በገለታ ገብረ ወልድ
ሕወሓት መራሹ የትግራይ ኃይል በትግራይ ክልል ከተደበቀበት የስምንት ወራት ደፈጣ ወጥቶ ማጥቃት ያለውን ዕርምጃ ጀምሯል፡፡ ይህንንም ድንበርተኛ በሆኑት በአማራ ክልል ሰሜንና ምዕራብ አካባቢዎች፣ እንዲሁም በአፋር ክልል ላይ አጠናክሮ መጀመሩን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት፡፡ በዚህም ባለፉት 15 ቀናት በርካታ ዜጎች የተሰው መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፣ ንፁኃን ዜጎች ጭምር ለከፋ ጉዳት መጋለጣቸውን በአፋር ክልል የተፈጸመውን ጭፍጨፋ በማጣቀስ የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
ቀደም ሲል ‹‹ተዳክሟል… ተደምስሷል…›› እየተባለ በመንግሥት አካላት ሲገለጽ የነበረው የሕወሓት ኃይል በአብዛኛው የትግራይ ሕፃናትንና ታዳጊዎችን በማስታጠቅ የጀመረውን ዘመቻ ለመመከት መንግሥት ሕዝቡን ተነስ ያለ ሲሆን፣ በተለይ የአማራ ክልል የክተት አዋጅ እስከ ማውጣት ደርሷል፡፡ ግጭቱ ጋብ ከማለት ይልቅ በመባባሱም መንግሥት በተናጠል ያደረገውን የተኩስ አቁም ዕፎይታ ቀልብሶ የህልውና ዘመቻ በመጀመር፣ የክተቱ አዋጁ በራሱ በሕወሓት ታጣቂ ላይ መዓት እያወረደበት መሆኑ አዲስ ክስተት ፈጥሯል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት ቃል አቀባይ አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ሰሞኑን፣ ‹‹ኢትዮጵያን ለማጥፋት የክህደት ክንዱን ያነሳው አሸባሪው ቡድን በአሁኑ ሰዓት በከፈተብን ወረራና ጦርነት ቀዳሚውን ጡንቻ ያሳረፈው የአማራ ሕዝብ ላይ ሲሆን፣ ሕዝባችንን በማጥፋት ካልሆነ በስተቀር እረፍት እንደማያገኝ በመናገርና በተግባርም በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ላይ እያደረገው ይገኛል፤›› ማለታቸው ድርጊቱ ወደ ከፋ የበቀል መንፈስና ደም የመቃባት አዙሪት እየገባ ስለመሄዱ አመላካች ነው፡፡
እንደ ኃላፊው ማብራሪያ ሕዝባችንን ለመከፋፈል እየሠራ ያለው ሕወሓት የያዘው አስተሳሰብ አገር አፍራሽ ነው፡፡ አሁን በተግባር እንደታየውም አርሶ አደሩን ከግብርና ሥራ አፈናቅሏል፣ ሴቶችን ባሎቻቸው ፊት ደፍሯል፣ ወጣቶችን ገድሏል፣ የመንግሥትን፣ የሕዝብንና የግለሰቦችን ሀብት እየዘረፈ ይገኛል። የአማራን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ለማዋረድም አሳፋሪ ነውር ፈጽሟል፡፡ ይህ ድርጊቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ በጁንታው ላይ ይበልጥ እንዲጨክንበት የሚያደርግ ነው፡፡
‹‹የአማራ ሕዝብ ደግሞ ከሚያዋርደውና ኢትዮጵያን ለማጥፋት ከሚሠራ አሸባሪ ጋር ኅብረት የለኝም ብሎ ከጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከልዩ ኃይሎች፣ ከአማራ ልዩ ኃይል፣ ፋኖና ሚሊሻ ጋር ተሠልፎ አሸባሪውን አይቀጡ ቅጣት እየቀጣው ይገኛል፤›› ያሉት ቃል አቀባዩ፣ ‹‹እንደተናገርነው የአማራ መሬት ለአሸባሪው ቡድን እሾህ መሆን ጀምሯል›› ማለታቸው ደግሞ፣ ሕወሓት እየገፋፋ ወደ ጦርነት እየማገዳቸው ያሉ የትግራይ ወጣቶችን ለዕልቂት እየዳረገ መሆኑን አመላካች ነው።
