የሚያገኙ አካባቢዎች እጥረት ሊገጥማቸው እንደሚችል የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ የደቡብና የደቡብ ምሥራቅ ቆላማ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሊያገኙ ስለሚችሉ በኩሬዎችና በግድቦቻቸው መያዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በተጨማሪም በሰሜን፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች በአብዛኛው ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ የዝናብ መጠን እንደሚጠበቅና አብዛኛው የደቡብ፣ የምዕራብ፣ የመካከለኛው፣ የምሥራቅና የደቡብ ደጋማ አካባቢዎች ዝናብ የማግኘት ዕድል እንዳላቸው ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
በነሐሴና በመስከረም ወራት አልፎ አልፎ በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ የሚጠበቅ መሆኑን፣ በዚህም ሳቢያ በወንዞች ዳርቻና በረባዳማ ቦታዎች ጎርፍ ሊከሰት እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የዘንድሮ ክረምት ካለፉት ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የጉም ክምችት ያለበት መሆኑን በመጠቆም፣ በነሐሴና በመስከረም ወራት ሊቀጥል እንደሚችል ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ሁለት ወራት በታችኛውና በላይኛው አዋሽ ጎርፍ እንደሚከሰትና የዓባይ ተፋሰስ አካባቢዎች፣ በዋቢ ሸበሌ፣ በጅግጅጋና በድሬዳዋ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ ስለሚኖር ተገቢው ጥንቃቄ መደረግ አለበት ብለዋል፡፡
በነሐሴና በመስከረም ወራት የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተሻለ ዝናብ ስለሚያገኙ፣ የድርቅ ሥጋት እንደማይኖር ትንበያው ማሳየቱ ተገልጿል፡፡