Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርጋዳፊና አራቱ በጎች

ጋዳፊና አራቱ በጎች

ቀን:

በዕዝራ ኃይለ ማርያም መኮንን

ኮሎኔል ጋዳፊ  በገነኑበት  1974 .ም.  ሌተና  ኮሎኔል  ፍስሐ  ደስታ  የደርግን  ልዑክ  መርተው  ወደ  ሊቢያ  ይጓዛሉ፡፡ ቡድኑም  ከኮሎኔል  ጋዳፊ  ጋር  ቻድ  አጠገብ  ከምትገኝ  ከሰብሃ  ከተማ  ወጣ  በሚል  ምድረ  በዳና  አሸዋማ  ቦታ  በአሮጌ  ድንኳን  ውስጥ  ይገናኛል፡፡  ኮሎኔል  ጋዳፊ፣ የግብፁን  መሪ  አንዋር  ሳዳትን  ‹‹የዓረቡን  ዓለም  ከድቶ  ለፅዮናዊነት  የተምበረከከ  ከሃዲ  ስለሆነ  መወገድ  አለበት፡፡ የሱዳኑ  ጃፋር  አል  ኑሜሪና  የሶማሊያው  ዚያድ  ባሬ  የአሜሪካን  ቡችሎች  ስለሆኑ  በአስቸኳይ  መገልበጥ  አለባቸው፡፡ የሰሜን  የመኑ  አብደላ  ሳለህም  ወላዋይ  በመሆኑ  ደቡብ የመኖች  እሱን  ማስወገድ ይኖርባቸዋል፡፡ የግብፁን መሪ ለማስወገድ ሊቢያ ኃላፊነቱን ትወስዳለች፤›› አሉ፡፡

ኮሎኔል ጋዳፊ እነ ሌተና ኮሎኔል ፍስሐ ደስታን  በሜዴትራንያን  ባህር  ዳር  በሚገኝ  የግል  መዝናኛቸው  ምሳ  ሲጋብዟቸው፣  ሻለቃ  ጃሉድ  አራት  በጎች  አስመጡና ከቡድኑ ፊት አስቆሙ፡፡ የመጀመርያው  በግ  የግብፁ ሳዳት፣ ሁለተኛውና ሦስተኛው  በጎች  አል  ኑሜሪና  ዚያድ  ባሬ ናቸው  ተብለው  ታረዱ፡፡  አራተኛው  በግ  አብደላ ሳለህ ስለሆነ ለጊዜው ይቆይ ተብሎ ከዕርድ ተረፈ፡፡

የኢትዮጵያ ልዑካን ወደ ሆቴላቸው እንደተመለሱ  ኮሎኔል  ጋዳፊ  መኪና  እየነዱ  ወደ  ሆቴሉ  መጡ፡፡  በደስታ  ተውጠው  ‹‹እንኳን  ደስ  ያለን!  ሳዳት ተገደለ!››  አሉ፡፡  የግብፅ  ፕሬዚዳንት  የነበሩት  አንዋር  ሳዳት  የተገደሉት  እ.ኤ.አ.  ጥቅምት  6  ቀን  1981  ሲሆን  በማግሥቱ  ሊቢያ  ቀኑን  ብሔራዊ  የበዓል  ቀን  አደረገች፡፡ መሥሪያ  ቤቶች  ዝግ  ሆኑ፣ መንገዶች የጥሩንባ ድምፅ በሚያሰሙ ተሽከርካሪዎችና በሰዎች ጭፈራና ሆታ ተጨናነቁ፡፡

ይህን ታሪክ  ያገኘሁት  ሌተና  ኮሎኔል  ፍስሐ  ደስታ  አብዮቱና  ትዝታዬ በሚል ርዕስ ከጻፉት ግለ ታሪክ መጽሐፍ ነው፡፡ አንዋር  ሳዳት እ.ኤ.አ. መስከረም 17 ቀን 1978 ከእስራኤሉ  ጠቅላይ  ሚንስትር  ሜንኺም  ቤጊን  ጋር  የካምፕ  ዴቪድ  ስምምነት  ተፈራርመዋል፡፡ ሁለቱም  መሪዎች  1978  የሰላም ኖቤል ሽልማት ተቀብለዋል፡፡  ሁለተኛው  የጋዳፊ  በግ ጃፋር  አል ኑሜሪ  ሲሆኑ  ለሱዳን  አራተኛው  ፕሬዚዳንት  ናቸው፡፡ አሜሪካ በጉብኝት ላይ እያሉ እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 6 ቀን 1985 ኩዴታ ተደረገባቸውና በግብጽ በስደት ኖረው እ.ኤ.አ. በግንቦት 1999 ወደ አገራቸው ተመለሱ፡፡ በሱዳን ኦምዱርማን በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ኖረው እ.ኤ.አ. ግንቦት 30 ቀን 2009 አርፈዋል፡፡ ሜጀር ጄኔራል ዚያድ ባሬ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት የነበሩትን አብድረሺድ ዓሊ ሸርማርኬን  እ.ኤ.አ. ጥቅምት  21 ቀን 1969 በኩዴታ ገድለው ፈላጭ  ቆራጭ  አምባገነን ፕሬዚዳንት ሆኑ፡፡  ታላቋ  ሶማሊያ ቅዠት  ተለክፈው  ከኢትዮጵያ  የኦጋዴን  ግዛት፣  ከኬንያ  የሰሜን  ምሥራቅ  ክፍሏንና  ጂቡቲን  እንዳለ  ወደ  ሶማሊያ  ለማጠቃለል ተነሱ ፡፡

በዘመኑ የኢትዮጵያ ጦር  ከሶማሊያ ጋር ሲነፃፀር በሠራዊት ቁጥርም ሆነ በጦር መሣሪያ ትጥቅ ዝቅተኛ የነበረ  ከመሆኑም  በላይ፣  በኢትዮጵያ  ከአፄ  ኃይለ  ሥላሴ  ሥርዓት  መወገድና  ደርግ  መምጣት  ጋር  በተፈጠረው  የሥርዓት  መጋጠሚያ  ፖለቲካዊ  ግርግር  ነበር፡፡  ሶማሊያ  ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም  በኢትዮጵያ  ድንበር  በምሥራቅ  በኩል 700  ኪሎ  ሜትር  በደቡብ  ደግሞ  300  ኪሎ  ሜትር  ሠራዊቷን  በማስገባት  ወረራ  ፈጸመች፡፡  ደርግም  የኢትዮጵያ  ሕዝብን  በማስተባበር  ባደረገው  መከላከል  በየካቲት  ወር  1970 .ም.  የኢትዮጵያ  ጦር  መልሶ  የማጥቃት  ጦርነት  ከፈተ፡፡  የሶማሊያ  ጦር  በኢትዮጵያ  ጦር  አሳፋሪ  ሽንፈት  ተከናነበ፡፡ ሶማሊያ በደረሰባት  ሽንፈትም  አንድ  ሦስተኛ  ሠራዊቷን፣ ሦስት  ብረት  ለበስ  ክፍሏንና  ግማሽ  የአየር  ኃይሏን  አጥታለች፡፡ የኩባ ወታደሮች በዚያ ክፉ ቀን ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም በጦርነቱ መስዋዕት በመሆን ያደረጉት ተጋድሎ ታሪክ አይዘነጋውም፡፡

ሶማሊያ በደረሰባት ሽንፈት ኢኮኖሚዋ  ክፉኛ ተንኮታኮተ፣ የሕዝቡ  የኑሮ  ደረጃ በማሽቆልቆሉና  የዴሞክራሲ ዕጦት ተጨማምሮ ሕዝቡ ተማሮ በዚያድ ባሬ ላይ አመፀ፡፡ አመፅ መቋቋም ተስኗቸው በጥር 1983 .ም.  ናይሮቢ ኬንያ  ሁለት ሳምንት ቆይተው ወደ ናይጀሪያ ተሰደዱ፡፡ ጄኔራል መሐመድ ፋራህ አልጋውን ያዙ፡፡ ባሬ እ.ኤ.አ. ጥር 26 ቀን 1995 ሌጎስ በልብ ሕመም አርፈው አስከሬናቸው ወደ ሶማሊያ ተመልሶ  በጊዶ  ክልል ጋር ባሪ ወረዳ  ተቀበሩ፡፡  በአገሪቱ  ማዕከላዊ  መንግሥት  ቢኖርም  በአልሸባብ ፅንፈኛ ቡድን ተፅዕኖ የተነሳ ሶማሊያ ከጦርነት አዙሪት አልወጣችም፡፡

