Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሰብዓዊ ድጋፉን የሚፈታተኑ እንቅፋቶች

ሰብዓዊ ድጋፉን የሚፈታተኑ እንቅፋቶች

ቀን:

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጠረው የፀጥታ ችግር በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን አፈናቅሏል፡፡ የሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመትም አስከትሏል፡፡ ይህ ዓይነቱ የሰብዓዊ ቀውስ ክስተት ደግሞ ሁሉን አቀፍ ምላሽ የሚሻ ነው፡፡ መንግሥት፣ ክልሎች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ረጂዎች ባለሀብቶችና ግለሰቦች ሊረባረቡበት የሚገባም ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በሰው ሠራሽም ሆነ በተፈጥሮ አደጋ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመድረስ የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ በደቡብ ተከስቶ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉትን ከመርዳት ጀምሮ ወደቀያቸው በመመለስ ረገድ ለተከናወነው ተግባር መንግሥት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና የግለሰቦች ስብስብ ያደረጉት ድጋፍ ተጠቃሽ ነው፡፡

በሶማሌ፣ በቤኒሻንጉልና ጉሙዝ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች ተከስተው በነበሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመድረስ የተደረጉ ጥረቶችም ከተረጂዎች እንዳንድ ቅሬታ ቢነሳባቸውም ውጤታማ ነበሩ፡፡ ለዚህ ደግሞ አካባቢዎቹ የጦርነት ቀጣና አለመሆናቸው ዕርዳታውን ለማድረስ ቀና መንገድ ፈጥሯል፡፡

በተለይ በማኅበርና በግል የተደራጁ በጎ ፈቃደኞች ያሰባሰቡትን ዕርዳታ ከሥፍራው ደርሰው ለማስረከብ፣ መንግሥትን ለማገዝና የተቸገሩትንም ለመጎብኘት አልተቸገሩም ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን በተለይ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተፈጠረው ወቅታዊ የፀጥታ ችግር በትግራይ ዙሪያ፣ በጎንደር፣ በወሎ፣ በአፋርና አጎራባች አካባቢዎች ንፁኃንን በሰብዓዊ ዕርዳታ ለመድረስና እያጋጠማቸው ካለው ሰብዓዊ ቀውስ ለመታደግ ከዚህ በፊት እንደነበረው ቀላል አልሆነም፡፡

መንግሥት፣ ክልሎችና የየአካባቢው ማኅበረሰብ እርስ በርሱ የሚያደርገው ድጋፍ ቢኖርም፣ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ይደረጉ የነበሩ የሰብዓዊ ድጋፍ እንቅስቃሴዎች ተቀዛቅዘዋል፡፡ ዛሬ ላይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥርም ሆነ የተረጂ ወገኖች የሚገኙበት አካባቢ ቆዳ ስፋት ሲጨምር የበጎ ፈቃድ ዕርዳታ የማሰባሰብ ሁኔታው ግን እንደቀደመው አልሆነም፡፡

‹‹ቅድሚያ ለሰብዓዊነት›› በሚል የሚታወቀው የሰብዓዊ ድጋፍ ጥምረት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተነሱ ግጭቶች ለተፈናቀሉት ሰብዓዊ ዕርዳታ በማቅረብ የሚታወቅ የበጎ ፈቃደኞች ስብስብ ነው፡፡

አርቲስት ያሬድ ሹመቴ፣ መሐመድ ካሳና ሌሎች በርካታ በጎ ፈቃደኞች የሚሳተፉበት ይህ ጥምረት፣ በአገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት በተከሰቱ ግጭቶች ለተፈናቀሉ ወገኖች የሰብዓዊ ዕርዳታ በማሰባሰብም ይታወቃል፡፡ አሁን ላይ ለምን ተቀዛቀዘ ስንል ያነጋገርነው አርቲስት ያሬድ ምክንያቶቹን ነግሮናል፡፡

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሕግ ማስከበር ዘመቻው ከመጀመሩ አስቀድሞም ሆነ በኋላ የሰብዓዊ ድጋፍ በሚፈለግበት ሁሉ ከበጎ ፈቃደኞች እያሰባሰቡ እነሱም በበጎ ፈቃድ ለተረጂዎች ያደርሱ ነበር፡፡ የአሁኑ ግን እንደ ቀድሞው ምሉዕ አልሆነም፡፡

አርቲስት ያሬድ እንደሚለው፣ ጥምረቱ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርና ከዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት (ግሎባል አሊያንስ) ጋር በመሆን ወቅታዊ የፀጥታ ችግር ባሉባቸው አካባቢዎችና አጎራባች ሥፍራዎች የሚገኙ ዜጎችን ለመርዳት፣ የተፈናቀሉና አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹ፣ በችግሩ ሳቢያ ሠርተው መብላት ያልቻሉ፣ ቤት ንብረት የወደመባቸው፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውና በሕይወት መጥፋት ምክንያት የተበተኑ፣ በተያያዥ ችግር የተጎሳቆሉና ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚሹ ወገኖችን ለመድረስ የጀመሩትን ጥረት አላቋረጡም፡፡ ሆኖም የተለያዩ ችግሮች ገጥሟቸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከዚህ ቀደም ዕርዳታ የሚቀበሉበት የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ዕድሳት ላይ በመሆኑ ዕርዳታ የመሰብሰቢያና የማከማቻ ቦታ አጥተዋል፡፡ በጣይቱ ሆቴል ለመሰብሰብ ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም፣ የተገኘውን ዕርዳታ ማከማቻ ማግኘት ፈተና ነው፡፡ ለጊዜው በጣይቱ ሆቴል ዕርዳታ እያሰባሰቡ ከሚገኙ ወገኖች ጋር አብረው እየሠሩ ሲሆን፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ግን በዚያው የሰብዓዊ ዕርዳታ ማሰባሰብ ይጀምራሉ፡፡

እንደ ችግር የተነሳው ሌላው ጉዳይ የትራንስፖርት ነው፡፡ ጦርነት ሲካሄድ ብዙ በደሎች ይደርሳሉ፡፡ ንፁኃን ይጎዳሉ ያለው አርቲስት ያሬድ፣ በጦርነት ቀጣና ላሉ ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ አዳጋች እንደሆነ ገልጿል፡፡

ከዚህ ቀደም ወደ ትግራይ የተላከ 2,000 ኩንታል ምግብና ምግብ ነክ ቁሳቁስ በግለሰብ መኪና ተልኳል፡፡ ነገር ግን ጥምረታቸው ይህ ምግብ ለተባለው አካባቢ ይድረስ አይድረስ የሚያረጋግጥበት ሁኔታ የለም፡፡

ከዚህ ቀደም በግጭት ሳቢያ የተፈናቀሉ ዜጎችን በሰብዓዊ ዕርዳታ ለመድረስ በነበረው ሥራ ከቀይ መስቀል ማኅበርና ከግሎባል አሊያንስ ጋር በመሆን ምግብ ሲላክ ከጥምረቱ አባላት አብረው ሄደው መድረሱን አረጋግጠው ይመጡ ነበር፡፡ አሁን ግን ይህንን ለማድረግ አልተቻለም፡፡

ከትራንስፖርት ወይም ከሎጂስቲክስ ችግር በተጨማሪ አሁን ላይ ኅብረተሰቡ እንደቀደመው እየለገሰ አይደለም፡፡ ከኮቪድና ከኑሮ ውድነቱ ጋር ተያይዞም የኅብረተሰቡ የመለገስ አቅም ተቀዛቅዟል፡፡ ይህ ሌላው ችግር ቢሆንም፣ በጣይቱ ሆቴል በትብብር እየተሰበሰበ ያለው ዕርዳታ እንደተጠናቀቀ የጥምረቱ የበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ ዕርዳታ አሰባሰብ እንደሚቀጥል አርቲስት ያሬድ ተናግሯል፡፡

ግለሰቦችና ጥምረቶች በበጎ ፈቃድ ከሚያሰባስቡት ሰብዓዊ ዕርዳታ በተጨማሪ ብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ የአሜሪካ ልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ)፣ ቀይ መስቀል ማኅበርና ሌሎች አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሰብዓዊ ዕርዳታ ያቀርባሉ፡፡ ሆኖም ትልቁን ድርሻ ይዞ እየሠራ የሚገኘው መንግሥት ነው፡፡

የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ፣ የዩኤስኤይድ ኃላፊ ሰማንታ ፓወር ከሳምንታት በፊት ኢትዮጵያን ሲጎበኙ እንዳስታወቁት፣ መንግሥት ትግራይ፣ አፋርና አማራ የተፈናቀሉ ዜጎችን በዕርዳታ ለመድረስ እየሠራ ሲሆን፣ ሌሎች አካላትም ዕርዳታ በመስጠቱ እንዲሳተፉ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡

ነገር ግን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ የተባለው የሕወሓት ቡድን በትግራይና አጎራባች ክልሎች እየፈጸመ ባለው ጦርነት በ2014 ዓ.ም. ራሳቸውን ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ የትግራይ ሆኑ የአጎራባች አካባቢ አርሶ አደሮች ከዕርዳታ ላይላቀቁ ይችላሉ፡፡

የተለያዩ ዓለም አቀፍ ዕርዳታ ድርጅቶች ዕርዳታ ለማድረስ አመቺ ሁኔታ ይፈጠር ሲሉ መጠየቃቸውን ተከትሎም፣ መንግሥት ድርጅቶች ገብተው ዕርዳታ እንዲሰጡ ዕድል ሰጥቷል፡፡ ነገር ግን እንደታሰበው ሰብዓዊ ዕርዳታውን እየሰጡ አይደለም፡፡ የፀጥታው ሁኔታም የሰብዓዊ ዕርዳታው በተፈለገው ጊዜ እንዳይደርስ ሲያስተጓጉል ተስተውሏል፡፡

በጦርነቱ ሳቢያ ከቀያቸው የሚፈናቀሉና ሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ከችግሮች ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡

የአማራ ክልል እንዳስታወቀው፣ በጦርነቱ ምክንያት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለው ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚሹ ሆነዋል፡፡ በአፋር ክልል ደግሞ ከ75 ሺሕ በላይ ዜጎች ወቅታዊ በሆነው ጦርነት ሰብዓዊ ዕርዳታ ይፈልጋሉ፡፡

በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ዕርዳታ የሚፈልጉትን ጨምሮ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች በጦርነቱ ምክንያት ሰብዓዊ  ዕርዳታ የሚፈልጉ ናቸው፡፡ በዚህም መንግሥት ቀዳሚውን ሥፍራ ይዞ እየሠራ ነው፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ ከሚሠሩት አንዱ የሆነው ዩኤስኤይድ ሰብዓዊ ዕርዳታ እየሰጠ ሲሆን፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ለተፈናቀሉ ከ136 ሺሕ ለሚልቁ ዜጎች ዕርዳታ መላክ መጀመሩን፣ ለተጨማሪ 340 ሺሕ ዜጎች ለመድረስም እየሠራ እንደሆነ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ላይ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ ድጋፍ እያደረገ የሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮራም በቀጣይ ስድስት ወራት የተመጣጠነ ምግብ ዕርዳታና የኑሮ ድጋፍ ለማድረግ የዕርዳታ ክፍተት ተፈጥሮብኛል ብሏል፡፡

ፕሮግራሙ ለቀጣይ ስድስት ወራት 11.9 ሚሊዮን ዜጎችን ለመመገብና የረዥም ጊዜ የምግብ ዋስትና መፍትሔ ለማቅረብ ከ288 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልገውም አክሏል፡፡

መንግሥት፣ ፕሮግራሙና ሌሎች አጋሮች በኢትዮጵያ ያለውን የምግብ ዋስትና ችግር ለመቅረፍ እየተረባረቡ እንደሆነ ያስታወቀው ፕሮግራሙ፣ ድርቅና ጎርፍ፣ የበረሃ አንበጣና የገበያ መቃወስ፣ የምግብ ዋጋ መጨመርና ኮቪድ-19 ከ13.6 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለምግብ ዋስትና ችግር እንዲጋለጡ ያደርጋል ሲልም ገምቷል፡፡ ችግሩ በትግራይና በሌሎች አካባቢዎች በተፈጠረው ችግር መባባሱንም ባወጣው መግለጫ አስፍሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...