Monday, May 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቀበቶን ጠበቅ!

እነሆ መንገድ! ከሜክሲኮ ወደ ቄራ ልንጓዝ ነው። ጋቢና የተቀመጠ ተሳፋሪ በስልኩ ያወራል።ስማ በአንተ ቤት ሰው መርጠህ ልብህ ውልቅ ብሏል። እኔ እያለሁ እስኪ ምን ሌላ ያስኬድሃል? ‘ሥጋ ሞኝ ነውአለ ያገሬ ሰው። ይኼው ለገንዘብ ብለህ የእጅህን አገኘህ…ይላል። ከጀርባው የተቀመጠ ጎልማሳ፣እውነት ነው! ሥጋ ሞኝ ነው። ታዲያ የበሬ ሳይሆን የሰው ሥጋ ነው ሞኝ…ይላል አጠገቡ ለተቀመጠች ቀዘባ። ወጣቷ፣መቼም ሰብቶ ከመታረድ የእኛ ይሻላል…ስትለው መሀል መቀመጫ የተቀመጠች መነጽር ያደረገች ወይዘሮ፣ባለፈው ሰሞን በሬዲዮ ስለመላላጫና ስለፈረሰኛ ሲያወሩብን ዋሉ። አሁን ደግሞ እዚህ ስለሥጋ፡፡ ምናለበት ኑሮ ጣሪያ ነክቶብን በባዶ ወሬ ባታስፈስኩን?” ስትል ትነጫነጫለች። ከጎኗ የተቀመጠ ቀበጥባጣ ወጣት ደግሞ፣አይገርምም? ዘንድሮ እኮ እኛነት ተረስቶ የራስ  የሥጋ ወሬ ደመቀ…እያለ ንዴቷን ያባብሳል። ሥጋ ኪሎው ሺሕ ብር ገባ እየተባለ በፍልሰታ ፆም የምን ተረብ ነው የተጀመረው ያስብላል፡፡ ጉድ ነው!

እርግጠኛ ነኝ ቀጣዩ የዓለም ጦርነት የሚነሳው በሥጋ በልና ቬጂቴሪያንመሀል ነው…ብላ ደግሞ አጠገቤ የተቀመጠች የዩኒቨርሲቲ ተማሪ መሳይ ስልኳ ላይ ስታፈጥ እታዘባለሁ። ጥቂት ቆይታኮሜንትስታበጥር ወደ ሌላ የማይ መስዬ በጎንዮሽ ሰረቅ አደርጋለሁ፡፡የአክራሪ ብሔርተኞችና የፖለቲካ ሴረኞች ሸር ሳያንሰን፣ የሥጋ በሎች የጦርነት ታሪክ ሊጻፍብን? አይደረግም…” ሲል አንዱ ሌላው በመቀጠል፣ እህል ከመሬት መስሎኝ የሚበቅል። ሥጋም ቢሆን ከመልካም የግጦሽ ሳር ነው የሚሰባው። እናም በእህል ለመጣላት እንደ መሬት በሊዝ የመንግሥት ነው እስኪባል መጠበቅ አለብን?” ይላል። ምድረ ጦር ጠማኝ እጅ ለእጅ እንደማይያያዝ አውቆ በቃላት ጠረባ አንዱ ሌላውን አፈር ድሜ ሲያስግጥ ማየቱ ቴክኖሎጂን የሚያስረግም ሲሆንብኝ፣ ጆሮዬን መጨረሻ ወንበር ወደ ተቀመጡት ጣል አደረግኩ። ሲናገሩ እንጂ ሲያዳምጡ መቼ ይገኛሉ?

እሺ እዚያ ጥግ?” ወያላው ጉዞ ከመጀመራችን ያጣድፈናል። መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡ አንድ አዛውንት በስተቀር ሦስቱ ይተዋወቃሉ። የሚጫወቱት ስለታሊባን ግስጋሴ ነው።የአበራሽን ጠባሳ ያየአይስቅምሆኖብኝ እንጂ እኔስ ሳቅ ሳቅ ይለኛል…ይላል አንደኛው።! ሰው ሲሞት የሚስቅ ቀጣዩ ሟች ነው ይባላል፣ አይደል አባት?” ብሎ አዛውንቱን ለፍርድ ያስገቡዋቸዋል።ይባላል!” ይመልሳሉ በአጭሩ። እኔ እኮ የምስቀው በሟቾች አይደለም፣ ምን ነክቷችኋል? ምንድነው የምድሩ አልበቃ ብሎ በሰማይ ቤት ስም ማጥፋት?” ካለ በኋላ፣እኔ ሳቅ… ሳቅ… ይለኛል ያልኩት የታሊባን አፍጋኒስታን ላይ እንደ ልቡ መሆን ነው። እዚህማ ወያኔ አያስባትም…ሲል አዛውንቱ አቋረጡት፡፡እግዜር ሲያበረታን ነዋ ልጄ፣ ሁላችንንንም እሱ አንድ ሲያደርገን ነው።እሱ ከተማን ካልጠበቀ ጠባቂ በከንቱ ይደክማልይላል መጽሐፉ። ምህላችን እያስጨነቀው ለቅሷችን ዙፋኑ ሥር እንደ ባህር ተንጣሎ እያየ፣ እንዲያ ላለ የሽብር ጥቃት እንዴት አሳልፎ ይስጠን? የቦምብ ፍንዳታ ስለማንሰማ እንጂ በየቀኑ ወገን ተገደለ ሲባል እኮ ነግ በእኛ የሚሉት ሥጋት የሚሉት የከፋ ሽብርስ አለ…አሉት። እውነታቸውን ነው!

