Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊፈጣን አገራዊ ምላሽ የሚጠይቀው የኮቪድ-19 ሥርጭት

ፈጣን አገራዊ ምላሽ የሚጠይቀው የኮቪድ-19 ሥርጭት

ቀን:

ላለፉት ጥቂት ወራት የኮቪድ-19 የሦስተኛ ዙር ወረርሽኝ ሥርጭት የቀነሰ መስሎ ቢታይም፣ በአሁኑ ወቅት ሥርጭቱ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ በመሆኑ አሥጊ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የበሽታውን ሥርጭት ለመግታት በመንግሥት በኩል እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አዎንታዊ ቢሆንም ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚወጡ መረጃዎች በኮቪድ-19 በሽታ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት እያደገ መሆኑን የጤና ሙያ ማኅበራት አስታውቀዋል፡፡

‹‹የኮቪድ-19 የሦስተኛ ዙር ወረርሽኝ የፈጠረው አሥጊ ሁኔታና ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመግታት አሁንም የተጠናከረና የተቀናጀ ፈጣን አገራዊ ምላሽ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን፤›› በሚል አሥራ አንድ የጤና ሙያ ማኅበራት ነሐሴ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ሁለተኛ ሳምንት ጀምሮ ባለው አንድ ወር ጊዜ ውስጥ ሪፖርት የተደረገው ወርኃዊ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 2,797 ነው፡፡

ይህም ከሐምሌ ሁለተኛ ሳምንታት ጀምሮ ካለው ተመሳሳይ ወቅት በአምስት እጥፍ አድጎ ወደ 13,122 እንዳሻቀበ ነው የተመለከተው፡፡

በተጨማሪም ከላይ በተጠቀሱት ጊዜያት በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥር ከ81 ወደ 138 በማደግ የ41 በመቶ እንዲሁም በተመሳሳይ የኮቪድ-19 ጽኑ ሕሙማን ቁጥር ከላይ በተገለጹት ጊዜያት በአማካይ በቀን 148 የነበረው ወደ 265 በማሻቀብ የ44.2 በመቶ ጭማሪ እንዳሳዩ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ መንገዶች (የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መጠቀም፣ ርቀትን መጠበቅ፣ የእጅ ንፅህና መጠበቅና የሕመም ምልክት ሲኖር ራስን መለየት) ትግበራ መዘናጋት ለኮቪድ-19 ሥርጭት መጠን መጨመር ምክንያት እንደሆነ ከመግለጫው ለመረዳት ተችሏል፡፡

በመግለጫው መሠረት፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በ15 ከተሞች ላይ ባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎችና በ48 ትምህርት ቤቶች ላይ ከጥቅምት ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ተከታታይ 38 ሳምንታት በተደረገ ምልከታና ክትትል ጥናት አማካይ የእጅ ንፅህና አጠባበቅ ከአሥር በመቶ በታች፣ የአካላዊ መራራቅ ትግበራ ከ25 በመቶ በታች እንዲሁም የአፍና አፍንጫ  ጭምብል አጠቃቀም 58 በመቶ ሆኖ ታይቷል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ምልክታ ከተደረገባቸው አሽከርካሪዎችና ረዳቶቻቸው መካከል የአፍና አፍንጫ አጠቃቀም ሲታይ በተከታታይ 50 በመቶና 32 በመቶ እንደሆነ አሳይቷል፡፡

ከአዲስ አበባ ውጭ የሚገኙ አሽከርካሪዎችና ረዳቶቻቸው የአፍና አፍንጫ ጭምብል አጠቃቀም በተከታታይ 14 በመቶ እና 5 በመቶ ደረጃ ላይ መሆኑ ምልከታ ጥናቱ አሳይቷል፡፡ ምልከታ ከተደረገባቸው ትምህርት ቤቶች የአፍና አፍንጫ ጭምብል ትግበራ በአዲስ አበባ 75 በመቶ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ትምህርት ቤቶች 35 በመቶ ሆኖ ታይቷል፡፡ የእጅ ንፅህና አጠባበቅ ደግሞ በአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች 18 በመቶ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ትምህርት ቤቶች ከአራት በመቶ በታች ሆኖ መታየቱን መግለጫው ሳይጠቁም አላለፈም፡፡

የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ፣ ሕክምናና ሚድዋይፎች፣ ነርሶች፣ የኅብረተሰብ ጤና አጠባበቅ መኮንኖች፣ የአካባቢ ጤና ባለሙያዎች፣ የፋርማሲ፣ የሳይኮሎጂ ባለሙያዎች፣ ሕክምና ላቦራቶሪ፣ አኒስተቲስቶችና የጥርስ ሕክምና ባለሙያ ማኅበራት በጋራ ካወጡት ከዚሁ መግለጫ ለመረዳት እንደተቻለው ለኅብረተሰቡ የሚሰጠው ትምህርትና የተጋላጭነት ተግባቦት እንዳለ ሆኖ ቀደም ብሎ በየአደባባዩ የነበሩት የጋራ የእጅ መታጠቢያ አገልግሎቶች ወደ ቦታቸው ተመልሰው አገልግሎት እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የሕዝብ ስብሰባዎችና የመንገድ ላይ ትዕይንቶች ለምሳሌ እንደ ስፖርት ጨዋታዎች፣ የሙዚቃ ድግሶች፣ የምሽት ቤት ጭፈራዎችና ሰላማዊ ሠልፎች፣ በገበያ ቦታዎች የሚታዩ ከፍተኛ የአደባባይም ሆኑ ሃይማኖታዊ በዓላት፣ ለሠርግና በዓል ዝግጅት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች በሙሉ የቫይረሱን ሥርጭት የበለጠ በመጨመር አሥጊ ደረጃ ላይ የሚያደርሱት መሆኑን መንግሥት ሊገነዘበው እንደሚገባ በመጠቆም ካሁን ቀደም ጤና ሚኒስቴር ባወጣው የኮቪድ-19 መመርያ መሠረት ወቅቱን የጠበቀ ተከታታይና ሕጋዊ ዕርምጃዎች እንዲወስድ አስገንዝበዋል፡፡

ከፍተኛ ኃላፊዎችና ሌሎች አስፈጻሚ አካላት የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች በትክክለኛው መንገድ በመተግበርና አርዓያ በመሆን ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ የሙያ ማኅበራቱ በመግለጫቸው ላይ አሳስበዋል፡፡

የኮቪድ-19 ጽኑ ሕሙማን ቁጥር በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ በመሆኑ እንደ ኦክስጅን ያሉ ዋነኛ የጽኑ ሕሙማን ክፍል ግብዓት በአገር ውስጥ በበቂ ለማምረት እንዲቻል በምርት ሒደት ለሚያጋጥሙ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ እንዲሰጥ ሊገነዘቡ እንደሚገባ፣ ብቸኛውና በሁሉም ረገድ ለአገራችን አዋጭ የሆነው መከላከል መሆኑን ተገንዝበን ተቀዛቅዞ የቆየው የማኅበረሰብ ንቅናቄ ማቀጣጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

አሁን እንደሚታየው በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በየጊዜው መጨመር የጤና አገልግሎቱ ሊሸከመው ከሚችለው በላይ ከመሆኑ በፊት በመከላከያ መንገዶች ላይ ትኩረት ማድረግ የግድ ስለሚል የማኅበረሰብ ንቅናቄን ማቀጣጠልና ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ አካላት ማኅበረሰቡን ስለኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከያ መንገዶች ማስተማራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ፣ የመገናኛ ብዙኃንም ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው በችግሩ ስፋት ልክ በመዘገብ ማኅበረሰቡ እንዲገነዘበው በማድረግ ረገድ በቂ ሽፋን እንዲሰጡ ምክራቸውን ሳይለግሱ አላለፉም፡፡

ካሁን ቀደም በሌሎች አገሮች የተከሰተውና በፈጣን መንገድ ይሠራጫል ተብሎ የሚታመነው አዲስ የኮቪድ-19 ልውጥ ዝርያ (ዴልታ ቫሪያንት) ወደ አገር ውስጥ ዘልቆ በኅብረተሰቡ ውስጥ እየተሠራጨ ሊሆን ስለሚችል፣ ወቅታዊና ሳይንሳዊ (ጄኔቲክ ስተዲ) ጥናት ለማካሄድ መንግሥት የጀመረውን ጥረት እንዲያፋጥን በግኝቱም መሠረት አቅም የማሳደግ ሥራ እንዲተገበር መክረዋል፡፡

የኮቪድ-19 ክትባት በተመለከተ ተደራሽነቱ እንዲጨምር ተጨማሪ ተግባራት መከናወን ይኖርባቸዋል ያሉት ማኅበራቱ ክትባቱን የወሰዱት ከአጠቃላይ የሕዝብ ብዛት ከሁለት በመቶ የማይበልጡ በመሆኑ አቅርቦቱን በመጨመርና የተለያዩ የክትባት ዓይነቶች እንዲገቡ መንግሥት ያላሰለሰ ጥረት እንዲያደርግ አበክረው ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...