ጠቅላይ ሚኒሰትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ጋባዥነት ከዛሬ ነሐሴ 12 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በቱረክ ጉብኘት እደሚያደረጉ የቱርክ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬትን ጠቅሶ አናዱሉ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጉብኝት የኢትዮጵያና የቱርክ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የተጀመረበትን 125ኛ ዓመት አስመልክቶ እንደሆነ በመረጃው ዘገበ፡፡
የቱርኩ ፕሬዚዳንቱ ከሳምንታት በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ጋር በስልክ በተወያዩበት ወቅት ቱርክ ለኢትዮጵያ የትኛውንም ዓይነት ድጋፍ ታደርጋለች በማለት መግለጻቸው ይታወሳል።
የጠቅላይ ሚኒስተሩ ጉብኘት ለምን ያክል ጊዜ እንደሆነ ባይገለጽም በቆይታቸው ሁለቱ አገሮች ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር መወሰድ ስላለባቸው ዕርምጃዎች እንደሚመክሩና እንደሚገምግሙ እንዲሁም ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ላይ ይመክራሉ ተብሏል፡፡
ቱርክ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት በማድረግ ከቻይና ቀጥላ ሁለተኛዋ አገር ስትሆን በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሷን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