Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

​​​​​​​የውርደት ፍፃሜ!

ሰላም! ሰላም! አዲስ ያልነው ዓመት እንደ ቀልድ ይኼው አሮጌ ሊባል እየገሰገሰ አይደል? ይገርማል! “እኛ የአሜሪካ መሰሪነት ከብዶናል ዓመቱ ግን መፈራረቁን ቀጥሏል…በማለት ሰሞኑን በሐሳብ ሲብሰለሰል የሰነበተው አንዱ የእኔ ቢጤ ደላላ ነው። እንዲህ ከማለቱ አብሮን የነበረ ሌላው ወዳጃችን፣እነ አሜሪካ ምን አለባቸው? የሰው አገር እያፈረሱ፣ በሰው አገር የውስጥ ጉዳይ እየፈተፈቱ፣ የአንድ አገር ሰዎችን ደም እያቃቡ፣ በመጨረሻ እንደ ቬትናምና አፍጋኒስታን ከእነ ውርደታቸው ሲባረሩ አያፍሩም…” አለን። በየምክንያቱ የምናነሳው ጉዳያችን የት ድረስ እንደሚለጠጥ አያችሁ? ከዓለም ጋር ያለን ጉዳይ ግን ኦዲት ሳያስፈልገው አይቀርም፡፡ዘመን ሲለዋወጥ የማይለዋወጠው የዚህ ክፉ ዓለም ባህሪ ብቻ ነው…እያለ የሚነግረኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣አንበርብር በዚህ ዘመን በተለይ ምን ያምርሃል ብትለኝ አገር የሚመሩ ሰዎች ቆፍጠን ብለው የዓለምን ተለዋዋጭ ባህሪ እንዲረዱ ነው፡፡ አሜሪካም ሆነች የአውሮፓ ኅብረት ልዑካኖቻቸውን ሲልኩብን እነሱን ስለኛ ጉዳይ ለማስረዳት ኢነርጂ ከመጨረስ ይልቅ፣ ምንድነው የምትፈልጉት ብሎ የሚሉትን ከሰሙ በኋላ ጥበብና ድፍረት የተሞላበት ምላሽ መስጠት ነው…ሲለኝ አባባሉ አስደመመኝ፡፡ እውነቱን እኮ ነው፡፡ መጽሐፉ “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” ይላል፡፡ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ደግሞ የፖለቲካ ጥበብ መጀመሪያ ዕውቀትና ድፍረት ነው እላለሁ፡፡ ደግሞ ለድፍረት!

ይህንን ወጋችንን ለሚቀጥለው መርሐ ግብር ይቆይ ብዬ ሐሳቤን ለወር ቀለብ የሚያስፈልግ የቤት ወጪ ዝርዝር ላይ ጣድኩት። ሰብስቦ ለመበተን ጠብ ሲል ለመድፈን አይደል የእኛ ኑሮ? በቃ! አንዱ የሠፈራችን ዘናጭ፣ ‹‹እየተለወጠ ያለውስታይላችንእንጂስታተሳችንአይደለምየሚል አባባል አለው። የሚገርማችሁ ታዲያ ከሁለቱ የእንግሊዝኛ ቃላት የማውቀውና ቶሎ የሚገባኝስታይልየሚባለው ነው።አቦስታይልይኑርህ!” “‘ስታይለኛነው እሱማለት የዘወትር ልማዳችን ስለሆነ ብቻ ሳይሆን፣ በይሉኝታ የታሰረው አኗኗራችን ውጤት ጭምር ይኼንን ቃል በደንብ እንዳውቀው ሳያግዘኝ አልቀረም መሰለኝ። ወሰብሰብ ካለው ነገር ወጥተን እንዲህ ባሉት ነገሮች ዘና ማለት ብንጀምር እኮ ቀለል ይለን ነበር፡፡ ዝም ብዬ ሳስበው የሕይወታችን መስመር ቀያሽ የሆነው አስተሳሰባችን ላይ ካልሠራን አያያዛችን አሁንም ወደፊትም አሥጊ ነው።ምን ዋጋ አለው? ዘናጭ ከተማ ገንብተው ያረጀና ያፈጀ አስተሳሰብ ሳያስተካክሉ መውረግረግ?” የምትለው ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ናት፡፡ ቆይ እስቲ ብዙ ጊዜ ስለኢንቨስትመንት ሲወራ ቁሳዊው ነገር ላይ እንበረታለን፡፡ ለአስተሳሰብና ለአመለካከት ምጥቀት ኢንቨስትመንቱ የታለ? ጥያቄ ነው ብቻ ነው የማቀርበው፡፡ ቁሳዊ ነገሮች ላይ እያተተኮረ ሰብዓዊ ዕድገቱን ወደ ጎን በመባሉ፣ ከባድ ኪሳራ እንደ ደረሰብን ማሳያው “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” መሆናችን ነው፡፡ አይደለም እንዴ!

እንደምታውቁት የዘመኑ ጨዋታ ዕድሜ ለኢንተርኔት በመረጃ ሆኗል። ምን ሆነ መሰላችሁ? ኮሚሽን ለማግኘትና ውዷ ማንጠግቦሽ የለመደችው እንዳይቀርባትሮጥ ሮጥ ማለት አለብኝአልኩና ተፍ ተፍ ማለት ጀመርኩ። የእኛ ነገር ምን ዓይነት ስም ቢወጣለት እንደሚሻል አላውቅም ወዲያው የሚያደናቅፈኝ በዛ። ማንጠግቦሽ ደወለች።ምን ሆንሽ?” ስላት ሠፈር ውስጥ በጠና ታመው ሲጠበቁ የነበሩ አዛውንት ማረፋቸውን አረዳችኝ። የኑሮ መርዶ በዝቶ ነው መሰል የሰው ሞት ማርዳት እንዲህ ቀላል ይሁን? “እና?” አልኳት እንዳትጠራኝ ፈጣሪን እየተማፀንኩ።ቶሎ መጥተህ ለቅሶ አብረን እንድረሳ…ተባልኩላችሁ። ደልቶት ለሞተውና ተኮራምቶ ለሞተው እኩል ለቅሶ ተቀምጠን እንዴት እንደምንዘልቀው አላውቅም። እሱ ብቻ አይደለም አያ ሞት አጅሬው በዚህ ዘመን ምን እንደሚያጀግነው አልገባኝም። በቅጡ ካስተዋላችሁ ሞት ይበዛል። ምንም እንኳን ማኅበራዊ ድረ ገጽ ማኅበራዊ ኑሮውን ቢተካውም፣ ሰው ያለ ሰው አይኖርምና እየተነጫነጭኩ ደረስ ብዬ ለመምጣት ከነፍኩ። ለቅሶ ሳሳድድ ባዶ እጄን እንዳልቀር ነዋ፡፡ “የሰው ሞት በርክቶ የስታትስቲክስ ማወራረጃ በሆነበት ዘመን ሞት ራሱ እንግዳ አልሆን አለ እኮ…” የሚለኝ ምሁሩ ወዳጄ ነው፡፡ ይገርማል!

ቆይቼም የባህልና የወግ ተፅዕኖን ለያይቼ ለማሰብ እየሞከርኩ ራሴን ለማፅናናት ብዙ ጣርኩ። ድንገት ግንቆይ ብቀርስ?’ ብዬ መሀል መንገድ ላይ መመለስ ጀመርኩ (ሰው ለካ ወዶ አያብድም እናንተ?)፡፡ የዘንድሮ ሰው እንኳን መንገድ ሰጥተውት እንዲያውም እንዲያው ነው፡፡ አሁን ለቅሶ ቀረ ብሎ መንደርተኛው ሰው ሊያደርገኝ ነው ብዬ ሳስብ ወደ ሥራ ያዞርኩትን እግሬንና ቀልቤን ወደ ለቅሶ ቤት ቀለበስኩት። አንዱን ሲነሳ አንዱን አያሳጣም፡፡ ለቅሶ ቤት ቁጭ ብዬ ሰው በሹክሹክታ የሚነጋገረውን እየሰማሁ ፈታ አልኩ። በሐሜትና በአሉባልታ የተከበበ ከመሆኑ ባሻገር እውነተኛው የንግግር ነፃነት፣ እውነተኛና ነፃ የሕዝብ ፓርላማ ማለት እንዲህ ያለው መድረክ ነው እስክል ድረስ። አንዳንዴ ሳስበው በሰነፎች የተሞላው መንግሥታችን በቋንቋም በባህሪም ከማያውቃቸው አገሮች ሳይቀር የተለያዩ ተሞክሮዎችን ከሚያሰባስብ፣ የለቅሶ ቤቱን እሴት ሳይንሳዊ ለማድረግ ቢጥር ዴሞክራሲያችን ባልቀጨጨ ያስብላል እኮ። ሰሚ ጠፋ እንጂ እሱስ ሲባል የኖረውማየሰው ወርቅ አያደምቅነበር፡፡ ምን ያደርጋል ዘመኑ ሰውን አርክሶ ወርቅን አድምቆ ይንጎማለልብናል፡፡ ያናድዳል!

 እናላችሁ ለቅሶ ቤት ብቀመጥም ቀልቤና ሐሳቤ እኔ ዘንድ አልነበሩም። በጎን ሞባይል ስልኬ ያለማባራት እየጮኸ ይበጠብጠኛል። እነሳለሁ፣ እቀመጣለሁ።መጣሁእላለሁ እዋሻለሁ። ይህን ያዩት ባሻዬ፣አንበርብር ኔትወርክ ተመርጦ መሰጠት ጀመረ እንዴ?” ብለው ሳቁ። ሰውን የሚያንቆራጥጠው የኔትወርክ ዕጦት እኔ ስልክ ላይ አለመከሰቱ የገረማቸው ይመስላሉ።እባክዎን ስንቱን ሥራ እኮ ነው በእንጥልጥል ትቼው ስሮጥ የመጣሁት…አልኳቸው። ይኼን ጊዜ፣እኔ የምለው ቫትክፍያውን መንግሥት ዘንድ ሄደን እናወራርደዋለን። እንዲህ ለሟች በማይጠቅምና ቋሚን በማያበረታ ጊዜ ማጥፋት የምናቃጥለው ዕድሜ ግን የት ይሆን የሚወራረደው?›› ቢሉኝ ሳቄ መጣብኝና ሰው እስኪታዘበኝ ድረስ ላለመሳቅ ታገልኩ። ማንጠግቦሽም ከሩቅ ዓይታኝ ኖሮ መሰስ ብላ መጥታ፣ኧረ አንተ ሰውዬ! ሰው ሲሞት የሚስቅ ቀጣዩ ሟች ነው ይባላል እኮ…ስትለኝ ባሰብኝ። ጭራሽ ዕጣ ወጥቶልኝ ይረፈው? ጉድ እኮ ነው ዘንድሮ እባካችሁ! እየቆየሁ ስሄድ የሞት ፍርኃት ወረሮኝ (ሰው ሲሞት ነው ሞት እንዳለ ትዝ የሚለን) መጨረሻውን ሳላይ የምለው ነገር በዛብኝ።እስኪ አስቡት አልወለድ ያለውን ዴሞክራሲያችንን መጨረሻ፣ አንበላም አንጠጣም ብለን ያዋጣንለትን የህዳሴ ግድባችንን መጠናቀቅ ሳላይ፣ በአገራችን ላይ የተነሳውን ጠላት ቀብር ሳልታደም እንዲህ እንደ ቀልድ ጭልጥ? “ዘራፍ አንበርብር!” ስል፣ኧረ ጠላትህ!” አሉኝ ባሻዬ። ለካስ ድምፄን ከፍ አድርጌው ኖሯል። ሊሞት አምስት ደቂቃ ብቻ ቀረው የተባለ ሰው በሞት ፍርኃት ፈንታ አምስቱን ደቂቃዎች ለተለያዩ ክንዋኔዎች ከፋፍሎ እንዴት ሊጠቀምባቸው እንደሞከረ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ያጫወተኝ ትዝ ቢለኝ ደግሞ እመር ብዬ ተነስቼ ወደ ሥራዬ ገሰገስኩ። ታዲያስ! ህያው ለመሥራት መሮጥ እንጂ ለሙታን ሲያለቅስ መኖር አለበት እንዴ? ‘ነፍስ ይማርማለትን አረሳሁም፡፡ እንዴት ይረሳል!

ደላሎች የምንሰበሰብበት ሥፍራ ስደርስ አካባቢው ቀውጢ ሆኖ ነበር የጠበቀኝ።ምን ሆናችሁ ነው አካባቢውን አፍጋኒስታን ያስመሰላችሁት?” ብዬ ብጠይቅ አንዱ፣ምነው አንበርብር? መፍትሔ የታጣለትን የአሜሪካ የውርደት ቀጣና ከእኛ ጋር ታመሳስላለው?››” አይለኝ መሰላችሁ? የሰው ልጅ አሽሙር ዕድገት ምጣኔ ለመጨመሩ ማሳያው፣ በዓለም ዙሪያ አሜሪካ የደረሰባት ውርደት መነጋገሪያ መሆኑ በራሱ የሚናገረው አለው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ እንደነገረኝ ከሆነ አሜሪካ በአፍጋኒስታን የደረሰባት ውድቀት ለእኛ ጠቃሚ ነው፡፡ ለምን በሉ እንጂ፡፡ “አሜሪካ ልዑካኖችን ወደ ኢትዮጵያ ስትልክ በመሪዎቻችን አንደበት በደንብ መነገር ያለበት፣ ኢትዮጵያ ታሪክ ያላት የዓድዋ ጀግኖች አገር እንጂ የማንም ወንበዴ መፈንጫ እንደማትሆን ነው፡፡ አሜሪካኖች ሆይ በውጭ ፖሊሲያችሁ ብልሽት ሳቢያ በቬትናም፣ በኢራቅ፣ በሊቢያ፣ በሶሪያና በሌሎችም ሥፍራዎች ያደረሳችሁት አልበቃ ብሎ አሁን ይኸው እያየናችሁ አፍጋኒስታንን ለታሊባን አሸባሪዎች አሳልፋች ሰጣችሁ፡፡ ኢትዮጵያ እንደ አፍጋኒስታን አሸባሪ እንዲፈነጭባት አንፈቅድም ብለው ኮምጨጭ ይበሉ፡፡ መፍረክረክ አያዋጣም…” ያለኝ ትዝ አለኝ፡፡ ወዳጆቼ ደላሎችም ሲነጋገሩ የነበሩት ይህንኑ ነበር፡፡ አሜሪካ በቃሽ መባል አለባት!