ነገሩ እየተያያዘ እንደ ሰደድ እሳት ወዴት እንደሚያመራ ወጣቶቹ ገብቷቸው አዛውንቱን ሊያናግሩ ይተነኩሳሉ።እውነት ነው እንግዲህ ወሳኙ ማጥቃት ይጀመራል ተብሎ ሽርጉድ እየተባለ ነው…አለ በሾፌሩ ትይዩ መስኮቱ አጠገብ የተቀመጠ። ጓደኛው ተቀበለና፣ “ዘንድሮማ የአገራችንን ጠላት አፈር አስግጠን ነው አዲሱን ዘመን የምንቀበለው…” ብሎ ብቻውን ሳቀ። ሳቁ በትንታ ሲቆራረጥ ተሳፋሪዎች ደንግጠው ወደ እሱ ዞሩ። ጓደኛው ደረቱን እየደቃ፣አይዞህ ይህን ሳቅማ እንደ ጀመርከው ትጨርሰዋለህይኼኔ እያለቀስክ ቢሆን ትን ባላለህ?” ይለዋል። ተሳፋሪዎች በሥጋት ስሜት ያዩታል። ፖለቲካው ሲጦዝ የሚጨፈግግ ስሜት በየቦታው መብዛቱ ሊገርም አይገባም፡፡ የሚገርመው ይህ ስሜት ባይኖር ነው!

መሀል መቀመጫ የተቀመጠ በስልክ ይነጋገር የነበረ ተሳፋሪ ድንገት፣እኔን ቁምነገር የሚባል አታውራኝ አሁን። ቁምነገር ነው የሰለቸኝ። ቁምነገር በማውራት ቢሆንማ በስብሰባ የምናጠፋው ጊዜ ተደምሮ የትና የት ባደረሰን ነበር?” ይላል። እንዲያ ሲል በስልክ የሚያናግረው ሰው ሳቀ መሰል፣ግዴለም እጠብቅሃለሁ ተረጋግተህ ሳቅህን ጨርስ…ሲል ሰማነውና ደነገጥን።እንዴ ይኼ ሰውዬ እስካሁን በስልክ እያወራ ነው?መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ወጣቶች አንደኛው አዳንቆ ጠየቀ።ምን ይታወቃል ኢትዮ ቴሌኮም የዓመቱ ምርጥ ደንበኛ ብሎ ነፃ አገልግሎት ፈቅዶለት ይሆናል…” ቢል ጎልማሳው ተሳፋሪዎች የምፀት ሳቃቸውንን ለቀቁት።ነፃው ቀርቶብኝ ላቤን ባልነጠቀኝይሉት ምፀት መሆኑ ነው! ጉድ እኮ ነው!

