ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች የተሳተፉበት የናይሮቢው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዛሬ እሑድ ነሐሴ 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ይጠናቀቃል፡፡
ኢትዮጵያ እስከ ዓርብ ድረስ 1 ወርቅ፣ 3 ብር እና 1 ነሐስ በድምሩ 5 ሜዳሊያዎች በማግኘት ሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ በወንዶች 15 ሴቶች አትሌቶች የተወከለች ሲሆን፣ ከ400 ሜ ድብልቅ ዱላ ቅብብል፣ 800 ሜ፣ 1,500 ሜ፣ 3,000 ሜ መሰናክልና 5,000 ሜትር ውድድሮች በሁለቱም ጾታዎች ተወዳድራለች፡፡ በቀን ለሁለት ጊዜ ለስድስት ቀናት ለወር ያህል የተዘጋጀው ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ኬንያ የተጓዘው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ከተጠናቀቀ በኋላ ነው፡፡
የ2019 የዓለም ከ20 ዓመት በታች አገር አቋራጭ የብር ሜዳሊያ ያገኘው ታደሰ ወርቁ በሻምፒዮናው በ3,000ሜ በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያ፣ በ5,000ሜ ደግሞ የብር ሜዳሊያ አግኝቷል፡፡
የዓለም አትሌቲክስ በድረ ገጹ እንደዘገበው፣ የ19 ዓመቱ ታደሰ ወርቁ በውድድሩ ያስመዘገበው ጊዜ 7፡34.75 የግሉ የተሻለ ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡ ውጤቱም ባለፈው ወር በሀንጋሪ ያስመዘገበውን 7፡42.09 ነው ያሻሻለው፡፡ በሁለተኛነት ተከትሎት የገባው ኢትዮጵያዊው አሊ አብድልመና ሲሆን፣ ኤርትራዊው ሀብቶም ሳሙኤል ሦስተኛ ሆኗል፡፡
ታደሰ ለመጀመርያ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ መወዳደር የጀመረው እ.ኤ.አ. በ2019 በዴንማርክ አርሁስ ከተማ በተዘጋጀው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ነው፡፡
በዚያው ዓመት የ17 ዓመት ዕድሜ ላይ ሳለ በ3,000ሜ ሩጫን 7፡43.24 ሲፈጽም፣ 5,000ሜ ሩጫን በ13፡18.17 አጠናቋል፡፡
ታደሰ በናይሮቢው የዓለም ሻምፒዮና በ5,000ሜ ፍጻሜ በ13፡20.65 ሁለተኛ በመሆን ሁለት ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችሏል፡፡ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አዲሱ ይሁኔ በ5,000ሜ 4ኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ ዲፕሎማ አግኝቷል፡፡
‹‹የኔ አርዓያ (ሮል ሞዴል) ሰሎሞን ባረጋ ነው›› ያለው ታደሰ ወርቁ፣ ‹‹በቶኪዮ ኦሊምፒክ ድል ሲያደርግ ማየቴ ኩራት እንዲሰማኝ አድርጓል፡፡ የርሱንም ዱካ በናይሮቢ በማሸነፍ ተከትያለሁ›› ማለቱን ወርልድ አትሌቲክስ ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል በሴቶች 3,000ሜ ፍጻሜ መልክናት ውዱ ሦስተኛ በመሆን የነሐስ ሜዳሊያን ስታጠልቅ፣ በ3,000ሜ መሰናክል ደግሞ ዘርፌ ወንድማገኝ ሁለተኛ በመውጣት የብር ሜዳሊያ፣ እመቤት ከበደ 4ኛ በመሆን ዲፕሎማ አግኝተዋል፡፡
ዛሬ ከሚካሄዱት የፍፃሜ ውድድሮች መካከል ኢትዮጵያ በሴቶች 1,500ሜ፣ በወንዶች 3,000ሜ መሰናክል፣ በሴቶች 5,000ሜ ተጨማሪ ሜዳሊዎች እንደምታገኝ ይጠበቃል፡፡ እስከ ዓርብ ሻምፒዮናውን ኬንያ በ3 ወርቅ፣ 1 ብር እና 2 ነሐስ ስትመራ ፊንላንድ በ2 ወርቅ፣ 1 ብር እና 1 ነሐስ ተከትላለች፡፡ ኢትዮጵያ በ1 ወርቅ፣ 3 ብር እና 1 ነሐስ 3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡
የወጣቶች ሻምፒዮና ለታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች መንደርደሪያ በመሆኑ አዳዲስ ሯጮች የሚገኙበት እንደሚሆን ይታመናል፡፡ በዚህ ረገድ ከቀደምት ሻምፒዮናዎች ተገኝተው ለዓለም ቁንጮነት የበቁት ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ አሰፋ መዝገቡ፣ አብርሃም ጨርቆሴ፣ መሠረት ደፋርና ገንዘቤ ዲባባ ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የዓለም ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ባለፉት 17 ሻምፒዮናዎች ተሳትፋለች፡፡ ኢትዮጵያ 37 የወርቅ፣ 32 ብር እና 29 ነሐስ ሜዳሊያዎች በድምሩ 98 ሜዳሊያዎች በማግኘት ከዓለም አምስተኛ፣ ከአፍሪካ ሁለተኛ ለመሆን ችላለች፡፡
በዘንድሮው ሻምፒዮና ካልተካፈሉት ዋና ዋና አገሮች አሜሪካ፣ እንግለሊዝ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ፣ ቻይና፣ ጃፓንና ኒውዝላንድ ይገኙበታል፡፡