ሰሞኑን እጅግ ቸግሮኝ የነበረ ነገር ቢኖር ያገኙኝ አላፊ አግዳሚዎች በሙሉ ‘አንበርብር ምነው ከሳህ?’ ሲሉኝ የነበረው ነው። “አንድ እንቁላል ስምንት ብር እየተሸጠ እንዴት ብለን ልንወፍርላቸው አስበው እንደሆነ እግዜር ይወቀው? ባልበላ አንጀታችን ሠልፍ በየነገሩና በየቦታው በሆነበት አገር ቆመን ስናዛጋ እየዋልን ከሳህ ብሎ ጉትጎታ ምን ማለት ነው? ሥጋት የገባኝ የዘረፋ ተጠርጣሪ መሰልኳቸው እንዴ ይህን ያህል?” እያልኩ ስነጫነጭ ማንጠግቦሽ ታዳምጠኝ ነበር። ውዷ ባለቤቴ እውነቴን ደግፋ እንዲህ ተናገረች። “ዝም አትላቸውም? ለነገሩ እንኳን ተራው ሰው መንግሥትስ በዚህ ዕድል መቼ ተጠቀመበት?” ብላ ወደ እኔ እየተመለከተች ጠየቀችኝ። “እንዴ ደግሞ መንግሥትን እዚህ ምን ዶለው?” አልኳት ትስስሮሹን እስክትገላልጠው እየተቁነጠነጥኩ። “መቼም በዚህ ጊዜ ሰው በደህና ቀን የሞላው ጎተራ ከሌለው በቀር፣ አልያም የደህና ባለሥልጣን ድጋፍ ካልኖረው፣ ይዞ መገኘትና በምቾት መታየት አይታሰብም። መንግሥት ቢያውቅበት ኖሮ ‘ካልጠቆማችሁኝ የት አገኛቸዋለሁ?’ እያለ እኛ ላይ ማፍጠጡን ትቶ ‘ቪ8’ቶችን እየተከተለ፣ በአንድ ምሽት በመቶ ሺሕ በሚቆጠሩ ብሮች አልኮል የሚንቆረቆርባቸውን መሸታ ቤቶች እያሰሰ፣ የታዳጊ ሴት ወጣቶችን ሕይወት እየሰለለ ቢተጋ ስንቱን ዘራፊ፣ ስንቱን ወገን አጥፊ በመነጠረልን ነበር?” አለችኝ። እንግዲህ በማንጠግቦሽ አገላለጽ ‘ሌብነት፣ የኑሮ ውድነትና የሞራል ዝቅጠት ጉዳዬ የሚላቸው አካል ጠፍቶባቸው ዓመታት በባከኑባቸው አገር ከሳህ ብሎ ሙግት ምን ይባላል? እንኳን ዜጋ አገር ከስታና መንምና የለ እንዴ!’ እባካችሁ ፀሐይ የሞቀውን እውነት አታስለፍልፉኝ፡፡ ኑሮ እንደ እሳት እየገረፈን ብሶት ሲጨመርበት ያማል፡፡ ያውም ፅኑ መታከሚያ የሚፈልግ ሕመም!