ዚያድ  ባሬ  ሞቃዲሾን  ሲለቁ  ሚዛን  ተፈሪ  ነበርኩ፡፡  የኮሎኔል  መንግሥቱ  አልጋ  ተቦርቡሮ  አልቆ  ነበርና  በደቡብ  ምዕራብ  ኢትዮጵያ  (ከፋ፣ ኢሉባቦርና  ወለጋ  አስተዳደር  አካባቢዎች)  አመራሮችን፣ የአገር  ሽማግሌዎችንና  የሁለተኛ  ደረጃ  መምህራንን  ሰብስበው  ስለአገሪቱ  ወቅታዊ  ሁኔታ  ገለጻ  ሲያደርጉ  ተሳታፊ  ነበርኩ፡፡  ወቅቱ  ኢሕአዴግ  አዲስ  አበባን  እየተንጎማለለ  የሚያይበትና  ኮሎኔል  መንግሥቱ  ለማይቀረው  ምፅዓት በምዕራብ  ኢትዮጵያ መሽገው ለመፋለም ቆርጠዋል  እየተባለ  የሚወራበት  ነበር፡፡  በሁለተኛው  ቀን  ኮሎኔል  መንግሥቱ  በንግግራቸው  መሀል  ‹‹ጓዶች!  እንኳን  ደስ  ያላችሁ!  ሰፊው  የሐረርጌ  ሕዝብ  በከፈለው  መስዋዕትነት፣ ሰፊው  የባሌ  ሕዝብ  በከፈለው  መስዋዕትነት፣ ሰፊው  የሲዳማ  ሕዝብ  በከፈለው  መስዋዕትነት  የዚያድ  ባሬ  ጎማ  ተንፍሷል፡፡  በቅርቡ  በእናንተ  በምዕራብ  በኩል  ያለው  የአል በሽር  ጎማ  ይተነፍሳል!››  ሲሉ አዳራሹ በጭብጨባ ተናወጠ፡፡ በሦስት ወራቸው አል በሽር ጎማ ሳይሆን  የእሳቸው  ጎማ  ተንፍሶ ወደ  ሐራሬ  ተሰደዱ፡፡  የሱዳኑ  አል በሽርም  ከኮሎኔል  መንግሥቱ ዛቻ በኋላ 30 ዓመታት ሱዳንን በፈላጭ ቆራጭነት ገዝተው በተነሳባቸው የሕዝብ ተቃውሞ ለስደት እንኳ ሳይበቁ ከርቸሌ ወረዱ፡፡

ጋዳፊ ወላዋይ ያሏቸው አራተኛው የበግ ተምሳሌት የየመኑ ዓሊ አብደላ ሳላህ ሲሆኑ፣ ለሰላሳ ዓመታት ሥልጣን ላይ ቆይተው  በፖለቲካ  ግፊትና  በሕዝባዊ  ዓመፅ  እ.ኤ.አ.  2012  ወደ  ሳዑዲ  ዓረቢያ  ተሰደዋል፡፡  በኢራን  ይታገዛሉ ከሚባሉት  ሁቲ  አማፂያን  ጋር  ኅብረት  ቢፈጥሩም  ኅብረቱ  እየተፈረካከሰ በመምጣቱ፣  ሁቲዎቹን ታጣቂዎች አውግዘው ከሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ለመታረቅ ሐሳብ አቅርበው ነበር። ሳላህ ከሰንዓ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በመጓዝ ላይ ሳሉ በሁቲ አማፂያን እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 4 ቀን 2017 በሰባ አምስት ዓመታቸው ተገድለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. 2015 ጀምሮ የጦር ዓውድማ የሆነችው የመን በጦርነቱ መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍእንዲሉ የመን እርስ በርስ ጦርነት በርካታ ዜጎቿን በሞት ተነጥቃለች፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿ አስከፊ ለሆነ የምግብ እጥረትና ለኮሌራ ወረርሽኝ ተጋልጠዋል፡፡ የመናውያን በበሽታ፣ በምግብ፣ በውኃና በሕክምና ዕጦት የተነሳ የሲኦል ኑሮ እየገፉ ነው፡፡

