Wednesday, March 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ​​​​​​​ፍጥነት የሚጠይቀው የቀበሌ ቤቶች ዕድሳት

​​​​​​​ፍጥነት የሚጠይቀው የቀበሌ ቤቶች ዕድሳት

ቀን:

ከፍራሻቸው ላይ እግራቸውን ዘርግተው ቁጭ ብለዋል፡፡ እርጅና የተጫጫናቸው አረጋውያንም በየፊናቸው ተቀምጠዋል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ የልጆቻቸውን ጉርስ ለመሙላት ደፋ ቀና ሲሉ ይታያሉ፡፡

ከዚህ ቀደም ይኖሩበት ከነበረው ቤት ወጥተው ለጊዜው ያረፉበት ትምህርት ቤት ለኑሮ እንደቀደመው አልተመቻቸውም፡፡ ምንም እንኳን ባረጀ ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበረ ቢሆንም፣ ከለመዱት ሥፍራ ለጊዜውም ቢሆን መውጣታቸው እንደከበዳቸው የሚገልጹ አሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በክረምት የበጎ ፈቃድ መርሐ ግብር ከዚህ ቀደም ይኖሩበት የነበረውን የመኖሪያ ቤታቸውን ለማደስ ቀን መቁረጡን  ተከትሎ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የቤት ዕድሳት ከሚደረግላቸው መካከል ትልቅ ችግር ውስጥ ገብተናል የሚሉት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ቀጣና ሁለት አካባቢ በቀበሌ ቤት ውስጥ ኑሯቸውን ያደረጉት ወ/ሮ ማርታ ደረጀ ናቸው፡፡ ወ/ሮ ማርታ የአንድ ልጅ እናት ሲሆኑ፣ ከአባታቸው፣ ከወንድምና ከእህቶቻቸው ጋር በቀበሌ ቤት ውስጥ አብረው ይኖሩ ነበር፡፡

አሁን እየኖሩ ካሉት የኑሮ ሁኔታ አነፃር ከዚህ ቀደም ይኖሩበት የነበረው ቤት አመቺ እንደነበር የገለጹት ወ/ሮ ማርታ፣ በአሁኑ ወቅት ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን በአስፋ ወሰን ትምህርት ቤት ውስጥ ለጊዜው እየኖሩ ነው፡፡

 ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ በተለይም የመሬት ወለሉ ከፍተኛ ቅዝቃዜ ስላለው እንደተቸገሩ ይናገራሉ፡፡ የማዕድ ቤት ባለመኖሩ ምክንያት አብስሎ ለመብላት እንደተቸገሩ አብዛኛዎቹ አባዎራዎች በዚያው አካባቢ ላይ የሚኖሩ ነዋሪዎችን አስቸግረው እንደሚጠቀሙ፣ የሌላቸው ደግሞ እንጀራ ገዝተው እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ በትምህርት ቤቱ ውስጥ በአጠቃላይ 25 አባዎራዎች እንደሚገኙ፣ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ ብቻ እስከ አሥር ሰዎች እንደሚገኙና ይኼም ኑሯቸው ላይ ጫና እንደፈጠረ ይናገራሉ፡፡

የከተማ አስተዳደሩም በፊት ይኖሩበት የነበረውን ቤት በአንድ ወር ከአሥራ አምስት ቀን ጊዜ ውስጥ ጨርሶ እንደሚያስረክባቸው ቃል እንደገባላቸው የሚናገሩት ወ/ሮ ማርታ፣ እንዳልተፈጸመና ዕድሳቱም ሳይጀመር አንድ ወር እንደሞላው አብራርተዋል፡፡

አሁን የሚኖሩበት ትምህርት ቤት አቅመ ደካማ ለሆኑ አረጋውያን ሆነ ለሕፃናት አመቺ እንዳልሆነ ይኼም ትልቅ ተፅዕኖ እንደፈረባቸው ገልጸዋል፡፡ የዕድሳት ሁኔታ በተመለከተ የሚመለከተው አካል ለማናገር ጥረት ማድረጋቸውን ነገር ግን ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡

በተለይም ዕድሳቱ ይጀመራል ተብሎ ቤቶች ፈርሰው ወደ ትምህርት ቤት ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ምን ሁኔታ ላይ ናቸው ብሎ አንድም የሚመለከታቸው አካል አለመምጣቱ ችግር እንደሆነባቸው አስታውሰዋል፡፡

ሌላኛዋ ነዋሪ ወ/ሮ ወርቅነሽ ንጋኔ እንደለገለጹት፣ በአንድ ክፍል ውስጥ ዘጠኝ አባወራዎች እንደሚገኙና ያሉበት ሁኔታም ፈተና የበዛበት መሆኑን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡ በእርግጥ የከተማ አስተዳደሩ ቤቶችን እንደ አዲስ ለመገንባት የጀመረው ጅማሮ መልካም የሚባል ቢሆንም፣ የት ገባችሁ የሚላቸው ሰው ማጣታቸው ግን በኑሯቸው ላይ ተፅዕኖ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

ያሉበት ሁኔታም የዕለት ጉርሳቸውን ለመሙላት ልጆቻቸውን ለማሳደግ አመቺ አለመሆኑን በተለይም ምግብ ማብሰያ ቦታ ባለመኖሩ መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

እንጀራ በመጋገር፣ ልብስ በማጠብና ሌሎች ሥራዎችን በመሥራት ኑሯቸውን እየገፉ የሚኖሩ ሰዎችም እጃቸውን አጣጥፈው ቁጭ ማለታቸውን ሪፖርተር  ቦታው ላይ ተገኝቶ ማየት ችሏል፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ቁጠባ ሠፈር አካባቢ ኑሯቸውን ያደረጉት አቶ የሱፍ ሱሌማን በአካባቢው ላይ መኖር ከጀመሩ 42 ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ አቶ የሱፍ የአምስት ልጆች አባት ሲሆኑ፣ ልጆቻቸውን ለማሳደግ ልብስ በመስፋት እንደሚተዳደሩ ገልጸዋል፡፡

ከባድ ዝናብ ሲኖር ፍሳሽ እንደሚያስቸግራቸው፣ ይኼም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት የአብዛኛዎቹ ቤት የደከሙና ረዥም ጊዜ ያገለገሉ በመሆናቸው ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ለ18 አባዎራዎች መጠቀሚያ ሆኖ እንዲያገለግል የተገነባው የመፀዳጃ ቤትም የአካባቢ ነዋሪ በሙላ እንደሚጠቀምበትና ቶሎ ቶሎ እንደሚሞላ በዚህም የተነሳ ልጆቻቸውም ሆነ እሳቸው ለተለያዩ በሽታዎች እንደተጋለጡ ይናገራሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም አብዛኛውን ቤቶች ደካማ የሚባሉ በመሆናቸው መንግሥት ዕድሳት ሊያደርግ መሆኑን በሰሙ ወቅት ደስታ እንደተሰማቸው የሚናገሩት አቶ የሱፍ፣ መንግሥት ያሉትን ችግሮች ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ አጥርቶና ቤቶቹን አድሶ የነዋሪውን መልስ ለነዋሪው ጥያቄ ምላሽ መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ሌላኛዋ ነዋሪ ወ/ሮ ዘምዘም የሱፍ በአካባቢው ላይ መኖር ከጀመሩ ከ30 ዓመታት በላይ አስቆጥረዋል፡፡ ወ/ሮ ዘምዘም ከእናትና ከወንድማቸው ከልጅ ልጆች ጋር ተደምሮ 13 ሆነው አንድ ቤት ውስጥ ባጠቃላይም ይኖሩ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