ማንም አጥቂ ሆነ ተከላካይ ሕወሓት የጀመረው የጦርነት መንገድ አገርን ወደ ብተና አነስ ቢልም ወደ አዘቅት እያስገባ በመሆኑ መወገዝ አለበት የሚባለው ከዚህ ተጨባጭ እውነታ አንፃር ነው፡፡ እውነት ለመናገር አሁን በሕወሓት የሚመራውን ጽንፈኛ ኃይል በርታ የሚለው ኖሮ ነው እንዴ ይኼ ሁሉ ሕዝብ የማስፈጀት ድርጊት እየተፈጸመ ያለው ያስብላል፡፡
ሕወሓት እኮ ባለፉት 27 ዓመታት አገር የመራ፣ ለሦስት ዓመታትም ከበርካታ ጥፋቶቹ ጋር የትግራይ ክልልንም ያስተዳዳረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በተካረረ የፖለቲካ አስተሳሰብ የተፈጠሩ ልዩነቶችን በውይይትና በመደማመጥ ከመፍታት ይልቅ፣ ወደ ኃይልና ጦርነት እስከ ወሰደው ጊዜ ድረስም ዳግም ሕዝብን የሚያስተላልቅና አገርን ለባዕዳን ጠላቶች እስከ ማጋለጥ የሚደርስ ዕርምጃ ውስጥ ይገባል ብለው የገመቱ ብዙ አልነበሩም፡፡ ይህም የጥፋቱ ብዛት ማሳያ ነው፡፡
የማይካደው እውነት ግን በሕወሓት የአገዛዝ የታሪክ ምዕራፎች ወቅትም ቢሆን የሕዝብን አብሮነትና አንድነት ማፈላቀቁ፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄዱ መበርታቱና የዘረፋና ኢፍትሐዊነት መንገዱ ሕዝብ ሲያስቆጣ መቆየቱ የሚዘነጋ አልነበረም፡፡ በተለይ የአገራችን ሕዝቦች ዋነኛ መገለጫ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ አለፍ ሲልም በመንደር መፈላለግና መናቆር ላይ እንዲያውጠነጥን ያደረገው የሕወሓት አስተሳሰብ ነው የሚለው ዕይታ እንደነበር ለምን ሊዘነጋ ቻለ?
በአብዛኛው በጥላቻና በተቃርኖ የተሞላው አስተሳሳብ፣ በፖለቲካ እምነታቸው ብቻ ሳይሆን በማንነታቸው ብሔረሰቦች እንዲናቆሩ እስከ ማድረግ ለመድረሱ ያሳለፍናቸው ሦስት ዓመታት አመላካች ነበሩ፡፡ ሕወሓት በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜም በፖለቲካ አደረጃጃት፣ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ወይም በማኅበራዊ ጉዳዮች የዘር መፈላላጉና መጎነታተሉ ሌላ ጣጣ እናዳያመጣ የሚሰጉ ብዙዎች ነበሩ፡፡
የተፈራው ደርሶ እንደ ሕዝብ ከመተባባርና አንድነትን ከማጠናከር ይልቅ ስንጠላለፍና አንዱ ሌላውን ሲያሳድድ፣ በተዘዋዋሪ በርታ የሚለው ከትናንት እስከ ዛሬ ሕወሓት መሆኑ ሲታይ ነው የዚህ ፅንፈኛ ኃይል አስተሳሳብ እሲኪከስም ድረስ ብርቱ ትግል ሊደረግበት ግድ የሆነው፡፡ ይሁንና ትግሉ በሠለጠነው የፖለቲካ መድረክና በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሊደረግ ሲገባው፣ በዋናነት በሕወሓት ኃይሎች ግትርነት ወደ ጦርነትና መበላላት መገባቱ እጅግ የሚያሳዝን ክስተት ሆኗል፡፡ ፈጥኖ መፍትሔ ካላገኘ ወይም ጁንታው ፈጥኖ ወደ ሕግ ካልቀረበ ጉዳቱ የሁሉንም በር ማንኳኳቱ አይቀርም፡፡
የሕወሓት አገዛዝ ለከፋፍለህ ግዛው ውስጣዊ ሥልቱ ተፈጸሚነት መለያያትና መብላላትን ረዥም ጊዜ መከተሉ፣ በተለይ የትግራይ ሕዝብን ለመጉዳቱ የትናንቱ ብቻ ሳይሆን የዛሬው ነባራዊው ሀቅ ቁልጭ አድርጎ ያሰያል፡፡ ዛሬ የትግራይ ክልል ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች በበሳ ደረጃ በጦርነት ተጎድቷል፡፡ ልጆቹን ለእሳት እየማገደና ከሌሎች ሕዝቦች ጋር እያዳማ ነው፡፡ እንኳን ምግብ፣ አልባሳት፣ መብራት፣ ውኃና ስልክ የናፈቀው አካባቢና ተረጂ ቀጣና መሆንም በዚሁ ሴረና ኃይል መዘዝ ነው፡፡