ታክሲያችን ድንገት ጥጓን ይዛ ቆመች። ወያላውና ሾፌሩ በዓይን ብቻ ተያይተው የቆምንበትን ምክንያት አውቀዋል። ጋቢና የተቀመጡ ሴትና ወንድ ተሳፋሪዎች “ምንድነው እሱ?” እያሉ ሾፌሩን በጥያቄ ሲያዋክቡት፣ ‹‹ራዲያተሩ ስለተቀደደ ውኃ ያፈሳል። አንዴ ብቻ እናስቸግራችሁ ውረዱ…›› ብሎ ያግባባቸዋል። ሌሎቻችን ትዕይንቱን በአትኩሮት እንከታተላለን። ከመቅጽበት ገና እንዳዩት ፅኑ ጠጪነቱን መመስከር የሚችሉለት ወጣት ምርቃትና እርግማኑን እያዥጎደጎደ በተከፈተ መስኮት አንገቱን አስገባ። ‹‹ወየውላችሁ ግቡ! አንገት ማስገቢያ ጎጆ ካጣችሁም ሱባዔ ግቡ! እንቢ ካላችሁ ጉድጓድ ግቡ! ለእኛ ፀሐይን ያወጣ አምላክ ለእናንተ የኮንዶሚኒየም ዕጣ ያውጣላችሁ። ‘ሙዱ’ ካልተሰረቀም ከዚህ አገር ያውጣችሁ። እንደዚህ ታክሲና እንደ ፖለቲከኞች ትንሽ ተራምዶ ከመቆም ወይም ከመበላላት ይሰውራችሁ…›› ካለ በኋላ ወደ ወያላውና ሾፌሩ ዞሮ ደግሞ፣ ‹‹…በዳያስፖራው ስናሾፍ ታክሲም አልፎላት በየመንገዱ ውኃ መጎንጨት ጀመረች? አይ ጊዜ! ትንሽ ቆይታችሁ በመንገድ ላይ ‘ባንኮኒ’ ካልተሠራ ብላችሁ ሠልፍ እንዳትወጡ ብቻ! ግድ የለም!›› አላቸው። እንዲህ አለ ለካ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወያላውና ሾፌሩ እንዴት ዘና ሲሉ እንደሚያነጉ እየተቀባበሉ ይጫወታሉ። መጨረሻ ወንበር የተቀመጡት ወጣቶች ስለሚደግፏቸው የአውሮፓ ቡድኖች ሲነዛነዙ ቆይተውየእኔ ቡድን አሠላለፍ ይበልጣል፣ አይበልጥም…’ እየተባባሉ ታክሲዋንቴክኒክና ታክቲክክፍል አስመስለዋታል። መሀላቸው የተቀመጡት አዛውንት ከዘራቸውን እየቆረቆሩ ሩቅ ያስባሉ። ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡት ጎልማሳና ኮረዳሰው በፍቅር እንጂ በሌላ አይሸነፍምይሸነፋልይከራከራሉ። እሷ ወቅቱን ተገን አድርጋ መሲሁን እንደ ምሳሌ እያነሳች፣በፈጣሪያችን አምነን እንድንፈጽም ያደረገን ፍቅር እንጂ ሌላ አይደለም…ትላለች። ጎልማሳው አዳምጦ ሲያበቃ፣ኳሷ መሬት ሳለች እንደ ፕላቶናዊቷዩቶፒያየማይጨበጥ ምሳሌ በአስረጂነት አትሰንቅሪ…ብሎ ይቆጣታል። ከእነሱ ጀርባ ወይዘሮዋ አጠገቧ ከተቀመጡት እናቶች ጋር በሸመታ ዙሪያ ሲጫወቱ የቅመምና የበርበሬ ወሬያቸው ጆሮ ይለበልባል። በአጠቃላይ ታክሲያችን ተንቀሳቃሽ የብሶት አዳራሽ ሆናለች።

ቄራ ደርሰን ወያላውመጨረሻ!” ሲል አጠገቤ የተቀመጠችዋን ወጣት ፌስቡክ በስላች ስቃኝ፣ታክሲ ሲሳፈሩና ቴሌቪዥን ሲከፍቱኢርፎንጆሮዎ ላይ መሰካትዎን አይዘንጉብላ ለጥፋለች።ኮሜንትይግተለተላል።ታክሲም የመንግሥት ሆነ?” ሲል ሌላው ከሥር፣ምን የመንግሥት ያልሆነ አለ? ነፍስህም ስለማትጨበጥ እንጂ ታሪክ እናይ ነበር…ብሎኮምቷል ልወርድ ስዞር ከደጅ ታክሲ ይጠብቅ የነበረ መንገደኛ ታክሲያችንን ሲያይ እየተግተለተለ መጥቶ በሩን አንቆ ቆመ። ወያላው፣ሳይወርዱ እንዴት ብላችሁ ነው የምትገቡት?” ይላል። የሚሰማው የለም። ሾፌሩ ተበሳጭቶ፣ኤጭ ሥልጣን መሰላችሁ እንዴ? የምን ግብ ግብ ነው ተሳፋሪዎች ይውረዱ መጀመርያ…ይላል። አይሰሙትም። ጥቂት እንደ ተጉላላን አዛውንቱ ከመቀመጫቸው ተነስተው፣ኧረ በዚህ ወቅት የምን መገፋፋት ነው?” አሉ። መንገዱ ተለቀቀ። በፍጥነት ወረድን። ሾፌሩ ዞር ብሎ፣አዳሜ መንገድ ሲለቀቅለት ሥልጣንም የሚለቀቅለት መስሎት ጉድ እንዳይሆን?” ሲል አዛውንቱ ሰምተውት ከት ብለው ከሳቁ በኋላ፣አንተ ጊዜን እንዳማልህ ነው? ሞኝህን ፈልግ…” እያሉት ዞር ብለው እያዩት፣ ‹‹ሰማህ ይልቁን በደንብ ታጠቅ…›› አሉት። ‹‹ምኑን?›› ሲላቸው ደንግጦ፣ ‹‹አይዞህ ጠመንጃ አላልኩህም፣ ያላላኸውን ቀበቶ አጥብቀህ ታጠቅ፡፡ ከጎንህ የሚቀመጡትንም ጠበቅ አድርገህ አስታጥቃቸው፡፡ መቀመጫ አልባ ሱሪ እንደ ዘበት እየታጠቃችሁ አትንዘላሉ፣ ለአደጋም አትጋለጡ፡፡ ሕግ ማክበርም ሆነ ማስከበር የሚቻለው አጥብቆ በመታጠቅ ነው…›› እያሉ መንገዳቸውን ሲይዙ አፋችንን ከፍተን አየናቸው፡፡ መልካም ጉዞ! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት