በአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አማካይነት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ እንዲሆኑ ከወራት በፊት የተሾሙት አንጋፋው ዲፕሎማት ጄፍሪ ፈልትማን ባለፉት ጥቂት ወራት ወደ ቀጣናው አገሮች፣ እንዲሁም በቅርቡ ወደሚገኙት የባህረ ሰላጤው አገሮች በዚህ ሳምንት የጀመሩትን ጨምሮ ለሦስት ጊዜያት ያህል ጉብኝት አድርገዋል፡፡
በዚህም መሠረት በተሾሙ ጥቂት ቀናት ውስጥ የመጀመርያ ጉብኝታቸውን በወርኃ ሚያዝያ ሦስት የምሥራቅ አፍሪካ አገሮችን ማለትም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሱዳንን በጎበኙበት ወቅት ሰሜን አፍሪካዊቷ ግብፅም የጉዟቸው አካል ነበረች፡፡
በወቅቱ ከየአገሮቹ ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከአፍሪካ ኅብረት፣ እንዲሁም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት አመራሮች ጋር በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ስላለው የድንበር ይገባኛል ውዝግብ፣ በተጨማሪም ኢትዮጵያን፣ ግብፅንና ሱዳንን የሚያነታርከውን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ መወያየታቸው የሚታወስ ቢሆንም፣ የጉዟቸው ማጠንጠኛና ዋነኛው አጀንዳ ግን የኢትዮጵያ ጉዳይ እንደነበር በወቅቱ የወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
ምንም እንኳን በወቅቱ የልዩ መልዕክተኛው የጉብኝት ዓላማ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በፀጥታ፣ በፖለቲካ፣ እንዲሁም ሰብዓዊ ቀውስን አስመልክቶ የሚታዩ ችግሮችንና መዛነፎችን በዘላቂነት በዲፕሎማሲያዊ መንገድ መፍታት የሚቻልበትን አቅጣጫ ለመተለም ያለመ እንደሆነ በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አስታውቆ የነበረ ቢሆንም፣ በትግራይ ክልል ያለውን ጦርነት ተከትሎ የተከሰተውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመፍታት እንዲቻል መንግሥት ለዓለም አቀፍ የዕርዳታ ተቋማት የመተላለፊያ ኮሪደር እንዲከፍት ግፊት እንዳደረጉም በወቅቱ ተዘግቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዲፕሎማቱ በወቅቱ ጉብኝታቸው ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች ማለትም የፌዴራል መንግሥትና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ኃይሎች የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ የሚችሉበት አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠርም ግፊት አድርገዋል፡፡ ሆኖም ሁለቱም ኃይሎች ተኩስ ለማቆም አልተስማሙም፡፡ በወቅቱ በተለይ መንግሥት ከአሸባሪ ድርጅት ጋር አልደራደርም በሚለው አቋሙ በመፅናቱ ምክንያት፣ የአሜሪካ መንግሥት በመንግሥትና በሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ላይ የጉዞ ማዕቀብ መጣሉ የሚታወስ ነው፡፡
በተመሳሳይ እኚሁ ዲፕሎማት ዳግም ወደ ኢትዮጵያ እንዲሚመጡ ከተገለጸ በኋላ፣ የኢትዮጵያ ጉብኝታቸውን በመሰረዝ ወደ ኳታር፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ እንዲሁም ኬንያን የጎበኙ ሲሆን፣ በወቅቱም ከሁለትዮሽ ግንኙነት በዘለለ ከየአገሮቹ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ጉዳይ መወያየታቸው አይዘነጋም፡፡