የሕወሓት የፖለቲካ ኃይል ከስግብግብ የሥልጣን ፍላጎቱ ይልቅ የሕዝቡ ደኅንነት ቢያሳስበው ኖሮ፣ ይህን ሁሉ አላስፈላጊ ኪሳራ በወገኖቹ ላይ ባልጫነ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ጦርነቱን ከመጫሩ በፊት በፕሮፓጋንዳ ብሽሽቅና በልዩ ልዩ ሴራዎች ባለፉት ሦስት የለውጥ ዓመታት በየአካባቢው ዜጎችን በዘራቸው አፋጅቷል መባሉ፣ የአገሪቱን ሀብት ማባከኑና ዘረፈ መባሉ አንሶት፣ በየአካባቢው በሚልካቸው አተራማሾች የሕዝብ ሀብት እያስወደመ እንደሆነ መከሰሱ ብዙ ጥላቻን እንዳተረፈለት ለምን እንደዘነጋው ግራ አጋቢ ነው፡፡
ትናንትም ሆነ ዛሬ በርከት ባሉት ኢትዮጵያዊያን ሥነ ልቦና ውስጥ ባንዳውና ፀረ አንድነቱ ሕወሓት ዜጎች በአንድ የጋራ ሰንደቅ ሥር እንዲሰባሰቡ ከማድረግ ይልቅ፣ የአንድነት የጋራ ምልክት እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡ በአናሳ ትከሻው ብዙኃኑን እየነጣጣለ ለመምታትና ለመብላት ሰፊ መለያየትን ፈጽሟል፡፡ ይህ ሁሉ ድርጊት ደግሞ አላወቀውም እንጂ ራሱ የትግራይ ሕዝብንም ቢሆን ከሌላው ጋር በሰላም እንዳይኖር የሚገፋ ነውር ድርጊት ነበር፡፡
እነሆ ዛሬ ቀኑ ደርሶ ወደ ለመደው ጦርነትና ጥፋት ሲገባም፣ በአገር ደረጃ ከዚያም ከዚህም የተሰባሰበና የተባባረ ተዋጊ እንደሚያበዛበትስ ለምን ካደው ማለት ይቻላል፡፡ ዛሬ የሕወሓት ኃይል እየተለበለበ ያለው ‹‹በታትኜዋለሁ›› በሚለው ሕዝብ የጋራ ክንድ መሆኑ ሲታይም የተሳሳተውን ሥሌቱን አጉልቶ ያሳያል (እዚህ ላይ በክተት አዋጁም ሆነ በሕዝቡ ከዳር ዳር ተነስቶ በጁንታ ላይ መዝመት ሕወሓት ክፉኛ መደናገጡን ሰሞኑን የቃል አቀባዩ ጌታቸው ረዳ እዚያና እዚህ የረገጠ ማብራሪያ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል!!)፡፡
ወደ ነጥቤ ስመለስ የጦርነቱን ክስ እንኳን ለጊዜው ወደ ጎን ብንል፣ ገና ከመነሻው በኢትዮጵያ አሁን ያለው ፌደራላዊ ሥርዓት በልዩነት ውስጥ ጠንካራ አንድነት እንደሚፈጥር የተጣለበትን ተስፋ ያጨለመው ወያኔ ነበር የሚለው ዕሳቤ እንዴት ይካዳል? የአስተዳዳር ክልል ከአወሳሰኑ ጀምሮ በዋናነት ብሔር ላይ ብቻ እንዲያተኩር፣ የሁሉም ክልሎች አከፋፈል ወጥ የሆነ መሥፈርት እንዳይከተል፣ የፈለገውን ሰፊ መሬት ወደ ራሱ ክልል ወስዶ፣ አወዛጋቢ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች እንዲንሰራፉ በማድረግ ፈንጂ ሲቀብር የኖረው ሕዝብ እያባላ ለዘመናት ለመግዛት ነበር የሚሉትን ከሳሾችንስ እንዴት አድርጎ በጦርነት ሊያሳምን ይችላልና ነው እሳት የለኮሰው ያስብላል፡፡
ሕወሓት አገር በመራባቸው ዓመታት ተቀናቃኝ ያላቸውን እያሳደደና መግቢያ መውጫ እያሳጣ፣ የዓላማ ተጋሪዎቹን ብቻ ሳይሆን፣ ዘር ማንዘሩን ጭምር ግልጽነት በሌለው መንገድና በኢፍትሐዊነት ሲያበለፅግ በገሃድ መታየቱ የሚያስቆጨው ሕዝብ አልነበረም ብሎ ያስብ ይሆን? በዚህ መዘዝ የአገሪቱን ወጣት ኃይል የበይ ተመልካች ማድረጉ ሳያንሰው እኔ ብቻ ባይነትን ዋነኛ ጠባይ ብሎም በጎጥ አስተሳሰብ ማዶና ማዶ ሆኖ መተጋተግን ልማድ እንዲያደርጉ ሲጎነጉን የኖረው የጥፋት ጊዜውን ለማራዘም መሆኑ ዛሬ ለወረራ ሲነሳ የሚጨክንብት እንዴት ይጠፋል?
በተቃራኒው ደግሞ አሁን የተረጋጋ ሁኔታ ባይገጥመውም ወደ ሥልጣን የመጣው ኃይል የሕዝቡን መናቆርና መለያየት ቀስ በቀስ በመቀነስ የአገር አንድነትን ለማምጣት መሞከሩ፣ የሕዝቡን በጋራ መነሳት አበረታቶታል ቢባል ምን ስህተት ይኖረዋል? በዚያ ላይ ተጀማምረው የነበሩ የልማት ሥራዎችና የኢኮኖሚ ለውጥ ዕርምጃዎች፣ ቀደም ሲል ሕወሓት በሌላው ኪሳራ የራሴ ለሚለው አካባቢ የመሠረተ ልማትና የማኅበረ ኢኮኖሚ ኢፍትሐዊ ዕርምጃ ማድረጉን በምን አስተባበለው? ቁጣ ከመቀስቀስ ባሻገር፡፡
የሕወሓት ጁንታ ለውጥ መጥቶ በሕዝባዊ ማዕበል ሲጠርገው፣ በአንድ በኩል በኖረበት ሴራ አገር እያተራመሰ (አሁን በግልጽ ተቀናጀን ከሚላቸው እንደ ኦነግ ሸኔ ካሉ አሸባሪዎች ጋር)፣ በሌላ በኩል ተላላኪዎቹ የሆኑትና በተንኮልና በበሰበሰ ሴራ የተካኑ ብሎም፣ የቂም በቀልና የጥፋት ፖለቲካ ምንደኞችን ሲጠፈጥፍ ነበር የከረመው። ይህ የጥፋት ትብብርም ቢሆን በሕዝቡ ይወደዳል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ነባራዊ ሁኔታውን ያልገመገመ የኪሳራ አስተሳሳብ ነው ማለትም ይቻላል፡፡
እንግዲህ እነዚህና ሌሎች በርካታ ጭብጦች ሲመረመሩ ነው የትግራይ ሕዝብ እስከ መቼ ነው በእንዲህ ያለው የተሳሳተ አስተሳሳብ እየተመራ ለከፋ ጉዳት ሲጋለጥ የሚኖረው የሚያስብለው፡፡ ለዚህም ማሳያው ጁንታው አገርንና መንግሥትን ለማፍረስ ሲደነፋ አንድም ተጋሩ ተው ማለት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ አብዛኛው ፈለገም አልፈለገም የድርጊቱ ተባባሪ እንዲሆን መደረጉን፣ አንዳንዱ የትግራይ ልሂቅ ተብዬም አብሮ ሲያራግብ ከርሞ አሁን ሕወሓት በፈጸመው ወንጀል ሲመታና ባነሳው ነፍጥ ሲጠየቅ አብሮ ሙሾ ከማውረድ አልፎ መልሶ አገር እየወጋ መሆኑ ነው።
በዚህም ይባል በዚያ የትግራይ ሕዝብ እንዲህ ያሉ የጥፋት ኃይሎችን ተሸክሞ አገር ከማፍረስ ድርጊት እንዲቆጠቡ ማድረግ ካልቻለ፣ ቀዳሚው ተጎጂ ራሱ ነው። ራሱ በመሥራችነት የሚጠቀስባትን አገር ከማዳከም፣ ለሰላም፣ ለልማት፣ ለአብሮነትና ለዴሞክራሲ አስተዋፅኦ ማድረግም ነበር የሚበጀው። የራሱ አብራክ ክፋዮችን ላልተገባ ዓለማ እየማገደ የት ሊደርስ ይችላል የሚለው ነጥብ ወደ ሁሉም የአገራችን ዜጎች አዕምሮ መምጣት አለበት፡፡