 ሙአመር ጋዳፊ 2003 .ም. የሕዝብ  ተቃውሞ  ተነሳባቸው፣ አማፅያኑን  ተላላኪዎች፣ አይጦች፣ ውሾች ብለው  ተሳደቡ፡፡ ‹‹ቁምሳጥን ውስጥ ብትገቡም አታመልጡኝም›› ብለው  ፎከሩ፡፡ በተደረገባቸው  የተቀናጀ  የአየር  ጥቃት  አንድ  ልጃቸውና ሦስት የልጅ ልጆቻቸው ተገደሉ፡፡ ጋዳፊ የተገደሉት እ.ኤ.አ.  ጥቅምት  20  ቀን  2011  ዓመፅ  ከተቀሰቀሰባቸው ከሰባት  ወራት  በኋላ  ነው፡፡  የሽግግሩ  መንግሥት  ወታደሮች  በትውልድ  ከተማቸው  በሲርት  ባካሄዱት  የመጨረሻ  ጥቃት፣  በተደበቁበት  የውኃ  መውረጃ  ቱቦ  ውስጥ  ተኩስ  ተከፍቶ  ቆሰሉ፡፡ ከቱቦ  ውስጥ  ተጎትተው  ወጡ፡፡ በወጣቶች  መንገድ  ላይ  ተጎተቱ፣ ተዋረዱ፣ በጥይት ተመትተው ተገደሉ፡፡

ጋዳፊ ‹‹ራሳቸውን  የመላው  ዓረብ  ዓለምና  የሙስሊም  አብዮት  መሪ አድርገው  ያቀረቡ  ሲሆን፣  የአፍሪካ  አገሮች  አንድ  አገር  መሆን  አለባቸው  ስማቸውም  የተባበሩት  የአፍሪካ  አገሮች ተብሎ መጠራት  አለበት››  ብለው  ያምኑ  ነበር።  ጋዳፊ  42  ዓመታት  አገዛዛቸው  እንደ  ማንኛውም  አምባገነን  ገዥ በሚያሳፍርና በሚያሳዝን ሁኔታ አከተመ፡፡ በበግ የመሰሏቸው የአራቱ አገሮች አምባገነን ፕሬዚዳንቶች መጨረሻ አላማረም፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ከጋዳፊ በኋላ ሊቢያ 1‚700 በላይ የታጠቁ ቡድኖች መፈንጫ ስትሆን፣ የሰው ልጅ ለገበያ ቀርቦ እንደ ሸቀጥ የሚሸጥና የሚለወጥባት ምድራዊ ሲኦል ሆናለች፡፡ በሴት ስደተኞች ላይ ወሲባዊ ጥቃት፣ በእስር ቤቶች ታስረው በሚገኙ ስደተኛ ወንዶች ላይ ደግሞ አስገድዶ የመድፈር ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡

‹‹The Migrant Project›› የተባለው ድረ ገጽ ሲኤንኤንን ጠቅሶ እንዳቀረበው፣ ስደተኞች በሊቢያ ገበያ በጨረታ እየተፈነገሉ ናቸው፡፡  በሊቢያ  ስደተኞች እንደ ዕቃ በጨረታ ይሸጣሉ፣ በባርነት የሚሸጡት ወደ አውሮፓ ለመሻገር በሊቢያ ለማቋረጥ ሲሉ የሚያዙት ናቸው፡፡ የተያዙ ስደተኞችም በረሃብ እየማቀቁ በአንድ ቦታ እንዲቆዩ ተደርጎ ወደ አዲሶቹ ጌቶቻቸውበባርነት ይተላለፋሉ፡፡

