ኦሊምፒያድ የሚባለው የበጋ ኦሊምፒክ ጨዋታ በቶኪዮ ከተማ (ጃፓን) ተፈጽሞ የኦሊምፒክ ሰንደቅ ዓላማ እ.ኤ.ኤ. በ2024 ማለትም ከሦስት ዓመት በኋላ ሠላሳ ሦስተኛውን ኦሊምፒያድ ለምታዘጋጀው ለፓሪስ (ፈረንሣይ) ከተማ ተላልፏል፡፡ የኦሊምፒክ ጨዋታ የሚባለው የበጋውና የክረምቱን ሲያጣምር ነው፡፡ የፓሪስ ከተማ ለመጨረሻ ጊዜ ኦሊምፒያድ ያዘጋጀችው እ.ኤ.አ. 1924 ስለሆነ ከሦስት ዓመት በኋላ መቶኛውን ዓመት ታከብራለች ማለት ነው፡፡ እኛም ኢትዮጵያውያን ከኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ጋር የተዛመድነው እ.ኤ.አ. በ1924 ስለሆነ ፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ መቶኛ ዓመታችንን እናከብራለን፡፡
እ.ኤ.አ. በ1924 ነበር የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴን (አይኦሲ) የመሠረቱትና ከክርስቶስ ልደት በፊት 776 ዓመት ለመጨረሻ ጊዜ በኦሊምፒያ ከተማ በግሪክ አገር ይካሄድ የነበረውን የኦሊምፒክ ጨዋታ ነፍስ በመዝራት የሚታወቁት ባሮን ፒዮር ደኩበርተን፣ ልዑል ራስ ተፈሪ መኰንንን ጋብዘዋቸው ነው በፓሪስ ኦሊምፒያድ ላይ የተገኙት፡፡ ከልዑልነታቸውም ጋር ለመጀመርያ ጊዜ በኦሊምፒክ ጨዋታ የተገኙት ኢትዮጵያውያን እነኚህ ናቸው፡፡ ራስ ኃይሉ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ ሥዩም መንገሻ፣ ራስ ጉግሣ አርአያ፣ ራስ ናደው አባወሎ፣ ደጃዝማች ገብረ ሥላሴ፣ ደጃዝማች ኃይለ ሥላሴ ዓባይነህ፣ ደጃዝማች ሙሉጌታ ይገዙ፣ ብላታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፣ አቶ ሳህሌ ጸዳሉ፣ አቶ ብርሃኑ ማርቆስ፣ ልጅ መኰንን እንዳልካቸው፣ አቶ ተስፋዬ ተገኝና ሊጋባ ወዳጄ ውቤ ነበሩ፡፡
ልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን ከፓሪስ እንደተመለሱ ኢትዮጵያ በአይኦሲ እንድትታወቅና የኢትዮጵያ ወጣቶች እ.ኤ.አ. በ1928 አምስተርዳም (ሆላንድ) ላይ በሚካሄደው ኦሊምፒክ ላይ እንዲካፈሉ ጥረት አድርገዋል፣ ነገር ግን አልተሳካም፡፡ ባሮን ፒዮር ደኩበርተንን የተካው ፕሬዚዳንት የቤልዢክ ተወላጁ ለኮንት ደባዬ ላቱርን አዲስ አበባ በሚገኘው የቤልጂንግ ኤምባሲ በኩል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የልዑሉን መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡ ዳሩ ግን አፍሪካ ዘመናዊ ስፖርትን እዚያው እንዲለማመዱ በማለት መልስ ሰጡ፡፡ የዘር ልዩነት በስፖርት የጀመረው ደባዬ ላቱር ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1948 ነው ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በነጋሪት ጋዜጣ የስፖርት ኮንፌዴሬሽን ያቋቋሙት ከአንቀጾቹ አንዱ የኦሊምፒከ ኮሚቴ እንዲቋቋምና ኢትዮጵያዊያን በኦሊምፒክ ጨዋታ እንዲካፈሉ ማድረግ ነው ይላል፡፡