የሕወሓት አስተሳሰብ ቅሪቶችና በትግራይ ሕዝብ ስም የሚነግዱ ባንዳዎች ዛሬም ‹‹ኢትዮጵያዊ አይደለንም፣ ሱዳን ትበልጥብናለች፣ የምንሻው መገንጠልና ትግራዋይ መሆን ነው፤›› እያሉ በሕዝቡ ላይ እየፈረዱበት ቆይተዋል። ይህ አልበቃ ብሏቸው በአካባቢውና በክልሉ ሁሉ ‹‹ተው›› ባይ የሌለ ይመስል ሕወሓትና በውስጡ ፈርጥሞ የነበረው ጁንታ ብሔራዊውን ጦር ወግተውና ንፁኃንን ፈጅተው፣ የለኮሱትን ጦርነት ክደው፣ መንግሥት ከመሬት ተነስቶ እንደ ወጋቸው እያስመሰሉና ሕዝቡን ወደ የማያባራ ደም መቃባት በመክተት ላይ መሆናቸው ሊያሳስበን የሚገባው ሁላችንንም ነው።
እጅግ አሳፋሪና ነውረኛ በሆነ የወረራ ድርጊትና በኃይል ሥልጣን እንይዛለን ወይም ሕዝቡን እረግጠን እንገዛለን ብሎ ማሰብስ ምን የሚሉት ዕብደት ሆኖ ነው በትግራይ ሕዝብ የሚነገዱበት እነ ጌታቸው ረዳ ‹‹እኛ ያልመራናትና ያልፋነንባት አገር ትበታተን›› ብለው አገር እያተራመሱ ያሉት፣ ወጣቱን ከዕድሜው ጭምር በአጉል ዕብሪትና ቡራ ከረዩ እየነዱ ወደ አማራና አፋር ክልል በማስገባት ለመውረር መሆኑ በግላጭ ታይቷል፡፡
የሚያሳዝነው ግን የትግራይ ወጣትና ሕፃናት ሳይቀሩ ክፉኛ እየተመቱ መሆኑን ስንመለከት ነው፡፡ ለሰላም የተዘረጋን እጅ እረግጦ መጥቷልና ደሙ ደመከልብ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከሕዝቡና ከሚሊሻው ጋር ጭምር በሚካሄደው ውጊያ ደም እየተቃባ በመሆኑ ነው። አሁንም ቢሆን መላው የአገራችን ሕዝብ በአንድ ላይ ቆሞ ሕወሓትን ሲታገል፣ በትግራይ ሕዝብ ስም የሚነግደውን ፅንፈኛ ኃይል ራሳቸው ተጋሩ አንቅረው ተፍተው እንደሚታገሉትና ከብዙኃኑ ወገናቸው ጋር ተሠልፈው እንደሚፋለሙት በመተማመን መሆኑን ግን መጠራጠር አይገባም።
ሲጠቃለል በጫናም ሆነ በተራ ሥጋት ከሕወሓት ፅንፈኛና አገር አፍራሽ የትግል ሥልት ወይም አስተሳሰብ ጋር ተቆራኝቼ ልሙት የሚል ግን፣ ራሱን ቆም ብሎ መፈተሸ አለበት፡፡ እኛ ኢትዮጵዊያን ወደድንም ጠላንም በታሪክ፣ በደምና በአጥንት፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ መስተጋብር የተሳሰርን ነን፡፡ ተግባራችን ሊሆን የሚገባው ቢያንስ መረዳዳትና መከባባር ብሎም መደጋጋፍ እንጂ፣ መገዳደልና መጠፋፋት አይደለም፡፡ ስለሆነም ምንም ቢባል ምንም ሕወሓትን የታሪክ ተወቃሽና ተጠያቂ ከማድረግ የማያድነው ጦርነት ማብቃት ወይም መቆም ያለበት እንዳይነሳ አድርጎ በመደምሰስ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