ከእናቷ ጋር በመሆን እንጀራ እየጋገሩ ለተለያዩ ሆቴል ቤቶች ያቀርቡ እንደነበር አሁን ላይ ግን መቸገራቸውን ይናገራሉ፡፡

ቤቶችን ላድስ ነው ሲል ግራ እንደገባቸው ለሪፖርተር የገለጹት ወ/ሮ ዘምዘም በአሁኑ ወቅት በተከሰተው ችግር ምክንያት ቤታቸው ለዕድሳት በመፍረሱ ምክንያት ከደንበኞች ጋር እንደተለያዩ ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ያሉብንን ችግሮች ተረድቶ ቤቶቻችንን ለማደስ ቅድመ ዝግጅቱን ቢያጠናቅቅም መጀመርያ የነዋሪውን ችግር ተረድቶ ምቹ ሁኔታ አለማመቻቸቱ ኑሮን አክብዶብናል ይላሉ፡፡

የዕድሳቱም ሁኔታ መቼ ተጀምሮ መቼ እንደሚያልቅ የሚታወቅ ነገር ስለሌለ ሁሉም የአካባቢ ነዋሪ ላይ ጥያቄ እንዳጫረ አስረድተዋል፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የወረዳ ስምንት ምክትል ሥራ አስፈጻሚና የቤቶች አስተዳደር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሰኒያ አብደላ መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአካባቢው የሚኖሩ ነዋሪዎች ባላቸው ቤት ልክ ዕድሳቱ ይከናወናል፡፡ ለዚህም ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ ነው፡፡

አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎችም ባልታሰበ ጊዜ ዕድሳቱ መፈጸሙ ቅሬታ እንዳላቸው የገለጹት ወ/ሮ ሲኒያ፣ ዕድሳቱ ተጠናቆ እስኪያልቅም አካባቢው ላይ በሚገኝ የመንግሥት ትምህርት ቤት እንዲቆዩ ተደርጓል ብለዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩም የቤቶችን ዕድሳት በአፋጣኝ በማደስና በፊት ከነበሩበት ሕይወት የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ለማድረግ የተጀመረው ጅማሮ የሚበረታታ እንጂ የሚያስወቅስ እንዳልሆነ ወ/ሮ ሰኒያ ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሄዶ እንደቃኘው አብዛኛው ነዋሪዎች የቤቶቹ ዕድሳት መቼ ተጀምሮ መቼ እንደሚያልቅ መረጃ የላቸውም፡፡

የክረምት በጎ ፈቃድም ተከትሎም የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ ግብርና ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮና ሌሎች ተቋሞችም በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የሚገኙ ዜጎችን ቤቶቻቸውን በማደስ በጎ ተግባር እያከናወኑ ይገኛል፡፡ ከዚህ በፊትም የክርስትናና የእስልምና ዕምነት ተከታዮች በተመሳሳይ መልኩ የክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብሩን በገንዘብ ለማገዝ ቃል መግባታቸው ይታወሳል፡፡

ሰኔ 18 ቀን 2013 ዓ.ም. የተጀመረው የክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር ‹‹በጎ ፈቃደኝነት ለመደገፍና ለመግባባት›› በሚል መሪ ቃል እስከ መስከረም 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ሲሆን፣ የክረምት ወቅት የአቅመ ደካሞችን ቤት ማደስም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መጀመሩ ይታወሳል፡፡

የ2013 ዓ.ም. የክረምት በጎ ፈቃድ መርሐ ግብር እየተከናወነ ሲሆን፣ በዚህም ከ2,000 በላይ የአቅመ ደካማ ቤቶች ዕድሳት፣ የትራፊክ ማስተግበሪያና በሌሎች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሁለት ሚሊዮን ወጣቶችና በጎ ፈቃደኞች መሳተፋቸውን ሪፖርተር ከዚህ ቀደም ዘግቦታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...

አወዛጋቢነቱ የቀጠለው የአዲስ አበባ የጤፍ ገበያ

ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጤፍ የተከሰተውን የዋጋ ንረት...