ለቅዝቃዜው ማባረሪያ ስል የባሻዬን ልጅ ደውዬ ግሮሰሪያችን ቀጠርኩት። ያራዳ ልጅ እኮ ብቻውን በልቶ አያውቅም! ‘…ሲያገኝም ያበላል ሲያጣም ያዝናል ሆዱእኮ ነው ግጥሙ። ከባሻዬ ልጅ ጋር ስንስቅ ስንጫወት ሸጋ ጊዜ በማሳለፍ ላይ እንዳለን በድንገት፣ስማ እንጂ አንበርብር?” ሲል ቀልቤን ሰበሰበው።እየሰማሁ ነው…ስለው፣ ‹‹እንዲህ የምንስቅና የምደሰተው ሠርተን በምናገኘው በላባችን ፍሬ ብቻ ይመስልሃል?” ብሎ ያላሰብኩትን ጠየቀኝ።ምን ይሆን ሌላው?” ብዬ መልሼ ጠየቅኩት።ሰላም!” አለኝ።አስተማማኝ ባይሆንም አገሩ አንፃራዊ ሰላም፣ ውስጣችን መለስተኛ ሰላም፣ ቤታችን ሥጋት ቢኖርም በመጠኑ ሰላም ቢሆን ነው እንጂ። እስኪ ከእነ ጭራሹ ሰላም አጥተን እርስ በእርስ እየተላለቅን የዓለም ሕዝብ መነጋገሪያ መሆናችን ከቀጠለ ግን አስበኸዋል?” አለኝ። እውነት ነው። የግሮሰሪያችን አስተናባሪ የባሻዬን ልጅ ሰምቶት ይሁን አላውቅም የመሐሙድ አህመድንሰላም ለሰው ልጆች!’ ዘፈን ደመቅ አድርጎ ከፈተው። እኛምሰላም ለሰው ልጆች! ሰላም ለአገራችን!’ እየተባባልን ቤቱን አሞቅነው።

በዚህ መሀል አንዱ፣ሰላም የሚገኘው በሞቅታ መንፈስ ውስጥ ሳይሆን ጠላትህን አንበርክከኸው አስገድደህ ለጠረጴዛ ዙሪያ ድርድር ስታመጣው ነው፡፡ ይልቁንስ በሰላም ስም እየተሳበበ ስለሚፈጸመው ማኬያቬላዊ ድርጊት መጥፎነት እየተነጋገርን፣ ጠላትን ሳይወድ በግድ እንዲንበረከክ ስለሚያደርገው ሰላም እናስብ…ሲለን ከሞቅታው በቀር አስተሳሰቡ የመጠቀ መሰለኝ፡፡ ሰውዬው ዲስኩሩን ሲቀጥል የባሻዬን ልጅ፣ይህ ሰው ምን እያለ ነው?” ብዬ ጠየቅኩት፡፡ የባሻዬ ልጅም የጠጠረው ሐሳብ እንዳልገባኝ ተረድቶ፣ሰውየው የሚለው ሰላምን ለማስፈን ኃይለኛ ሆነን እንቅረብ ነው የሚለው፡፡ እኛ በምንፈልገው መንገድ በምናመጣው ሰላም እንጠቀም ማለቱ መሰለኝ…ሲለኝ አሁን ገና ገባኝ፡፡ ‹‹ሰማህ አንበርብር ዙሪያህን ተመልከት፡፡ ሁሉም ቦታ ቅራኔ አለ፡፡ ቤተሰብ ውስጥ፣ በወዳጆች መሀል፣ ሃይማኖት ውስጥ፣ ትምህርት ቤትና በመሳሰሉት ሥፍራዎች ያልተወራረዱ ሒሳቦች አሉ፡፡ በአገሪቱ ላለፉት በርካታ ዓመታት ያልተወራረዱ የፖለቲካ ሒሳቦችና አሁን ደግሞ ከዘር ጋር የሚደመሩት ችግሮች የሰላም ጠንቅ መሆናቸውን አትዘንጋ፡፡ የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት፣ የመልካም አስተዳደርና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ጥያቄዎች እንዲወራረዱ ግን መጀመሪያ ለአገራችን ህልውና ስንል አንድ እንሁን…ሲለኝ ሁሉም ነገር ግልጽ ሆነልኝ፡፡ “እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ አፍጋኒስታውያን የአሜሪካና የመሰሎቿ መቀለጃ መሆን የለብንም፡፡ ሩሲያዊያን በአሜሪካውያን የአፍጋኒስታን ሽንፈት ሲያላግጡ ያሉትን ሰምተሃል?” ሲለኝ አለመስማቴን ነገርኩት፡፡ “America’s Inglorious End” ወይም “የአሜሪካውያን የውርደት ፍፃሜ” ነበር ያሉት፡፡ እኛ ግን እንደ እነሱ አንሆንም…” ሲለኝ ያድርግልን ነበር መልሴ፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት