ትናንት ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሰዓት በአዲስ አበባ ከተማ የጣለው በረዶ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ ምክንያት በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ተከስቶ በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል፡፡
በአስኮ፣ በአደይ አበባ፣ በጀርመን አደባባይና በጎልፍ ክለብ አካባቢ በደረሰው ከፍተኛ የጎርፍ አደጋ መንገዶች ጭምር ተዘጋግተው ቆይተዋል፡፡ የድንገተኛና የእሳት አደጋ ሠራተኞችም በቦታዎቹ በመገኘት የከፋ ሰብዓዊ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥረት በማድረጋቸውን ምክትል ከንቲባ አዳነች አበቤ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በደረሰው ጉዳት ከልቤ አዝናለሁ፤›› ብለዋል።
ተጎጂዎችንም ወደ ሕክምና መስጫ በማጓጓዝና የመጀመርያ ሕክምና ዕርዳታ እንዲያገኙ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡ የከተማው አስተዳደር ከክረምቱ ማየል ጋር ተያይዞ አስቀድሞ የመከላከል ሥራዎችን እየሠራ የነበረ ቢሆንም፣ ትናንትና ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. የደረሰው የጎርፍ አደጋ ተጨማሪ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ ያመላከተ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በመጪዎቹ ቀናት ከፍተኛ መጠን ያለው የዝናብ ሥርጭት ስለሚኖር ነዋሪዎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።