Saturday, December 2, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሕንፃ ያለ ዕውቀት

በያሬድ ኃይለ መስቀል

የአዲስ አበባን ኮሜርስ ኮሌጅ የአዲስ አበባ አስተዳደር ሕንፃውን አፍርሶ መሬቱን ለባንኮች ለመሸጥ እንደወሰነ እየተነገረ ነው። ይህንን በመቃወም በርካታ ሰዎች ሕንፃው መፍረስ እንደሌለበት የሚከራከሩት ከሕንፃውና ከትምህርት ቤቱ ታሪካዊ ቅርስ ተነስተው ነው። ይህ ትክክል ነው። በርካታ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ የቀየሩና ለባንኩ የኢኮኖሚ መስክ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሰዎች የወጡበት ከዚህ ኮሌጅ ነበር። በዚህ ኮሌጅ ከዛሬ 78 ዓመት ጀምሮ የኢትዮጵያ ዘመናዊንግድ፣ባንክ፣ኢንሹራንስና የአስተዳደር ዕቅድ የተጀመረው በዚህ ኮሌጅ ውስጥ በተማሩ መሪዎች ነው።  ስለዚህ ታሪካዊ ቅርስ በመሆኑ ብቻ  መፍረስ የለበትም። 

ለአዲስ አበባ ከንቲባዎች ይህ ቅርስ ብዙም ዋጋ የለውም። ችግሩ አለመታደል ሆኖ አዲስ አበባ አንድም ከተማ የተወለደ ሰው ከንቲባ ሆኖ ተሾሞበት አያውቅም። ስለዚህ ለብዙዎቹ ከንቲባዎች የፎቅ ርዝመት የሚያስደምማቸው ሥልጣኔ ነው።

እነዚህ ሰዎች የኦክስፎርድ፣ቬኒስ፣ሮም፣ባት ከንቲባ ተደርገው ቢሾሙ ዶዘር ይዘው ገብተው አፍርሰው የመስታወት ፎቅ ደርድረው እዩ ሥልጣኔያችንን ይሉ ነበር። የገጠር ሰው ፎቅ ይወዳል አይፈረድበትም። ችግሩ የገጠር ሰው ከተማን የሚያይበት ዓይን ለከተማ ዕድገት ችግር ፈጣሪ መሆኑ ነው።

እኔ ደግሞ ትምህርት ቤቱም ሳይጠፋ እነሱ ደስ የሚላቸውም ፎቅ ተጨምሮ ይህንን ታሪካዊ ኮሌጅ ትልቁ የፋይናንስ፣ባንኪንግ፣ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ ኢንተርኔት ሴኪዩሪቲና ዲጂታል ከረንሲ የሚጠናበት፣ የሚማርበት ትልቅ ዩኒቨርሲቲ ሊሆን ይችላል። ባንክ የዕውቀት ሥራ እንጂ የመስታወት ሕንፃ ውስጥ ከረባትና ሱፍ የለበሱ ሰዎች መቀመጫ አይደለም። 

የእኔ ክርክር ሊገነባ ከታቀደው የባንኮች ሕንፃ በላይ ይህ ኮሌጅ ጠቃሚ ይሆናል በማለት ነው።  የኮሜርሻል ዩኒቨርሲቲው ለሚፈጠረው የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ዋነኛ ሞተር መሆን ይችላል። ምክንያቱም በትልቅ የዓለም አቀፍ የባንክና የፋይናንስ ቦታዎች ውስጥ ትልልቆቹ የፋይናንስና የኢንቨስትመንት ዩኒቨርሲቲዎች አሉና። በለንደን፣ኒዮርክ፣ፍራንክፈርት፣ፓሪስ፣ጄኔቫ፣ቶኪዮ፣ ሆንክ ኮንግን መጥቀስ ይችላል።

ውዶቹ የፋይናንስ፣ የቢዝነስ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ትምህርቶች በቅርብ ገበያ ያላቸው ወደ ባንኮች የቀረቡና ለባንኮቹ የሚጠቅም ኮርሶች ስለሚቀርፁ፣ ምርምር ስለሚያደርጉ፣ ሴሚናር ስለሚያዘጋጁ፣ የምርምር ውጤት ስለሚያሳትሙ፣ ሥልጠና ስለሚሰጡ፣ ስለሚያማክሩ፣ ችግር ስለሚፈቱ ነው። ባንኮች ደግሞ ገንዘብ ስላላቸው ሩቅ ሳይሄዱ ትልቅ ቤተ መጽሐፍት፣ የዳታ ሴንተር፣ ኮንፍረንስ ማዘጋጃ፣ ሥልጠና መስጪያ፣ ምርምር ማድረጊያ ተቋም ይፈልጋሉ። ሞቅ ያለ ብርም ይከፍላሉ።

ባንክ ሕንፃና ከረባት ያሰረ ሰው ገብቶ ቢደረደር በዕውቀትና በምርምር የሚያግዘው ተቋም ከሌለ አያድግም። ባንክ በጭንቅላት፣ በዕውቀትና በዓለም አቀፋዊ ገበያ ተፎካካሪ ሆኖ መገኘት የሚጠይቅ የኢኮኖሚ ክፍል ነው። ተጀምሮ እስኪጨረስ የዕውቀት ሥራ ነው።

ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች ብቻ ሳይሆን፣ የባንክ ኤክስፐርቶች ባለሙያዎች (Practitioners) ሄደው ልክ ቸር የሚሰጡበት፣ የምረቃ ተማሪዎችን የሚያማክሩበት ተመጋጋቢ ተቋም ነው። ታዲያ ለኮሜርሻል ስኩል ከዚህ የበለጠ ዕድል ይመጣል። ለአንድ ሰዓት አንድ የባንክ ሪስክ ማናጀር ወይም ኢንተርኔት ሴኪዩሪቲ ኤክስፐርት የሚሰጠው ሴሚናር አንድ ሴሚስተር አንድ ፕሮፌሰር ከሚሰጠው ትምህርት በላይ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ታዲያ ከዕውቀት የራቀ ረጃጅም ሕንፃ ቢገነባ ለዚህ ተግባር የሚሠማራ ዕውቀት ያለው ሰው ካልተፈጠረ ሕንፃው ምን ጥቅም ይፈጥራል? ለከተማ ሰው አረንጓዴ ሜዳ፣ አረንጓዴ ማረፊያ ፓርክ ሲያስደምመው ከባላገር ለመጣ ደግሞ አረንጓዴ ሳር ሳይሆን የመስታወት ፎቅ ያስደምመዋል። ይኼንን ማስታረቅ ለጊዜው አይቻልም። ስለዚህ ኮሜርስ አይፍረስ። ይሁንና ባለው በትርፍ ቦታ ደግሞ ለከንቲባዎቹ ዓይን ማረፊያ የሚሆን ባለ 20 ደርጃ ፎቅ ይገንባና ትልቁን የፋይናንስና የኢንቨስትመንት ባንከሮችን የሚሠለጥኑበት ዩኒቨርሲቲ ይደረግ።

ይህ ያስታርቃል። ኮሜርስ የእርሻ ኮሌጅ አይደል ባንክ አቋቁሞ የፋይናንስ ኮሌጅ መዝጋት በታሪክ መሳቅያ ያደርጋልና። ኮሜርስ እንዳይፈርስ፣ እንዲያውም ትልቅ ቀን ይውጣለት እላለሁ። ሌላው አደጋ ከንቲባዎቹ ሊረዱ ያልቻሉት (Risk) አለ። ሁሉን ባንክ አንድ ቦታ መሰንሰን የኢትዮጵያ ፋይናንስን ወደ አደጋ ይከተዋል። እሳት ቢነሳ፣ ቴረሪዝም ቢመጣ የኢትዮጵያ ባንክ ሥርዓት አደጋ ላይ ይወድቃል።

እኔ ለመኪና አምራች ፋብሪካዎች ሠርቻለሁ። መኪና የሚያመርቱ ፋብሪካዎች እንኳን የመኪናቸውን ዕቃ አንድ ፋብሪካ፣ አንድ አገር፣ እንዲመረት አይፈቅዱም። አንድ አገር ቢረበሽ ፋብሪካ ቢቃጠል በአንድ ብሎን መጉደል ብቻ ፋብሪካ እንደሚቆም ስለሚገምቱ  ሁሌም ቢያንስ ሁለት አምራች፣ ሁለት አገር፣ ኮንትራት ይሰጣሉ። 

የእዚህ ጥቅም ደግሞ የታየው በጃፓን ፏኮሽማ ኒውክለር አደጋ ጊዜ ነው። በጃፓን ሁሉም ፋብሪካዎች ሲዘጉ ኢሮፕ፣ አሜሪካና ኤሽያ  ያሉ የቶዮታ፣ የሆንዳ፣ የኒሳን ፋብሪካዎች ወዲያው ነው ምርት የጨመሩት።

ፎቅ አንድ መንደር ሲደረደር ደስ ይል ይሆናል ግን የአገሪቷን ባንኮች ለአንድ ሰደድ እሳት ማጋለጥ ደግሞ አይመከርም። ኢንሹራንስ ካንፓኒ እንኳን ኢንሹራንስ ሲሰጥ አንዱን ሕንፃ ብቻ ሳይሆን፣ ይህ ሕንፃ ከአጠገቡ ካሉ ሕንፃዎች በምን ያህል ይርቃል ብሎ ያጠናል።  ያኛው ሕንፃ እሳት ከያዘ የሚቀጥለው መንደዱ አይቀርምና። ትልልቅ መሰላልና ሄሌኮፕተር የሌለው የእሳት አደጋ መከላከያ ይዘን ፎቅን በአንድ ሠፈር መደርደር አይመከርም።

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢንቨስትመንት አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles