ቀጠሮ ተሰብሮ ምስክሮቹ እንዲሰሙ አቤቱታ እንደሚያቀርቡ ጠቁመዋል
የፌደራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በእነ አቶ እስክንድር ነጋ ላይ የቆጠራቸው ምስክሮች በግልጽ ችሎት መሰማታቸው ለደኅንነታቸው ስለሚያሠጋቸው፣ ከመጋረጃ ጀርባና በዝግ ችሎት እንዲሰሙለት እስከ የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ያደረገው ክርክር ውድቅ ተደርጎ በግልጽ ችሎት እንዲሰሙ ተወሰነ፡፡
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ምስክሮቹ በግልጽ ችሎት እንዲሰሙ ውሳኔ የሰጠው ነሐሴ 10 ቀን 2013 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ሲሆን፣ የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎትና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ሰጥተውት የነበረውን ውሳኔ በማፅናት ነው፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተደጋጋሚ በሰጠው ውሳኔ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች መሰማት ያለባቸው በግልጽ ችሎት ነው ማለቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ በማለቱ መዝገቡን ለጥቅምት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ቀጥሮት ነበር፡፡
ሰበር ሰሚው ችሎት ሥር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በመፅናቱ ቀጠሮ ተሰብሮ ዓቃቤ ሕግ ምስክሮቹን እንዲያሰማ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው፣ ለረቡዕ ነሐሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. አቤቱታ እንደሚያቀርቡ የተከሳሾቹ ጠበቆች ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