የኮንፌዴሬሽኑ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ከዚህ የሚቀጥለው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ጄኔራል ዓብይ አበበ፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ፊታውራሪ ደምሴ ወልደ አማኑኤል፣ አባሎች ኮሎኔል ክፍሌ ዕርገቱ፣ ሙሴ ኤድዋር ቪርቪሊስ፣ ሙሴ ካቺክ ቦጎሲያን፣ ዋና ጸሐፊ አቶ ዓምደ ሚካኤል ደሳለኝ፣ ገንዘብ ያዥ ሻለቃ ኮስትሮፍ ቦጎሲያን ነበሩ፡፡
ሙሴ ኤድዋር ቨርቪሊስ አዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የግሪክ ተወላጅ ስለ ኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ከሁሉም የተሻለ ዕውቀት ስላላቸው ኢትዮጵያን በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንድትታወቅ ኃላፊነቱ ተሰጣቸው፡፡ እርሳቸውም ለብዙ ዓመታት ከተጻጻፉ በኋላ እ.ኤ.አ. በ1954 እንደ አጋጣሚ አቴን ላይ የተሰበሰበው የአይኦሲ ጉባዔ ኢትዮጵያን በአባልነት ተቀበለ፡፡
ለዚህም ውሳኔ አስፈላጊ የነበሩት ሰነዶች በአምስት ኢንተርናሽናል ፌዴሬሽኖች መታወቅ ነበር፡፡ በመጀመርያ ዕውቅና የተገኘላቸው የስፖርት ፌዴሬሽኖች እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቦክስ፣ ብክሌትና ቅርጫት ኳስ ነበሩ፡፡ ሙሴ ቪርቪሊስ የኮንፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ ሆነው ያገለገሉ፣ ከኢትዮጰያ ኦሊምፒክ ቡድን ጋር ለመጀመርያ ጊዜ እ.ኤ.አ. በ1956 በሜልቡርን (አውስትራሊያ) ኦሊምፒክ ላይ የተገኙ ናቸው፡፡
የኦሊምፒኩ ልዑካን መሪ የነበሩት ከዓመታት በፊት ለክብር ዘበኛ እነኛን ትልልቅ ፈረሶች ለመግዛት አውስትራሊያ ሄዴው የነበሩት ሻለቃ (በኋላ ኮሎኔል) ኮስትሮል ቦጎሲያን ናቸው፡፡ የአውስትራሊያው ጉዞ የተካሄደው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በጃንሆይ ፈቃድ ባዋሰው ዲሲ3 አውሮፕላን ሲሆን፣ መቶ ሃምሳ ሰባት ሰዓት በዘጠኝ ቀን ውስጥ ከበረሩ በኋላ ነው ሜልቡርን የደረሱት፡፡
ከአትሌቶቹ መካከል የ200፣ 400 እና 800 ሜትር ሯጮች ነበሩ፡፡ የስፖርት ኮንፌዴሬሽኑ እ.ኤ.አ. 1966 ድረስ ኢትዮጵያ በአይኦሲ ዘንድ ወክሎ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. በ1967 ነው የመጀመርው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተቋቋመው አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ፕሬዚዳንት፣ እኔ ፍቅሩ ኪዳኔ ዋና ጸሐፊ ሆነን የተመረጥነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ስለ ኢሊምፒክ ፍልስፍና ጨዋታና እንቅስቃሴ እንዲረዳ በማለት እ.ኤ.አ. በ1960 ‹‹የኦሊምፒክ ጨዋታ›› የሚል መጽሐፌን አሳትሜ ሐምሌ 16 ቤተ መንግሥት ሄጄ ለጃንሆይ አበረከትኩ፡፡ የማተሚያ ቤቱን ወጪ እንዳልከፈልኩ ነግሬያቸው አባ ሃና እንዲከፍሉልኝ ታዘዙ፡፡ አባ ሃናን ያኔ በጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ ኩዴታ ላይ ስለተገደሉ ትዕዛዙ ሳይፈጸም ቀረ፡፡ እኔው ራሴ ከፍዬ ወደ አምስት ሺሕ የሚጠጋ መጽሐፍ ለትምህርት ሚኒስቴር በየተማሪ ቤቱ እንዲታደል አስረከብኩ፡፡
የኢትዮጵያን የኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ድራሹን ያጠፋው ኮሙዩኒስት ነን ባዮች ደርጎች ናቸው፡፡ እኛ የነጮቹን ደቡብ አፍሪካ ከዓለም ስፖርት ድርጅቶች እንዲታገዱ ካደረገን በኋላ፣ የኒውዚላንድ ራግቢ ቡድን ለወዳጅነት ግጥሚያ ደቡብ አፍሪካ ሄዶ ስለነበረ ከሞንትሪያል ኦሊምፒክ እንዲታገድ ቀበጦች የሆኑ የአፍሪካ ስፖርት መሪዎች ጠይቀው ስላልተሳካላቸው አፍሪካ መውጣት አለበት የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ፡፡ ያለ ሴኔጋልና ኮት ዲቭዋር በቀር እ.ኤ.አ. በ1976 ሞንትሪያል በተዘጋጀው ኦሊምፒክ የተካፈለ የአፍሪካ አገር የለም፡፡ ሴዳር ሴንጎር እና ሑፍዌት ባኚ በአዕምሯቸው የሚጠቀሙ ፕሬዚዳንቶች ነበሩ፡፡ የተወሰደው ዕርምጃ ስህተት መሆኑን አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ለደርግ ቢያስረዳም ጆሯቸው የተደፈነ ስለሆነ ሊሰሙት አልቻሉም፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ አሜሪካ እ.ኤ.አ. በ1980 የሶቪየት ኅብረት ሞስኮ ላይ ባዘጋጀችው 22ኛው ኦሊምፒያድ ላይ ስላልተካፈለች በተራቸው የኮሙዩኒስት አገሮች ኢትዮጵያ ጭምር እ.ኤ.አ. በ1984 ሎስ አንጀለስ ከተማ በተዘጋጀው 23ኛው ኦሊምፒያድ አንካፈልም አሉ፡፡ ከዚያም ደርጎች የሰሜን ኮሪያ ወዳጅ ሆነው እ.ኤ.አ. በ1988 ሴውል ደቡብ ኮሪያ ላይ በተዘጋጀው 24ኛው ኦሊምፒያድ ኢትዮጵያ እንዳትካፈል ከለከሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1951 እስከ 1953 ድረስ በኮሪያ ጦርነት የቃኘው ሻለቃ የክብር ዘበኛ ጦር አፈር ድሜ ካስበላት ሰሜን ኮሪያ ጋር ወዳጅ ሆነው አዋረዱን፡፡
ወደ ኦሊምፒክ ጨዋታ የተመለስነው እ.ኤ.አ. በ1992 በባርሴሎና ስፔን ደራርቱ ቱሉ በአሥር ሺሕ ሜትር ሩጫ የወርቅ ሜዳሊያ ያጠለቀች ጊዜ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ የዘር ልዩነት ጠፍቶ ኔልሰን ማንዴላ በተገኙበት አገራቸው ወደ ኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ተመልሳ ሁለተኛ የወጣችው ኤሌና ማያር ከደራርቱ ቱሉ ጋር ተቃቅፈው ስታዲዮሙን ሲዞሩ መላው ዓለም ነው ያደነቀው፡፡ አንድ ጥቁርና አንድ ነጭ አትሌቶች አብረው ማየቱ የዘር ልዩነት መጥፋቱንና የአፍሪካን አንድነት የሚያመላክት ነበር፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም እንድታወቅና እንድትከበር ያደረጉ የኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮኖች ሁላችንም የምንኮራባቸው አትሌቶች ናቸው፡፡ ከአበበ ቢቂላ፣ ከማሞ ወልዴ አንስቶ እነ ምሩፅ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ሰለሞን ባረጋ፤ ከሴቶች ደራርቱ ቱሉ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሠረት ደፋር፣ አልማዝ አያና፣ ለተሰንበት ግደይ የዓለም አሥርና አምስት ሺሕ ሜትርን ሪኮርድ ባለቤትነት ድረስ በብዙ ቀልጣፋ አትሌቶች ብርታት ነው፡፡