 ቢቢሲ በሠራው የጋዜጠኝነት ምርመራ እንደደረሰበት ከሆነ፣ ባለቤትነቱ ከአንድ ሩሲያዊ ባለሀብት ጋር የተገናኘ እንደሆነ ፍንጭ ተገኝቷል፡፡ በሊቢያ ለዓመታት በጦርነት ውስጥ ተሳትፎ ሲያደርግ የነበረው ዋግነር የሚባል ቅጥረኛ ተዋጊ ኩባንያ ነው፡፡ ስለዚሁ ኩባንያ ማንነትና ተግባራት ቢቢሲ ነሐሴ 11 ቀን 2013 .ም. በድረ ገጹ ባቀረበው ጽሑፍ አጋልጧል፡፡  

ከሊቢያ ደኅንነት ሰዎች ለቢቢሲ የደረሰ አንድ የሳምሰንግ ታብሌት ቁልፍ የዋግነር ቅጥረኛ ኩባንያ መረጃዎችን ይዟል፡፡ ምንም እንኳ ሩሲያ ከዋግነር የቅጥር ተዋጊዎች ጦር ኩባንያ ጋር ግንኙነት የለኝም ብላ ብታስተባብልም፣ በሊቢያ ይገኙ የነበሩ ሩሲያዊ ነፍሰ ገዳዮች፣  የጦር  አበጋዞች ሚስጥራዊ ስም፣ የመሣሪያ ግዥ ዝርዝርና ሌሎች ጠቃሚ የጦር መረጃዎችን ይዟል። ይህ የጦር ተዋጊዎች  ኩባንያ  ስሙ  በሩሲያ፣ በሞዛምቢክ፣  በሱዳንና በሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ተደጋግሞ ሲነሳ እንደነበር ቢቢሲ ገልጿል፡፡

ቢቢሲ ሚስጥራዊ ከሆነው የዋግነር የተዋጊዎች ቡድን ጋር በተዋጊነት ከተሠለፉ የቀድሞ ሁለት ጦረኞች ባገኘው መረጃ፣ ዋግነር የጦርነት ሥነ ምግባርን የማይከተል በጭካኔው ወደር የሌለው ነው፡፡ አባላቱም  እስረኛን  ወይም  ምርኮኛን  መመገብ  አላስፈላጊ  ወጪ  ነው  ብለው  ስለሚያስቡ  መግደልን  ይመርጣሉ፡፡ ‹‹ማንም  የእስረኛን  ሆድ  በየቀኑ  የመሙላት  ፍላጎት  የለውም፣  በሊቢያ  ሆን  ብሎ  ንፁኃንን መግደል እንደ አንድ የጦር ስትራቴጂ ተደርጎ ሲወሰድ ቆይቷል፤›› ብሏል፡፡ ይህም ሊቢያ የሲኦል ምድር መሆኗን ያመለክታል፡፡

በተለያዩ ፍላጎቶችና አመለካከቶች የተወጠሩ የሊቢያ ኃይሎችና ሌሎች አገሮች በሊቢያ ጣልቃ በመግባት አገሪቱን ሰላም ነስተዋታል። የረዥም ዘመን መሪ ከነበሩት ሙአመር ጋዳፊ ሞት በኋላ ሊቢያ የበርካታገሮች መፋለሚያ የጦር ዓውድማ ሆናለች፡፡  በርካታ  የውጭ  ኃይሎች  እጃቸውን  በማስገባታቸው  በእርስ በርስ ጦርነትና በውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ምስቅልቅሏ ወጥቷል። ዜጎቿ የተሻለ ኑሮ ይኖሩባት የነበረችው ሊቢያ አገሪቱን የተቀራመቱት ኃይሎችና ሚሊሻዎች በሚያካሄዱት ውጊያ ይበልጡን ደቃለች፡፡

ሊቢያ በተፈጥሮ ጋዝና በነዳጅ ሀብት የበለፀገች ብትሆንም፣ በጦርነቱ የተነሳ በሺሕ ዎች የሚቆጠሩ ሊቢያውያን ሕይወታቸውን ሲያጡ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፡፡  ‹‹በሊቢያ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ለምን በዛ?›› የሚል መሠረታዊ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ ሊቢያ በአፍሪካ ከፍተኛ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ያላት መሆኗ፣ የሕዝብ  ብዛቷ ከሰባት ሚሊዮን በታች መሆኑና ለአውሮፓ ቅርብ መሆኗ ትኩረት ሳቢ አድርጓታል፡፡ በተጨማሪ ሁለት ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ የሜዴትራንያን ባህር ወሰን ስላላት ነዳጅዋን በሜዲትራያኒያን ላይ አቋርጣ በቀላሉ ለአውሮፓ ገበያ ለማቅረብ ምቹ በመሆኗ የበርካታ አገሮችን ልብ ታማልላለች። በዚህም የተነሳ ሊቢያ የዓለም ትኩረትን መሳቧ የሚጠበቅ ነው፡፡ ጽንፈኛው አይኤስ ከኢራቅናሶሪያ ድል እየተመታ ቢሆንምበሊቢያ በረሃዎች ላይ እግሩን በማሳረፉ ለሊቢያ፣ ለጎረቤት አገሮችና ለምሥራቅ አፍሪካ ብቻ ሳይሆን፣ ለዓለም ደኅንነት ሥጋት መሆኑ ይታመናል።

 ሰው ነህ!“ (You are but a Man)

የዓለም ታሪክ  የሚያስገነዝበን  ጅማሬያቸውና  ፍፃሜያቸው  ያማረ  መሪዎች  ጥቂት መሆናቸውን ነው፡፡ የምወደውን አንድ አባባል ላቅርብ፡፡ በሮማውያን  ዘንድ  የአንድ ጄኔራል  ድል  አድራጊነት  ዝና  ከጽንፍ  እስከ አፅናፍ  ሲያስተጋባ  ትልቅ  ሰረገላ  ይዘጋጅለትና  በከተማዋ  አደባባዮች  እንዲዘዋወር  ይደረጋል፡፡  ከዚያ  ያማረና  ያጌጠ  የጀግና  ሰረገላ  ውስጥ  አንድ  ባሪያ አጠገቡ  ይቀመጥና  በጆሮው  ውስጥ  አንዲት አነስተኛ፣ ዳሩ ግን ቁም ነገሯ ታላቅ የሆነ መልዕክት ጣል ያደርጋል፡፡

ቃሉ ሰው ነህ!”  (You are but a Man) የሚል ነው፡፡ ይህም ሲባል ራሱን ከሞት አምልጦ እዚህ ደረጃ  (አሸናፊነት) መድረሱን እንዳይረሳና በንቀት ተወጥሮ እንዳይታበይ ነው፡፡ ትሁት  የነበረው  ሲከብር  ትዕቢተኛ  መሆኑ፣  ሽቁጥቁጥ  የነበረው  ደግሞ  አንዳች  ድሎትና  ፍስሐ  ሲያጋጥመው  ኩራተኛ  መሆኑ  ከጥንት  ጀምሮ  ያለና  ወደ  ፊትም የሚኖር ነው፡፡ ጥንት  የዓለም  ገዥ  የነበሩት  ሮማውያን  በልሂቃኑ  ሰረገላ  ውስጥ  ሰው ነህ!(You are but a Man) የሚላቸውን  ባሪያ  ማስቀመጥ  ትተው  አወዳሾችንና  ዕቁባቶቻቸውን  ማስቀመጥ  ሲጀምሩ  ትኅትና፣  ጥንቁቅነት፣ ልከኝነት፣ ጀግንነትና  ፈሪኃ አምላክ ከመንፈሳቸው ጠፉ፡፡  በምትካቸውም  ያለ  ህሊና  መኖር፣ ትዕቢት፣ ኩራት፣ ስድነት፣ ቅምጥልነትና ጌትነት በሚያጣቸው ቅብጠት መንፈሳቸው ተሞላ፡፡ ውርደት ውስጥም ገቡ፡፡

ጋዳፊና በበጎች የመሰሏቸው የአራቱ አገሮች መሪዎች እንዲሁም ሊቢያ፣ ሶማሊያና የመን ከደንበኛው አገርነት ወርደው (Failed State) የጦር ዓውድማ ሆነዋል፡፡ ሱዳንም ለሁለት ተከፍላለች፡፡ ደቡብ ሱዳናውያን ከሰሜን ሱዳን ለመገንጠል ለበርካታ ዓመታት ተዋግተው ነፃ አገር ቢሆኑም፣ በእርስ በርስ ጦርነትከእጅ አይሻል ዶማሆነዋል፡፡ ሰሜን ሱዳን በጋለ ብረት ምጣድ ላይ የተቀመጠች አገር ስትሆን ግብፅ በውጥረት ውስጥ ነች፡፡

ኮሎኔል ጋዳፊን ጨምሮ በአራቱ በጎች የተመሰሉት አምባገነን ገዥዎች ዛሬ በሕይወት የሉም፡፡ አምባገነን ገዥዎች ምንጊዜም ሰው ነህ! “You are but a Man” የሚለውን ምክር በጆሯቸው ጣል የሚያደርግላቸው መካሪ  አልፈለጉም፡፡  ‹‹የረቱ ዕለት አምቧቻሪ፣ ዘምበል ያለ ዕለት ምሶ ቀባሪ›› በሆኑ ክፉዎች መከበባቸውን አላስተዋሉም፡፡ በጎ መካሪዎቻቸውን አስረዋል ወይም ገድለዋል፡፡ በዚህም ፍፃሜያቸው አላማረም፡፡ መሪዎችን የሚያበሏሻቸው በዙሪያቸው የተኮለኮሉ መሶብ ሃይማኖተኞች፣ ለሆዳቸውና ለመፍቀዳቸው የሚኖሩ አምቧቻሪዎች ናቸው፡፡

 ‹‹ታሪክ በግዛቶች ፍርክስካሽና በመሪዎች መንኮታኮት የተሞላ  ነው›› እንዲሉ፣ መጨረሻቸው ያማረላቸው ለልጆቻቸው ዕፍረትን  የማያወርሱ  መሪዎች  ጥቂቶች  ናቸው፡፡  መጨረሻቸውን  የሚያስቡ፣ እጃቸው  በደም  ያልጨቀየ፣ ጭንቅላታቸው  በጋኔን  ያልተሞላ፣ የንፁኃን  ደምና  ዕንባ  በሌሊት  ከእንቅልፋቸው  ቀስቅሶ  የማያስጮሃቸው መሪዎችን ያገኘ ሕዝብ የታደለ ነው፡፡

የኢጣሊያ ሕዝብ ተከፋፍሎ በነበረበት ዘመን ጋሪባልዲ፣ ለጀርመን  አንድነት ቢዝማርክ፣ ለአገራችን  አፄ  ምንሊክ (የተለያየ  አመለካከት ቢኖርም በእኔ ዕይታ)፣ ጋማል አብዱል ናስር ለግብፅ፣ ንክሩማህ ለጋና፣ ጆሞ ኬንያታ ለኬንያ፣ እንዲሁም በሁለተኛው ዓለም ጦርነት የእንግሊዙ ዊንስተን ቸርችልና የፈረንሣዩ ደጎል ትናንት፣ ዛሬና ነገ ያልተሳከሩባቸው የአገራቸውና የዓለም ታላላቅ ነፍሶች ነበሩ፡፡ ታሪክንም ቀይረዋል፡፡

‹‹መሪዎችን  የሚፈጥረው  ሕዝብ  ነው››  የሚል  ድንቅ  አባባል  አለ፡፡  ኢትዮጵያውያንም  የፍቅር፣ የበጎነት፣  የትኅትና፣ የፍትሕ፣ የታላቅነት፣ የነፃነትና  የአንድነት ዋርካ የሆነ መሪ መፍጠር ይገባናል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...