ምንም እንኳን ልዩ መልዕክተኛው የተሾሙት አጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድን አካባቢያዊ ሁኔታዎች ከአሜሪካ መንግሥት ጥቅሞች አተያዮች አንፃር ለመቀየስና ጂኦ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ለማሳረፍ የታለመ ቢሆንም፣ አሁን በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት በየዕለቱ ጠረጴዛቸው ላይ ከማይጠፉ አጀንዳዎች ዋነኛው እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ከወራት በፊት በአሜሪካው ሰላም ተቋም (Peace Institute) አማካይነት የተደረገ ጥናት እንደሚጠቁመው፣ አሜሪካ በሥፍራው ያላትን ተሰሚነትና ተፅዕኖ ለማጠናከር ካሻች ይህን ጉዳይ ለዋኛነት የሚከታተል ልዩ መልዕክተኛ ወይም ልዑክ እንደሚያስፈልጋት ከዘረዘራቸው የመፍትሔ ሐሳቦች አንዱ ነበር፡፡
ከወራት በፊት በዚህ ተቋም የታተመው ሪፖርት፣ ‹‹Senior Study Group on Peace and Security in the Red Sea” የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን የዚህ ሪፖርት አዘጋጆች ከሆኑት አንጋፋ ዲፕሎማቶች መካከል አንዱ ደግሞ አሁን በፕሬዚዳንቱ ለቀጣናው ልዩ ልዐኩ ሆነው የተሾሙ ጄሪፍ ፈልትማን ናቸው፡፡ ከዚህ በጨማሪም ሌላው አንጋፋ ዲፕሎማትና የፕሬዚዳንቱ ከፍተኛ አማካሪ፣ እንዲሁም የቀድሞ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆኒ ካርሰንና ሌሎች አንጋፋ ዲፕሎማቶችን ያካተተ የጥናት ተቋም ነው፡፡
የትግራይ ጦርነት ከመጀመሩ ሳምንታት በፊት ይፋ የሆነው የዚህ ተቋም ሪፖርት በቀጣናው በተለይም በቀይ ባህር ላይ የአሜሪካ ተፅዕኖ መቀነስ አሳሳቢ መሆኑን ከመግለጽ ባለፈ፣ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ያለው ጂኦ ፖለቲካ ባለፉት አምስት ዓመታት ዓይነተኛ የሆነ የለውጥ ምኅዋር ውስጥ መሆኑንም ያትታል፡፡
ከዚህ አንፃርም በቀጣናው ያሉ አገሮችን የሚመለከቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚዊ፣ ማኅበራዊ፣ እንዲሁም የፀጥታ ጉዳዮችን የሚያትትና ከዚህ አንፃርም ያሉ ለውጦች፣ ተስፋዎችን፣ እንዲሁም ሥጋቶችን በዝርዝር ከየአገሮቹ ጠቀሜታ አንፃር ተንትኖ አቅርቧል፡፡
ለአብነትም ያህልም ኢትዮጵያና ሱዳን ከቀዝቃዛው ጦርነት መገባደድ በኋላ ወሳኝ የሆነ የፖለቲካ ሽግግር ውስጥ እየቀዘፉ መሆኑን በመጥቀስ፣ ከዚህ ባለፈም ሁለቱ አገሮች በአካባቢው ካሉ አገሮች ጋር በንፅፅር ሲታዩ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛትና የታሪክ፣ የባህል፣ እንዲሁም የኢኮኖሚ ተመሳሳይነት ያላቸው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሁለቱ አገሮች የሚታየው የለውጥ ተስፋ ወደ ሌሎች የአካባቢው አገሮች የመዛመት ዕድል እንዳለው ተስፋውን ያስቀምጣል፡፡
ሆኖም ግን በተመሳሳይ በሁለቱ አገሮች የሚስተዋለው የሽግግርና የለውጥ ንፋስ ወደ ሌሎች የመዛመት ዕድል እንዳለው ሁሉ፣ የመፍረስ አደጋንም እንደተሸከመ ከመግለጽ ባለፈ የሁለቱ አገሮች የለውጥ መጨንገፍ የሚያስከትለው የመፍረስ አደጋ ‹ከፍተኛ የሆነ የቀውስ ወሀብ› በቀጣናው፣ በአኅጉሩ፣ እንዲሁም በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሊያስከትል ይችላል የሚል ሥጋቱንም ያጋራል፡፡
በዚህ የጥናት ወጤት ማዕቀፍ ውስጥ ወቅታዊውን የኢትዮጵያ ጦርነት ከተስተዋለ አሜሪካ አስቀድሞ እንደገለጸችው፣ የአካባቢውን ደኅንነትና ፀጥታ የሚያውኩ እንቅስቃሴዎችን በአፅንኦት መከታተል እንዳለባት የሚያትት ከመሆኑ አንፃር የልዩ ልዑኩ ተደጋጋሚ ጉብኝት ላያስገርም ይችላል፡፡
ነገር ግን ከመቶ ዓመታት በላይ በዘለቀው የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት በጂማ ካርተር ፕሬዚዳንትነት ጊዜ ከተፈጠረው ወዲህ እንዲህ ያለ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ካለማወቁም አንፃር፣ የሁለቱ አገሮች ዲፕማሲያዊ ግንኙነት ወደ ከፋ ደረጃ ሊሸጋገር እንደሚችል የሚያመለክቱም አልታጡም፡፡
በዚህ አጣብቂኝ መሀል የሰነበተው የሁለቱ አገሮች ሁለትዮሽ ግንኙነት ተስፋ ሳይገኝበት አሜሪካ የትግራይ ክልል ጦርነት በአስቸኳይ በውይይት እንዲፈታ ስትወተውት፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ከአሸባሪ ድርጅት ጋር አልደራደርም የሚለው አቋሙን ሳይለውጥ ነው ልዩ ልዑኩ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጡ የተገለጸው፡፡
ለቀናት የሚቆየው የልዩ ልዑኩ ጉብኝት በዚህኛው ዙር ደግሞ መነሻውን በጎረቤት አገር ጂቡቲ አድርጎ እሑድ ነሐሴ 9 ቀን 2013 ዓ.ም. የተጀመረ ሲሆን፣ ልዩ ልዑኩም ለተመሳሳይ ዓላማ ማለትም ለትግራይ ግጭት መቋጫ ለማበጀት ወደ ኢትዮጵያም ጎራ ይላሉ፡፡ ነገር ግን አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም የተለወጠ አይደለም፡፡
ለዚህም ማሳያ ከጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ጋር አጠር ያለ ቆይታ ያደረጉት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ቢቂላ ሁሬሳ (ዶ/ር) የሰጡትን ማብራሪያ መመልከት ይቻላል፡፡ ‹‹መንግሥት አሸባሪ ብሎ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወሰነውን አካል አሸባሪ በሚል ደረጃ አሜሪካ እስካልተረዳቸው ድረስ፣ የኢትዮጵን ችግር በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይቻላል ብለን አናምንም፡፡ ለፈጠሩት ምስቅልቅል ተጠያቂ መሆን አለባቸው ብለን ነው የምናምነው፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ልዩ ልዑኩ ወደ ኢትዮጵያ ሳይገቡ እንዲህ ያለው የመንግሥት አቋም የልዩ ልዑኩን ቆይታ አስቸጋሪ፣ የሚያቀርቡትን የተደራደሩ ጥያቄም ፈታኝ እንደሚያደርገው ከወዲሁ የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡
ከዚህ በተረፈም በማኅበራዊ የመገናኛ ዘዴዎች በተለይም ደግሞ በትዊተር የልዩ ልዑኩን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሚቃወሙ ጽሑፎች በርከት ብለው የሚታዩ ሲሆን፣ በተለይ የአሜሪካ ከአፍጋኒስታን መውጣትን ተከትሎ የተፈጠረውን ቀውስ በማውሳት “Fetlman Go Back to Kabul” የሚለው አገላለጽ በበርካታ ኢትዮጵያውያን ተጋርቷል፡፡ ሆኖም ምዕራባውያን የኢትዮጵያን ሁኔታ በቅጡ አልተረዱም የሚለውን ስሞታ ከመሠረቱ ለማረቅ፣ እንዲህ ያሉ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ሲገኙ አጋጣሚውን ተጠቅሞ ያለውን ነገር ማስረዳት እንደሚያስፈልግ የሚሞግቱም አሉ፡፡
በዚህ ሁሉ ፅንፍ የረገጠ የሐሳብ ገበያ መካከል ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ልዩ ልዑኩ ይዘው የመጡትን አጀንዳ ለማስፈጸም ዳገት እንደሚበዛባቸው እየተገለጸ ቢሆንም፣ ጉብኝቱን ተከትሎ ለመንግሥታቸው የሚያቀርቡት የሪፖርት ውጤት ግን የሁለቱን አገሮች ቀጣይ የግንኙነት አቅጣጫ የሚያመላክት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