በእኛ ዘመን አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የመንግሥታችንን አቅም ስለሚያውቅ በኦሊምፒክ ጨዋታ ለመካፈል የሚጠይቀው በጀት የተወሰነ ስለሆነ ሁሉንም ማስደሰት አይቻልም ነበር፡፡ እኔ ራሴ ዕድሜ ልኬን የኢትዮጵያን ስፖርት ያገለገልኩት ወጪዬን ችዬ ነው፡፡ ማስታወስ ያለብን በመጀመርያ ዓመታት የኢትዮጵያ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን በጄት ሃያ ስምንት ሺሕ ብር ነበር፡፡ የባጀቱ ዝርዝር ወጪ እንደሚያመለክተው፣ ለቴሌፎን ኪራይ በወር ስምንት ብር፣ ለተቀዳ ውኃ አሥር ብር፣ ለኤሌክትሪክ አሥራ አምስት ብር፣ ለፖስታ ሣጥን ኪራይ በዓመት ሠላሳ ብር፣ ለቴሌግራፍ አድራሻ ሃያ ብር፣ ለኢንተርናሽናል ፌዴሬሽኖች የዓመት መዋጮ አምስት መቶ ብር፣ የፖስታ ቴምብር አሥራ አምስት ብር በወር፣ ወዘተ በብሔራዊ ፌዴሬሽኖቹ መሪዎች ብርታት የተፈጸሙት ክንውኖች የሚያስመሰግኑ ነበሩ፡፡ ምንም ደሃ ብንሆንም በዕውቀታችን በመጠቀም እንቅፋቶችን እናስወገድ ነበር፡፡
አቶ ይድነቃቸው ተሰማ የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ተማሪ ስለነበረ ከጦርነቱ በኋላ የኢትዮጵያን ፉትቦል ፌዴሬሽን ሲመሠርት በሥራ አስኪያጁ ኮሚቴ ውስጥ እንዲያገለግሉ የመረጣቸው ወዳጆቹንም ጭምር ነው፡፡ ሌተና ጄኔራል ከበደ ገብሬ፣ ሌተና ጄኔራል ነጋ ኃይለ ሥላሴ፣ ኮሎኔል አበበ ደገፉ፣ ኮሎኔል ታምራት ይገዙ፣ ሌተና ጄኔራል ወልደ ሥላሴ በረካ፣ ሜጀር ጄኔራል ኃይሌ ባይከዳኝ፣ ጄኔራል ወልደ ዮሐንስ ሽታ፣ ጄኔራል ጋሻው ከበደ፣ ጄኔራል ጽጌ ዲቡ፣ አቶ ማሞ ታደሰ፣ አቶ ሥዩም ሐረጎት፣ አቶ ከተማ ይፍሩ፣ አቶ ሰይፉ ማኅተመ ሥላሴ፣ አቶ አብተው ገብረየሱስ፣ ልጅ እንዳልካቸው መኰንን፣ አቶ ከበደ ሚካኤል፣ ልጅ ካሳ ወልደማርያምና ብዙ ታዋቂ ቤተሰቦች ነበሩ፡፡
የኢትዮጵያ ስፖርት አማተር እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ስብሰባ ሲመጣ የራሱን ሻይ ከፍሎ የሚጠጣ ነበር፡፡ የሚሰጠው አገልግሎት ሁሉንም ወጪ ችሎ ነው፡፡ በሌሎች ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ውስጥ ያገለግሉ የነበሩትም በዚሁ መንፈስ ነበር፡፡ እኔ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የብስክሌት ፌዴሬሽን፣ የቴኒስ ፌዴሬሽን፣ የሸዋ ፉትቦል ሊግ ዋና ጸሐፊ የፉትቦል ፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሆኜ ስላገለገልኩ አብረውኝ ይሠሩ የነበሩ ሁሉ የሚደነቁ፣ አገራቸውን የሚወዱና የስፖርቱ ሕይወት እንዲበለፅግ የሚታገሉ ንፁህ ኢትዮጵያውን መሆናቸውን አረጋግጣለሁ፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ስፖርት ቅጡ የጠፋው የስፖርት ሚኒስቴሩ ወይም ኮሚሽኑ የሥራ ፈቶችና የጡረታ ጠባቂዎች መሰብሰቢያ ስለሆነ ነው፡፡
የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክና ኢትዮጵያ
