የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበራት ጥምረት ዓርብ ነሐሴ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በውጭ አገር የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት በአገራዊ ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን እንዲቆሙ ጠየቀ፡፡
የጥምረቱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሮ ሶስና ወጋየሁ በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ ሆነው እንደሚከታተሉ ተናግረዋል፡፡
የሚታየው አገራዊ ችግር ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች እየተጓዘ እንደ ሶሪያ፣ ሊቢያና አፍጋኒስታን ኢትዮጵያን የጦር ቀጣና እንዳያደርጋት ዳያስፖራው በጋራ እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡
ጥምረቱ የጠፋው ሰላም ተመልሶ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውረው እንዲኖሩና እንዲሠሩ፣ ከመንግሥት ጋር በመሆንም የኢትዮጵያን ሰላም ለመጠበቅና ደኅንነቷን ለማስከበር እንደሚሠራ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡
የዳያስፖራው አባላት በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በሚለጠፍ ጽሑፎች ላይ አስተያየት ከመስጠትና ከፀብ አጫሪ ንግግሮች ከማድረግ በመቆጠብ፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ሀብት እናፈላልግ እያሉ ከሚያጭበረብሩ አካላትና ሐሰተኛ መረጃዎች እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡
ከተመሠረተ አንድ ዓመት ያስቆጠረው የዳያስፖራ ማኅበራት ጥምረት፣ በተለያዩ አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውን በመሠረቷቸው አሥር ማኅበራት ነው፡፡
ጥምረቱ በተቀናጀ አካሄድ ዳያስፖራውን ወደ አንድ በማምጣት፣ እንደ ህንድና ሌሎች አገሮች ኢትዮጵያ ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ ማግኘት ያለባትን ጥቅም እንድታገኝ ታስቦ የተመሠረተ መሆኑ ሰብሳቢዋ ገልጸዋል፡፡
ለኢትዮጵያ መጠናከር በውጭ አገር ያለው የዲፕሎማሲ ሥራና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማደግ ያለው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ፣ ዳያስፖራው በያለበት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
መንግሥት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ማካሄድ ከጀመረ ጀምሮ በበርካታ የዳያስፖራ አባላት መካካል ክፍፍል መፈጠሩን ያስታወሱት ሰብሳቢዋ፣ ለአብነትም በወዳጅነት አብረው የኖሩና ለ30 ዓመታት ይተዋወቁ የነበሩ የዳያስፖራ ጓደኛሞች ጭምር መለያየታቸውን አስረድተዋል፡፡
በውጭ ያሉ የዳያስፖራ አባላት የመንግሥትን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ለመቀላቀል ፍላጎት እንዳላቸው የገለጹት ወ/ሮ ሶስና፣ እንዲህ ዓይነቱን ተነሳሽነት መንግሥት በራሱ የሚሄድበት ይሆናል ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ በውጭ ያለው ማንኛውም ዓይነት ጫጫታና ሁካታ በአገር ውስጥ የሚከናወነው ማንኛውም ዓይነት ድርጅት ነፀብራቅ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚታየው ችግር በጋራ መፍትሔ መስጠት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በውጭ ዓለም ችግሩ ገዝፎ ለማመን በሚከብድ ደረጃ የደረሰውን የዳያስፖራውን የመከፋፈል ችግር በመፍታት፣ የዳያስፖራ አባላት በጋራ እንዲቆሙ ማድረግ ይቻላል ሲሉ አስታውቀዋል፡፡