የኦሊምፒክ ኮሚቴ የተወዳዳሪዎች ምርጫ ውስጥ ምንም አያገባውም፡፡ ቶኪዮ የተፈጠረውን ረብሻ እየተከታተሉ ጨዋነታቸው ላይ ተመርኩዘው የተወዳደሩ የኢትዮጵያ አትሌቶች ብቻ ናቸው፡፡ ተቸግረውም ቢሆን ባለው አቅማቸው የሚቻላቸውን ያህል በመጣር ውድድራቸውን ጨርሰዋል፡፡ ለሁሉም ምስጋናና አክብሮት ይገባቸዋል፡፡ ትልቁ ችግራችን ኢትዮጵያ ውስጥ አሠልጣኞች ማጣት ነው፡፡ ቶኪዮ ላይ ውድድራቸውን ሳይጨርሱ የወጡትና ሜዳ ላይ ማጣሪያውን ማለፍ ያቃታቸው፣ ሙቀቱን ሳይለማመዱ በመቅረታቸው አንዱ ምክንያት ሲሆን፣ የቴክኒክ ስህተትም ሁለተኛው ነው፡፡ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠንቋይ ጠይቆ እንደሆነ አላውቅም አትሌቶቹን በመከፋፈል ነው ወደ ኦሊምፒክ ከተማ የሚልከው፡፡ ይህም ትልቅ ስህተት ነው፡፡
በእኛ ዘመን አትሌቶቹ በሙሉ አብረው ነው የሚሄዱት፡፡ ወጪያቸውን አዘጋጂው አገር ስለሚከፍል ምንም ችግር የለም፡፡ ይልቁን በእኛ ዘመን ራሳችን ነበር የምንከፍለው፡፡ ማራቶን ሯጮቹ ቀደም ብለው መጥተው ሙቀቱን ቢለማመዱ ኖሮ አይዋረዱም ነበር፡፡ የሴቶች አትሌቶቻችንን ደኅንነት የሚከታተል የሴት ኃላፊ ከቡድኑ ጋር አይጓዝም፡፡ አንድ ቀን የማባለግ ዜና እንዳንሰማ እንፀልያለን፡፡
የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ደራርቱ ቱሉና የአትሌቶቹ ቡድን መሪ ዶ/ር በዛብህ ወልዴ ኦሊምፒክ መንደር እንዳይገቡ ስላስከለከላቸውና በሠላሳ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ስለቀበራቸው ነው ችግር የተፈጠረው፡፡ ለሆላንድ የምትሮጠዋ ናዝሬት ተወልዳ ያደገችው ሲፋን ሐሰን እና ለባህሬን የምትሮጠው ቃል ኪዳንን ከአገራችን ተወዳዳሪዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያን ይወዳሉ፡፡ ሲፋን ሐሰን ከኦሮሚያ ሚዲያ ጋር ስትወያይ የኢትዮጵያ ሴቶች አትሌቶች ከአሠልጣኞቻቸው ጋር የሚግባቡ አይመስለኝም ብላ ተናግራለች፡፡ በነገራችን ላይ ለልዩ ልዩ አገሮች የሚሮጡ ትውልዳቸው ኢትዮጵያዊ የሆኑ አትሌቶችን እነሆ፡፡ በማራቶን ለእስራኤል ሦስት ለአውስትራሊያ አንድ፣ ለስዊስ አንድ፣ ለጣሊያን አንድ፣ ለጀርመን አንድ፣ ለባህሬን ሁለት፣ ከኬኒያዊው ቀጥሎ ሁለተኛና (ሆላንድ) ሦስተኛ (ቤልጂክ) የወጡት ሶማሌዎች ናቸው፡፡ ድንገት የኦጋዴን ሶማሌ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ በቶኪዮ ከተማ ‹‹ኦሊምፒክ አጎራ›› ተብሎ በተሰየመ ኤግዚቢሽን ላይ ከኦሊምፒክ እንቅስቃሴ ታሪክ ውስጥ ለሌሎች አርአያ የነበሩ ሃያ ሦስት አትሌቶች የግል ማስታወሻን የጃፓን ሕዝብና የኦሊምፒክ ቤተሰብ እንዲመለከተው አድርጓል፡፡ ከሃያ ሦስቱ አትሌቶች መካከል ጀግናው አበበ ቢቂላ ይገኝበታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1960 በሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ መሮጡን የዓለም ሕዝብ ያስታውሳል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1964 በቶኪዮ ኦሊምፒክ ለመካፈል ሲዘጋጅ አሲክስ የተባለ የጃፓን ስፖርት መሣሪያ ኩባንያ ተጠሪ ኦሊምፒክ መንደር ድረስ መጥቶ አበበን፣ ‹‹በልክህ ጫማ ልሰፋልህ እፈልጋለሁ፤›› አለው፡፡ የኢትዮጵያ ቡድን መሪ በነፃ መሆኑን ካጣራ በኋላ እንዲሰፋለት ተስማሙ፡፡ በዚያ ጫማ ሮጦ ነው እንደገና ያሸነፈው፡፡ ጫማውን ያሰፉት አዛውንት ናቸው እ.ኤ.አ. በ1992 የኩባንያው ፕሬዚዳንት ሆነው ለአበበ ባሰፉት ጫማ ልክ በብር አሠርተው አንዱን ለአበበ ባለቤት በእኔ አማካይነት ባርሴሎና ድረስ የመጣች፣ ሁለተኛውን ለአይኦሲ ፕሬዚዳንት፣ ሦስተኛውን ለኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ያበረከቱት፡፡ ይህን የብር ጫማ ነው ቶኪዮ የሄዱት ቱሪስቶች ሳይጎበኙት የተመለሱት፡፡
በእኔ ዘመን አትሌቶቻችን ለኦሊምፒክ ጨዋታ የሚሄዱባትን አገር ባህሉንና ታሪኩን በአጭሩ እናስረዳ ነበር፡፡ የአይኦሲ ቴሊቪዥን ድርጅት የምርጥ አትሌቶችን ታሪክ መዝግቦ ለዓለም ሕዝብ አቅርቧል፡፡ ከመላው ዓለም ከተመረጡት አትሌቶች መካከል ባለሁለት የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ ባለቤትና የዓለም ሻምፒዮናዋን ደራርቱ ቱሉ አሸብር የሚያንገላታት ትገኝበታለች፡፡ የአይኦሲ ቴሌቪዥን ቡድን ኢትዮጵያ ድረስ ተጉዞ በአዲስ አበባና በበቆጂ ሃያ ስድስት ደቂቃ የሚሆን የሕይወት ታሪኳን በፊልም ቀርፆ አሠራጭቷል፡፡
አንዱ ችግራችን የእኛ አትሌቶች የእንግሊዝኛ ቋንቋን በደንብ ያለ ማወቅ ነው፡፡ ልክ እንደ ሌሎች አገሮች የስፖርት ልምምድን እያከናወኑ ሊማሩም ይችላሉ፡፡ መሮጥ፣ መዝለልና መወርወር ቢያቆም በጣም የሚያገለግላቸው በትምህርት የገበዩት ዕውቀት መሆኑን ማስረዳት የስፖርት መሪዎቹ ኃላፊነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የስፖርት መሪዎች አርቆ ማስተዋል ይሳናቸዋል፡፡
የአፍሪካ አገሮች ነፃ ከወጡ በኋላ በመጀመርያ የተካፈሉበት የኦሊምፒክ ጨዋታ እ.ኤ.አ. በ1964 በቶኪዮ በተዘጋጀው 18ኛ ኦሊምፒያድ ነበር፡፡ የጋና ልዑካን ቡድን የአገር ልብስ ለብሶ መሠለፉን አይተን እኛም እ.ኤ.አ. በ1968 ሜክሲኮ ኦሊምፒክ ላይ እንለብሳለን ብለን ወሰንን፡፡ መከራው በተሰጠን ባጀት ተስፋዬ ዘለለው ዘንድ ሱፍ ልብስ አሰፍተን ጨረስነው፡፡ አንድ ግብዣ ላይ ስለሜክሲኮ ጉዞ ሳወራ የአገር ልብስ ለማሰፋት የገጠመንን ችግር አስረዳሁ፡፡ ከተጋባዦቹ አንዱ ነፍሱን ይማረው አቶ ደበበ ሀብተ ዮሐንስ የአዲስ አበባ ባንክ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ እኔ አሠፋላችኋለሁ በማለት ቃል ገባ፡፡
ወደ ሜክሲኮ ለሚጓዘው ለብሔራዊ ቴአትር ቡድን፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን፣ በአቶ አለ ፈለገ ሰላም አማካይነት ዕድሜያቸው ከአሥራ ሁለት ዓመት በታች የሆነ የሥዕል ውድድር አሸናፊ እና ለኦሊምፒክ ቡድኑ በጠቅላላው ወደ ስድሳ ለሚደርስ ልዑካን የአገር ልብስ አሰፍቶልን እንድንኮራና እንድንንቀባረር አድርጎናል፡፡ በለውጡ የምስጋና ደብዳቤ ደርሶታል፡፡
መንግሥት ጣልቃ መግባት የለበትም የሚል ተረት ብዙ ጊዜ እሰማለሁ፡፡ በዓለም ውስጥ ለተቋቋሙ የስፖርት ማኅበሮች ዕውቅና የሚሰጡ መንግሥታቱ ናቸው፡፡ ስፖርት በየአገሩ እንዲስፋፋ ኃላፊነት ያለባቸው መንግሥታት ናቸው፡፡ አስፈላጊውን ባጀት የሚፈቀዱ ፓርላማዎች ናቸው፡፡ የኦሊምፒክ ጨዋታ በሚዘጋጅበት አገር ኃላፊነቱን የሚረከብ መንግሥት ነው፡፡ አጭበርባሪዎች ብቻ ናቸው መንግሥት ጣልቃ መግባት የለበትም የሚሉት፡፡ የኦሊምፒክ ኮሚቴን የሚመርጡት ስፖርታቸው በኦሊምፒክ ፕሮግራም ላይ የሚገኙ ስፖርት ፌዴሬሽኖች ናቸው፡፡ አሸብርን ሊያባርሩ ይችላሉ፡፡ መከራው ከስፖርት ኮሚሽኑ አንስቶ አብዛኛዎቹን ወረቀት ላይ ብቻ የሚገኙ ፌዴሬሽኖች በሙስና ወጥመድ የተያዙ ስለሆኑ እንዲነግሥ አድርገውታል፡፡ ወደፊት ከቦሊንግ ሌላ የዳማ፣ የራሚኖ ካርታ ጨዋታ፣ የእንቆቅልሽ ፌዴሬሽኖች እንዲቋቋሙ መጣሩ አይቀርም፡፡
አሸብር በበኩሉ ጠርቶ ለኦሊምፒክ ኮሚቴ ሳይመረጥ የሾመው ምክትል ፕሬዚዳንት ኃይሌ ገብረሥላሴ መሆኑ በጣም ያሳፍራል፡፡ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆና ሰባት ፎቅ ሕንፃ የገነባች፣ የገቢ ምንጭ ይሆን ዘንድ ሆቴል የገዛች፣ በስታዲየም አጠገብ የአትሌቶች ማማሟቂያ ሜዳ ያሠራች በአፍሪካና በዓለም ደረጃ የታወቀችው ወ/ሮ ብስራት ጋሻውጠና ነች፡፡ በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ውስጥ ይህን የመሰለ ግዳጅ ያከናወነ መሪ እሷ ብቻ ነች፡፡ ስለዚህ ወ/ሮ ብሥራት ጋሻውጠናን የመሰሉ መሪዎች ስፖርቱን እንዲረከቡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
አሸብር የኦሊምፒክ ኮሚቴ ሠራተኞችን አባሮ በዘመዶቹ መተካቱ ይነገራል፡፡ ዋናው ግፍ ግን አይኦሲ ስኮላርሺፕ ሰጥቶ በሩሲያ ሶቺ ከተማ ውስጥ በሚገኘው የኦሊምፒክ ዩኒቨርሲቲ ለመማር የሄደውን አቶ ዳንኤል ክፍሌን በማባረር ቤተሰቦቹን በደመወዙ እንዳይረዳ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ያገለገለውን አቶ ታምራት በቀለንም አሰናብተዋል፡፡ ያልቀየረው ዘበኛውን ብቻ ነው፡፡ እሱም አይቀርለትም፡፡
አሸብር ሳንድዊች የሚያጎርሳቸው ጋዜጠኞች የእሱን ክንውኖች የሚያሠራጩ ናቸው፡፡ ከቶኪዮ ሲመለስ የተቀበሏቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ይዘውት የነበረው ፎቶግራፋቸው ያለበት ሰሌዳ ‹‹ሞያቸውን ለጥቅማቸው የሸጡ ‘ጋዜጠኞች‘›› ይላል፡፡ አንድ ጊዜ አንዱን ጋዜጠኛ ለምን አትጽፍም ብዬ ብጠይቀው፣ ‹‹ተወኝ ልጆቼን ላሳድግበት…፤›› የሚል መልስ ሰንዝሯል፡፡ ኢትዮጵያ በአካባቢ ላይ የተመሠረተ ምርጫ ካልከለከለች በስተቀር ምንም መሻሻል አይኖርም፡፡
ለማንኛውም የኢትዮጵያን ስፖርት የሚመሩ ሁሉ የሥነ ምግባርን ምርመራ ማለፍ አለባቸው፡፡ ከፍርድ ሚኒስቴር ወይም ከፖሊስ ኮሚሳሪያት ከወንጀል ነፃ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ያሻል፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያ በዘሩ ሳይሆን በችሎታው ብቻ ተመርጦ ማገልገል አለበት፡፡ ደራርቱ ቱሉም ሆነች እኛ ታዛቢዎች መንግሥት አለ ወይ ብለን እስከ መጠየቅ የደረስነው እንደ አሸብር ዓይነት ‹‹ያለ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን ሊመራ የሚችል ሰው የለም›› በማለት ሲፎክር የነበረውና እስር ቤት የሚገኙት የሕወሓት እስረኞች የስብሐትና የተክለወይኒ ሽርካ የኢትዮጵያን ስፖርት ሲያመሰቃቅል መንግሥት ዝም ብሎ በመታዘቡ ነው፡፡
አሸብር የብልፅግና ፓርቲ አባል ሆኖ በአነ አባዱላ አማካይነት ስለተመረጠ የሚነካው ሰው የለም ይባላል፡፡ እውነትም የዓብይ አህመድ ፓርቲ አባሎች የኢሕአዴግንና የሕወሓትን ጭፍራዎች አቅፎ አገራችንን የማንም መጨፈሪያ ካደረገ መቃወማችን አይቀርም፡፡ በቱሪዝም ሚኒስትሯ የተመረቁ ቶኪዮ ይዘዋቸው ከሄዱት ቱሪስቶች መካከል ከቦሊንጉ ተጠሪ በስተቀር የአማራ ክልል ስፖርት ተጠሪ ይገኝበታል፡፡
ለማንኛውም ክብርት የኢትዮጵያ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት እመቤት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ በጠየቁት መሠረት፣ የቱሪዝም ሚኒስትሯና ኮሚሽነሮቹ የኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ የአትሌቲክስ፣ የዋና፣ የብስክሌትና የቴኳንዶ ፌዴሬኖች ሪፖርት ማቅረብ አለባቸው፡፡ ክብርት ፕሬዚዳንቷን የምንጠይቀው ሪፖርቶቹ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይፋ እንዲሆኑና አስፈላጊ ዕርምጃ እንዲወሰድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ስፖርትና ማኅበራዊ ድርጅቶች ውስጥ እንዳይካፈል መንግሥት እንዲከለክለውና ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠው ምኞታችን ነው፡፡
የቶኪዮ ኦሊምፒክን በሜዳሊያ ብዛት አሜሪካ አንደኛ፣ ቻይና ሁለተኛ፣ ጃፓን ሦስተኛ፣ ኬንያ አሥራ ዘጠነኛ፣ ዑጋንዳ ስድሳ ስድስተኛ፣ ደቡብ አፍሪካ ሃምሳ ሁለተኛ፣ ግብፅ ሃምሳ አራተኛ፣ ኢትዮጵያ ሃምሳ ስድስተኛ፣ ቱኒዝያ ሃምሳ ስምንተኛ፣ ሞሮኮ ስድሳ ሦስተኛ፣ ናይጄሪያ ሰባ አራተኛ፣ ናምቢያ ሰባ ሰባተኛ፣ ቦትስዋና፣ ቡርኪናፋሶ፣ ኮትዲቮርና ጋና ሰማንያ ስድስተኛ ወጥተዋል፡፡፡ ከሁለት መቶ ስድስት ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ሰማንያ ስድስቱ ሜዳሊያ ተቀብለዋል፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ከጋዜጠኝነታቸው ባሻገር በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ የስፖርትና የኦሊምፒክ ተቋማት ከ1950ዎቹ ጀምሮ ከሰጧቸው ሁለገብ አገልግሎቶች መካከል በውጭ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊና አማካሪ፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት አማካሪ ነበሩ፡፡ እንዲሁም ለአሥራ አራት ዓመት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በማስታወቂያ ክፍል የሠሩና በኒውዮርክ የድርጅቱ ጠቅላላ ጉባዔ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ተጠሪ ሆነው ለብዙ ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በአገር ውስጥ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ፣ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሕዝብ ግንኙነት ሆነው ያገለገሉባቸው ይገኙበታል፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